Saturday, 11 June 2016 12:34

ረመዳን - የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የነጻነትና የክብር መገለጫ ይሁንልን

Written by  በተሾመ ብርሃኑ ከማል
Rate this item
(2 votes)

      በረመዳን ወር ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በርካታ በረከት የሚያስገኙ መልካም ነገሮች ያከናውናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡  በዚህም ምክንያት ሙስሊሞችና የሌላ እምነት ተከታዮች ወሩ መልካም የጾም ጊዜ ሆኖ እንዲያልፍ ምኞታቸውን ይገልጻሉ። እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያና የመሳሰሉት አገራት መሪዎች ደግሞ ኅብረተሰቡ በሰላም፣ በመረጋጋት፣ በነጻነትና በክብር እንዲያሳልፈው መልዕክታቸውን በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን ያስተላልፋሉ፡፡  በረመዳን ወር እንደዚህ ያለውን የላቀ ኢስላማዊ  ስነምግባርን ሲያሳይ በአካባቢው የሚገኙ የሌሎች እምነት አባቶችና ተከታዮች የላቀ ከበሬታን ይሰጡታል። በልዩ ልዩ አገሮች የሚገኙ የክርስትናና የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች «የእንኳን አደረሳችሁ» መልእክት የሚያስተላልፉ ከመሆናቸውም በላይ ለዚህ ወር ትኩረት በመስጠት ስለ ዓለም ሰላም፣ አብሮ መኖር፣ መቻቻል፣ የእርስ በርስ መተሳሰብና ፍቅር እንዲሰፍን ያስተምራሉ፡፡
በሃይማኖቶች መካከል የአስተምህሮት ልዩነት ቢኖርም ሁሉም ከፈጣሪ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደሚያመሳስላቸው አበክረው ያወሳሉ፡፡ እንደ ኩዌት ባሉ አገሮች አብያተ ክርስቲያናት፣ ሙስሊሞች ጾም እንዲይዙባቸው ወይም ጾመው ከዋሉ በኋላ እንዲያፈጥሩባቸው ይጋብዛሉ፡፡ ከሙስሊሞች ጋርም አብረው አንድ ማዕድ ይመገባሉ፡፡ «በአንድ ማዕድ ስንበላ የበለጠ አንድ እንሆናለን» በማለትም ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች ለሰላምና ለፍቅር ተቀራርበው መጣር እንዳለባቸው ማስተማሩን በተግባር ያሳያሉ፡፡ እንዲህ በሚያደርጉ አገሮች በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ረመዳን በዋነኛነት ከማንኛውም ወር ሁሉ በበለጠ መልኩ ራስን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት፣ በሰላምና በመቻቻል ማለፍ ያለበት ወር መሆኑን በሃይማኖቱ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው አባቶች አበክረው ያሳስባሉ፡፡ ሙስሊሞች ወርሃ ረመዳንን ራሳቸውን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት ያሳልፋሉ ሲባል በሰዎች ውስጥ የሚገኝን የስግብግብነት፣ የራስ ወዳድነት፣ የምቀኝነት፣ የተንኮል፣ የጠብ ጫሪነት፣ የትንኮሳ፣ የሌሎችን መብት የሚጻረር ተግባር፣ ከመሳሳሉት መጥፎ ባሕርያትን ሁሉ በመቆጣጠር ራሱን ለፈጣሪ ያስገዛል ማለትን ይጨምራል፡፡
ቅዱስ ቁርዓን የሚያስተምረው ኅብረተሰቡ የዘር፣ የጾታ፣ የሃይማኖት፣ የዜግነትና የቀለም ልዩነት ሳያደርግ ከሁሉም ጋር ተቻችሎ እንዲኖር፣ በጥልቅ ሃይማኖታዊ ስሜት፣ በፍቅር፣ በመደጋገፍ፣ የሰውን ታላቅነት ተቀብሎ አስፈላጊውን ሁሉ ክቡር መስጠት፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተቸገሩን በመርዳት እንዲያሳልፈውና ከፈጣሪ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያድስ ነው፡፡
