Monday, 26 September 2016 00:00

ኢህአዴግ ላባውን በማራገፍ ንሥር ሊሆን አይችልም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

   ከዘረ-አዳም በሞገስና በጥበብ፤ በፍቅርና ልዕልና አንቱ ብዬ የማይበቃኝ ምናልባትም የእርሱን ታሪክ አሥቤና አንብቤ የማልጠግብለት አብርሃም ሊንከን፤ ዛሬም የፅሁፌ ክር መምዘዣ፣ የሃሳቤ መሥፈንጠሪያ ሊሆን ወድጃለሁ፡፡ ዓለማችን ምርጥ መሪዎችን አፍርታለች፤ ዴሞክራሲን ጨብጣለች ማለት የደፈረና የሞከረ ሰው፤ ከቶማስ ጀፈርሰን ቀመር ይነሣ እንጂ ገቢራዊነቱ ላይ የሊንከንን ያህል ያሳየ፣ ሰዋዊ ክርስቶስ የለም የሚል ሃሣብ አለኝ፡፡ ብዙዎችም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡
 ስለ መሪነትና መሪዎቻችን ጉዳይ በጥልቀት ከማንሳቴ በፊት የሊንከንን ሃሳቦች ልንደርደርባቸው ብዬ ተነሣሁ፡፡ በተለይ ደግሞ እነዚህን፡-
You can not strengthen the weak by wreaking the strong.
You can not enrich the Poor by Impoverishing the rich.
You can not build character and courage by taking man’s initative and    independence.
You can not farther the brotherhood of man by inciting class hatred.
አንዱን ለማጠንከር፣ ጠንካራውን ማድከም አይገባም፤ የሰውን መነሳሳትና ነፃነት ነጥቆ ጥንካሬና ማንነቱን መፍጠር አይቻልም፤ አንድነትና ወንድማማችነት በቡድንና በጎጥ ለይቶ ጥላቻ በመዝራት አይመጣም… የሚል አንደምታ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሃሳቦች እኛንም ይመለከቱናል፡፡
መሪዎቻችን ሕልማቸው ምን እንደሆነ ባናውቅም በየዓመታቱ መሀል እያንቀላፉ ድንገት የሚባንኑ እስኪመስል ድረስ የሆነ ኮሽታ ሲፈጠር ብቻ ‹‹በስብሰናል፤ ዘቅጠናል፤… ተሰባብረናል፤ እንጠገንና እንሻሻላለን›› በማለት ሲቸግራቸው ሰበብ ያበጁለታል፡፡ በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤መንግሥታቸውን እንደ ንሥር በየጊዜው የሚታደስ አድርገው ቆጥረውታል፡፡ ግና ንሥር እኮ ከሩቅ የሚያይ፣ አልሞ የማይስት ነው፡፡ ለምሳሌ ኤሊን ካነሳ፤ አነጣጥሮ ከዐለት ጋር የሚያጋጭና ሥራውን በጥራት የሚሰራ እንጂ እንደ ኢህአዴግ ቀሚሴ አደናቀፈኝ የሚል አይደለም፡፡ ጠላቶቹንም የሚያሸንፈው እንደ እባብ በመሹለክለክ ሳይሆን የበረራ ከፍታውን ከሌሎች ከፍታ በላይ፣ ወደ ማይደርሱበት ጥግ በማሻቀብ ነው፡፡ መንቁሩንና ጥፍሩንም ሲሰብር፣ ለመታደስ እየታመመ እንጂ እንደ ኢህአዴግ ላባውን ነጭቶ “ታድሻለሁ” ለማለት ብቻ እያራገፈ አይደለም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ የመዘዟት ሌላኛዋ ሀሳብም ለማንፀሪያነት አትበቃም፡፡ ኢህአዴግ በአለት ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡ ታዲያ በአለት ላይ ከተመሠረተ፣ ለምን በየጊዜው የመጣ ዐውሎ ንፋስ መሬት እያስላሰ አበሳ ያሣየዋል…? አለት ላይ መቆም እኮ አለመውደቅ ብቻ ሳይሆን መፅናትም ነው፤ አለመናወጥ! ለእኔ ግን ፓርቲው በአሸዋ ላይ የተመሠረተ ይመስለኛል፡፡  
ኢህአዴግ እርሻ ነው ቢሉ ኖሮ በተሻለኝ፡፡ ምክንያቱም እንክርዳድ ለሚባሉት ሰዎች አረምነት ማሥረገጫ ይሆን ነበር፡፡ ይሁንና አሁን ያለው የመንግሥት ማንነት ፈፅሞ መልኩን የሚያበላሽ፣ ከዚህ ቀደም የነበረውንም የተወሰኑ በጎ ነገሮች አፈር የሚያሥልስ ነው፡፡ ለሕዝብ ቆሜያለሁ፤ ለሕዝብ እሰራለሁ እያሉ፣ ለተቃውሞ የወጣ ህዝብ ላይ መተኮስ በምን መመዘኛ ይሆን ህዝባዊነት የሚሆነው? ይህ ሃሳብ የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራን ግጥም አንድ አንጓ /አርኬ/ አስታወሰኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
የኔ ልጅ
በጊዜ ስግደት እንዳይመስልሽ፤ ባደባባይ ጭብጨባ፤
በሚቆምልሽ ሀውልት፤ በሚነፋልሽ ጥሩንባ፤
መኖርሽ ትርጉም የሚያገኝ፤ እውነትሽ የሚለካ፡፡
በህዝብ ልብ ያልሠረፀ ገድል፤ ሀገር ያልተቀበለው እውነት፤
ሸራ ወጥረው ቢነድፉት
ጊዜ ጠብቆ ይነሳል፤
ቀኑ ሲነጋ ይፈርሳል፡፡
እውነት ነው፤ በህዝብ ልብ ውስጥ ያልሰረፀ እውነት ሥር የለውም፡፡ በሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሰረተ መንግስት በጠብ-መንጃ ብቻ አይፀናም፡፡ ሺህ ውሸቶች አንድ እውነት ሆነው ልብን አይማርኩም፡፡ ኢሕአዴግ ግን ከዚህ እውነት በእጅጉ እያፈነገጠ ነው፤… ርቀቱን እየጨመረ፣ ጉድጓዱን እያጠለቀ ነው፡፡ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› እንዲሉ፣ የሕዝብን ጥያቄ ከማዳመጥ ይልቅ የካድሬዎቹን ምክር እያናፈሰ፣ እኛንና ራሱን ወደማንወጣበት አዘቅት ውስጥ እየከተተ ነው፡፡
ለመሆኑ በፓርቲ ያልተደራጀ፣የራሱ ጥያቄ ያለው ሕዝብ፣ ምላሹ ጥይት የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?... የሰለጠነ ወታደር ወይም ከጠላት ጋር አብሮ የመጣ ነፍጠኛ አይደል፤.. ለጥያቄው መልስ ሰጥቶ ሀገሪቱን በማረጋጋት፣ታሪካዊ ሃላፊነትን መወጣት ሲገባ፣ እንደ ጎረምሳ ሁሌ ጡንቻን ማሳየት ምን የሚሉት ሥልጣኔ ነው? ወደ እርጅናው ዕድሜ ክልል ለገቡት የፓርቲው መሪዎች አሳፋሪ ይመስለኛል። ቆይ ---- እስከ መቼ ነው የሰው ደም ላይ ቄጠማ ጎዝጉዞ መዝፈን የሚቀጥለው? ይልቅስ ጠቢቡ ሰለሞን፤ ‹‹ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤›› ይላል። አርባ ሶስት ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ቀጥሮ ያሰራ የነበረው የስኮትላንዱ ተወላጅ በኋላም የአሜሪካ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ አባት አንድሪ ካርኔጌ፣ ከሰዎች ጋር አብሮ ስለ መሥራትና ስለ መምራት እንዲህ ብሎ ነበር፡- Dealing with people is like digging gold, you have to move tons of dirt to get an ounce of Gold.
