Saturday, 11 June 2016 12:25

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና የወላጆች ኃላፊነት!- ፪

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(1 Vote)

     ልጆችና ቴሌቪዥንን አስመልክቶ ብዙ ስለማይነገርለት የወላጆች ኃላፊነት በክፍል አንድ ጽሑፌ የመነሻ ሐሳቦችን ሰጥቼ ነበር፡፡ የአገራችን ወላጆች (ሁሉም ባይሆኑ አብዛኛው) በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች በልጆቻቸው ባሕሪና አስተሳሰብ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ጊዜ ወስደው ለማሰብ የሚጨነቁ አይመስለኝም። በቅርብ ከማውቃቸው ወላጆች መካከል በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው የልጆቻቸውን የቴሌቪዥን ዕይታ የሚከታተሉና ጥንቃቄ የሚያደርጉት፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግድ ከማጣት በተጨማሪ አለማወቅም ነው ባይ ነኝ፡፡ በዚህ ጽሑፍ፣ቴሌቪዥን በልጆች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስመልክቶ የተካሄዱ ጥናቶችን በመቃኘት የተጽዕኖውን ልክ ለመመልከትና ወላጆች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተሰጡትን ምክሮች ለኢትዮጵያዊያን ወላጆች ግንዛቤ እንዲረዳ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
የሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን የቴክኖሎጂ አብዮት ካፈራቸው ግኝቶች መካከል አንዱ የሆነው ቴሌቪዥን፤የዕድሜ ታላቁ የሆነው ሬዲዮ ለሰው ልጅ ከሰጠው መረጃን በድምጽ የማስተላለፍ ዕድል አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ምስልን በማከል፣በአካል ልንገኝባቸው በማንችላቸው ሥፍራዎች ሁሉ እንድንገኝ አስችሎናል፡፡ የመረጃ፣ የመማሪያና የመዝናኛ ምንጭ በመሆን የሚሰጠው ጠቀሜታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው። በተለይ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን በቴክኖሎጂው መዘመን የተነሳ [በተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን አማካኝነት] በእጃችን መዳፍ ላይ እስከመገኘት ድረስ ተራቋል፡፡
 በዘመናችን የቴሌቪዥን ቻናሎች በጣም በዝተዋል፡፡ ብዛታቸው የፈጠረው ውድድር ቀደም ባለው ጊዜ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ የነበረው የአየር ላይ ቆይታቸው ወደ ሃያ አራት ሰዓታት እንዲያድግ አድርጓል፡፡ ድሮ በባለ ዘንግ አንቴና በየቤታችን ይደርስ የነበረው የቴሌቪዥን ስርጭት፣ ዛሬ በዲጂታል ስርጭት መቀበያ ሳህን (dish) እና የስርጭት መቀበያ መሣሪያ (decoder) እየመጣ ፣ ከሁለትና ሦስት ቻናሎች በላይ የማይታዩበት ጊዜ አልፎ በሺ የሚቆጠሩ ቻናሎችን በቴሌቪዥናችን መስኮት እየተመለከትን ነው፡፡  
ይህ የቻናሎችና የፕሮግራሞቻቸው መብዛት አማራጭ በመስጠት በኩል ጥሩ የሚባል ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ተመልካቾች እንደ ምርጫና ፍላጎታቸው የተለያዩ ቻናሎችን እያማረጡ መመልከት በመቻላቸው መረጃ በማግኘት፣ በመማርና በመዝናናት ረገድ እርካታቸው ጨምሯል። በሌላ በኩል ግን በጊዜ ያልተገደበና ምርጫ-አልባ የሆነ ቴሌቪዥን የመመልከት ልምድ ቀላል ያልሆነ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ለረዥም ሰዓታት ቴሌቪዥን መመልከት የጤናና የሥነ-ልቦና ጉዳት እንደሚያስከትል በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይህ ጉዳት የቅርብ ክትትል በሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ላይ ብቻ ሳይሆን በአዋቂዎችም ላይ የሚደርስ እንደሆነም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሌላው የቴሌቪዥን ጉዳት፣ የሚቀርቡት ፕሮግራሞች በተመልካቾችን አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በማስተማር፣ በማሳወቅ፣ መረጃ በመስጠትና በማዝናናት ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ቢሆንም፣ በተለይ ደግና ክፉውን ለይቶ ለማወቅ ገና የሆኑት ሕጻናትና ታዳጊዎች ሊመለከቷቸው የሚገቡትን ፕሮግራሞች መርጦ እንዲመለከቱ ማድረግ ካልተቻለ በወደፊት ባሕሪያቸው ላይ አደገኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጠራል፡፡
ጥናቶች ምን ይላሉ?