የተለያየ እምነት፣ ዘር፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ቀለም ወዘተ ያላቸው ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ አንድ መሆናቸውን የሚቀበል ሙስሊም፤ በረመዳን ወር የበለጠ ማሰብ የሚኖርበት ሰዎች በሰውነታቸው አንዳቸው ሌላቸውን ሳይጎዱ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመግባባት፣ በስምምነት፣ በወንድማማችነት ስሜት እንዴት እንደሚኖሩ በማሰብ መሆን እንዳለበት ቅንጣት እንኳን የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በራሱ የሚተማመንም በዕውቀት ለመብለጥ እንጅ በኃይል ለማንበርከክ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ያውቃል፡፡ የፈጣሪን ትእዛዝ እቀበላለሁ የሚል አማኝም፤ ዕውቀት ተቀዳሚው ሥራ እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ ለእምነት ሲባል የሚወጣ ወጪ ቢኖር ከፍተኛው ለትምህርት መዋል እንዳለበት እሳቤ ይሰጣል፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በጭፍን በደል እያነሳ ከሚቆዝም ወደፊት ላለው ኅብረተሰብ የሃይማኖት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የሕግ፣ የወታደራዊ ጥበብ፣ የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ጥበብ፣ የሕክምና፣ የምሕንድስና፣ ወዘተ ምሁራን የመኖራቸው አስፈላጊነት ከምን ጊዜውም የበለጠ ግልጽ ሆኖ ሊታየው ይገባል፡፡ በዚህ ዓመት ረመዳን መታሰብ ያለበትም በዚህ መልኩ እንደሆነ የዚህ ጽሐፍ አዘጋጅ ያምናል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የረመዳን ወር
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የረመዳን ወር ማስታወስ ያለባቸው ሌላው ዋነኛው  ቁም ነገር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ክልል፣ ኩሩ የመሆናቸውን ያህል ከሌሎች አገሮች በሚነሳ ማዕበል የማይናጡ ጠንካራ ሕዝቦች መሆናቸውን ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል የእምነት ልዩነት ቢኖርም ሰብአዊ ፍጡር መሆናቸውን፣ ተመሳሳይ ባህል፣ ተመሳሳይ ታሪክ፣ ተመሳሳይ ልምድ፣ ተመሳሳይ ሥነ አእምሮ የሚጋሩ መሆናቸውም የበለጠ ቢያዳብር እንጂ አያቀጭጭም፡፡
በመሠረቱ በአገራችን ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ክፍሎች የሚኖሩት አብረው ነው፡፡ በአንድ ግቢ ብቻ ሳይሆን በአንድ ቤት ውስጥ ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች አብረው የመኖራቸው ጉዳይ እንግዳ አይደለም፡፡ በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ መስክ አንዱ የሌላው ጓደኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ አንዱ ሌላውን ከእምነቱ ተከታይ የበለጠ ያምነዋል። ያከብረዋል፡፡ ይህ ጾታን፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብን፣ ዘርን፣ ክልልን፣ የሚለይ አይደለም። ሐዘን ወይም ደስታ ቢኖር ሙስሊሙ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ የሐዘን ተካፋይ ወይም የደስታ ተካፋይ ቢሆን፤ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ጎን መስጊድ ቢሠራ፤ የአንዱን ጸሎት ሌላው ቢያዳምጥ የሚሰማው የከፋ ስሜት የለም፡፡ ከሚያለያዩት ነገሮች ይልቅ የሚያገናኙት ነገሮች እንደሚበዙ ስለሚገነዘብም ተቻችሎ ይኖራል፡፡ ስለዚህም፣ «ኢትዮጵያ፣ ሕዝቦቿ በሰላም፣ በመከባበር፣ በመፋቀር፣ በመተባበር፣ የሚኖሩባት የተቀደሰች ስፍራ ናት፤» ተብሎ የሚነገርላትም ለዚህ ነው፡፡ ከሠላሳና ከአርባ ዓመታት በፊት በፖለቲካ መሪዎች አነሳሽነት አልፎ አልፎ ሁከት ሲፈጠር በቀላሉ ይቀዘቅዝና ይረሳ የነበረውም ለዚህ እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ፣ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሙስሊሞች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ለሕዝቦች በሰላም አብሮም መኖርና መከባበር ጠንክረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ፣ ቱርክ፣ ሊባኖስ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ፓኪስታን፣ ናይጀሪያ፣ ማሌዢያ፣ ያሉ የተለያየ ሃይማኖት የሚገኝባቸው አገሮች በመጫወት ላይ ያሉት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ከሃይማኖታዊ ምክንያት ይልቅ ፖለቲካዊ አመለካከት እያየለ አልፎ አልፎ ችግር መስተዋሉ አልቀረም፡፡ ይህም በአገራችን ሙስሊም፣ ክርስቲያንና ኦሪታውያንን እርስ በእርስ በማለያየትና አንዳቸውን ከሌላቸው በማበላለጥ ይጠቀሙበት እንደነበረው ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ኢስላምን በሚመለከት በአልመኢዳህ (5፡48) «ወደ እናንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በእርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በእውነት አወረድን። በመካከላቸውም አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፡፡ እውነቱም ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌዎችን አትከተል። ከአንተ ለሁሉም ሕግና መንገድን አደረግን፡፡ አላህ በሻ ኖሮ አንድ ሕዝብ ባደረግሁት ነበር፡፡ ግን በሰጣችሁ ሕግጋት ሊሞክራችሁ (ለያያችሁ)፡፡ በጎ ሥራዎችንም ለመሥራት ተሽቀዳደሙ፤ መመለሻችሁ በጠቅላላ ወደ አላህ ነው፡፡ በእርሱም ትለያዩበት የነበራችሁትን ነገር ይነግራችኋል» ተብሎ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ነቢዩ መሐመድም (ሱዓወ) ከክርስትናና ኦሪት ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ተከባብረው አብረው ኖረዋል። አቡዳውድ የተባሉት የነቢዩ ሙሐመድ ሐዋርያ እንደጠቀሱት፤ «ማንኛውም ሙስሊም ያልሆነ ዜጋን የጎዳ እኔን እንደጎዳ ይቆጠራል፤» በማለት በመጀመሪያው የሙስሊም ዓለም የሃይማኖት ነፃነትና ብዝህነትን ያረጋገጡትም እርሳቸው ናቸው። በሌላ አነጋገር እንኳንስ በተመሳሳይ እምነት ጥላቻን ማናፈስ በተለያየ ሃይማኖት ላይ ተመሳሳይ ችግር መፍጠር ትክክል አለመሆኑን ነው፡፡ ዳሩ ግን ሙስሊሙ በእንዲህ ያለው ጥብቅ መሠረት እምነት የሚመራ እንጅ አክራሪም፣ አሸባሪም አለመሆኑን በተግባር ማሳየት ያለበት ራሱ መሆኑን ነው፡፡  
ዶክተር አስላም ዓብዱላህ የተባሉ የሃይማኖት አባት የረመዳን ጾምን፤«ሙስሊም ያልሆኑ ወዳጆቻቸውን ወደ ቤታቸው በመውሰድ አብረዋቸው እራት እንዲበሉ መጋበዝ፣ ቤት የሌላቸውን በመመገብ፣ ሕዝባዊ ጠቀሜታ ላለው መልካም ተግባር ገንዘብ አዋጥቶ በመስጠት፣ በሌሎችም ሆነ በራሳችን ምክንያት የተፈጠረ ችግር ቢኖር ይቅርታ በመጠየቅና ይቅርታ በማድረግ፣ ምንም ያህል የሚያስቆጣ ሁኔታ ቢገጥመን ታጋሾች በመሆን... ልናሳልፈው ይገባል፤» ሲሉ መክረዋል፡፡
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ፤ፈትሑላህ ጉለን በጥልቅ ዕውቀታቸውና በተባ ብዕራቸው «የነፍሳችን ሐውልት» በሚል ካዘጋጁት መጽሐፍ ያገኘውን እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡  
