Monday, 15 August 2016 08:54

(*የፖለቲካ ቀውስ *የዜጎች ሞት *የተቃውሞ ጩኸት *አለመረጋጋት)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ - በተለይ ለአዲስ አድማስ

በፀጥታ ኃይሎች ችግሮችን ለማስታገስ የሚደረገው ሙከራ ብዙ ርቀት አያስኬድም
ህዝቡ ውስጥ ያለው መሰረታዊ ጥያቄ፣አሁን ባለው አስተዳደር ያለመርካት ነው
በሰላማዊ ሰልፍ የአንድ ሰው ህይወት እንኳ ማለፍ የለበትም
ወልቃይት በትግራይ ሥር እንዴት ተካለለች? ጀነራሉ ያብራራሉ

የቀድሞ የህወሓት ታጋይና የመከላከያ አዛዥ የነበሩት ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ፤ በሀገሪቱ
ወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የህዝቡ ተቃውሞ መንስኤ---፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየተባባሱ የመጡ ግጭቶች-
--፣ተቃውሞዎችን በጸጥታ ኃይሎች ማስታገስ-- ፣የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ጉዳይ-- ወዘተ- ----ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ሰሞኑን በሌ/ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ቢሮ ተገኝቶ
አነጋግሯቸዋል፡፡

   በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ተቃውሞዎች፣ ምንጫቸው ምንድነው ብለው ያስባሉ?
እኔ አሁን በመንግስት የስራ ኃላፊነት ላይ ስለሌለሁ በተደራጀ መንገድ የሚመጣ መረጃ የለኝም። እንደ ማንኛውም ዜጋ ግን የምሰማቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ ዋናው ምክንያት እሱ ነው፣ አይደለም የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ቢሆንም የድንበር ጥያቄ አለ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከማስተር ፕላን ጋር የተያያዘ ጥያቄ ተነስቶ ነበር፤እነዚህ የጥያቄዎች መነሻ እንጂ ህዝቡ ውስጥ ያለው መሰረታዊ ጥያቄ አሁን ባለው አስተዳደር ያለመርካት ነው፡፡
የፖለቲካዊ ስርአቱን ስንመለከት፣በተለይ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ፤ ህዝብ ገዥው ፓርቲ ባስቀመጠለት አደረጃጀት ብቻ ሳይሆን እሱ በፈለገው አደረጃጀት ሃሳቡን የሚገልፅበት ሁኔታ እየጠፋ ነው የመጣው፡፡ አሁን ባለው የመንግስት አወቃቀር፣ገዥው ፓርቲና ለ5 ዓመት አስተዳድራለሁ ብሎ ስልጣን የያዘው መንግስት የሚባለው መዋቅር ምንም ልዩነት በሌለው መልኩ ተደበላልቋል፡፡ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር ውሏል። ይሄ ደግሞ በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው የሚመራው፡፡ በዚህ ምክንያት የህዝቡን የተደራጀ ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ የማይጋብዝ መሆኑ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በተጨማሪ ሰፊ የስራ አጥነት፣ የኑሮ መወደድ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ናቸው ችግሮቹ ብዬ የማምነው፡፡
መንግስት ለተቃውሞዎች እየሰጠ ያለውን የአጸፋ ምላሽ እንዴት ይገመግሙታል? ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች፣በርካቶች ህይወታቸውን እንዳጡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል፡፡ መንግስት ኃይል መጠቀሙ ተገቢ ነው?