ታዲያ መንግስት ማለት ሕዝቡን የሚወድድ፣ ሕዝቡ ውስጥ የሚፈጠሩና የሚኖሩ ችግሮችን ሳይቀር ታግሶ የሚያስተዳደር እንጂ በጥይት እየደበደበ ቡቃያውን የሚያጠፋ አይደለም፡፡… ለዚያውም መሰረታዊ ጥያቄ ለምን ጠየቃችሁ ብሎ። ህዝብ በየቢሮው፣ በየፍትህ አዳራሹ፣ ገብቶና ወጥቶ ሰልችቶት፤ ቋቅ ብሎት አደባባይ ሲወጣ፣ በገዛ ሀገሩ በወታደሮች መታደኑና መገደሉ በእጅጉ የሚያሳዝንና ታሪክ የሚያቆሽሽ ተግባር ነው፡፡ ለመሆኑ እንዴት አንድ ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት፣ ስለ ታሪክና ትውልድ አያስብም? … ሕዝቡን ቢጠላ እንኳ የበቀለበት ቤተሰብ፣ እርሱ ሲያልፍ ነውር ወይም ክብር ተሸክሞ የሚኖር ትውልድ እንዴት አይታሰበውም? መቼም ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” የሚለው መንግስት ለሚለው ስያሜ የሚመጥን ተረት አይመስለኝም፡፡   
ዛሬም መንግሥት አደብ ገዝቶ፣ እንደ መንግስት በጥሞና ካላሰበ፣ ቻርልስ ዲከንስ በፃፈው  “የሁለት ከተሞች ወግ” ላይ በፈረንሳይ የተፈፀመው አይነት ከባድና መራራ የሆነ ነውጥና ደም መፋሰስ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡ ይሁንና አሁንም መንግስት ራሴን ለማደስ ተዘጋጅቻለሁ ይላል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፤ የንስር ዓይነት ተሀድሶ፣ መንቁርን መስበር፣ የአመፃ መሳሪያ የሆነውን ጥፍርንም መንቀል ይጨምራል እንጂ ላባን ማራገፍ ብቻ አይደለም፡፡ … ለውጥ ላይ ነን የሚሉት መሪዎች፤ ዛሬም የንግግር፣ የመግባባትና ጥያቄዎችን የመመለስ አዝማሚያ ሳይሆን የዱላና የኃይል ዘመቻ ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ ይልቅ የሕዝቡን ጥያቄዎች በበሰለ ሁኔታ መመለስ ቢቻልና ለታሪካዊ ጠላቶቻችን እጅ ባንሰጥ የተሻለ ነው፡፡
 … አሁንም መንግስት እንዳይታለል፤ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ፣ እንደ ወይን የተብላሉና ተስፋ ከመቁረጥ በኋላ የመጡ ተቃውሞዎች በጠመንጃ የሚበርዱ አይደሉም፡፡ ይልቅስ በተረጋጋ መንፈስ፣ በሰከነ አእምሮ መልስ በመስጠት የሚፈቱ እንጂ፡፡ የቀደሙት አመፆች በተወሰኑ አካባቢዎች በተወሰኑ ሰዎችና ፓርቲዎች የተቀሰቀሱ ነበሩ፡፡ የአሁኑ ግን እንደዚያ አይደለም፣ የተብላላ፣ የሁሉንም ደጅ ያንኳኳ፣ የዋለ ያደረ፣ መልስ ያጣ፣ ህዝቡ ጠብቆ ጠብቆ ተስፋ በማጣት፣ በሕይወትና በሞት መካከል ያለው ድንበር እስኪጠፋው ያንገፈገፈው ስለሆነ፣እንደቀደሙት እሳቱ ላይ ውሃ በመድፋት አይመለስም፡፡  
