Saturday, 11 June 2016 13:38

‘የአዲሳባ ልጅ’ የሥዕል ትርዒት ዳሰሳ (Exhibition Review

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የትርዒቱ ርዕስ፡ የአዲሳባ ልጅ
    ሠዓሊ፡ መዝገቡ ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር)
      የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ስራዎች
ብዛት፡ ሃያ ስራዎች
      የቀረበበት ቦታ፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም፡ ጊዜያዊ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ፡ አዲስ አበባ
     ጊዜ፡ ግንቦት 05-ሰኔ 03: 2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ(የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
እንደ መሻገሪያ
ይህ ዳሰሳና ትችት ‘ወቅቱን ያልጠበቀ’ ወይም ‘ያለፈበት’ ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያት? ትርዒቱ የዕይታ ጊዜው አልፎበታል፡፡ ሆኖም፡ ’የአዲሳባ ልጅ’ የተሰኘው የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሥዕል ትርዒት በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ በተለይም በያዝነው ዓመት ከቀረቡ የሥዕል ትርዒቶች መሃከል በይዘትም ሆነ በቅርጽ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ የዕይታ ጊዜው ቢያልፍበትም ባያልፍበትም ለመዳሰስና ሂስ ለመስጠት አይነተኛ ነው፡፡ እንቀጥል?
1. ‘ቢስ!’ ፡ ‘ይደገም!’  
ረዳት ፕሮፌሰር መዝገቡ ተሰማ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ‘ንግስ’ በሚል ስያሜ በብሔራዊ ሙዝየም፡ ጊዜያዊ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ ለዕይታ ያቀረበው ትርዒት በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ የሠዓሊውንም ሆነ የትርዒቱን ልዩ አሻራ ትቶ ያለፈ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እውነታን ከምጡቅ ምናብ አሰናኝቶ በተለይም ሠዓሊው ከልጅነት እስከ እውቀት፣ በእዝነ-ልቦናው ግዘፍ ነስተው የተቀመጡ የተፈጥሮና የመልክዓ ምድር ቅርጾችን፣ ለዕይታችን እጅግ ገዝፈውና እጅግ ደቅቀው የሚገኙ አካላት ከሰው ልጅና እንስሳት አንጻር፣ የሶስት አውታረ መጠንነትን  በሁለት አውታረ መጠን ሥዕል መተግበር መቻሉን በስራዎቹ አሳይቶ ነበር። ታዲያ ይህ ትርዒት  ‘ቢስ!’ ወይም ‘ይደገም!’ የሚል ጥያቄ ከተመልካች እንደቀረበለት ይነገራል፡፡ ‘ንግስ’ ታላቅ ነበረና ጥያቄው መቅረቡ የሚያስገርም አይመስለኝም! የአቅም ጉዳይ ሆኖ እንጂ በሙዝየሙ ብቻ ሳይሆን ‘ንግስ’ በመላው ሃገሪቱም ተዟዙሮ መታየት ነበረበት፡፡ አሊያም አሁንም የአቅም ጉዳይ ሆኖ ይመስለኛል እንጂ የ’ንግስ’ ትርዒት ሙሉ በሙሉ በሙዝየሙ ቋሚ ስብስብ መካተት ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ምናልባት ወደፊት ይሆናል፡፡ የ’ንግስ’ የ’ይደገም!’ ጥያቄ እውነት ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባልሆንም ረዳት ፕሮፌሰር መዝገቡ ተሰማ  ባሳለፍነው ወር ‘የአዲሳባ ልጅ’ የተሰኘ ሰፊ የተመልካች ዓይነት፡ እጅግ በርካታ ምናልባትም በጎብኚዎች ቁጥር ከፍተኛ የሆነ፡ የተመልካቹን ቀልብና ተመስጦ የገዛ ትርዒት ለሕዝብ ዕይታ አቅርቦ ነበር፡፡ ‘የአዲሳባ ልጅ’፤ የ’ንግስ’ ‘ቢስ!’ ወይም ‘ይደገም!’ ከሆነ ምክንያታዊ መሰረቱ በ’የአዲሳባ ልጅ’ ትርዒት ከቀረቡት ስራዎች ጋር ይጣረሳል፡፡ ‘ቢስ!’ ካልሆነና ራሱን ችሎ የቀረበ ከሆነም ቀጥሎ የማቀርበው ነጥብ ይጎድለዋል፡፡
2. ‘የአዲሳባ ልጅ’ ፡ የትርዒቱ ማንነት(The Identity of the Exhibition)
የትርዒት ማንነትና ምንነት የሚገለጸው ባካተታቸው የስራዎች የአሳሳል ዘዬ(style)፣ ይዘት (content)፣ ቅርጽ (form)፣ ዓይነ-ግብ (subject matter)፣ አቀራረብ (presentation)  እንዲሁም እኒህ ሁሉ ሲጣመሩ የሚሰጡት የትርዒቱ አንድምታዎች ነው። ከነዚህ አኳያም ‘የአዲሳባ ልጅ’ የራሱ የሆነ የትርዒት ማንነቱን የተሟላ ለማድረግ እምብዛም የተጨነቀ አይመስልም። እያንዳንዱን የትርዒቱ አናስራት(elements) ነጥለን ስንመለከት የጎደለው ነገር እንዳለ አይሰማንም፡፡ በዚህ ረገድ ከሠዓሊው የዳበረ ልምድ፡ ከገነባው ሥነ-ጥበባዊ ግለሰባዊነትና ከዘለቀበት ከፍታ አንጻር እንዲያው በደፈናው (by default) የሚጠበቅ ነው፡፡ በርግጥም ምሉዕ ሥነ-ጥበባዊ ሰብዕናውን በእያንዳንዱ ስራው ላይ እናያለን፡፡ ሆኖም፡ አንድ ትርዒት የመታያ ጊዜው ካበቃ በኋላ በተመልካቹም ሆነ በሠዓሊው እዝነ-ልቦና የሚቀረው ትርዒቱ ትቶለት ያለፈው ወጥ ምስልና እሳቤ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ግን ‘የአዲሳባ ልጅ’ ጠንካራና ሁለንተናዊ ምስል እንዲሁም የተገራ የትኩረት አቅጣጫ ትቶልን ያለፈ ትርዒት እንዳልነበረ ምክንያቶቼን በመደርደር እተቸዋለሁ። ጠንከር ያለ ትችት ማቅረብ ከማይቻልበት አንደኛው ነጥብ ብጀምር፣ ‘ከብርሃን ተቃራኒ’ የተሰኘው ስራው በዘዬ፣ በይዘትና በዓይነ-ግብ ከሌሎች ተነጥሎ ለብቻው የሚታይ እንጂ በአንድ ትርዒት ለመቅረብ አጥጋቢ ምክንያት የለውም። በእርግጥ ይህ የብርሃንን አቅጣጫ ለማጥናትና ሌሎች ስራዎቹ ላይ የሚጠቀምበትን ቴክኒክ ማሳያ ሊሆነው ይችላል። ነገር ግን፡ ይህ ከስያሜም የሚልቅ ‘የአዲሳባ ልጅ’ በሚል ርዕስ በቀረበ ትርዒት ውስጥ (እንደ ሟሟያ) መካተቱ ለትርዒቱ አውራ ትኩረት መነፈጉን ያሳያል፡፡
ለትርዒቱ ተብሎ በተዘጋጀው ካታሎግ ውስጥ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ስራዎቹን የሰራበትን መነሾዎችና መደንግጉን (artist statement) ከማቅረብ ይልቅ ትምህርታዊ ጽሁፍ ነው ያቀረበው፡፡ ሙሉ መብቱ የሠዓሊው ነው፡፡ ይህ አይነቱ አቀራረብ በራሱ ጥልቅ ምሁራዊ እይታና ምርምር ይጠይቃል፡፡ በመምህርነት የአንድ ትውልድ እድሜ የሚሆን ጊዜ በአዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ላሳለፈው ረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ይህ የሚቻለው በመሆኑም ነው ያደረገው።  