ህዝብ ተቃውሞውን በሠላም የመግለፅ ሙሉ መብት አለው፡፡ መንግስት ይሄን መብት በተሟላ መንገድ መፍቀድ አለበት፡፡ ህዝቡ ይሄ መንግስት አይመቸኝም፤እንዲቀየር እፈልጋለሁ ብሎ ሃሳቡን መግለፅ ይችላል፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎች ዘረኛ ከመሰለው፣ ዘረኛ ናቸው ብሎ መግለፅ መብቱ ነው። በአጠቃላይ  ህዝቡ፤ ህገ መንግስታዊ መብቱን እስካሁን ሳይጠቀምበት በመቅረቱ ሊወቀስ እንጂ ማንም ሊከለክለው አይገባም፤በተሟላ መልኩ መመቻቸት አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት የሃገር ደህንነትና ፀጥታን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። እንዲሁም በቀውስና በጫጫታ ሃገር መፍረስ የለበትም፡፡ አንዴ ከፈረሰ መመለሻ ስለሌለው መንግስት ይህን ሃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ መወጣት አለበት፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡ ያሻውን ተቃውሞ በሠላም እንዲገልፅ መፍቀድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ ሃይሎች ተገፋፍተውም ይሁን በራሳቸው ተነሳስተው ወደ ብጥብጥ የሚያመሩትን እየለየ ለህግ ማቅረብ አለበት፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በሃገሪቱ በጣም ከባድ የሆነ የህዝብ ጥያቄ፣በፖለቲካዊ ስርአቱ ላይ እየተነሳ ነው። ፖለቲካዊ ስርዓቱ ዲሞክራሲያዊ ነው? አሳታፊ ነው? የህዝብ ፍላጎትን የሚያስጠብቅ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ከህዝቡ እየተነሱ ነው፡፡ መንግስት ይሄን በጥልቀት ማወቅ አለበት፡፡ አውቆም በሰለጠነ መንገድ የፖለቲካዊ ስርአቱን ሰላም የሚመልስበትን መንገድ ካላበጀ በስተቀር ፀጥታና ሠላም አስከብራለሁ በሚል፣ትናንሽ ችግሮችን ጭምር በሃይል ለመፍታት የሚሞክር ከሆነ ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ አይፈታውም፡፡
ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታና ሰላም እንዲሰፍን ምን መደረግ ይኖርበታል?
ሁለት ነገሮች መሠራት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል መበጣበጥ ተፈጥሮ ሃገር እንዳይፈርስና መቋጫ የሌለው ችግር ውስጥ እንዳይገባ፣ መንግስት የሀገሪቱን ፀጥታ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይሄ እንግዲህ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፡፡ ዋናው መፍትሄ የፖለቲካዊ ስርአቱ ቀጣይነት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ስለገባ፣መንግስት በጥልቀት ማሠብ ይኖርበታል፡፡ ማዘጋጃ ቤቶች አስተዳደር ሰውን ያለማቋረጥ እያስተዳደሩ፣ለህብረተሰቡ የሚወሰነውን ውሳኔ እየወሠኑ፣ የፀጥታ ሃይሎች በበኩላቸው፤የሃገሪቱን ከውስጥም ከውጭም የሚመጡ ጥቃቶችን በተለየ ያልጨረስነው ጦርነት አለ ከዚያ አካባቢ ሊነሱ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው።  ይሄን እነሱ እየሰሩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ያለው ችግር በዚህ ሁኔታ መቀጠል የሚገባው መሆኑን አውቀው በዘላቂነት የሚፈታበት ጉዳይ ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በተለይ ደግሞ ህብረተሰቡ በሚፈልገው መንገድ ይሄን ችግር እንዴት ነው የምንፈታው በሚለው ላይ ቁጭ በለው መወያየት አለባቸው፡፡ ችግሮች ደረጃ በደረጃ የሚፈቱበትን አቅጣጫ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
