Saturday, 16 July 2016 12:05

ቴሬሳ ሜይ የእንግሊዝ ሁለተኛዋ ሴት ጠ/ ሚኒስትር ሆኑ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ህዝበ ውሳኔ ማድረጓን ተከትሎ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን የለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፣ ባለፈው ረቡዕ ስልጣናቸውን ለአዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ያስረከቡ ሲሆን ሜይ በአገሪቱ ታሪክ ከማርጋሬት ታቸር ቀጥለው ሁለተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
ላለፉት ስድስት አመታት የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ዋና ጸሃፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት የ59 አመቷ ቴሬሳ ሜይ በአፋጣኝ የካቢኔ አባላትን የማዋቀርና መንግስት የመመስረት ስራ ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱንና የፋይናንስ ገበያዋን የማረጋጋትና ሌሎች ወሳኝ ስራዎችን የመስራት ተልዕኳቸው እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን መነገሩን ገልጧል፡፡
እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ለመውጣት ያሳለፈቺውን ህዝበ ውሳኔ ተፈጻሚ የማድረጉን ሃላፊነት የሚወጣውን ሚኒስትር የመምረጡ ሃላፊነትም፣ አገራቸው በህብረቱ አባልነት እንድትቀጥል ይፈልጉ የነበሩት የአዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጣይ ተልዕኮ ይሆናል ብሏል ዘገባው፡፡
ቴሬሳ ሜይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን መያዛቸው፣ ወሳኝ በሆኑ የስልጣን ቦታዎች ላይ የሚቀመጡ የአገሪቱ ሴቶችን ቁጥር ያሳድገዋል ተብሎ እንደተገመተም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የ49 አመት እድሜ ያላቸውና ላለፉት 6 አመታት  አገሪቱን የመሩት ተሰናባቹ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ከ1895 ወዲህ በዚህ በአነስተኛ እድሜያቸው ስልጣን የለቀቁ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ የ59 አመቷ ቴሪሳ ሜይ በበኩላቸው፤ ከ1976 ወዲህ እድሚያቸው ከገፋ በኋላ ስልጣን ላይ የወጡ የመጀመሪያዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 1243 times