Saturday, 11 June 2016 12:31

የአፍሪካ ፍልስፍና ያደረገው የአርነት ተጋድሎ

Written by  መልሰው ሉል
Rate this item
(5 votes)

     የዚህ ጽሁፍ ዓላማ  ግንቦት 20 በአዲስ  አድማስ ጋዜጣ የጥበብ አምድ ላይ “ዋግ የመታው አፍሪካዊ ፍልስፍና” በሚል ርዕስ በደረጀ ይመር ለተጻፈው ፅሁፍ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ ጽሁፉን በጥቂት አስተያየቶች እጀምራለሁ፡፡ ስለ አፍሪካ ፍልስፍና በጋዜጣ አምድ ላይ መውጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን በመጀመሪያ የምንጽፈው ጽሁፍ አላማ  ሊኖረው ይገባል፡፡ ርዕሰ ጉዳዩንም በደንብ ልናጤነው ይገባል፡፡ ያ ካልሆነ ግን  ጽሁፋችንን ዋግ ይመተዋል። የጥበብም ጥሪ ከንቱ ይሆናል፡፡
ወደ ቀዳሚው ነገር ስገባ፤“ዋግ የመታው አፍሪካዊ ፍልስፍና” ጸሀፊ እንዳለው ፍልስፍና የሚጀምረው በመደመም ነው፡፡ ነገር ግን  ጥበበ-መደመሙ ግብና አላማ ቢስ አይደለም፡፡ በእርግጥ የጥበብ መጨረሻ ይሄ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ጥበበኛው አንድ ጥበብ ጨበጥኩ ሲል ሌላ  የጥበብ  ድምፅ ይጠረዋል፡፡ የሶቅራጥስ፤ አፍላጦንና አርስጣጣሊስን የፍልስፍና ዘይቤ መጥቀስ በቂ ነው። የነኝህ ፈላስፎች የግብረ-ገብና የፖለቲካ ፍልስፍና በወቅቱ በነበረው ማህበረሰባዊ  ሁኔታዎች የተቃኘና አስተዳደራዊ፤ ሞራላዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ህጋዊና ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት ላይ ያተኮረ ነበር። ልህቀት ምንድን ነው፤ ፍትህ ምንድን ነው፤ጥሩ ማለት ምን ማለት ነው፤ እዉቀት ማለትስ ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ  ለመመለስ ያተኮረ ነበር። የሶቅራጥስ ግብረገባዊ  የአደባባይ ላይ አስተምሮ  እንዲሁም የአፍላጦን ዜጎችን የማስተማር ፕሮጀክት ዝም ብሎ አልነበረም፤ የአቴናን  ችግር ለመፍታት እንጅ፡፡ የአፍሪካ ፈላስፎች  ጥረትና ልፋትም ከዚህ አይለይም፡፡
ታዋቂው አፍሪካዊ ፈላስፋ ሞጎቤ ራሞሴ እንዳለው፤ “ራስን  ከጥቃት  መከላከል ተፈጥሯዊ ነው”፡፡ የመከላከያው መንገድ ግን እንደየጥቃቱ  አይነትና መጠን ይለያያል፡፡ አፍሪካ ዓይነተ-ብዙና መጠነ-ሰፊ ጥቃት ከአውሮፓ ደርሶባታል። ከዲስኩራዊ እስከ አካላዊ፤ በቃል፣በጽሁፍና በተግባር የአውሮፓ የጥቃት ሰለባ ነች፡፡ የማንቋሸሽ፣ የማዋረድ፣ የዘረኝነት፣ የባርነት፣ የሀብት ምዝበራ፣ የኢምፔሪያሊዝምና  የቅኝ ግዛት  አለንጋዎች  አፍሪካን ገርፈዋታል፡፡ ለእነዚህ ጥቃቶች  አፀፋ መስጠት ምክንያታዊ፣ ተገቢ፣ ሞራላዊ፣ ሰብአዊና ፖለቲካዊ ግዴታ ነው፡፡ ሀይማኖታዊም  ሊሆን ይችላል፡፡ የእግዜር ፍጡር አይደለህም ስትባል፣ አዎ የምትል ከሆነ  ፈጣሪ ሊያዝን ይችላል፤ በእሱ አምሳል ፈጥሮሀልና! የአፍሪካ ፍልስፍና የሚለውም የሚያደርገውም ይህንን ነው፡፡
