Saturday, 25 June 2016 12:27

በዚህ ሳምንት 10 ሺህ የቻይና ውሾች ይበላሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የምግብ ፌስቲቫሉ አለማቀፍ ተቃውሞ ገጥሞታል

   በደቡባዊ ቻይና ከ10 ሺህ በላይ ውሾች ለምግብነት የሚቀርቡበት አመታዊው የዩሊን የምግብ ፌስቲቫል ከእንስሳት መብት ተከራካሪዎች አለማቀፍ ተቃውሞ ቢገጥመውም ባለፈው ማክሰኞ በይፋ ተጀምሯል፡፡
11 ሚሊዮን የሚደርሱ የእንስሳት መብት ተከራካሪዎችና እንስሳት ወዳጆች የምግብ ፌስቲቫሉ በእንስሳት ላይ የሚደረግ የግፍ ጭፍጨፋ ነው በሚል፣ ፌስቲቫሉ እንዳይካሄድ የተቃውሞ ፊርማቸውን አሰባስበው ባለፈው ሳምንት ለቻይና መንግስት ቢያቀርቡም አቤቱታቸው ሰሚ ማጣቱንና ፌስቲቫሉ በይፋ መጀመሩን ቢቢሲ አመልክቷል፡፡
ለአስር ቀናት በሚቆየው በዚህ የምግብ ፌስቲቫል ላይ ከ10 ሺህ በላይ ውሾችና በሺህዎች የሚቆጠሩ ድመቶች በጅምላ እየተገደሉ ለምግብነት እንደሚውሉ የጠቆመው ዘገባው፣ምንም እንኳን ቻይናውያን ውሻን መመገብ ከጀመሩ 500 አመታት ያህል ቢያስቆጥሩም፣ በዚህ መጠን በአንድ ሳምንት እንስሳቱን መጨፍጨፍ አግባብ አይደለም የሚል ተቃውሞ በስፋት ተስተጋብቷል፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ እንስሳትን በጭካኔ መጨፍጨፍ አግባብ አይደለም በሚል በርካታ የፌስቲቫሉ ተቃዋሚዎች በእንግሊዝ በሚገኘው የቻይና ኢምባሲ ደጃፍ የተቃውሞ ሰልፍ ቢያደርጉም፣ኤምባሲው ተቃውሞውን እንዳልተቀበለ ተዘግቧል፡፡
ሂውማን ሶሳይቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የመብት ተሟጋች ተቋምና የእንስሳት ወዳጆች የሆኑ በርካታ ግለሰቦች በፌስቡክ በከፈቱት ዘመቻ፣ በፌስቲቫሉ ለእርድ ሊቀርቡ የነበሩ 1 ሺህ ያህል ውሾችን ገዝተው ወደ ቤታቸው በማስገባት ከሞት ማዳናቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡


Read 1736 times