Saturday, 21 May 2016 17:25

የፊሊፒንሱ ቦክሰኛ በምክር ቤት ምርጫ አሸነፈ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   16 ሚ. ድምጾችን አግኝቷል፤ ወደ አገሪቱ ፕሬዚዳንትነት ተጠግቷል ተብሏል
     ፊሊፒንሳዊው የአለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ማኒ ፓኪዮ ከትናንት በስቲያ ይፋ በተደረገው የአገሪቱ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ውጤት፣ ለምክር ቤት አባልነት የሚያበቃውን ድምጽ በማግኘት አሸናፊ መሆኑንና ወደ አገሪቱ ፕሬዚዳንትነት ተጠግቷል መባሉን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ ምክር ቤቶች ምርጫ መከናወኑን ያስታወሰው ዘገባው፤የምርጫ ኮሚሽኑ ሃሙስ ዕለት ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት፣ የአገሪቱ የላዕላይ ምክር ቤት አባል ለመሆን የሚያስችላቸውን ድምጽ ካገኙ አዳዲስ ተወዳዳሪዎች መካከል፣ ከ16 ሚሊዮን በላይ ድምጾችን ያገኘው ቦክሰኛው አንዱ መሆኑን አስታውቋል ብሏል፡፡
“በቦክሱ አለም ሳደርገው እንደቆየሁት ሁሉ፣ ወደ ፖለቲካው ስገባም፣ አገሬን ለመጥቀም በትኩረትና በስነ-ምግባር ተግቼ እሰራለሁ!... እንደ አንድ አዲስ የምክር ቤት አባልነቴ፣ በሁሉም ደረጃዎች ትምህርት በነጻ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር የተቻለኝን ጥረት አደርጋለሁ” ብሏል የ37 አመቱ ቦክሰኛ ፓኪዮ፣ የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፡፡
ፓኪዮ ባለፈው አመት በተከናወነውና የክፍለ ዘመኑ ፍልሚያ በተባለው የቦክስ ግጥሚያ ላይ ከታዋቂው ፍሎይድ ሜዌዘር ጋር ተጋጥሞ ድል ባይቀናውም ምርጫው ከመከናወኑ ከአንድ ወር በፊት ከአሜሪካዊው የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ቲሞቲ ብራድሊ ጋር በላስቬጋስ የቦክስ ግጥሚያ አድርጎ ድል እንደቀናውም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1581 times Last modified on Saturday, 21 May 2016 17:31