Monday, 15 August 2016 09:20

ህንዳዊቷ ለ16 አመታት የዘለቀውን የረሃብ አድማቸውን አቆሙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በህይወት የቆዩት በግዳጅ በአፍንጫቸው በሚሰጣቸው ምግብ ነው
   የህንድ መንግስት ያወጣውን አንድ አነጋጋሪ ህግ በመቃወም ላለፉት 16 አመታት ምግብ ሳይመገቡ የዘለቁት ኢሮም ሻርሚላ የተባሉት ህንዳዊት፤ ባለፈው ማክሰኞ የረሃብ አድማቸውን አቁመው ምግም መመገብ መጀመራቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ።
ለአገሪቱ የጦር ሃይል በማኒፑር ግዛት የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ለመቆጣጠር ያልተገባ ስልጣን ይሰጣል የተባለውን ህግ የተቃወሙት ሻርሚላ፤ላለፉት 16 አመታት ምግብና ውሃ አልወስድም ብለው በረሃብ አድማቸው ጸንተው መዝለቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የመንግስት ሃይሎች በሴትየዋ አፍንጫ በተተከለ ቱቦ አስገድደው በሚሰጧቸው ምግብ ህይወታቸውን እንዳቆዩት ገልጧል፡፡
የማኒፑሯ ብረት የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው የ44 አመቷ ህንዳዊት፤ እ.ኤ.አ በ2000 የመንግስት ሃይሎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸማቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ወታደሮች ዜጎችን ያለ እስር ትዕዛዝ ማሰር እንዲችሉና ሃይል እንዲጠቀሙ የሚፈቅደውን ህግ በመቃዎም የረሃብ አድማ መጀመራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡ ሴትዮዋ ለ16 አመታት የዘለቀውን የረሃብ አድማቸውን ለማቋረጥ የወሰኑት፣ ከረሃብ አድማው ይልቅ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ ህጉን ለማሰረዝ ያስችለኛል ብለው በማሰባቸው ነው ያለው ዘገባው፤አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን የህንዳዊቷን ውሳኔ መቃወማቸውን ጠቁሟል፡፡

Read 1115 times