Monday, 04 April 2016 09:21

ግብጻውያን በሜሲ የጫማ ስጦታ ክፉኛ ተበሳጭተዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    አርጀንቲናዊው የአለማችን የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ፤ ከዚህ በፊት ይጠቀምበት የነበረውን ጫማውን በግብጽ ለበጎ አድራጎት የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚደረግ ጨረታ ላይ ለሽያጭ እንዲቀርብ በስጦታ መልክ ማበርከት እንደሚፈልግ መናገሩ በርካታ ግብጻውያንን ማበሳጨቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ሜሲ መልካም ነገር በማሰብ ጫማውን በስጦታ ለማበርከት እንደሚፈልግ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቢናገርም፣ ጉዳዩ በግብጻውያን ዘንድ በንቀት መተርጎሙንና ሰሞንኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ ፓርላማ አባል የሆኑ ግለሰብም አልአሲማህ በተባለው ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የሜሲን ድርጊት በማውገዝ፣ለሜሲና ለአርጀንቲና የራሳቸውን ጫማ እንደሚሰጡ መናገራቸውን ገልጧል፡፡
የግብጽ እግር ኳስ ማህበር ቃል አቀባይ አዝሚ መጋሄድ በበኩላቸው፤ የሜሲን ድርጊት በማውገዝ፣ግብጻውያን የእሱን ድጋፍና እርዳታ እንደማይፈልጉና ጫማውን ራሱ እንዲጫማው አልያም የድሆች መናኸሪያ ለሆነች የአርጀንቲና ምንዱባን እንዲሰጥ መክረውታል፡፡
የእግር ኳስ ተጫዋቹ ድርጊት በግብጽ ላይ የተደረገ ብሄራዊ ንቀት ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሊሆን የቻለው ጫማ በግብጽና በሌሎች የአረብ አገራት እንደ አንድ የንቀት ምልክት ተደርጎ የሚታይ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡

Read 1960 times