Saturday, 09 April 2016 10:09

አሜሪካ ኤምባሲ በፊልም ውድድር ዳኝነት ላይ ያሳየው ቸልተኝነት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(1 Vote)

      ይህ ፅሁፍ የአሜሪካ ኤምባሲ በዚህ ዓመት ባዘጋጀው የአጭር ፊልም ውድድሮች ላይ የተፈፀሙ መሰረታዊ የሆኑ የዳኝነት ስህተቶችን የሚጠቁም ነው፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት ከሚሳተፉት የውጭ ሀገር ኤምባሲዎች መካከል የአሜሪካ ኤምባሲ ቀዳሚ ነው፡፡ ኤምባሲው ይሄንንም ተግባሩን ከሌሎች ኤምባሲዎች በላቀ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በማስተዋወቅ፣ ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ እንዲሳተፉ ከፍተኛ ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም ለኤምባሲው ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያከናውናቸው ማህበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ የሴቶች ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በዚህም ኤምባሲው “Women’s History Month” ብሎ የሰየመውን በዓል በዚህ ዓመት መጋቢት ወርን ሙሉ አክብሯል። ከክብረ በዓሉ አንደኛው በኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ የሚያተኩር የ3 ደቂቃ የፊልም ውድድር ማዘጋጀት ነበር፡፡ “Her Story Video Challenge” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው በዚህ የፊልም ውድድር ላይ 190 ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፡፡
የውድድሩ አሸናፊዎችም መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ይፋ ሆኗል፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረው የውድድሩ ዳኞችን በማስተዋወቅ ነበር፤ ዳኞቹም በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ጥሩ ስም ያላቸው አርቲስቶች፡- አዜብ ወርቁ፣ ዘላለም (ዘሌማን ፕሮዳክሽን) እና ቴዎድሮስ ተሾመ (ቴዲ ስቱዲዮ) መሆናቸው ተነገረ፡፡
በቃ! ዳኞቹ እነዚህ አርቲስቶች ብቻ ናቸው! ውድድሩ የፊልምና የስርዓተ ፆታ ጉዳይ ስለሆነ ተጨማሪ ዳኞች ይኖራሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። የፊልሞችን የጥራት ጉዳይ እነዚህ አርቲስቶች ይገምግሙት ቢባል እንኳ፣ የፊልሙን የስርዓተ ፆታ ይዘትስ ማን ሊገመግመው ነው? “አርቲስቶቹ?” ጉድ ነው መቼም! አእምሮዬ በዚህ ሀሳብ እየተብሰለሰለ ሳለ፣ ጭራሽ ብዙ ችግሮች ያሉበት ፊልም አንደኛ መውጣቱ ሲነገር ግራ ተጋባሁ፡፡ “ይሄ ኤምባሲ ምንድን ነው እያደረገ ያለው?” አልኩ ለራሴ፡፡ በዚህም ኤምባሲው የዳኝነት ሂደቱ ላይ በቸልተኝነት የፈፀማቸውን ሁለት ስህተቶች ተመለከትኩ፡፡
የኤምባሲው የመጀመሪያ ስህተት “ለፍትሃዊ ዳኝነት” ጥበቃ አለማድረጉ ነው፡፡ ይሄም በቀጥታ የሚመለከተው ዳኞችና ተወዳዳሪዎች በስራ ወይም በሌላ አጋጣሚ (በዝምድና ሊሆን ይችላል) እርስበርስ የሚተዋወቁ ቢሆኑ ወይም ጓደኝነት ቢጤም ቢኖራቸው ዳኝነቱ ላይ “የፍትህ” ነገር እንዴት ትሆናለች? የሚለው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኤምባሲው “የጓደኛ ዳኝነት”ን የሚከላከልበት ስርዓት አልዘረጋም፡፡
“ኤምባሲው “የጓደኛ ዳኝነትን” የሚከላከልበት ስርዓት አልዘረጋም፤” የምለው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያቴ፣ ያው ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በጓደኝነትና በመጠቃቀም ኔትወርክ የተቆላለፈ ነው፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ይሄንን የተገነዘበ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ረገድ አንደኛ የወጣው ፊልም ውስጥ የተሳተፉት ታዋቂ አርቲስቶች (ሚካኤል ሚሊዮን፣ ኤፍሬም ታደሰ - በአሁኑ ወቅት በኢቢሲ በሚተላለፈው “ዋዜማ” ድራማ ላይ የሚተውን፣ ወዘተ) ከዳኞች ጋር የሚተዋወቁ መሆናቸው ነው፡፡ ነገሩን ወደ መርህ እንቀይረውና፣ አንድን ሰው በሚያውቀው ሰው