Saturday, 11 June 2016 12:24

ትቸው! ረስቸው!

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(7 votes)

ትቸው ረስቸው ሆኜ እንደነገሬ፤
በምን አስታውስኩት ይህን ጉዳይ ዛሬ?
“መድረክ ንጉሳዊ ነው እንዴ?” በሚል ግርማ ሰይፉ አንድ የኔንም ስም የሚጠቅስ ጽሁፍ አቅርቧል።
አቶ አሰፋ ጫቦ በቅርቡ ባሳተመው መፅሀፍ ውስጥ የሸዋ ንግስና ከተመለሰ የእኛም መመለስ አለበት የሚል ስላቅ አቅርቦ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር በየነም ቤተሰቦቻቸው በአካባቢው እንዲህ ዓይነት የንግስና ጥያቄ ከሚጠይቁት ወገን ናቸው ስለሚባል፤ ይህ እስኪመጣ ድረስ መድረክን የንግስና መለማመጃ ያደረጉት መስለኝ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ብዙ ሙከራ አድርገው ያልተሳካላቸውን የአመራር ቦታ ቢቻል ፖለቲካውን ጭምር መተው ለምን ተቸገሩ?
መጀመሪያ ከት-ከት ብዬ ሳቅኩ:: ሁለተኛም አንድ፤ ”እዚያ መድረስ ክልክል ነው!” ብዬ የሾህ አጥር ያጠርኩበት መንደር አደረሰኝ። ስለ ዶክተር በየነ ጴጥሮስ ያለው ነው። ፈርቼ፤ አለሳልሼ፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የቆመለትን አላማ፤ እኔም ጠንሳሽ መሥራች የሆንኩትን ድርጅት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕብረት አገር እያየ መቃብር ሲያወርደው ዝም አልኩ። ዝም እንኳን አላልኩም። አገር ሳያውቀው ፀሐይ ሳይሞቀው በ email ብዙ አልኩት። መንፈሱ  “አትቅበረን! አትከፋፍለን!አማራጩ መንገድ ይህ ነው!” የሚል ነበር። አሁን በግርማ ምክንያት ለበየነ ጴጥሮስ የላኩለትን መልእክት ሳነበው ገረመኝ። ዛሬ የገረመኝ ከ2003 በፊት ጀምሮ የላኩት መልእክት በጣም ብዙ፤ረዣዥምም ነበሩ። ይህ ባይመጣ ኖሮ ለሕይወቴ ታሪክ ያልኩት ነበር።
በየነን  ያውቅሁ በነሐሴ 1983  አፍሪካ አዳራሽ፤ “የስላምና ዲሞክራሲ ስብስባ” ሳቢያ ሒልተን ሆቴል የሰነበትን ሰሞን ነበር። ደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች ሕዲያን ጨምሮ የፖለቲካ ዝንባሌ የነበራቸው ባብዛኛው እንተዋወቃለን። በየነ ከዚያ ውስጥ አልነበረምና ሳየው ገርሞኝ፤ “አንተ ደግሞ ከየት መጣህ?” ያልኩት በውስጤ ነበር። በዚያ ስብሰባ ሳቢያ የደቡብ ህዝቦች ህብረት ፈጠርን። የ11 ብሔረሰብ ተወካዮች ተፈራረምንበት። የተፈራርምነው የሒልተን ሆቴል አርማ (Letterrhead) ባለበት ወረቀት ነበር። አንድ ቅጅ ለሆቴሉ ማነጀር ሰጠሁ። እኔ የለኝምና አስቀምጦት ከሆነ ታሪካዊም ይመስላል። እኔ ሊቀመንበር፣ ተስፋዬ ሐቢሶ ዋና ጸሐፊ ሆነን ተመረጥን። በየነ ጴጥሮስ ወዲያው ስራውን ጀመረ።