ለመሆኑ ቴሌቪዥን በሕጻናት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን እንኳን ይህንን ስለመሰለው ጉዳይ ቀርቶ በጣም አንገብጋቢ ስለሆኑ ጉዳዮቻችን ጥልቅ ጥናቶች አይደረጉም፣ ቢደረጉም እንኳን በተሟላ ሁኔታ ተደራጅተው ስለማይቀመጡ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም፣ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከታቸው ጥናቶች ባደጉት አገሮች የተደረጉትን ይሆናል፡፡ የእነዚህ ጥናቶች ውጤት በተወሰነ መልኩ ከአገራችን ሁኔታ የሚለይባቸው መልኮች ቢኖሩትም፣ መነሻው ግን ተመሳሳይ ስለሆነ ከጥናቶቹ በመነሳት ለእኛ የሚሆነውን ድምዳሜ መውሰድ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ቴሌቪዥን በሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስመልክቶ የሚደረጉ ጥናቶች የትኩረት አቅጣጫዎቻቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ ይህ ጽሑፍ፡-
ልጆች በቀን ለምን ያህል ሰዓታት ቴሌቪዥን ይመለከታሉ?
 በጨቅላነት ዕድሜ ቴሌቪዥን መመልከታቸው ምን ዓይነት ውጤት ያስከትላል? እና
ልጆችን ከአሉታዊ የቴሌቪዥን ተጽዕኖ ለመጠበቅ ምን ይደረግ?
የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሞክራል፡፡
ሲንዲ ስሚዝ የተባሉ የንግግር ነክ ሕመሞች ተመራማሪ (speech pathologist) “Television Watching: Practical Advice for Parents of Young Children” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ወላጆች ለምን ልጆቻቸው ቴሌቪዥን እንዲመለከቱ እንደሚያደርጉ ከልምዳቸው ተነስተው ሲያብራሩ፤ ”አንዳንዶቹ ‘ልጄ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ስለሚወደው፣’ ወይም ‘ ፊደላትን ስለሚማርበት’፣ ሌሎቹ ደግሞ ‘ልጄ ምግብ አማርጣ የምትመገብ ናት፤ ቴሌቪዥኑ ከተከፈተ ግን እየበላች እንደሆነ ስለማታስተውለው ያለምርጫ ትመገባለች፣’ ወይም ‘እኔ እራት ሳዘጋጅ ልጄ ቴሌቪዥን በማየት ስለምትጠመድ አትረብሸኝም’ የሚሉና መሰል ምክንያቶችን ይሰጣሉ” ይላሉ፡፡
ባለሙያዋ በጥናታቸው ቴሌቪዥን ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 11 ዓመት ድረስ በሆኑ ሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ተመልክተዋል፡፡ ጥናታቸው ሕጻናትና ታዳጊዎች በቀን ውስጥ ለስንት ሰዓታት ቴሌቪዥን እንደሚመለከቱ የሚፈትሽ ሲሆን በተገኘው ውጤት መሠረት በአሜሪካ አንድ ልጅ በአማካይ በቀን ከ4 ሰዓታት በላይ ቴሌቪዥን ሲመለከት፣ በካናዳና አውስትራሊያ በቀን ከ2 ሰዓታት በላይ፣ እንዲሁም በእንግሊዝ ከ2 ሰዓት ተኩል በላይ ልጆች ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፡፡
ከዚህ በመነሳት፤ ”አንድ ልጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በክፍል ውስጥ ካሳለፈው ጊዜ ይልቅ በቴሌቪዥን ፊት ተቀምጦ ያሳለፈው ይበልጣል” ይላል ጥናቱ፡፡
ይህ የልጆች የቴሌቪዥን ልምድ ታዲያ ”ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል” ባይ ናቸው ስሚዝ፡፡ ጉዳቶቹ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተመድበዋል፡-