የመደንግጉ (artist statement) አለመኖር የሚያመላክተው ክፍተት ግን ለትርዒቱ ማንነትና ምንነት የሰጠው ቦታ አለመኖሩን ነው፡፡ በተለይ በይዘት ከሌሎቹ ስራዎች ጋር ለማይደጋገፉትና የትርዒቱን ስያሜ ለተሸከሙት ከቁጥር 1-3 ላሉት፣ ‘የአዲሳባ ልጅ’ ለተሰኙት ስራዎች ማብራሪያ እንኳን ባይሆን የዓይነ-ግብና የይዘት ለውጥ ያሳየበትን አመክንዮ ጠቆም አለማድረጉ፣ ትርዒቱን እንደ ትርዒት ማንነት የሚያሳጣው ነጥብ ነው፡፡ እነዚህ ስራዎች ከሌሎቹ ጋር ያላቸውን የሃሳብ ዝምድና ለማየት የሞከርን እንደሆነም ትርዒቱን አንድምታ ያሳጣዋል፡፡
ተመልካች ስለ ትርዒቱ ወጥ እሳቤ እንዳይኖረው ተደናቅፏል ባይ ነኝ፡ ይልቅስ በተለይ ዓይኑና የዕይታ ባሕሉ ያልሰለጠነው ተመልካች፤ እንደ ሠዓሊው ፍላጎት፣ ቅርጽና እይታዊ መስህብ እንዲሁም ‘የቀለም ቅብ ምትሃታዊ እንቅስቃሴ’ ላይ እንዲደመም ሆኗል፡፡ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ስለ ስራዎቹ ከሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡና ከአድናቂዎቹ ጋር ባደረገው ውይይትም፤ ’የሥነ-ጥበብ እድገት ሊረጋገጥ የሚቻለው ለቅርጽ በሚሰጥ ትኩረት’ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ሥነ-ጥበብን ከነባራዊው የሃገራችን ዓውድ አንጻር ስንመለከተው፣ ሰዓሊው የሚሞግተው ነጥብ አግባብነት ያለው ይሆናል።  ሠዓሊው የሚጠቀማቸው ዓይነ-ግቦች ቀጥተኛ መረዳት፡ ግንኙነትና እይታዊ መስህብ ሊፈጥርላቸው ለሚችልላቸው ተመልካቾች ወይም የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለስራዎቼ ይስማማልኛል ለሚላቸው የቅርጽ አትኩሮቶች አጽንኦት መስጠቱ ብልህነት ነው፡፡
ለይዘት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለመስጠት አሁንም በሠዓሊው ፈቃድና ነጻነት ስር የሚያልፍ መሆኑን ሳልዘነጋ፤ ሥነ-ጥበብ ለምንኖረው ሕይወት የሰላ እይታ እንዲኖረን እሴት ከመጨመር አንጻር የሚኖረውን ፋይዳ እንደ ‘የአዲሳባ ልጅ’ የትርዒት አርዕስትነትና እንደ ሰዓሊ  መዝገቡ ተሰማ ባለ ታላቅ ሠዓሊነት ከመዳሰስም አልፎ፣ ረገጥ ተደርጎ መወያያ መሆን ነበረበት የሚል ነው አቋሜ፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ከትርዒት ማንነት ባሻገር የሥነ-ጥበብን ህላዌ እንድንፈትሽ ያስችለናል፡ ስለ ትርዒት ማንነትና ምንነት ማንሳት የፈለግኩትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
3. ‘የአዲሳባ ልጅ’ - ውይይት
በሃገራችን የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ በሥዕል ትርዒት ዙሪያ ውይይት ሲደረግ በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች ያውም ከከያንያኑ የዘለለ ተሳታፊዎችን ማየት ብርቅ ነገር ነው፡፡ ‘የአዲሳባ ልጅ’ በርካታ የሥነ-ጥበብ ቤተሰቦችን ያፈራ እንደነበር ውይይቱ ላይ የተገኙት ከሶስት መቶ በላይ ተሳታፊዎች የትርዒቱን ስኬታማነት ያመላክታሉ፡፡ ይሄ ያስደስታልም፡ ያኮራልም፡፡ የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ የግል ጥንካሬ በመሆኑም መመስገን ይገባዋል፡፡