በነጋታው በጥብቅ እፈልግሃለሁ ብሎ ቡና ጋብዞኝ፣ ተስፋዬ ሐቢሶ ላይ ክሱን ሲደረድር አቋረጥኩት። በሐዲያና ከምባቶች መካከል ያለውን የአካባቢ አለመግባባት በመጠኑም አውቅ ስለነበረ፤ከሁሉም በላይ ተስፋዬ ሐቢሶን የተሻለ የማውቀውም ስለነበረ ክሱን አልተቅበልኩትም። የሆነ ሆኖ ነገሩን ከተስፋዬ ጋር ሳነሳው፤ “በየነ ዋና ጸሀፊ ለመሆን ስለሚፈልግ ይውስደው!” አለኝና አቃለለኝ። ዋና ጸሐፊም ሆነ።
በሕዳር ወር 1984 ወደ አውሮጳና አሜሪካ ለመጓዝ ዝግጅት ላይ እያለሁ ፒያሳ  ቲ- ሩም ምሳ ሊጋብዘኝ እንደሚፈልግ ነገረኝና ተገናኘን። “የምትሔድ ከሆነ ስራውን በተሻለ ለማጠናከር  የሊቀመንበርነቱን ስራ በውክልና ስጠኝ”  አለኝ። ወረቀት ይዞ ነበርና እዚያው ፈርሜ “እስከምመለስ ድረስ በየነ ጴጥሮስ ሊቀ መንበር ሆኖ እንዲስራ” ብዬ ጻፍኩለት። ለዚህ ጉዳይ ምሳ መጋበዝ ድረስ መሔዱ ያኔም አሁንም ይገርመኛል። ምሳ የሚያስጋብዝ ትውውቅ የለንምና ነው።
ከዚያም እኔ በህዳር 1984 ከኢትዮጵያ ወጣሁ። መመለሻ ድልድዬን መለስ ዜናዊ ቦደሰውና በዚያው ቀረሁ። በየነ ጴጥሮስ ድርጅት ማፈራረሱን፤መከፋፈሉን፤ማኩረፉን ተያያዘው። ይህንን ስራውን የሚቃወም የሚመስለውን፤የሚጠረጥረውን ሰው ያኮርፋል። ይህን ወዳጃችንን ዶክተር መረራ ጉዲናና መጠየቅ ነው። አንዴ ኢድሐቅ ለሚባል የኢሕአፓ ስዎች ያሰባሰቡት ድርጅት ሊቀ መንበርነት፣ ከበየነ ጋር ተወዳድሮ መረራ ሲያሸንፍ ጊዜ አኮረፈው። ሌሎች ስማቸውን ለጊዜው መጥራት የማልፈልገው ሁለት የደቡብ ኢትዮጵያ ድርጅቶች መሪዎች የነበሩም ማኩረፉን ነግረውኛል። ከኔም ጋር ያለው ግንኙነት የኩርፊያ ያክል ነው። ለዚያውም እኔ ተጠንቅቄ፣ ሸሽቼ እንጅ ተቀናቅኜም አላውቅም። የምሸሸው “አሰፋ እንዲህ አለኝ !” የሚል ምክንያት ላለመስጠት ነበር።
መጀመሪያ የበተነው የኛን ድርጅት ኦሞቲክን ነበር። ኦሞቲክ ከድርጅቱ  በስነ ሥርአት ጉድለት ያሰናበታቸውን ሁለት ሰዎች፤ ፊታውራሪ መኮንን ዶሪንና ደምሴ ጻራና የምክር ቤት አባል አስደረጋቸው። የሚገርመውኮ ፊታውራሪ መኮንን ኢህአዴግ  ሆኖ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴር ሆኖ የተሾመው ከኦሞቲክ በተገለለ ማግስት ነበር። ሌላው በጥር ወር 1984 ወደ 2,000 የሚጠጋ አዲስ አበባ ኗሪ፤ የጋሞ ጎፋ ሰው ”መኮንንና ደምሴ ከሐዲዎች ናቸው !”ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ ማንነታቸውን በአደባባይ ገልጧል’ኮ።
የኦሞቲክን ማህተምና ሌሎች ሰነዶች በድርጅቱ ደንብ መሠረት ከሚይዘው ከነጋሽ ቤት በየነ ጴጥሮስ በፖሊስ አስገድዶ ወስዶ፣ አስወስዶ ለደምሴ ጻራና መኮንን ዶሪ ሰጠ። አሰጠ!