ለመንግስት የሚበጀው ጥፋቱን አምኖ፣ ጠመንጃውን አስቀምጦ፣ … የበደለ ወገን እንደሚያደርገው ሁሉ ጡንቻውን አርግቦ፣ ሀገሪቱንና ራሱን ከጥፋት ማዳን ነው፡፡ አለበለዚያ ሀገርን በደም እያጠቡ፣ ሥልጣኔን አፀናለሁ ማለት ብልሃት የጎደለው ምክር ይሆናል፡፡  
ሊንከን ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደር፣ ስታንተን የተባለ ሰው በእጅጉ እየተከታተለ ስሙን ያጠፋና ይሰድበው ነበር፡፡ በእርግጥም ስታንተን ሊንከንን ይጠላው ነበር፡፡ ይሁንና ሊንከን ምርጫውን አሸንፎ ስልጣን ሲይዝና ካቢኔውን ሲያቋቁም፣ ለስታንተን የምትሆንና እርሱ ቢቀመጥ ለሀገሪቱ የተሻለ ውጤት የሚያመጣበት ቦታ ነበረች፡፡ ሉተር ኪንግ እንዲህ ይላል፡- “Can you imagine whom Lincoln chose to fill this post?” የሚደንቅ ነበር- የመረጠው ስታንተንን ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ግን ተቃወሙት፡፡ ስህተት ሰርተሃል! አሉት፡፡ “He is your enemy”  “He will seek to sabotage your Programme” ሲሉ አጣደፉት፡፡ ሊንከን ግን ህሊናው ሰማ፡፡ ከእርሱ ጋር ስለተጣላ ከሀገሩ ጋር አልተጣላም፣ እናም ቦታውን ሰጠው፡፡ ውጤታማም ሆነ፡፡ መሰልጠን እንዲህ ነው፡፡ በሀሳብ ልዩነት  እያሳደዱ መግደልና ማሰር ግን እልም ያለ ኋላ ቀርነት ነው፡፡
አሁንም ሰልፍ የወጣን ሁሉ ገድሎና አስሮ ሀገር ማረጋጋት ስለማይቻል፣ መንግስት ወደ ቀልቡ ተመልሶ፣ ከማይሆን ቅዠት እውን ወደሚሆን እቅድ ቢመለስ የተሻለ ይመስለኛል፡፡
ጀምስ ዴቪድ በርቤር ስለ ፖለቲካ በፃፉባት የቆየች መፅሃፋቸው እንዲህ ይላሉ፡- Force is a poor substitute for consent, a last resort, which reduces political power if used too often. When a politician must use force, he is already in trouble as a leader.
ሰሞኑን የፌስቡክ ገፄ ላይ የፃፍኩትን የመሪ ብቃትን የሚያመለክተውን የጆን ሲ ማክስዌልን ሃሣብ አስፍሬ ላብቃ፡፡ አንድ ዶሮ አርቢ ሰው፤ በየክረምቱ ጎርፍ እየመጣ ዶሮዎቹን ይወስድበት ነበር፡፡ ያንን የእርባታ ቦታ ሊተካ የሚችል ሥፍራ ለመግዛት ገንዘብ አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ለሚስቱ ችግሩን አካፈላት፡፡ ሚስቱ አንድ ሀሳብ አቀረበችለት።
‹‹ዶሮዎቹን ሽጥና ዳክዬ ግዛ!››
የሚስቱን ሃሳብ ተቀብሎ ዳክዬዎች ገዛ፤ ጎርፍ ሲመጣ ዳክዬዎቹ ዋኝተው በጎርፍ ከመወሰድ ዳኑ። ችግር ተቃለለ፡፡ መሪ ማለት በችግር ቀን ሁነኛ መፍትሔ የሚያፈልቅ እንጂ ወንበር የሚያሞቅ አይደለም!

Read 1774 times