የአውሮፓ የ17ኛውና 18ኛው ክፍለ ዘመን የፍልስፍና ዲስኩር “አፍሪካዊያን ሰው አይደሉም፤ ለሳይንስና ለፍልስፍና የሚበቃ አእምሮ የላቸውም” የሚል  መደምደሚያ ነበረው፡፡ የሰው ዘርንም በደረጃ ከፋፍሏል፡፡ ለቅኝ ገዛት ህጋዊነትና ተገቢነትም እንደ ማስረጃና ማረጋገጫ  ቀርቧል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ የሚያስደምም፣ የሚያስገርምና የሚያስደነግጥ ነገር አለ? እንደ እንግዳ በግ ገመድ የታሰረበት፣ እንደ ከብት ጥርሱ ሲቆጠር የነበረ እና እንደ ጥቁር ሸክላ ለሰውነቱ ማረጋገጫ የተዳሰሰ አፍሪካዊ ምን ሊያስደምመው ይችላል? እንደ ሴዳር ሴንጎርና አሜ ሲዛየር ያሉ አፍሪካዊ ፈላስፎችን ያስደመማቸው ይህ ነበር።  ያስደመመንን ለማወቅ  መሻት ተፈጥሯዊ ነው፤ መጥፎም ደግም ሊሆን ይችላል፤ አፍሪካውያንን  ያስደመማቸው ግን መጥፎ ነገር ነው፡፡ ከዚህ መጥፎ ነገር ለመውጣት ምንነቱን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አባባል ዘረኝነትን ለመዋጋት በዘረኝነት ዲስኩር ዉስጥ ማለፍ የግድ ነው፡፡ ያልተዋረደን አፍሪካዊ ማንነት መግኘት የአውሮፓውያንን የዘረኝነት ዲስኩር ለመገሰፅና ለማክሸፍ አይነተኛ መንገድ ነው፡፡
ዘረኝነትን ማውገዝና የዘረኝነት ዲስኩር መሰረተ-ቢስነትን ማወጅ ዘረኝነት አይደልም። ነፃነትን ለማወጅ ስለ ባርነትና ጭቆና መደስኮር አይቀርም፡፡ የእውቀትን ደግነት ለማብሰር የአላዋቂነትና ድንቁርናን መጥፎነት መለፈፍ ግድ ነው፡፡ አፍሪካዊ ፈላስፎችም የአውሮፓዊያንን የዘረኝነት ጥላሸት  ለማፅዳት ስለ ዘረኝነት ደስኩረዋል፡፡ ነገር ግን ዘረኝነትን አይደለም ያበሰሩት፤ ዘረኛም አያስብላቸውም፡፡ ለነጻነት ወይም ከዘረኝነት ስለመላቀቅ ነው የሞገቱት፡፡ ፍልስፍናም ይህንን ነው የሚሰብከው፡፡ የሰውን ልጅ ከማንኛውም አድሏዊነት ማላቀቅ ነው፡፡ ዘረኝነት ደግሞ የአድሏዊነት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህ  የአፍሪካዊያን ፈላስፎች ዲስኩር  ለጭቁን አፍሪካውያን የተደረገ ትዕምርታዊ (symbolic) ፍልስፍናዊና  ሰብአዊ  ጥሪ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሴንጎር “ኔግርቲውድ” ቅኔ የአርበኝነትና ጀግንነት ትወራ ሳይሆን  የአፍሪካን ማንነት የሚተውር  ፍልስፍናዊ ቅኔ ነው፡፡ ይኸውም ስለ አፍሪካ ሰብአዊነት፣ መንፈሳዊነት፣ ርህሩህነት፣ አብሮነትና በልቡና አዋቂነትን  ይሞግታል። “ኔግርቲውድ” የአፍሪካ ሰብዕና መገለጫ እንጅ የአርበኝነት ልፈፋ አይደልም፡፡ “ኔግርቲውድ” የአፍሪካን ማንነት፣ ሰብአዊነትና እኩልነት ለማረጋገጥ ሞክሯል፤ ወደፊትም ተራምዷል፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍና በዚህ ረገድ  ብዙ ርምጃ ተራምዳለች፡፡
