Monday, 25 July 2016 09:01

በህንድ ሴት የሚወልዱ ነፍሰጡሮች በነጻ ይታከማሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በህንድ ጉጅራት አውራጃ የሚገኘው ሲንዱ የተባለ ሆስፒታል ሴት ልጆችን ለሚወልዱ ነፍሰጡር እናቶች ያለምንም ክፍያ የማዋለድና የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
በአገሪቱ የሚገኙት አብዛኞቹ ነፍሰጡር እናቶች ወንድ ልጅ ለመውለድ እንደሚፈልጉና ሴት ሲወልዱ እንደሚበሳጩና እንደሚያዝኑ የጠቆመው ዘገባው፤ሆስፒታሉም ነፍሰጡሮች ሴት ልጆች ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ በማሰብ ነጻ የህክምና አገልግሎቱን እንደ ማበረታቻ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
በህንድ ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት የተዛባ በመሆኑ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሴት ልጅ ጽንሶች በውርጃ እንደሚቋረጡ ወይም እንደተወለዱ እንደሚገደሉ የጠቆመው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ይህን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር እየሰራ እንደሚገኝና  የሆስፒታሉ ነጻ የህክምና አገልግሎትም የዚህ ጥረት አካል እንደሆነ ገልጧል። በሆስፒታሉ ሴት ልጆችን የሚገላገሉ ነፍሰ-ጡር እናቶች ለህክምና አግልግሎቱ መክፈል ከሚገባቸው 20 ሺህ የህንድ ሩፒ  ነጻ እንደሚደረጉ ተነግሯል፡፡
እናቶች የአገሪቱ መንግስት ከ1994 አንስቶ ተግባራዊ ባደረገው ህግ ነፍሰጡር ሴቶች ከወሊድ በፊት የጽንሱን ጾታ በምርመራ እንዳያውቁ መከልከሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ይህም የተደረገው እናቶች ሴት ማርገዛቸውን ቀደም ብለው በማወቅ ጽንሱን ከማስወረድ ለመግታት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ይህም ሆኖ በህንድ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ብቻ 12 ሚሊዮን የሚደርሱ የሴት ጽንሶች በወላጆቻቸው የተዛባ የጾታ አመለካከት ሳቢያ በውርጃ እንዲቋረጡ መደረጋቸው በጥናት መረጋገጡን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1323 times