«መጾም ለመክሳት ሲባል ወይም ከምግብና ከመጠጥ ራስን ለተወሰነ ጊዜ ለመከልከል ሲባል የሚደረግ በፍጹም አይደለም፡፡ በየዕለቱ የሚደረጉ ጸሎቶች ለመቀመጥና ለማጎንበስ ታስበው የተዘጋጁ የአካል ማሰልጠኛ ስፖርቶች አይደሉም፡፡ ምጽዋት መስጠት ካለው ገቢ ትንሽ ግብር መክፈል ወይም በማያውቁት አገር የሚገኙ ለማያውቋቸው ችግረኛ ሰዎች ከችግራቸው ፋታ እንዲያገኙ ሲባልና፣ ለማይታወቅ ዓላማ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሐጅ መሄድ ሲባል ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመጓዝ ያጠራቀሙትን የአገር ውስጥ ገንዘብ ወደ ውጭ ምንዛሪ ለውጦ ማጥፋት አይደለም። ወይም ወደ ሐጅ ለጸሎት የሚሄዱበትን መሠረታዊ ምክንያት አውቀው ካልሄዱ በስተቀር «ሐጅ» የሚለውን ስምና ከዚያ ጋር የሚገኘውን ዝና ለማግኘት ከመሆን አይዘልም። እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች በምሕዋራቸው ዙሪያና በተዘረጋላቸው መስመርና መንፈስ በተግባር ካልዋሉ በስተቀር ከሌላው የዕለት ተዕለት ተመሳሳይ ሥራ እንደምን ተለይተው ሊታዩ ይችላሉ? በአምልኮ ተግባር ውስጥ ቁጥርን ለማብዛት መንቀሳቀስ ከልጅነት ጨዋታ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥያቄ ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር በከንቱ መጮህና ማንቧረቅ የድምፅ ሳጥንን ከማለማመድ/ከማሰልጠን የተለየ ሊሆን አይችልም፤» በማለት ያስረዳሉ፡፡
የረመዳን ወር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ልቦና የሚመለስበት፣
የረመዳን ወር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ልቦና የሚመለስበት፣ ተክሎች አበባ በሚያወጡበት ወራት እንደሚያምሩት ሁሉ የሙስሊሙም ልቦና የሚያብብበትና የሚያምርበት፣ ራሱን በፈሪሃ እግዚአብሔር (ረቢል ዓለሚን) የሚያስገዛበት፣ ልቡን የሚያጠራበት፣ የደረቀ ቀልቡን የሚያርስበትና የሚያረሰርስበት፣ የፈጣሪ ጥልቅ ፍቅር በልቦናው የሚያድርበት፣ በደግነትና በቸርነት የሚሞላበት፣ ሁለመናው ጥሩ እንዲሠራ ጥረት የሚያደርግበት ነው፡፡ እያንዳንዱ ስለ ኢስላም የሚያውቅ የሚያደርገው ነገር ሁሉ በረመዳን ወር ከሰባት እስከ መቶ እጥፍ ድርብ ምንዳ (በረከት) እንደሚያገኝበት አጥብቆ ይገነዘባል፡፡ ሙስሊሙ በረማዳን ወር ከመስረቅ፣ ከመቅጠፍ፣ ከማጭበርበር፣ በሐሰት ከመመስከር፣ ከመመቅኘት፣ ወዘተ ርቆ በፀፀት ያሳልፋል፡፡ ፀፀቱም ዳግም ላለመሥራት መሆኑንም ለራሱና ለፈጣሪው ቃል ይገባል፡፡ ትክክለኛ ነገር ማድረግን ይመርጣል፡፡ የተቀደሱ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
ከረመዳን ወር በፊት በነበሩት ወራት ያደርገውን የነበረ በጎ ተግባር ያልቃል፡፡ በሽተኛን ይጠይቃል፡፡ የተራበን ያበላል፡፡ የታረዘን ያለብሳል፡፡ የሞተን ይቀብራል፡፡ የታሰረን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም ይፀልያል፡፡ ምህረትንም ይጠይቃል፡፡ የሙስሊሙንና የሌላውን ኅብረተሰብ ሰላም ከሚያደፈርሱ ነገሮች ሁሉ ይርቃል፡፡ በረመዳን ወር ድባቡ ሁሉ ደስ በሚሉና ደስ በሚያሰኙ ተግባራት ይሞላል። አንዳንድ ሰዎች መፆም እንደሚያደክም ይናገራሉ፡፡ በእርግጥም የሚፆመው ከ13 ሰዓት በላይ ነውና ሊያደክም ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ወር ከፍተኛ ምንዳ ለማግኘት ለሚሻ ወሩ እንዲረዝምለት ባይሻም በእየአንዳንዱ ቀን፣ ሰዓትና ደቂቃ በጎ ነገር ለማከናወን ይጥራል፡፡ በበጎ ነገር ይደሰታል፡፡ በበጎ ሥራው ይፈነጥዛል፡፡ የቀንም የሌሊትም ሐሳቡ ፈጣሪውንና ሰውን ማስደሰት ነው፡፡ አንድ ቀን አልፎ ሌላው ሲተካ የምኞቱን ያህል ሳይሠራ የሚቀር ስለማይመስለው የበለጠ በጎ ነገር ለመሥራት ይጣደፋል። ወሩ እየተገባደደ ሲሄድም ‹‹አይ እኔ፣ ለመሆኑ ፈጣሪን የሚያስደስት ተግባር ምን ያህል አከናወንኩ?›› ብሎ ራሱን ይጠይቃል፡፡ ‹በሚቀጥለው ዓመት ላይ ደርሼ ተመሳሳይ በጎ ተግባር ለማከናወን እችል ይሆን?›› ብሎም በፍርኃት ፈጣሪውን ያስባል፡፡ የሌላው እምነት ተከታይ በረመዳን ወር ሙስሊም ወንድሙ ሲፆም ማሰብ የሚኖርበትም ይህንን በጎ አመለካከት ነው፡፡ ይህን ሲያደርግም አጻፋውን ከሰውም ከፈጣሪም ያገኛል፡፡
የሙስሊሙና የሌላው እምነት ተከታዮች ትብብር ከምን ይመነጫል?
ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የተለያዩ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም በአንድ ፈጣሪ ብቻ ማመናቸው፣ በነቢያት፣ በመላዕክት፣ በፆም፣ በመስገድ፣ በምፅዋትና በመጨረሻው ቀን እምነታቸው በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ከሌሎች ሃይማኖቶች በተለየ ሁኔታ የበለጠ ተቀራራቢ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም የፈጣሪ ባሮችና አገልጋዮች መሆናቸውን፣ ሁለቱም በዚች ዓለም ላይ የሚደርስባቸውን የፈጣሪ ፈተና አልፈው ገነት እንደሚገቡ ወይም ካላለፉ ሲኦል እንደሚወርዱ ያምናሉ፡፡ ይልቁንም ሙስሊሞች ኢየሱስ የፈጣሪ ቃል እንደነበረና ያም ቃል በቅድስት ማሪያም ማህፀን አድሮ ሰው ሆኖ መወለዱና በኋላም የፈጣሪን ቃል አስተምሮ ማረጉን ያምናሉ፡፡ ኢየሱስን የማያፈቅርም የተሟላ ሙስሊም ሊሆን አይችልም፡፡ ቅድስት ማሪያምን ያከብራል፡፡ ያፈቅራል፡፡ ለክርስቲያኑ ፈጣሪ ‹‹ሕያው ዘይመውት ነው፡፡›› ለሙስሊሙም እንደዚሁ፡፡ ክርሰቲያኑ ‹‹እንአምን በሐዱ አምላክ›› ይላል፡፡ ሙስሊሙም እንዲሁ፡፡ ሁለቱም በጾም፣ በጸሎት፣ ለፈጣሪ በመስገድ፣ በመጨረሻይቱ ዕለትና በፍርድ ቀን ያምናሉ፡፡ ክርስቲያኑ ‹‹ካለኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ›› የሚለውን ቃል አጥብቆ ይከተላል፡፡ ሙስሊሙም ከፈጣሪ ጋር ሌላ አያጋራም፡፡ ከእርሱ ጋር ሌላም አያወዳድርም፡፡ በቀጥታ ፈጣሪን ብቻ ይለምናል፣ የሚፈልገውንም እሱን ብቻ ይጠይቃል፡፡
የዚህ ዓይነቱ በጎ አመለካከትና የጠለቀ ዕውቀት ሲኖር የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ መምህራን ለሥጋና ለመንፈሳዊ ልጆቻቸው አንደኛው ሌላውን ከማንቋሸሽ፣ ስም ከመስጠት፣ ከማጠልሸት፣ ከማዋረድ ይልቅ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ መፋቀር፣ መቻቻል እንዲኖር ማስተማር የላቀ መሆኑን ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ በእርግጥም የነገው ብሩህ ተስፋ፣ የመቻቻልና የመፋቀር ዓለም በዛሬ ልጆች ላይ የተመሠረተ ነውና በቤት ውስጥም ሆነ ውጭ ስለ ሌላው ሃይማኖት ሲናገሩ በአክብሮት እንጂ በማንቋሸሽና በማጥላላት እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከተቻለም ልዩነቶችንና ተመሳሳይነቶችን አውቆ ማስረዳት ይገባል፡፡ በተለይም በረመዳን ወር ሙስሊሙ ለክርስቲያኑ ደግነትን፣ መከባበርን፣ መቻቻልን፣ በአጠቃላይ በጎ አርዓያነት ማሳየት፣ አስተምህሮቱን፣ መለያ ምልክቱን፣ ቤተ አምልኮቱንና እሴቱን ማክበር ሲኖርበት፤ ክርስቲያኑም ለሙስሊም ወንድሙ ተመሳሳይ ሁኔታ ማሳየት ይጠበቅበታል። ይህም ማለት ‹‹ትክክል ነው? አይደለም፤ ፀዳቂ ነው? አይደለም፤›› የሚሉትን ሁሉ ለራሱ ለፈጣሪና ለእምነቱ ተከታይ በመተው በሰውነቱ ሊቀበለው፣ ሊያውቀውና ሊያከብረው ይገባል፡፡