በፀጥታ ኃይሎች ላይ ያለውን ጫና እያቃለለ መሄድ የሚችለው ፖለቲካዊ ችግሩን ለመፍታት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚንቀሳቀሱበት እድል ሲኖር ነው፡፡ አሁን ካለው ገዥ ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ መሆናቸውን ህብረተሰቡ እያረጋገጠ የሚሳተፍባቸው ውይይቶችን ነው መፍጠር የሚያስፈልገው፡፡ ይህ ሂደት በዚህ መንፈስ መጀመር አለበት፡፡ መንግስት ውስጥ ካለው ለሀገር የማሰብ ነገር ባልተናነሰ ደረጃ፣ብዙ እውቀት ባለው ለሀገር የሚቆረቆር ዜጋ ዘንድ እንዳለም መታወቅ አለበት፡፡ ይሄን የህብረተሰብ ክፍል አደራጅቶ መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሀገር ከፈረሰ በኋላ የፖለቲካ መፍትሄ ሊመጣ እንደማይችል አስቦ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ያለውን ጫና እየቀነሱ፣ ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ሀሳቡን ገልፆ፣ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ለህብረተሰቡ እያሳዩ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ካልተጀመረና እኛ ብቻችንን እንፈታዋለን ወይም ደግሞ በተለምዶ እንደሚደረገው፣ እነሱ መስማት የሚፈልጉትን ንግግር ብቻ የሚናገር ሰው ሰብስበው፣የህዝብ ውይይት አድርገናል የሚል ጨዋታ ውስጥ ከተገባ፣ችግሩ መቼውንም ቢሆን አይፈታም፡፡ መንግስትና ገዥው ፓርቲ መስማት የማይፈልጉትን የሀገር ችግሮች ማሳየት የሚችሉ ሰዎችን አማክሮ፣ የሀገሪቱ ችግር የሚፈታበትን መንገድ ማመቻችት ያስፈልጋል፡፡
የፖለቲካው መፍትሄ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው የሚሆነው፡፡ ከህገ መንግስቱ በቀር ህጎች ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡ የምርጫ ህጉ ሊሻሻል ይችላል፡፡ መሻሻል ያለባቸው መሻሻል እንዲችሉ ማድረግና የፖለቲካ ምህዳሩን እያሰፉ፣ የሰው ተሳትፎ በዲሞክራሲያዊ ስርአት ተጠናክሮ የሚሄድበትን መደላድል ማስቀመጥ አለብን፡፡
እነዚህ የመፍትሄ ሃሳቦች ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተው፣ ግጭቱ ከቀጠለ መጨረሻው ምን የሚሆን ይመስልዎታል?
እንደ እኔ አሁን ባለው መካረር  ከቀጠለ፣ ሀገሪቱን እስከመበታተን ሊያደርስ ይችላል፡፡ ሀገራችን ውስጥ ሰፊ የስራ አጥነት ችግር አለ፤ የተማረው ስራ እያገኘ አይደለም፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች በስርአቱ ያለመርካት ነገር አለ፡፡ በሌላ በኩል፣“የተወሰነው ስልጣን የያዘው ክፍል ሀብቱንም ስለያዘ ነው ችግሮች የተፈጠሩት” እያለ ጥላቻ የሚያሰራጭ አካል አለ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ነገሮች ሲገናኙ ችግሩን የበለጠ ያባብሱታል። ይሄ “ተደርጓል አልተደረገም” የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው። አንዳንዶቹ ችግሮች በቢሮክራሲው ውስጥ ያሉ ሰዎች ይሄን ግርግር እየፈለጉት ይሆን? የሚል ጥያቄ ነው የሚያስነሳው፡፡ አንዳንዶቹ ብዙ ገንዘብ ዘርፈዋል ነው የሚባለው፡፡ ይሄን የዘረፉትን ለመሸሸግ  ግርግሩን እንደ መደበቂያ አድርገውታል ይባላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ሁኔታው ህዝብን ከህዝብ ወደ ማናቆር ሊሄድ ይችላል። ህዝብ ከህዝብ ከተናቆረ ደግሞ ሀገር