Saturday, 11 June 2016 12:30

የሦስት ደብዳቤዎች አዙሪት

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(39 votes)

“ጨለማውን ደጋግመህ ስላወገዝከው መብራቱ አይበራልህም”

  የአንድ ትልቅ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረ ሰው ከደርጅቱ ሲለቅ ለተተኪው ሰው ሦስት ደብዳቤዎችን በሦስት ፖስታዎች አሽጎ በላያቸውም ላይ 1፣ 2 ና 3 ቁጥር ጽፎ ሰጠው፡፡ ተተኪውም ‹ምን ላድርጋቸው?› ሲል ጠየቀው፡፡ ‹ድርጅቱን በምታስተዳድርበት ጊዜ ችግር በገጠመህ ቁጥር በየተራ ከፍተህ አንብባቸው› አለና መለሰለት፡፡ ርክክቡም በዚህ ተጠናቀቀ፡፡
አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ሥልጣኑን እንደተረከበ ከያቅጣጫው ተቃውሞ በረታበት፤ በጉጉት ጠብቀውት የነበሩት ሁሉ ተስፋ ያደረጉትን ለውጥ በአጭሩ ማየት ስላልቻሉ መበሳጨትና ግፊት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ‹ከበሮ በሰው እጅ ሲይዙት› እንደሚባለው ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ የሞሰቡ መስፊያ ጠፋበት፡፡ የዘሐውንም ውል ማግኘት አልቻለም። ድርጅቱም በችግር ተወጠረ፡፡ ከዚህም ከዚያም ተበደልን፣ መብታችን ተረገጠ፣ ተገፋን፣ ተናቅን፣ የሚሉ ድምጾች በረከቱ፡፡
በዚህ ጊዜ ቁጥር አንድ የሚለውን ፖስታ ከፈተና የተጻፈውን አነበበው፡፡ ‹ካንተ በፊት የነበረውን ኃላፊ ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ውቀስ› ይላል። የድርጅቱን ሠራተኞች ሰበሰበና ከእርሱ በፊት የነበሩት ኃላፊዎች ያጠፉትን ጥፋት፣ የሠሩትን ስሕተት፣ ያደረሱትን በደልና የፈጠሩትን ችግር መዘርዘር ጀመረ፡፡ አሁን ለተከሰተው ነገር ሁሉ ተጠያቂዎቹ እነርሱ መሆናቸውንና እርሱ የመጣው ችግሮቹን ጠራርጎ ለማስወገድ መሆኑን ደሰኮረ፡፡ በወደቀ ዛፍ ላይ ምሣር ማብዛት ቀላል በመሆኑ ሰውም አብሮ ወቀሰ፤ ኮነነ፤ አወገዘ፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው በየሄደበት ቦታ ሁሉ ስለወደፊቱ ሳይሆን ስለትናንቱ ማውራትን ልማድ አደረገው፡፡ ራሱን በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች ኃላፊዎች ጋር ሳይሆን ካለፉትና ከሞቱት ኃላፊዎች ጋር ማወዳደር ጀመረ፡፡ ወንበር በቀየረ ቁጥር ‹ያለፉት ኃላፊዎች በእንጨት ወንበር ነበር ደርጅቱን የሞሉት፤ እኔ ግን የቆዳ ወንበር አስገዝቼላችኋለሁ› ይልና ያስጨበጭባል፡፡ ፀሐይ በማለዳ ከወጣች ‹በድሮ ኃላፊዎች ዘመን ፀሐይ ዘግይታ ነበር የምትወጣው፤ አሁን ግን ይሄው በማለዳ መውጣት ጀምራለች› ይላል፡፡ ቀን ዝናብ የዘነበ ጊዜ ‹የድሮ ኃላፊዎች ቤታቸው ከገቡ በኋላ ነበር ዝናብ የሚወርደው፤ አሁን ግን ይሄው በቢሮ ሰዓታችን ዝናብ መምጣት ጀመረ› ብሎ ይለጥፋል፡፡ አንዳንድ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞችም አድናቆታቸውን ይገልጣሉ፡፡ ያለፉት ኃላፊዎች በሠሩት ቤት እየኖረ ይወቅሳቸዋል፤ በገነቡት ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ እያዘዘ ያወግዛቸዋል፤ የገዙትን መኪና እየነዳ ያጣጥላቸዋል፡፡ ‹እማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ› የሚባለውን አላወቀውም፡፡