ሙስሊሙ ፀሎት የሚያደርገው ለራሱና ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን በአንድ ፈጣሪ ለሚያምኑ ሁሉ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የሌላው እምነት ተከታይ በአንድ ፈጣሪ ለሚያምነውና በራሱ መንገድ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለሚፈጽመው ሙስሊም ኅብረተሰብ ቢቻል በፀሎት፣ ይህ ካልሆነ በጎ ነገር በማድረግና ደግ በመሆን በሚቻለው መንገድ ሁሉ መርዳት ይጠበቅበታል፡፡ ለመሆኑ አንደኛው ሌላውን ሲረዳና ሲያከብር ማየት ይሻላል? ወይስ አንደኛው ሌላውን ሲያጠቃና ሲያንኳስስ? አንደኛ ሌላው ተደስቶ ሲያይ ቢደሰት ይሻላል? ወይስ በአንዱ ደስታ ሌላው ቢከፋ? ሁለቱ ሃይማኖቶች ምቀኝነትን፣ ክፋትን፣ መጥፎ ምኞትን ይሰብካሉን? ሁለቱም ሃይማኖቶች መከባበርን አይሰብኩምን? ለመሆኑ እንኳንስ ስለ ሌሎች ስለ ራሳችን እምነት ምን ያህል ጠልቀን እናውቃለን? አንደኛው ወደ ሌላው የሚሳበው በፍቅር ወይስ በጥላቻና በእብሪት? መመራት የሚገባውስ በመጻሕፍቱ ወይስ በስሜት? ስሜታችንን ስንከተል ልንሳሳት እንችላለን። በመጻሕፍቱ ስንመራ ግን የመረዳዳትንና የመከባበርን ትሩፋት ልንጎናጸፍ እንችላለን፡፡ በኃይል፣ በጥላቻ፣ በመናናቅና በጦርነት ለመሳብ ወይም ለማንበርከክ የሚሻ ቢኖር ዘመኑ ያለፈበት አስተሳሰብ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል፡፡
የሌላ እምነት ተከታዮች ለሙስሊሞች ምን ሊያደርጉላቸው ይችላሉ?
ሌላው እምነት ተከታይ የራሱን ፆም ሲፆም የሚሰማው ሁሉ ሙስሊሙ ኅብረተሰብም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊሰማው ስለሚችል በሚከተሉት መንገዶች ርህራሔንና ደግነትን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከሁሉ አስቀድሞ ራስን ከጥላቻና ከንቀት ማራቅን ይጠይቃል፡፡ በእርግጥም ዓለም ከተፈጠረና ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ስናስበው ከጥላቻና ንቀት መርዝ የሚመነጨው አጸፋው ነውና ራስን ከጥላቻና ከንቀት ማላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ሙስሊሙ ፆመኛ መሆኑን ወይም መሆኗን በመቀበል እንደራስ ማሰብ፣ በፍቅርና በአክብሮት ማየት ይገባል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች አበክረው ያሳሰቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ‹‹በራስህ ላይ ሊደረግብህ የማትሻውን በሌሎች ላይ አታድርግ›› የሚለውን ወርቃማ ቃል ማስቀመጥ ይቻላል።
ሰዎች በእምነታቸው የተለያዩ ቢሆኑም በማኅበራዊ ሕይወታቸው ችግረኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የሙስሊሙ ጎረቤት የሆነ ክርስቲያን ደሃ ወይም የሙስሊም ጎረቤት የሆነው ክርስቲያን ሀብታም ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ አንዳቸው የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆኑ ሌላቸውን መርዳት እንዳለባቸው የታወቀ ነው። ስለሆነም የሌሎች እምነት ተከታዮች ሙስሊሙ ጎረቤታቸው የሚበላ ነገር የለውም ወይም የላትም ብለው ካሰቡ፣ በሚቻል መንገድ ሁሉ የሚበላና የሚጠጣ ነገር መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ባህል በኢትዮጵያ ሥር ሰዶ የቆየ ቢሆንም በአንዳንድ አላዋቂዎች በመመራት እንዳይበረዝም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