ሰላም አይሆንም፡፡ መጨረሻችን ወዴት ሊሄድ ይችላል ከተባለ - አላውቅም። በተለይ ህዝብ ከህዝብ ከተጋጨ አደጋ ነው፡፡ ይሄን ሊያመጡ የሚችሉ አንዳንድ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ እነዚህ በቶሎ መፍትሄ ማግኘት አለባቸው፡፡ የሀገር ሉአላዊነትን በማይፈታተን መንገድ ወደ መፍትሄው መሄድ አለብን፡፡ ችግሩን እያዘገየነው በሄደ ቁጥር መፍትሄው እየተወሳሰበ ነው የሚሄደው፡፡ ከስር ያለው ግፊት የፈነዳ እንደሆነ፣ ሁሉንም ጠራርጎ ነው የሚሄደው፤ማስቆም አይቻልም፡፡ የመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ይሄን አውቀው፣ጉዳዩ ከስልጣናቸውና ከፓርቲው በላይ መሆኑን ተገንዝበው፣ የመፍትሄ መንገዱን መጀመር አለባቸው፡፡
ኢህአዴግ በግንቦት 2007 ምርጫ፣መቶ በመቶ ማሸነፉን በገለጸ ማግስት በተቃውሞ መጥለቅለቁን በመጥቀስ የምርጫ ስርአቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እኔ ምርጫው ችግር አለበት ነው የምለው። በምርጫው ሂደት ውስጥ ስላልነበርኩ በዝርዝር ባላውቀውም እንደ አንድ የፖለቲካ ተከታታይ ሰው ሳየው፣ ምርጫው በትክክለኛ መንገድ ቢደረግ መቶ በመቶ የሚባለው ውጤት አይመጣም ነበር፡፡ ምናልባት ከ50 እና 60 በመቶ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ህዝብ በሙሉ አንድን ፓርቲ መርጧል ብሎ ለመቀበል አይቻልም፡፡ ይሄ ሞኝነት ነው፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው እያሞኙ ነው የሚል አመለካከት ነው ያለኝ። ምርጫው፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ እውነታ አያንፀባርቅም፡፡ ራስን በራስ ማሞኘት የትም ርቀት አያስኬድም፡፡ አሁንም ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ፣ ራሳቸውን ብቻ የችግሩ አዋቂና ፈቺ አድርገው መቁጠራቸው፣ራሳቸውን ብቻ ከመስማት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ሌላ መንገድ መቀየስ አለባቸው፡፡
አንዳንድ ወገኖች በተለያዩ ሀገራት ያጋጠሙ ክስተቶችን በመጥቀስ፣ግጭቶች ተባብሰው ከቀጠሉ  በግርግሩ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሊከሰት ይችላል ይላሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
የሀገራችን ወታደር እንዲህ ያለውን ነገር እያሰበ ይሁን አይሁን ማወቅ አልችልም፡፡ ግን እንዲህ አይነት ያለመረጋጋት ሲፈጠር ከወታደር ብቻ ሳይሆን ከህብረተሰቡም፣“ወታደሩ የሚገደለውን ገድሎ አንድ ጊዜ አዋጅ አውጆ ቢያረጋጋልን ይሻላል” የሚል የጭንቀት ሃሳብ ሊነሳ ይችላል፡፡ እንደኔ ይሄ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ሀገሪቱን መልሶ ወደ ማትነሳበት አዘቅት ነው የሚከታት፡፡ ደርግ የሰራውን ስህተት መልሶ መድገም ነው የሚሆነው። ወታደሩ ከፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ ነፃ  መሆን አለበት። በፖለቲካ ጉዳይ እየገባ ተፅዕኖ መፍጠር የለበትም። ፖለቲካውን ለህዝቡ መተው አለበት፡፡ የሀገሪቱን ሉአላዊነትና ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ የሱ ሥራ ፖለቲካ ውስጥ ሳይገባ የሀገር መረጋጋት መፍጠር ነው፡፡  
ተቃውሞና ግጭቶች ባየሉባቸው አካባቢዎች፣ዜጎች በቀጥታ በጥይት እየተገደሉ መሆኑን አለማቀፍ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ የኃይል እርምጃ በመውሰድ፣ ተቃውሞን ለማስቆም መሞከር ምን ያህል ያዋጣል?
የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ብዙ መረጃ የለኝም፤ ግን በእንዲህ አይነት ጉዳይ፣የአንድ ሰው ህይወት እንኳ ማለፍ የለበትም፡፡ እንዲህ ያለው የኃይል አማራጭ መቅረት አለበት፡፡ ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፎችን ሲደርግ የተነሱ ነገሮች አሉ፡፡ ከህዝቡ ፍትሃዊና ትክክለኛ ጥያቄ ጋር አያይዘው ጥያቄውን ወደሌላ አቅጣጫ ለማስያዝ የሚሞክሩ ኃይሎች ይኖራሉ፡፡ የመንግስት ኃይሎችም በሰልፉ ወቅት በሚፈጠር ውጥረት፣ከተገቢው በላይ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የተለየ አማራጭ አለ ወይ? ከተባለ፣በሌሎች ሀገሮች አለ፡፡ እኛ ሀገር እዚያ አቅም ላይ ስለመደረሱ አላውቅም፡፡ እኔ በነበርኩ ጊዜ ሰላማዊ ተቃውሞ በጥይት ሳይሆን በሌላ  የምንበትንበት አማራጭ አልነበረንም፡፡ እስካሁን ግን ያንን አቅም ካልፈጠሩ መፍጠር ነበረባቸው፡፡
አሁን ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ችግሮችን በፀጥታ ኃይሎች ለመፍታት የሚደረገው ማንኛውም ሙከራ የበለጠ ነገሩን እያካረረ፣ የበለጠ የሰው ህይወት እያጠፋና በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን የመፍቻ መንገዱ እየመነመነ ነው የሚሄደው፡፡ በዚህ ረገድ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ የህዝብ ተቃውሞዎችን በፀጥታ ኃይሎች መልሼ፣እድሜዬን ትንሽ እገፋለሁ የሚል መንግስት ካለ በጣም የሚገርም ነው፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ሀገር እንዳይፈራርስ ትንሽ ማቆያ ይሆናል እንጂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ዋናው መፍትሄ፤ ገለልተኛ የፖለቲካ ሂደቱን መጀመር ነው፡፡ በአመፅና በግጭት መንግስትን መቀየር፣ እስካሁን የተሰሩትን ስራዎች ይጠራርጋቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የወደፊቱን ማወቅ አያስችልም፡፡ ይህ እንዳይከሰት ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ፣ ከህገ መንግስቱ በመለስ ሌሎችን ህጎች ከልሶ፣ በቀጣይ ውጤቱ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡
ህገ መንግስቱ መሻሻል ካለበት፣ራሱ ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት ነው መሻሻል ያለበት፡፡ ለምሳሌ ዝም ተብሎ አንቀፅ 39ኝን እናንሳ ከተባለ፣ የባሰ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው የሚሆነው፡፡ ዋናው ነገር ግን በፀጥታ ኃይሎች ችግሮችን ለማስታገስ የሚደረገው ሙከራ ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡
ገለልተኛ የፖለቲካ ሂደት መፈጠር አለበት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አሁን  ያለውን የሥራ አስፈፃሚ እንቅስቃሴ እያስቀጠሉ፣ በሚቀጥለው ምርጫ ማንኛውም ፓርቲ ተወዳድሮ ተአማኒነት ያለው ውጤት እንዲመጣና፣ በትክክል ያሸነፈ ፓርቲ ስልጣን እንዲይዝ አልያም እንዲጋራ የሚያስችል ሂደት ይጀመር ማለቴ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን የሃገሪቱ ፀጥታ እየተጠበቀ፣ ተከታታይ ፖለቲካዊ ውይይቶች እየተደረጉ፣ የሚሻሻለው እየተሻሻለ መጓዝ አለብን፡፡
አንዳንድ ፓርቲዎች የሽግግር ጊዜያዊ መንግስት ይቋቋም የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ?
 የሽግግር ጊዜያዊ መንግስት ይቋቋም የሚባለው ሃሳብ፣ በምን የህግ ማዕቀፍ ሆኖ ነው የሚቋቋመው የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡ አንዳንዴ በምክክር፣ሃሳቦች ከህብረተሰቡ መፍለቅ አለባቸው ስል ፤“ይሄ ሞኝነት ነው÷አሁን ያለው መንግስት ከዚህ ቀደም ይሄን ነገር አድርጎ አያውቅም÷ሁሉንም ነገር የሚያደርገው በሃይል ነው፤ አንተ ደግሞ ከፓርቲውና ከመንግስት ነፃ የሆነ የፖለቲካ ሂደት ይጀምር ትላለህ፤ እንዴ ሆኖ ነው ይህ የሚሆነው?” የሚል ጥያቄ ያነሱልኛል፡፡
እኔ ከሁለት ነገር ነው የምነሣው፡፡ አንደኛ፤ ያለው የህግ ማዕቀፍ የሚፈቅደው ይሄንኑ መንገድ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ከሆነ፣ ጉልበት ያለው ይህን መንግስት ካፈረሰ በኋላ የሚመጣ ነው የሚሆነው፡፡ ያ ደግሞ ዋስትና የሌለው፣ ጠቃሚ ያልሆነ  መንገድ ነው፡፡ እኔ ላልኩት አማራጭ ግን ዋስትና የሚሆነው ህዝቡ ነው፡፡ የትግሉ ባለቤት ስለሆነ፡፡ በኃይል መንግስት የሚያወርደውና ስልጣን ሊይዝ የሚችለው ማን አንድ ጉልበተኛ ኃይል ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ገለልተኛ የፖለቲካ ንግግር ሂደቱ የሚካሄድ ከሆነ ግን በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ውጤት ሊገኝበት ይችላል፡፡ ይሄን ሊያደርግ የሚችለው ህዝብ ብቻ ነው፡፡ እኔ የማምነው ዲሞክራሲ፣ ሀሳብ ያላቸው ግለሰቦች ወይም “እኛ እናውቅልሃለን” የሚሉ ፓርቲዎች የሚያመጡት አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ በህብረተሱ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችና አደረጃጀቶች፣ በሚያደርጉት ፍትጊያ የሚመጣ ነው፤ እስከ ዛሬ ግን ያለው፣ ለህዝብ እኔ አውቅልሀለሁ አይነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የት እንደሚያደርስ አይተነዋል፡፡ ስለዚህ ለወደፊትም ቢሆን ዋስትናው፣ የራሱ የህዝብ ጥቅም ነው፡፡ ይሄን አልፎ ለመቀልበስ የሚፈልግ ኃይል ከወታደሩም ይሁን ከሲቪሉ ቢመጣ፣ ሂደቱ የህዝብ ከሆነ አይቀለበስም፡፡
በሰሜን ጎንደር አካባቢ ያለው ተቃውሞ በተለይ ከ“ወልቃይት አማራነት” ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በምን አግባብ ነው መፈታት ያለበት?
እኔ የወልቃይት ጉዳይ ለአንዳንድ ፖለቲካዊ አላማዎች ሽፋን ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ እንዴት ነው የሚፈታው ላልከው፣እኔ የሚታየኝ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሄ ትልቅ ጉዳይ መደረግ አልነበረበትም፡፡ ህውኃትና ብአዴን ተመካክረው መፍታት የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረስ ነበረባቸው፡፡ ማቆየት ካስፈለጋቸውም ህዝብ አሳምነው ማቆየት ይችሉ ነበር፡፡ አሁንም ያለውን ችግር ማወሳሰቢያ እንዳይሆን ሁለቱ አካላት ቢነጋገሩበት ጥሩ ነው፡፡ ደም ከመቃባትና ቁርሾ ከመፍጠር ይልቅ በአካባቢው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች ሰብስቦ መምከር ያስፈልጋል። በህጋዊ መንገድ ስትሄድም ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ መፍታት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የህገ መንግስት ሊቅ አይደለሁም ግን ክልሎች በሚወሰኑበት ወቅት ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪ አካል ውስጥ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ ቋንቋና የህዝብ አሰፋፈርን መሰረት አድርገን እንወስን በሚል ነው የወሰነው፡፡ በዚህ መሰረት ደግሞ የተወሰነው ተወስኗል፡፡  
በወቅቱ ወልቃይት እንዴት ነው ወደ ትግራይ የተካለለው?