እንዲህ እያለ አንድ ዓመት ያህል ተቀመጠ፡፡ ሠራተኛውም ያለፈውን እየወቀሰ፣ ለሚመጣውም የተስፋ ቀብድ እየተቀበለ፤ የችግሩ ሁሉ መነሻና መድረሻ የቀደሙት ናቸው የሚለውን እየደገመ ከረመ፡፡ እየሰነበተ ሲሄድ ግን ያለፉት ኃላፊዎች የሠሩት እየፈረሰ፤ አዲስ ይሠራል የተባለውም የሕልም እንጀራ እየሆነ ሲመጣ፣ ሠራተኛውም እንደገና ማጉረምረም ጀመረ፡፡ ችግሮቹም አየተባባሱ ብቻ ሳይሆን እየተወሳሰቡም ሄዱ፡፡ ያለፉትን ኃላፊዎች የኮነነበትን ሁሉ እርሱ ራሱ እየደገመ መሥራት ጀመረ፡፡ ‹የድሮ ኃላፊዎች ሠራተኛ ሲያባርሩ በደብዳቤ ነበር፤ አሁን ግን በኢሜይል ሆኗል› ተብሎ ለውጡ ተነገረ፡፡ የድሮ ኃላፊዎች ሠራተኛ ሲቀጥሩ በዘመድ ነበር፤ አሁን ግን ተሻሽሎ በዘር ሆነ፡፡ ነገሩ ግን እየባሰ እንጂ እየተሻለ ሊመጣ አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ሥራ አስፈጻሚው ሁለተኛውን ፖስታ ከፈተ፡፡
ሁለተኛው ፖስታ ውስጥ የተጻፈው ነገር ‹ድርጅቱን እንደገና አዋቅረው(Restructure the organization)› ይላል፡፡ ይህንን ተቀብሎ እንዳለ ድርጅቱን ገለባበጠው፡፡ አንድ የነበሩትን ተቋማት ሁለት፤ ሁለት የነበሩትን አንድ፤ ድርጅት የነበሩትን አጀንሲ፤ ዋና ክፍል የነበሩትን ዳይሬክቶሬት፤ የክፍል ኃላፊ የነበሩትን የሥራ ሂደት ባለቤት፤ ኮሚቴ የነበሩትን አንድ ላምስት አደረጋቸው። ከፊሎቹ ሠራተኞች ተባረሩ፤ ከፊሎቹ ተዛወሩ፤ ከፊሎቹ ተሾሙ፤ ሌሎች ደግሞ ተቀጠሩ፡፡ አዳዲስ መመሪያዎች ተዘጋጁ፣ አዳዲስ ሕንጻዎች ተከራዩ፤ ቢል ቦርድ ተዘጋጀ፤ ራእይና ተልዕኮ ተጻፈ፤ የደረት ባጅ ተጀመረ፤ የመሥሪያ ቤቱም ስም ተቀየረ፤ መግለጫ ተሰጠ፡፡ ድግስም ተደገሰ፡፡ የሠራተኛውም ሥራ ሥልጠና፣ ስብሰባ፣ ተሞክሮ ልውውጥ ሆነ፡፡
በድንጋጤው ብዛት በጥይት የተመታውን ቁስል እንደሚረሳ ወታደር፣ ከትርምሱ የተነሣ ችግሩ የተፈታ መሰለ፡፡ አዲስ ሕንጻ ሲከራዩ፣ አዲስ ወንበር ሲገዙ፣ አዲስ ስም ሲይዙ፣ አዲስ ቢል ቦርድ ሲያሠሩ፣ አዲስ ሐሳብ ያመጡ መሰላቸው፡፡ ሁሉም ከትርምሱ እንደገና ተስፋ ሰነቀ፡፡ ነገር ግን መኪናዋ ኮፈኗ ብቻ ነበር እንጂ ሞተሯ አልተቀየረም ነበር። ቀለሟ ነበር እንጂ ውስጧ ያው ነበር፡፡ ይህም ለጥቂት ጊዜ ማመካኛ ሆነ፡፡ ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ‹ከአዲሱ አሠራር ጋር ባለመላመድ የመጣ ነው፤ መሥሪያ ቤቱ ኮምፒውተራይዝድ እየሆነ ነው፤ ካለፈው አሠራር ለመላቀቅ በሽግግር ላይ ስለሆንን ነው፤ ኅብረተሰቡ አዲሱን አሠራር ስላላወቀው ነው፤ ቢሮ ሲቀየር ፋይል ስለጠፋ ነው፤ ዳታ ቤዙ ስላልተስተካከለ ነው፤ ኔት ወርክ ስለሌለ ነው› ይባል ጀመር፡፡