የአፍሪካ ፍልስፍና ማንነት ፀሀፊ እንደሚለው “ዋግ የመታው አፍሪካዊ ፍልስፍና” አይደለም፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍና  በባህልና ትውፊቶች ውስጥ  ያለ እውነትን የሚያቀነቅን (ethnophilosophy)  ብቻ አይደለም፡፡ የዚያ ቤልጅየማዊ ቄስ ፋዘር ፕላሲድ ቴምፕልስ “ባንቱ ፊሎሶፊ” የተሰኘው ድርሳን  የአፍሪካ ዘዴኛ (systematic) ፍልስፍና መጀመሪያና አንድ ቅርንጫፍ  ብቻ ነው፡፡ ይህ ቄስ 30 እና 40 ካጠና በኋላ ነው “ባንቱ ፊሎሶፊ”ን የጻፈው፡፡ ጸጉረ ልውጥ ስለሆነ ብቻ ፍልስፍናውን ወለፈንዲ አያደርገውም፡፡ የእነ ሴንጎር የአርነት ወይም የነፃነት ፍልስፍና፣ በሄነሪ ኦዴራ ኦሩካ የተተወረው የጠቢባን ወይም የብልሆች ፍልስፍና፣ በእነ ፓውሊን ሆንቶንዥ የሚቀነቀነው ፕሮፌሽናል ፊሎሶፊና በእነ ፀናይ ሰርቀብርሀን የሚተወረው ሄርመኒዮቲክ (hermeneutic) ፊሎሶፊ  የአፍሪካ  ፍልስፍና ዘውጎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የአፍሪካ  ፍልስፍና ዘውጎች እርስ በእርሳቸው ይከራከራሉ ይተቻቻሉ። ይህም የፍልስፍና መሰረተ-ባህርይ ነው። የአፍሪካ ፍልስፍናን ትክክለኛነት እንጅ ክስረትን ወይም በዋግ መመታትን  አያሳይም፡፡ ያለ ክርክርና ትችት ፍልስፍና ሊራመድ አይችልም፤ እንዲያውም ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍና  የተጫወተው ሚና ይህ ብቻ አይደለም። ዋናውና ቀዳሚው አፍሪካውያን ሰብአዊነት፣ ፍልስፍና እና አመክኗዊ አዕምሮ እንዳላቸው በማሳየት የአውሮፓውያንን የዘረኝነት ዲስኩር  እንዲገረጣ አድርጓል፡፡ ባርነትንና ጭቆናን በመዋጋት ረገድም የአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ  የይስሙላ  አፍሪካን የማሰልጠን ተልዕኮ፣ እርባና ቢስነትንና እኩይነትን አስገንዝቧል፡፡ ብዙ ድርሳናትንና  መፅሀፍትን ለአፍሪካና ለዓለም አበርክቷል፡፡ በተጨማሪም ጥቂት የማይባሉ የፍልስፍና ዘዴዎችንና ትወራዎችን አበርክቷል፡፡ የምዕራባዊያን ፍልስፍና እራሷን እንድትፈትሽና እንድትመረምርም ረድቷል፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍና ፍሬ ማፍራት ጀምሯል፤በሙሉ አቅሙ እንዲያፈራና ዋግ እንዳይመተው መንከባከብ የኛ ስራ ነው፡፡