ሌላው፣ረዣዥም emails ለበየነ ጴጥሮስ ከላኩበት ጉዳዮች አንዱ በዋሺንግቶን አካባቢ በደቡብ ድርጀት ስም የሚፈጸመውን የሚመለከት ነበር። የመጀመሪያው የሰሜን አሜሪካ ወኪል አድርጎ የመደበው አንድ እድሜው ወደ 30 የሚጠጋ ጎልማሳ ሐዲያ ነበር። የወጣለት ቀና ሰው ሆኖ አገኘሁት። ሆኖም የፖለቲካ ሀ ሁ አያውቅም። ኦነግን  (ኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር)  ወያኔ ካባረረው በኋላ አቢዩ ገለታ DC የኦነግ ቢሮ ከፍቶ ነበር። ወይም የነበረውን፣ የነበሩትን አስወጥቶ ተረከበ። አንድ ቀን ጎብኝቸው ነበር። ግድግዳው ላይ ያለው የጀነራል ታደሰ ብሩ ፎቶግራፍ ነው። ብቻ የሚያስቅ የሚያሳዝንም ትርእይት አይቼ ተመለስኩ። አብዩ DC ባደረገው የኦነግ ስብሰባ፣የደቡብ ሕብረት የኦነግ ተለጣፊ መሆኑን የሚያሳይ ዝግጅት ተደርጎ፣ ቪድዮም ፎቶግራፉም ተሰራጬ። ይህንኑ ለበየነ ጻፍኩለት። ፍንክች!
ሁለተኛው ያንን ልጅ ተከተው ወኪል አድርጎ የመደባቸው ሁለት ተጻራሪ ሰዎች ነበሩ። ዋንኛው ሙሉ ለሙሉ ለኢሕአፓ የሚሰራ ነው። ሌላው ለደቡብ ሕብረት ለመሥራት የሚጥር ነበር። ተቆላልፈው ቁጭ አሉ! ከሎስ አንጀለስ  DC  መጥቼ ዉትብትቡን ለመፍታት ሞከርኩና  አልቻልኩምና፤ “እስቲ መላ እንምታ”  የሚል 3  ገጽ email ለበየነ ጴጥሮስ ላኩኝ። ፍንክች!
አሁን ዘመኑን በረሳሁት በየነና መኮንን፣ አሜሪካ ይመጡና እኔ የነበርኩበት ቤት ያርፋሉ። ምንም ምንም እንዳልሆነ አድርጌ አስተናገድኳቸው። የመጡት ፕሬዚዳንት ካርተር፣ አትላንታ ባዘጋጁት የሆነ የእርቅ ስብስባ ላይ ለመገኘት ነበር። የትኛውን ድርጅት ወክሎ እንደመጣ፣ እንኳን እኔ በየነም የሚያስታውሰው አይመስለኝም። ሊቀመንበር የሆነውን ድርጅት ብዛት ማስታውስ የሚችል አይመስለኝም። ዘመኑም ራቅ ብሏል። የማስታውሰው አቶ ተሾመ ገብረ ማርያምም አብሮ መጥቶ ነበር። ቦስተን ሆኖ ለበየነ ስልክ ሲደውል አንድ ሁለቴ አነጋግሬያለሁ። ካርተርንም በስልክ ያነጋገርኩት በዚያ አጋጣሚ ነበር። ብቻ ብዙ አብረው የመጡ ስልክ ይደውሉለታልና ያነጋግራል። እሰማለሁም!! በተመሳሳይ ጉዳይ ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ መልስ ሲስጥ እሰማዋለሁ:: ይገርመኛል!!
አንድ ጥዋት ሎስ አንጀለስ (Los Angeles) በእግራችን ሽርሸር ስናደርግ “በየነ፤አንተ ከደቡብ ኢትዮጵያ አትመስለኝም!” አልኩት። ከት ከት ብሎ ስቆ፤ (ሳቁ ትርጉሜ ጭምር ገብቶትና በአድናቆትም እንደተናገርኩት ቆጥሮ  ይመስለኛል) “እንዴት? ለምን?” አለኝ። “ሁለመናህ !” አልኩት። “አባቴ ፖሊስ ነበሩ። ያደኩትም ጋሞ ጎፋ ነው” አለኝ። አንድምታው ተንኮሉን የተማርኩት ከፖሊሱ አባቴ ነው ለማለት መሰለኝ። የጨንቻ ሰዎች ”የፖሊስ ዘመድ የቤንዚን አመድ የለውም!” ሲሉም እሰማ ነበር። እኔ “ከደቡብ ኢትዮጵያ አትመስለኝም!” ስለው፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሰው፤ ይህ አነባበሮ ጠባይ የለውም ለማለት ነበር።
ከብዙ በጥቂቱ፣በየነ የጋሞ ልጆችንም አበጣበጠ። የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የሚባል ነበርና መሪዎችን አልፎ፤ተቀናቃኝ ፈጥሮ፣ በነዚያ ተቀናቃኞች አማካይነት ማባላቱን ጀመረው። ይህ መባላት የጋሞ መሠረታዊ ባሕርይም ስላልሆነ፣ እንዴት እንደተሳካላት አሁንም ይገርማኛል። በዚህ ምክንያት ያደረኩት email አሁን ሳነበው ታሪካዊ ሰነድ ይመስለኛል። አጥጋቢም ሆነ የሚረባ መልስ አልሰጠኝም። የዚህ የemail ጥሩ ነገሩ፣ በየነ አልደረሰኝም ሊል አይችልም። ከደረሰ ደረሰ ፤ካልደረሰ “ተቀባይ የለውም!” ብሎ መልሶ ለላኪው ይልክለታል። መልሶ አልላከልኝማ!