ደንበኛውም ሠራተኞቹ ሲለምዱ፣ የጠፋው ፋይል ሲገኝ፣ ሽግግሩ ሲያበቃ፣ ኮምፒውተራይዜሽኑ ሲጠናቀቅ፣ ችግሩ ይፈታል ብሎ እንደገና ታገሠ። የተስፋ ቀብድም ተቀበለ፡፡ እየቆየ ሲያየው ግን ተዋንያኑ ቢቀየሩም የፊልሙ ‹ስክሪፕት› ተመሳሳይ ሆነበት፡፡ ‹ቁንጮን ሲያታልሏት ፓንክ ብለው ጠሯት› እየሆነ ታየው፡፡ “ፈሰስም ተጋቢኖም ያው ሽሮ ነው” ማለት ጀመረ፡፡ እንደገናም በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ችግር ተፈጠረ፡፡
በዚህ ጊዜ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሦስተኛውን ፖስታ ከፈተ፡፡ እንዲህ ይላል፤ ‹አሁን አንተም ለተተኪህ ሦስቱን ፖስታዎች አዘጋጅ›፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቁጭ ብሎ ሦስቱን ፖስታዎች አዘጋጀ፡፡ በሰም አሽጎ ቁጥር ጻፈባቸው፡፡ እርሱ አሽጎ ሲጨርስ የስንብቱ ደብዳቤ መጣለት፡፡ እርሱም በተራው ለተተኪው እነዚያን ሦስት ፖስታዎች ሰጠው፡፡ ተቀባዩም በተራው ‹ምን ላድርጋቸው?› ሲል ጠየቀ። መላሹም፤ ‹ድርጅቱን ስትመራ ችግር ከገጠመህ በየተራ እያወጣህ ተመልከታቸው› ሲል መከረው፡፡ አዙሪቱም እንደገና ቀጠለ፡፡
ሀገራችን በዚህ አዙሪት ውስጥ ናት፡፡ ያለፈውን መኮነንና ማውገዝ፤ ከዚያም የነበረውን እንዳልነበረ አድርጎ ›ለሥር ነቀል ለውጥ› መነሣት፤ በመጨረሻም ሌላውን አዙሪት አዘጋጅቶ መሄድ፡፡ እስኪ አስቡት? ሥር ተነቅሎ ለውጥ እንዴት ይመጣል? ከመጣም ለውጡ መድረቅ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ጣል የተደረገ ቅቤ፣ ሲቁላላ ጀምሮ የነበረውን ሽንኩርት አንዴት ያወግዛል፡፡ መጀመሪያ ካንተ በፊት ለሠሩት ዋጋና ክብር ስጥ፤ ከዚያም የተሳሳቱትን በብቃት አርም፤ በመጨረሻም በመሠረቱ ላይ ግድግዳውን፣ በግድግዳው ላይ ድምድማቱን፤ በድምድማቱም ላይ ጣሪያውን እያስቀመጥክ ሂድ፡፡ ሰውዬው ራስ አለው ብለህ ሳትስማማ፤ እንዴት ፀጉሩ መስተካከል አለበት ትላለህ? ያለፈውን በደንብ አለማወቅ ያለፈውን ስሕተት በባሰ ሁኔታ እንድትደግመው ያደርግሃል፡፡
ጨለማውን ደጋግመህ ስላወገዝከው መብራቱ አይበራልህም፡፡ አንድ ሻማ ብትለኩስ ግን ጨለማውን መግፈፍ ትችላለህ፡፡ ልጅ ምንም አዲስ ፍጡር ቢሆን ከእናትና ከአባቱ የሚወስደው ነገር አለ፡፡ በየቀኑ ልጅ እንጂ አዳም አይፈጠርም። ካለፉት ምንም ያልወሰደ አዳም ብቻ ነው፡፡ ሌሎቻችን ግን ካለፉት የሆነ ነገር ወስደን፣ አዲስ ነገር ጨምረን ነው አዲስ ትውልድ የሆንነው፡፡ ካለፉት ምንም ሳይወርስ ሰው ለመሆን የቻለ ማነው? ሁሉንም አፍርሰን፣ ሁሉን አዲስ አርገን፣ ሁሉንም ለውጠን አንችለውም። ካለፈው እንነሣለን፣ ዛሬ ላይ እንሠራለን፤ ወደፊት እንሄዳለን፡፡ ይሄው ነው፡፡
ያለበለዚያ ግን በሦስቱ ፖስታዎች አዙሪት ውስጥ እንወድቃለን፤ መላ ዘመናችንንም ዘይት እንደሚጨምቀው ግመል እንዞራለን፤ ግን አንራመድም፡፡ እንደክማለን፣ ግን ፈቀቅ አንልም፡፡ አዙሪት ውስጥ ስንገባ እንዲህ ነው፡፡     


Read 24541 times