ወይም በጓደኛው ማስዳኘት በመርህ ደረጃ ትክክል አይደለም፡፡ በርግጥ ይሄን የምለው አርቲስቶችም ቢሆኑ እንደማንኛውም ሰው የመወዳደር መብታቸውን ሳልዘነጋ ነው፡፡ አርቲስቶቹ ይሄንን የኤምባሲውን ክፍተት እየተጠቀሙ ይመስላል፡፡ “ኤምባሲው ‹የጓደኛ ዳኝነትን› የሚከላከልበት ስርዓት አልዘረጋም፤” የምልበት ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ፣ በውድድሩ ላይ አንደኛ የወጣው ፊልም እንዲያልፍ የተደረገው ሦስት የኤምባሲውን ህጎች ባላከበረበት ሁኔታ መሆኑ ነው፤ አንደኛው ህግ፣ “ፊልሙ መዘጋጀት ያለበት በአማርኛ ቋንቋ ሆኖ የእንግሊዝኛ ትርጉም (subtitle) ሊኖረው ይገባል!” ይላል፡፡ አንደኛ የወጣው ፊልም ግን ከፊልሙ ርዕስ ጀምሮ አብዛኛዎቹ ምልልሶች (dialogues) የእንግሊዝኛ ትርጉም የላቸውም፡፡ ሁለተኛው ህግ፣ “ፊልሙ የምስልና የድምፅ ጥራት ሊኖረው ይገባል!” ይላል፡፡ አንደኛ የወጣው ፊልም ግን የምስል ጥራቱ በንፅፅር ደካማ ሲሆን፣ ምልልሶቹማ ጭራሽ የማይሰሙ ናቸው፡፡ 3ኛው ህግ ደግሞ፣ “ፊልሙ ወጥ ስራ (original) መሆን አለበት” ይላል፡፡ አንደኛ የወጣው ፊልም ግን ስክሪፕቱ “Nairaland” ከሚባል የናይጄሪያ ማህበራዊ ድረ ገፅ (Http://www.nairaland.com/126845/she-housewise-she-doesnt-work) የተወሰደ ነው፡፡ በርግጥ የኦሪጂናሊቲ ጉዳይ ግጥምጥሞሽም ሊሆን ይችላል፡፡
እንግዲህ፣ “እነዚህን የኤምባሲውን ህጎች ያላከበረ ፊልም እንዴት አንደኛ ሊወጣ ቻለ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “ዳኞቹን የጓደኝነት ወይም የትውውቅ መንፈስ ተጭኗቸው ነው፤” ከማለት ውጭ ሌላ መልስ ሊኖረው አይችልም፡፡ (በነገራችን ላይ አንደኛ የወጣውን ፊልም የኤምባሲው የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ማየት ይቻላል፤)
የኤምባሲው ሁለተኛው ስህተት፤ “የሙያ ጭፍለቃ” ማካሄዱ ነው፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ያዘጋጀው የፊልም ውድድር ሁለት ርዕሰ ጉዳዮችን አጣምሮ የያዘ ነው - ፊልምንና ስርዓተ ፆታን። የውድድሩ መልዕክት ስርዓተ ፆታ ሲሆን ይሄንን መልዕክት ለህዝቡ የማስተላለፊያ መንገድ ደግሞ ፊልም ነው፡፡ በመሆኑም የፊልም ውድድሩን ለመዳኘት የሁለቱም የባለሙያዎች ቡድን መኖሩ ግድ ነው፡፡ የፊልም ባለሙያዎች የፊልሙን ጥራት ሲዳኙ፣ የስርዓተ ፆታ ባለሙያዎች ደግሞ የመልዕክቱን ይዘትና ፈጠራ ላይ ዳኝነት ይሰጣሉ፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ ግን “ሴቶችን” እየዘከርኩ ነው እያለ፣ የስርዓተ ፆታውን ጉዳይ ረስቶት ነገሩን ሁሉ የፊልም ጉዳይ ብቻ አድርጎታል፡፡ የስርዓተ ፆታ ባለሙያዎች በዳኝነት ሂደቱ ላይ ባለመሳተፋቸው በውድድሩ እንዳሸነፉ የተነገረላቸው ፊልሞች፤ በአብዛኛው የሴቶቻችን ጉዳይ በአዲስ እይታና ጥልቅ በሆነ አስተሳሰብ በማስተላለፍ ረገድ በጣም ደካማ፣ እስከዛሬ ከምናውቀው በተለየ መንገድ ልዩ ፈጠራ የሌለባቸውና ድግግሞሽ የበዛባቸው ሆነው ታይተዋል፡፡
ኤምባሲው የፊልሞቹን የስርዓተ ፆታ ይዘት በአርቲስቶቹ ማስገምገሙ የበለጠ ኢ-ፍትሐዊ የሚያደርገውም የሴቶችን ጉዳይ ከዳኞቹ ንቃተ ህሊና ከፍ ባለ አዲስ እይታ (ለምሳሌ ፍልስፍናዊ እይታ) ለሚሳዩ ተወዳዳሪዎች ትክክለኛ ፍርድ መስጠት አለመቻላቸው ነው፡፡
የስርዓተ ፆታ ባለሙያዎች በዳኝነቱ ላይ ባለመሳተፋቸው ኤምባሲው ሁሉን ነገር የጨረሰው በአርቲስቶቹ ዳኝነት ብቻ ነው፡፡ በዚህ አርቲስቶቹ በፊልሞቹ ጥራት ላይ ብቻ ሳይሆን የፊልሞቹ ምልልሶች (dialogues) በትክክል በእንግሊዝኛ መተርጎማቸውን እንዲያረጋግጡለትና የስርዓተ ፆታ ይዘታቸውን ሁሉ እንዲገመግሙለት ኤምባሲው ያልተገባ ስልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡
የፊልሞቹን የስርዓተ ፆታ ይዘት በአርቲስቶች በማስዳኘትም የአሜሪካ ኤምባሲ የስርዓተ ፆታ ሙያ ላይ በደል ፈፅሟል፡፡
መፍትሄ
የአሜሪካ ኤምባሲ ፍትህን “ከጓደኛ ዳኝነት” ለመጠበቅ የፊልም ዳኞችን ከሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ኔትወርክ ውጭ የሆኑ የመስኩ ባለሙያዎችን ወይም መምህራንን መመደብ አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የሙያ ጭፍለቃንም ለማስቀረት በፊልም ውድድሩ ላይ የስርዓተ ፆታ ባለሙያዎችንም በዳኝነት ማሳተፍ አለበት፡፡

Read 1373 times