በሥነ-ጥበብ ዙሪያ ትንታኔዎችን በማቅረብና የሥዕል መሳያ ቀለሞችን በሃገራችን በማምረት የሚታወቀው ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ፤ ስለ ትርዒቱ፡ ስለቀረቡት ስራዎች በተለይም ረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ  አሜሪካ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ስራዎቹ ስለመቀየራቸው ባቀረበው ጽሁፍ ነበር ውይይቱ የተጀመረው፡፡ ሠዓሊ  መዝገቡ ተሰማ  ስለዚህ ጉዳይ አስተያየትም ሆነ ማብራሪያ አለመስጠቱ፣ተሳታፊው ራሱ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ የፈቀደ ይመስላል፡፡ ሆኖም ይህ አይነቱ ገለጻ፤ ከሠዓሊው የአሰራር ልምድ፡ ሂደትና ለውጥ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ፣ የሠዓሊው አተያይ ይጠቅም ነበር ባይ ነኝ፡፡ ቀጥሎ ከመድረክ የቀረበው ጽሁፍ የጋዜጠኛ ይትባረክ ዋለልኝ ሲሆን የአቶ ሰለሞን ተሰማን ጥናታዊ ጽሁፍ መሰረት ያደረገና የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ  መዝገቡ ተሰማ’ን ስራዎች፣ሃገረሰባዊ ማንነት በማላበስ የሚያትት ነበር፡፡ ከታዳሚው ወደ ቀረቡ አስተያየቶች ስንመጣ፡  ሠዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ፤ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ባዳበረው አሳሳል ተከታዮች እያፈራ በመሆኑ ‘መዝገብኛ’ ተብሎ ሊሰየም የሚችል አሳሳል መምጣቱን በመጠቆም አስተያየት የሰጡ ሲሆን ከረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ የተሰጠ ምላሽ  አልነበረም፡፡
በሥነ-ጥበብ ታሪክ ግለሰቦችና ቡድኖች ያዳበሩትንና የሚከተሉትን ዘዬም ሆነ ፍልስፍና በManifesto አስደግፈው ያውጃሉ፡፡ የሥነ-ጥበብ ታሪክ አጥኚዎችና ተመራማሪዎችም ስለ ሠዓሊዎች ስራ፡ አሰራርና ፍልስፍናም ጥናትና ምርምር በማድረግ ስም ያወጡላቸዋል፡፡ የሠዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ ግላዊ አስተያየት፣ ምን ያህል በጥናት የተደገፈ እንደሆነ ባላውቅም ‘መዝገብኛ’ የሚለው ስያሜ አሁንም የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ’ን ሥነ-ጥበባዊ ጉዞ መሰረት ያደረገ በመሆኑ፣ የሠዓሊው ይሁንታ ወይም አሉታ አሊያም ማብራሪያ ያስፈልግ ነበር ባይ ነኝ፡፡ ውይይቱ ካስተናገዳቸው አዝናኝ አስተያየቶች መሃከል ፤’ጥበብ በፍቅር ቃላት ብቻ ነው የምትዳብረው’ በሚል ከዚህ ውጪ ትችት አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚሰብከው አስተያየት አንዱ ነበር፡፡ የፍቅር ቃላት ብቻ ሳይሆን ጥበብና ፍቅር የሚነጣጠሉ አይደሉም፡፡ ሆኖም፡ ያለ ትችትና ያለ ሂስ የሥነ-ጥበብ አካሄድ ሊቃና አይችልም፡፡ ቸር ይግጠመን!





Read 883 times