“አብዛኞቹ የአፍሪካ ፈላስፎች ከአፍሪካ ምዕራባዊ ክፍል የወጡ ስለሆነ ከበቀሉበት አካባቢ አንጻር ብቻ ይተነትናሉ” የሚለው መደምደሚያ ውሀ የማይቋጥር ነው፤ ያ ቢሆን እንኳ በምዕራብ አፍሪካ የደረሰው የቅኝ ግዛት በደል በአፍሪካ ላይ የደረሰውን ሰብአዊ ጥቃት በደንብ ይወክላል፤ የአፍሪካ ፍልስፍናም ለቅኝ ግዛት የማስመሰል ዲስኩሮች፣ ቅኝ ግዛትንና  የአፍሪካን የቅኝ ግዛት ጠባሳዎች ምላሽ ነው የሚሰጠው፡፡ ከዚህ ባሻገር ፈላስፋዎች ፍፁም  አንድ ወጥ አቋም  ሊኖራቸው አይችልም፡፡  ሁሉም የምዕራብ አፍሪካ ፈላስፋዎች አንድ ከበሮ ብቻ አይደልቁም፡- ማለትም የአፍሪካን የቀደመውን ማንነትና ባህላዊ ትውፊቶችን ማወደስ ላይ ብቻ አይጨፍሩም ፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-አቢዮላ አየርል እና ፓውሊን ሆንቶንዥ የተባሉ እውቅ የምዕራብ አፍሪካ ፈላስፎች ሁለንተናዊ ፍልስፍናን ያራምዳሉ፤የባህል ብሔርተኝነትን  ይተቻሉ፣ ባህልን ብቻ ማወደስ የአፍሪካን ችግር አይፈታም ብለው ይሞግታሉ፣ አፍሪካን ባለችበት አዘቅት ሊያቆያት ይችላል ብለው ይከራከራሉ፡፡
በአህጉሪቱ ላይ ቀደም ብለው ብቅ ብለው የከሰሙ የስልጣኔ ዘይቤዎች  ተፈትሸው ገሃድ አለመውጣታቸው መፈታት ያለበት ችግር ነው፡፡  ነገር ግን የአፍሪካ ፍልስፍና ብቻውን ሊወቀስ  አይገባም። ቢሆንም ግን የአፍሪካ ፍልስፍና  ቀደምት የስልጣኔ ዘይቤዎችን በማፈላለግና በመመርመር ላይ ነው፡፡ የሸክ አንታ ድየፕ “አፍሮ-ኤዥያቲክ ሩት ኦፍ ግሪክ ፊሎሶፊ” እና የማርቲን በርናል “ብላክ አቴና” የተሰኙት ድርሳናት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ሂስቶሪኮ-ኸርመኔዮቲክ የተባለው የፍልስፍና ዘዴና ዘይቤም የሚያቀነቅነው ይህንን ነው፡፡ ሆኖም ግን ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም፡፡ የአፍሪካ  ፍልስፍና  አካዳሚያዊ ቅርፅ መያዝ ከጀመረ  50 ወይም 60 አመት ቢሆነው ነው፡፡ ቸኩለን ልንነክሰው አይገባም፡፡
“ቀደምት የኢትዮጵያ የስልጣኔና የፍልስፍና ዘይቤዎች በአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ ተገቢ ቦታ አልተሰጣቸውም” የሚለው ክስም  እውነተኛ ክስ አይደልም፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ስልጣኔና ፍልስፍና ብዙ ነገር ተብሏል፡፡ ለአብነት ያህልም ክሎውድ ሰምነር የተባሉት ፈላስፋ “አፍሪካን ፊሎሶፊ” በተሰኘው  መጽሀፋቸው፤ ስለ ዘረያዕቆብና ወልደ ህይወት ሀተታ በጣም ብዙ ነገር ጽፈዋል፡፡ የኬንያው ፈላስፋ ሄነሪ ኦዴራ ኦሩካን፣ የተጻፈ ፍልስፍና በአፍሪካ ምድር ዉስጥ ይኖር እንደሆነ ብለው  ምዕራባዊያን ፈላስፎች በጠየቋቸው ጊዜ፣ የዘረያዕቆብና ወልደ ህይወትን ሀተታ ከኢትዮጵያ የፊደል ገበታ ጋር ነው ያቀረቡት፡፡ የሆነው ሆኖ  የአፍሪካን ፍልስፍና በብሄርተኝነት እርሾ የተቦካ ነው ብለን ከወቀስን ቀደምት የኢትዮጵያ የስልጣኔና የፍልስፍና ዘይቤዎች   ትኩረት እንዲሰጣቸው መሞገት ሌላ ብሄርተኝነት ነው፣ እርስ በራሱ የሚጣረስ ነው፡፡ እውነታው ግን የአፍሪካ ፍልስፍና ስለ አፍሪካ ችግሮች ቢጨነቅ ቢጠበብ ብሄርተኝነት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የስልጣኔና የፍልስፍና ዘይቤዎች መመርመርም ተገቢነት ከዚህ አንጻር ነው፡፡  እኛ ኢትዮጵያውያንም ስለ ኢትዮጵያ ስልጣኔና ፍልስፍና ልንዋትትና  ልናጤን ይገባል፤ናይጀርያውያን ወይም ኬንያውያን  ስለ ስልጣኔያችንና ፍልስፍናችን እንዲጠበቡ አንሻ፡፡
የአፍሪካ ፍልስፍና ቀዳሚው ተግባር የአፍሪካውያንን የተሰበረ ልብ በስነ-ልቦና ወጌሻ ማፅናናት አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን  እንደ መፅናኛ አያገለግልም ማለት አይደለም፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ የአውሮፓ ዘረኛ ፍልስፍናዊ ዲስኩር  የአፍሪካን ሰብአዊነት፣ በሰው ዘር ግርጌና በእንስሳ ራስጌ መካከል አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ቀዳሚው የአፍሪካ ፍልስፍና ስራ በዚህ የዘረኛ ዲስኩር  ዉስጥ ያለውን ህፀፅና አንድምታ  ማውገዝ፣ማረምና ውድቅ ማድረግ ነው፡፡ ህፀፁም ጊዜያዊና ውጫዊ በሆኑ የባህልና ማህበረሰብ ውጤቶች ላይ ተመርኩዞ ለሰው ልጅ ዘር ደረጃ መስጠቱ ነው፡፡ ይህ ደረጃ ምክንያታዊ መሰረት የለውም፤ምክንያቱም የሳይንስና የቴክኖሎጅ እድገት ብቻውን የሰውን ልዕልናና ዝቅተኛነት በትክክል አያሳይም፡፡ የሰው ልጅ ዋነኛ መገለጫው መንፈስ ነው፡፡ የመንፈስ ከፍታ የሰውን ልጅ ልዕልና ያሳያል፤ ምክንያቱም  ፈጣሪዉን ያስመስለዋልና! ምነው ቢሉ ሰውን ከፈጣሪ አንድ የሚያደርገው  መንፈሳዊ ፍጡር መሆኑ ነው፡፡ ለመንፈስ ደረጃ ማውጣት ግን አይቻልም፤ቢወጣ እንኳ የተንጋደደ ይሆናል፡፡ የአውሮፓን መንፈስ ከፍ ከፍ፣ የአፍሪካን መንፈስ ዝቅ ዝቅ ያደረገው የዘረኛ ፍልስፍናዊ ዲስኩር እንድምታው አፍሪካ ቅኝ ግዛት ይገባታል ለማለት ነው፡፡ አፍሪካውያን የተሟላ ሰብዕናና ግብረገብነት የሌላቸው  ፍጡር ስለሆኑ ቅኝ ቢገዙና ባሪያ ቢሆኑ ስህተት አይደለም፤እንዲያውም አፍሪካዊ ሰው  የምዕራባዊ ሰውን  ለማገልገል ነው የተፈጠረው። ስለዚህ ለአፍሪካዊ ሰው ባርነትና ቅኝ ግዛት  ህጋዊና ሞራላዊ ነው፤ ለዚያም ነው  አውሮፓውያን ፀረ-ባርነትን ለራሳቸው ባወጁበት (17ኛውና 19ኛው ክ/ዘመን)  ማግስት  ለአፍሪካ  ባርነትንና ቅኝ ግዛትን በይፋ ያወጁት፡፡ ለዚህ ነው የአፍሪካ ፍልስፍና በቅድሚያ በምዕራባዊ ዘረኛ ዲስኩር  ዉስጥ ያለውን ህፀፅና አንድምታ  