አካላዊ ጤና፡- በምዕራባዊያን አገሮች ለሕጻናት ውፍረት ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ከሚወሰዱት ነገሮች መካከል አንዱ ልጆች ቴሌቪዥን፣ ቪዲዮና ዲቪዲ ለመመልከት፣ እንዲሁም የኮምፒዩተር ጌም ለመጫወት ሲሉ በርካታ ሰዓታትን ተቀምጠው ማሳለፋቸው ነው (ይህ ልምድ በአሁኑ ጊዜ ወደ አገራችንም እየመጣ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ በዚህም የተነሳ የልጆች የአካል እንቅስቃሴ ልምድ ቀላል በማይባል ደረጃ እየቀነሰ ይገኛል፡፡
ሥነ-ባሕሪያዊ ጤና፡- እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፣ አንዳንድ ለሕጻናት ተብለው የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች በአማካይ በሰዓት 20 የሚደርሱ የግጭት/ረብሻ/ ትዕይንቶችን የያዙ ናቸው። እነዚህ ትዕይንቶች በካርቱን ፊልሞች ላይ ከሚታየው የገጸ-ባሕርያት የእርስ በርስ መጋጨት አንስቶ በእውነተኛ ገጸ-ባሕርያት እስከሚተወኑ የረብሻ (violence) ድርጊቶች ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች፤ ”ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የሕጻናትና ታዳጊዎች የቴሌቪዥን ዕይታ ድርጊቶችን መሞከር፣ ፍርሃትንና ችግሮችን በኃይልና በጉልበት የመፍታት ዝንባሌን ያዳብራል” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ቋንቋ እና አጠቃላይ ትምህርት፡- ይህንን ክፍል አስመልክቶ በርካታ ጥናቶች የተደረጉ ሲሆን ውጤታቸው የተለያየ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን ”ዜናው ጥሩ አይደለም” ይላል የስሚዝ ጽሑፍ፡፡ እንደነዚህ ጥናቶች ከሆነ፣ ለማስተማሪያ ተብለው የሚዘጋጁት ፕሮግራሞች ሳይቀሩ በጨቅላ ሕጻናት የቋንቋ ትምህርት ብቃት ላይ መቀነስን አስከትለዋል፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው?
ሲንዲ ስሚዝ የተለያዩ ባለሙያዎችና ተቋማት፣ ወላጆች የልጆቻቸውን ጤናማ የቴሌቪዥን ዕይታ ለማረጋገጥ ”ያግዟቸዋል” በማለት ካስቀመጧቸው የመፍትሄ ሐሳቦች መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አቅርበዋቸዋል፡-
የቴሌቪዥን መመልከቻ ሰዓትን መወሰን፡- ሕጻናት እንደ ዕድሜያቸው የተለያየ የቴሌቪዥን መመልከቻ የሰዓት ገደብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ለረዥም ሰዓት ቴሌቪዥን መመልከት የለባቸውም፡፡ በዚህ መሠረት፡-
ሀ. ከ2 ዓመት በታች፡- የአሜሪካ የሕጻናት ሕክምና ማኅበር (American Association of Pediatrics) እና በርካታ ኤክስፐርቶች ”ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በጭራሽ ቴሌቪዥን መመልከት አይኖርባቸውም” ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የጨቅላ ሕጻናት አዕምሮ በፈጣን ሁኔታ የሚለዋወጡ ምስሎችና ንግግሮችን ለማስተናገድ በሚያስችል ደረጃ የተዋቀረ ያለመሆኑ ነው፡፡
ለዚህ የዕድሜ ክልል ተብለው የሚዘጋጁ ዲቪዲዎች ቢኖሩም እንኳ ”አንድ ሕጻን የግንኙነትና የተግባቦት ክህሎቱን ሊያዳብር የሚችለው ከሌሎች ሰዎች ጋር አብሮ በመሆኑ ብቻ ነው እንጂ በዲቪዲው ዕይታ ምክንያት አይደለም” ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡
ለ. ከ2 እስከ 3 ዓመት፡- በእንግሊዝ የታወቁት የንግግርና የቋንቋ ቴራፒስት ዶ/ር ሳሊ ዋርድ በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናት የቴሌቪዥን መመልከቻ ጊዜ በቀን ለግማሽ ሰዓት ብቻ መሆን እንዳለበት ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡
ሐ. ከ3 እስከ 5 ዓመት፡- እንደባለሙያዎቹ ለዚህ የዕድሜ ክልል በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ ቴሌቪዥን መመልከት በቂ ነው፡፡
ቴሌቪዥንን በማይታይበት ጊዜ ማጥፋት፡- በቤታችሁ ውስጥ ቴሌቪዥን ተከፍቶ የሚመለከተው ሰው ከሌለ አጥፉት፡፡ ከቴሌቪዥኑ የሚወጣው ድምጽ ትኩረትን የሚሠርቅ ስለሆነ ልጆቻችሁ በሌሎች ጠቃሚ ነገሮች (ለምሳሌ የወላጆች ድምጽ) ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ከሰዎች ጋር የግንኙነት መዘግየት ችግር ላለባቸው ልጆች ”ይህ ጠቃሚ መፍትሄ ነው” ይላሉ ባለሙያዋ፡፡
ተስማሚ ፕሮግራሞችን መምረጥ፡- ልጆቻችሁ የሚወዷቸውን፣ ነገር ግን ለዕድሜና የዕድገት ደረጃቸው የሚመጥኑና የአዋቂ ይዘት (adult theme) የሌላቸውን ፕሮግራሞች እንዲመለከቱ ፍቀዱላቸው፡፡  በተለይ ልጆቻቸሁ በወደፊት ሕይወታቸው ውስጥ ከሚገጥሟቸው ተመክሮዎች ጋር የተገናኙ ፕሮግራሞች ተመራጭ ናቸው፡፡
ፕሮግራሞችን አብሮ መመልከትና መወያየት፡- በተቻላችሁ መጠን ከልጆቻችሁ ጋር የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ለመመልከት ሞክሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ በፕሮግራሙ እየተደረገ ስላለው ነገር አብዝታችሁ ከልጆቻችሁ ጋር ተወያዩ። ሁልጊዜ አብራችሁ ለመመልከት ካልቻላችሁ የፕሮግራሙን ተስማሚነት አስቀድማችሁ አረጋግጡ፡፡ ለሕጻናት በሚቀርቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ውስጥ የተለመዱት ገጸ-ባሕርያት ተወዳጅ ቢሆኑም፣ አስፈሪ የሆኑትን ግን እንዳይመለከቱ ተጠንቀቁ፡፡
ልጆችን ከንባብ ጋር ማስተዋወቅ፡- ቴሌቪዥንን አብዝተው የሚመለከቱ ልጆች አልፎ አልፎ የንባብ ችሎታ ማነስ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ ንባብ በልጆች የወደፊት የትምህርት ስኬት ላይ ወሳኝ ግብዓት በመሆኑ ልጆቻችሁን በትንሽነት ዕድሜያቸው ከመጻሕፍት ጋር እንዲላመዱ ጥረት አድርጉ፡፡ ልጆች በጨቅላነታቸው ጊዜ ማንኛውንም ዕቃ (አሻንጉሊቶቻቸውን ጨምሮ) የመወርወር፣ ከግድግዳ ጋር የማጋጨትና ለማኘክ የመሞከር ልማድ ስላላቸው በዚህ ዕድሜያቸው የምትገዙላቸው መጻሕፍት የጠንካራ ፕላስቲክ፣ የጨርቅ፣ ወይም የካርድቦርድ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ”በዚህ መልኩ ከመጻሕፍት ጋር የተዋወቁ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር መጻሕፍትን አብሮ ማንበብን ይወዳሉ” ሲሉ ባለሙያዋ ይመክራሉ፡፡
እስካሁን የተመለከትነው ቴሌቪዥንን በአግባቡ አለመመልከት በሕፃናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖና ይህንን ተጽዕኖ ለመከላከል ወላጆች ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚሉትን ነው፡፡ በቀጣዩ ጽሑፌ ደግሞ በአገራችን የልጆችን የቴሌቪዥን መመልከት ልምድ አስመልክቶ ወላጆች ምን እያደረጉ እንደሆነ የታዘብኩትንና ለጤናማ የልጆችና የቴሌቪዥን ግንኙነት ምን ቢደረግ የተሻለ እንደሚሆን ያሉኝን ሐሳቦች አቀርባለሁ፡፡



Read 1833 times