Saturday, 09 July 2016 10:20

በ192 ኪ.ግ ክብደት፣የአለማችን እጅግ ወፍራሙ ልጅ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የኢንዶኔዢያ ህጻናት የውፍረትም፣ የመቀንጨርም ተጠቂዎች ናቸው

   አራያ ፔርማን የተባለውና 192 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው ኢንዶኔዢያዊ ታዳጊ በአለማችን በክብደቱ አቻ የማይገኝለት እጅግ ወፍራሙ ልጅ መባሉን ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ዘገበ፡፡
የ10 አመት ዕድሜ ያለው ፔርማን፤ክብደቱን ተቋቁሞ ቆሞ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ሳቢያ ትምህርቱን አቋርጦ ቤት እንደሚውል የጠቆመው ዘገባው፤ ወላጆቹ ልጁን በአግባቡ ለማሳደግ መቸገራቸውንና በልኩ የተሰፋ ልብስ ከገበያ ላይ በማጣታቸው ጨርቅ እያለበሱት እንደሆነ ገልጧል፡፡
በቀን አምስት ጊዜ ያህል እጅግ ብዙ መጠን ያለው ምግብ የሚመገበው ታዳጊው፤ክብደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የዕለት ከዕለት ህይወቱን አስቸጋሪ እያደረገበት በመሆኑ፣ ወላጆቹ ለልጆቻቸው የሚሰጡትን የምግብ መጠን ለመቀነስ መገደዳቸውንም አስረድቷል፡፡የስምንት አመት ዕድሜ ሳለ ክብደቱ በፍጥነት መጨመር የጀመረውና የምግብ ፍጆታው እጅግ እያደገ የመጣው ታዳጊው፣ በአንዴ የሚመገበው ምግብ፣በአዋቂ እድሜ ላይ ለሚገኙ ሁለት ሰዎች የሚበቃ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፤ታዳጊው አሁን በዳይት ላይ የሚገኝ ሲሆን ጥቂት ኪ.ግ ክብደትም ቀንሷል ተብሏል፡፡
በርካታ የኢንዶኔዢያ ህጻናት በከፍተኛ የክብደት መጨመር ችግር እየተሰቃዩ የመሆናቸውን ያህል፣ ብዙዎቹ የአገሪቱ ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጠቂ እንደሆኑና 8.4 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የመቀንጨር ችግር ተጠቂ መሆናቸውን ዩኒሴፍ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

Read 3366 times