Saturday, 09 July 2016 10:06

በዚምባቡዌ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ተቃዋሚዎቹ ሙጋቤ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል

   የዚምባቡዌ መንግስት ለሰራተኞቹ ደመወዝ መክፈል አልቻለም፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚም ወደ ከፋ ቀውስ እየከተተው ነው በሚል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እየተባባሰ መምጣቱንና በመዲናዋ አብዛኞቹ አካባቢዎች የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የትምህርት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቋረጡን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት የዶላር እጥረት በማጋጠሙ ከደቡብ አፍሪካ ይገዙ የነበሩ የመሰረታዊ ሸቀጦችን ግዢ መከልከሉን ተከትሎ ባለፈው አርብ ቢትብሪጅ በተባለቺው የአገሪቱ የድንበር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ተቃውሞ ማሰማታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ማክሰኞም በርዕሰ መዲናዋ ሃራሬ የታክሲ አሽከርካሪዎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማታቸውንና ይሄን ተክትሎ ፖሊስ 113 አሽከርካሪዎችንና የተቃውሞው ተሳታፊዎችን ማሰሩ ብዙዎችን ማስቆጣቱንና ተቃውሞውን ማባባሱን ገልጧል፡፡ባለፈው ረቡዕም ደመወዛችን አልተከፈለንም ያሉ የአገሪቱ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ተቃውሞውን መቀላቀላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በሃራሬ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና በመዲናዋ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን አስረድቷል፡፡አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በበኩሉ፤የሮበርት ሙጋቤ መንግስት ባጋጠመው የኢኮኖሚ ድቀትና የገንዘብ እጥረት ሳቢያ ለመንግስት ሰራተኞች መክፈል የሚገባውን ደመወዝ ከሚገባው ጊዜ ማዘግየቱን በመጥቀስ፣ በመንግስት ላይ ይደረጉ የነበሩ ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች ሰሞኑን ተባብሰው መቀጠላቸውንና ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ስልጣን እንዲለቁ እስከመጠየቅ መድረሱን ዘግቧል፡፡የአገሪቱ መንግስት የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ሳቢያ ያልከፈለውን ደመወዝ በስራ መስኮች ከፋፍሎ በቀናት እድሜ ውስጥ ለመክፈል ቃል በመግባት ዜጎቹ ተቃውሞውን አቋርጠው በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጥሪ ቢያደርግም፣ ተቃውሞው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መቀጠሉን ያመለከተው ዘገባው፤ተቃዋሚዎች ጎዳናዎችን በመዝጋትና ጎማ በማቃጠል ድርጊቶች ላይ መሰማራታቸውንና የአገሪቱ ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙንና በርካቶችን ማሰሩን ገልጧል፡፡


Read 1481 times