ማውገዝ፣ማረምና ውድቅ ማድረግ  አለበት ያልኩት፤እያደረገም ያለው ይህንኑ ነው። ይህን ሳያደርጉ “ነፃ ጥበብ”ን ለመያዝ የሚደረግ አዕምሯዊ መዋተት እንደ ግሪካዊው የአፈ-ታሪክ ሰው ሲሲፐስአሎሎ ድንጋይ  ቀጥ ባለ ተራራ ወደ ላይ ለዘላለም መግፋት  ነው የሚሆነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከእጅ-አዙር ቅኝ ግዛት አልፎ ለዳግም ቅኝ ግዛት ራስን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡
ለዚህም ሲባል የአፍሪካን ማንነት አንጥሮ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም  አፍሪካ አሁን ያላት ማንነት ከአውሮፓዊያን የተሰጣትና የተጫነባት  ነው፡፡ ራስን ለማበልፀግም ሆነ ራስን ከጥቃት ለመከላከል  ራስን ማወቅና  ማንነትን ፈልጎ ማግኘት አይነተኛ ቁልፍ ነው፡፡ ራስን  ማወቅ የፍልስፍናም የመጀመሪያ መርህ ነው፡፡ ሶቅራጠስ፤ “ራስህን መርምር፤እወቅ” ያለውም ለዚህ ነው፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍናም የአፍሪካን ማንነት  ለማግኘት የቃተተበት ምክንያት ከዚህ አንፃር ሊታይ ይገባል፡፡ የሴንጎር “ኔግርቲውድ” አብሮነትና ፍቅር እንጅ ግለኝነትና  ወራሪነት የአፍሪካ ማንነት አይደለም ያለውም በዚሁ የተነሳ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የአፍሪካ ፍልስፍና ስለ አፍሪካ ማንነት የሚዋትተው አፍሪካን ከዘረኛ የዲስኩር ወጀብ  ለመከላከል እንጂ ፀሀፊው እንዳለው፣ የአፍሪካን ማንነት በዘረኛ እርሾ አቡክቶ  ለመጋገር አይደለም፡፡ ያለበለዚያ የአፍሪካ ፍልስፍና የወንጀለኛ ግብር-አበር ብቻ ይሆናል፡፡
የአውሮፓ የዘረኛ ዲስኩር ውድቅ ከማድረግና የአፍሪካን ማንነት ከማግኘት በተረፈ  የአፍሪካ  ፍልስፍና ቅኝ ግዛት ለወለዳቸው ፖለቲካዊ፣ሞራላዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሌሎች  አንገብጋቢና አስከፊ ችግሮች  መፍትሄ ማበጀት አለበት፡፡ ማንኛውም ትርጉም  ያለው ትወራ ወይም ፍልስፍና አፍሪካን ቅኝ ግዛት ካመጣው ቀውስና አዘቅት ዉስጥ ማውጣትና ማላቀቅ አለበት። እውቀት ትርጉም የሚኖረው የሰውን ልጅ ሲታደግና ወደ ከፍታ ሲወስድ ነው፤ያለበለዚያ የጋን ውስጥ መብራት ነው፡፡ የፍልስፍና አንዱ አላማ የሰውን ልጅ ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ስቃይና ሰንሰለት ነፃ ማውጣት ነው፡፡ የፍልስፍና አጀማመር መደመም ይሁን እንጅ አላማው በምናባዊ ሁዳድ ዝም ብሎ ለመጋለብ አልነበረም፤የግሪክን ማህበረሰብ ከአፈ-ታሪክና ከጥንቆላ እስረኛነት እንዲሁም ከፖለቲካዊና ሞራላዊ መላሸቅ ለማላቀቅ ነበር፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍና ጥረትም አፍሪካን ከሁለንተናዊ የቀውስ ሰንሰሰለት  ነፃ ለማዉጣት ነው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ፍልስፍና ግሪክ ለፍልስፍና የለገሰቻትን የ“የነፃ ጥበብን  መሻት” ማዕረግ ነጠቀቻት  የሚለው “ዋግ የመታው የአፍሪካ ፍልስፍና” ፀሀፊ ክስ መሰረተ-ቢስ ነው፡፡
በአጠቃላይ የአፍሪካ ፍልስፍና ለቅኝ ግዛት ፍልስፍናዊ አፀፋ ነው፡፡ የ17ኛውና የ18ኛው ክ/ዘመን  የአውሮፓ  ፍልስፍና ለቅኝ ግዛት መንገዱን አመቻችቷል፤ ቅኝ ግዛትንም አሞካሽቷል፡፡ የአፍሪካን የበታችነትና የአውሮፓን የበላይነት በመስበክ  ለቅኝ ግዛት ቀኝ እጅ በመሆን አገልግሏል፡፡ የስብከቱ መሰረት ግን ከባህል ውጤቶችና የቆዳ ቀለም የዘለለ አልነበረም፡፡ አሁን በያዝነው ክ/ዘመን እንኳ  አውሮፓውያን “የአፍሪካ ፍልስፍና  አለ ወይ?” ብሎ በመጠየቅ የአፍሪካን ሰብአዊነትና አመክኗዊነት ከሞት አፋፍ ጥለውታል፤ምክንያቱም ጥያቄው አፍሪካውያን ማሰብ አይችሉም ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። ይህ ካልሆነማ በአሁኑ ወቅት በፍልስፍና የተካኑ አፍሪካውያን እንዳሉ  ያውቃሉ፡፡ ይህ እሳቤ ሞጎቤ ራሞሴ እንዳለው፤“ሰው የሚያስብ እንስሳ ነው” የሚለው ብሂል አፍሪካን እንደማያካትት ያመለክታል። የአውሮፓውያን ቅኝ ግዛትና እጅ-አዙር ቅኝ ግዛት አፍሪካን ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ጥሏታል፡፡ ለዚህ ቀውስ  ምላሽና መፍትሄ መስጠት ሰብአዊ፣ሞራላዊና ተፈጥሯዊ  ግዴታ ነው፡፡ “ጥበብን ለጥበብ” የሚለው ብሂል የማይመስል ነው፤ ምክንያቱም ጥበብን መሻት አንድም ለስጋ እርካታ አንድም ለመንፈስ ሀሴት ነው። የአፍሪካ ፍልስፍና ጥረትና ልፋትም  ቅኝ ግዛት  የሰረቀውን የአፍሪካ አካላዊና መንፈሳዊ  ሀሴት ማስመለስ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ለማድረግ የተኮላሸውን የአፍሪካ ማንነትና ሰብአዊነት ነፃ ማውጣት፣በዘረኛ ዲስኩሮች ውስጥ የተቀበሩ ፈንጂዎችን ማክሸፍና ለወቅቱ የአፍሪካ አንገብጋቢ ቀውሶች ምላሽ መስጠት የግድ ነው፡፡ ይህ ዘረኝነት አይደለም ሰብአዊነት እንጅ፤ አድሏዊነትና ወገንተኝነት ሳይሆን ምክንያታዊነት ነው፤ብሄርተኝነት ሳይሆን ነፃነትን መሻትና ማወጅ ነው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ፍልስፍና አፍሪካንና ፍልስፍናን ራሷን ነፃ ለማውጣት በዘረኝነትና ቅኝ ግዛት ዲስኩር ላይ የታወጀ አዕምሯዊና ፍልስፍናዊ ጦርነት ነው፡፡                                  
ጥበብን  ለነፃነት እናውል!!

Read 2426 times