አሁን እየጠየከኝ ያለኸው መረጃ ነው፡፡ ይሄን መረጃ አሁን አላስታውሰውም፡፡ እንደዚህ ሆኖ ነበር ብዬ ለማለት አልችልም፡፡ የተጠቀምንበት አቅጣጫ ግን የፌደራሊዝሙን መነሻ ነው፡፡ የህዝቦች ቋንቋና ባህልን መነሻ አድርገን ነው የከለልነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ እዚያ አካባቢ ያለው አብዛኛው ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ነው፤ ባህሉ የትግራይ ነው፤ በትግራይ ውስጥ ሊካተት የሚችል ህዝብ ነው፡፡ የሆነውም በዚህ አግባብ ነበር፡፡ ግን ቆይቶ የማንነት ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ያኔ ስለተወሰነ በቃ መነሳት የለበትም ተብሎ መታሰብ የለበትም፡፡ ጥያቄው ሲነሳ ህገ መንግስታዊና ሰላማዊ ሆኖ ነው መነሳት ያለበት፡፡ በህዝቦች መካከል ግጭት መፈጠር  የለበትም፡፡ ህገ መንግስቱንና አሁን ያለው የፌደራል ስርአት የተዋቀረበት መርህ መነሻ አድርጎ ነው መፈታት የለበት፡፡ አሁን ያለው የፌደራል ስርአት አወቃቀር፣በህገ መንግስቱ ይከለስ ተብሎ ተቀባይነት ካገኘ ደግሞ ጉዳዩም ይከለሳል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ አግባቦች ነው መፈታት ያለበት፡፡
እርስዎ፤ በወልቃይት ጉዳይ የተፈጠረውን ችግር፣ ህውሓትና ብአዴን መፍታት ነበረባቸው ብለዋል፡፡ ሆኖም የሁለቱ ግንኙነት ሻክሯል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ የሰሙት ነገር ይኖር ይሆን?
የአሁን ግንኙነታቸውን አላውቅም፡፡ የድርጅት አባልነቴን ካቋረጥኩ 20 ዓመት አልፎኛል፡፡ ችግር አለባቸው የሚለውን እንደ ማንኛውም ሰው በወሬ ነው የምሰማው፡፡ ድሮ ግን ጠንካራ የትግል አጋርነት ነበረን። አብረን ተዋግተናል፤ ብዙ ስራ ሰርተናል፡፡ ብአዴን እንዲጠነክር  ህውሓት ረድቶታል፡፡ ጥሩ መግባባትና አብሮ የመስራት ባህል ነበረን፡፡ ይሄ ማለት በወቅቱ የሚነሱ ጥቃቅን ችግሮች አልነበሩም ማለት ሳይሆን ሲነሱ በውይይት ነበር የምንፈታው፡፡  እንደዚያ ጊዜ ቢሆኑ ኖሮ አሁን ያለው ችግር በምንም መመዘኛ እዚህ ደረጃ አይደርስም ነበር፡፡ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ነው፡፡ ከዚያ ግንኙነት በመነሳት ነው፤ አሁን ያለው ችግር እንዴት እዚህ ደረጃ እንደረሰ ለኔም የሚገርመኝ፡፡



Read 13100 times