የፍትሕ አካላት ልዩ ልዩ ፍትሐዊ ጉዳዮችን ሲያስፈጽሙ ከረመዳን ጋር በተያያዘ ሁኔታ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በማረሚያ ቤት ያሉ ሙስሊሞች በተቻለ መንገድ በተመቸ ሁኔታ እንዲፆሙ ማድረግ፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ ቢኖራቸው በጧት ማድረግ፣ ወህኒ ቤቶች ሥራ ቢኖራቸው ቀላል ሥራ ማሠራት፣ መርማሪዎች ጠበቅ ያለ ምርመራ ማድረግ ቢኖርባቸው ረመዳንን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት፣ በአጠቃላይ ሙስሊም የሕግ ታራሚዎች በረመዳን ወርም ፍትሕ መኖሩን እንዲያምኑ በሚያደርግ ሁኔታ መያዝ ግንባር ቀደም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በመሠረቱ ለሌላው ሰው ደግ እንዲሆን የሚመኙትን ያህል ለሙስሊሞችም ደግ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ገነት የምትገኘው ደግ ነገር መሆኑን የሚያምን፣ የሌላውን እምነት ተከታይ መብት በመጋፋት ወይም ክፉ በመሆን ገነትን ለመውረስ አይመኝም፡፡ ስለሆነም ደግ ሆኖ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ደግነትን ማሳየት ይገባል፡፡
ሙስሊሙ በረመዳን ወር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ባልተለመደ ሁኔታ ቸልተኛ ቢመስልና ጉዳዩ ባልሆነ ነገር ጣልቃ ባይገባ ከፆምና ከፀሎት ጋር የተያያዘ መሆኑን በመገንዘብ ሁኔታዎችን መቀበል፡፡ ሙስሊሙ’ኮ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም የሚያስብ ነው። ሲመርቅም ‹‹አገራችንን ሰላም አድርግልን፣ ረሃብና እርዛትን አስወግድልን፣ ክፉን ነገር ሁሉ አርቅልን›› በማለት ለሁሉም የሚፀልይና የሚመኝ ነው፡፡ ስለዚህም የሚደረግለት ትብብር ለጋራ ዓላማም ጭምር ነው፡፡
ማጠቃለያ
አገራችን በሰላም ለመገንባት፣ የበለጡ የድል ውጤቶችን ለማስመዝገብ፣ ከድህነት ማጥ ለመውጣት፣ አንገታችንን ቀና አድርገን ለመጓዝ እንችል ዘንድ መተባበር፣ መፋቀር፣ መቻቻልና መተጋገዝ ይኖርብናል። መንፈሳዊ ፍላጎቱ ያልሞላለት በቁሳዊ ተግባር ሊፈተን አይችልምና ረመዳንም አንዳች ጥሩ ነገር ለማከናወን የምንችልበት ለልማታችን የሚበጅ መልካም አጋጣሚ አድርገን ልናየው እንችላለን፡፡ ውዲቱ ሀገራችንን፣ በታሪክ የበለፀገችና የብዙ አገሮች ባለውለታ የሆነችው አገራችንን፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ተፋቅሮና ተቻችሎ የኖረባት አገራችንን  ለማያውቁና በውስጣቸው ባዕድነት ለሚሰማቸውም ሐቁን እንዲገነዘቡ ልናደርግ የምንችለው ባላገሮች መሆናቸውን በተግባር በማስተማር ነው። ለዚህም የእርስ በእርስ ፍቅራችንን ስናደረጅ ነው፡፡ ለኔ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድሜ፣ እህቴ፣ ልጄና ዘመዴ ነው፡፡ ፈጣሪ ፍቅር፣ መተባበር፣ መረዳዳት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብ፣ መከባበር ይስጠን፡፡ አገራችንን በሁሉም ረገድ የበለጸገች ያድርግልን፡፡ ረመዳን ሙባረክ፡፡ ረመዳን ከሪም፡፡ አሜን፡፡



Read 1806 times