ግርማ ሰይፉ፤ ስለ ንጉስና በዝርያ አልጋ መውረሱን ሲያነሳ፣ ኃይለ ሥላሴን አስታወሰኝ። በ1966 ንጉሱ ጃጅተው ነበር:: ያም ሆኖ ስልጣንዋን የሙጥኝ ብለው ያዟት። ከዚያ በኋላ ደርግ የሆነው የወታደር ስብስብ  ሰላምታ ይሰጥና፤“እገሌንም እገሌንም ወህኒ ማውረድ እንፈልጋለን!” ሲሉ ”ውሰዷቸው!” ይሉ ነበር። አድሮ ”ልጆችዎንም፣ የልጅ ልጆችዎንም !” ሲሏቸው “ውሰድዋቸው!” ሆነ። በመጨረሻም ራሳቸውን አንዲት እዚች ግቢ በማትባል መኪና አስገብተው ወሰዷቸው። ”ከስልጣን ሞት ነው የሚለየን!” የማለት ጥሩ ምሳሌ ይመስሉኛል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ1983 ጀምሮ ስማቸው ያልተለየ 3 ሰዎች አሉ። በየነ ጴጥሮስ፤ኃይሉ ሻውል (ይቅርታ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል) እና ዶክተር መረራ ጉዲና ናቸው። ኢንጂነሩ አሁን  በተፈጥሮ ግዴታ ገሸሽ ያሉ  ይመስላል። መረራ ስለ ትላንት፣ ስለ ዛሬ፣ ስለ ነገም ይጽፋል። ይናገራል! በፖለቲካዉ ቦታ፤በቀጥታም በተዘዋዋሪም ስፍራ (Relevance) ያለው ይመስለኛል።
በየነ ጴጥሮስ፤ከላይ በጨረፍታ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤መላውን አለም ደጋግሞ ዞሯል’ኮ! በዚህ 25 አመት ሙሉ የድርጅቶች መሪነቱ ምን ፈየደ? ምንስ ተናገረ? ምንስ ጻፈ? የሚል ቢኖር ጉዱ ይፈላ ነበር። አለመኖሩ በጀው። እንዳይኖሩ አድርጎ ይሆን? አሁን ግርማን ላከበት? አንዳንዴ ያኔ ከባንክ ገንዘብ ይዞ ጠፍቶ በኋላ የወያኔ አባል ሆኖ፣ የገንዘብም ምክትል ሚንስቴር እንደሆነው ሰውዬ፣ በየነ  ጴጥሮስም የወያኔ አባል ይሆን? እላለሁ፡፡ ይኸው ለ25 አመት ያ ሁሉ ሰው ወህኒ ሲወርድ፣ በየነ አለምን ይዞራል።
ይህ ሁሉ እንግዲህ የትላንት ያለፈ የቀብር ስነ ስርዐት ታሪክ መሆኑ ነው። አንዳች ትምህርት ቢኖረው ትዝብት ብቻ ይመስለኛል። ወይም የትዝብት ሸቀጥ እጥረት አንዳንዶቻችን ላይ ጎልቶና ፈክቶ መታየቱ ይመስለኛል:: ትምህርትም አለው ብዬ አምናለህ። አንድ ቦታ፣ ጸጋዬ ቲያትር ውስጥ፣ አንዱ ገጸባሕርይ “ሌላ ብላ! እኔ’ኮ ቱሪስትና ፒስ ኮር እለያለሁ!” ይላል። በነገሰና ሊቀመንበር በሆነ መካከል ያለውንም ልዩነት የሚያሳይ ይመስለኛል።
ጎበዝ! ያለበለዚያ ኢትዮጵያ’ የወጣቶች አገር’ኮ ነች!!
ዘኃለፈ ስርየት ይባልና ለንስሀ ሞት አብቃኝ!! ተብሎም ይጸለያል’ኮ

Read 3026 times