Monday, 04 April 2016 09:23

ሳምሰንግ ከፔሌ የ30 ሚ ዶላር ክስ ቀረበበት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       ከአለማችን ዘመን አይሽሬ የእግር ኳስ ከዋክብት አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ብራዚላዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ፣ ያለፈቃዴ የምርቶች ሽያጭ ማስታቂያ ሰርቶብኛል በማለት የደቡብ ኮርያውን የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ በ30 ሚሊዮን ዶላር መክሰሱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፔሌ ቺካጎ ውስጥ ለሚገኝ ፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ፣ ኩባንያው እጅግ ዘመናዊውን የቴሌቪዥን ምርቱን በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ባስተዋወቀበት ወቅት ምስሌን ያለፍቃዴ ተጠቅሟል፤ ለዚህም ቢያንስ 30 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጠኝ ይገባል ሲል መጠየቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
ሳምሰንግ ከዚህ ቀደም የፔሌን ምስል ለምርቶቹ ማስታወቂያነት ሲጠቀም እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በተጫዋቹና በኩባንያው መካከል የነበረው የማስታወቂያ ስራ ውል ከ3 አመታት በፊት መቋረጡን ጠቁሟል፡፡
ፔሌ ሳምሰንግ ምስሌን ተጠቅሞ ማስታወቂያ ሰርቶብኛል ቢልም፣ በማስታወቂያው ላይ የወጣው ፎቶ ግን የራሱ የፔሌ ሳይሆን ከፔሌ ጋር እጅግ የሚመሳሰል የፊት ገጽታ ያለው ሌላ ግለሰብ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  
ይሄም ሆኖ ግን ኩባንያው ከዚህ በፊት በፔሌ ምስል ምርቶችን ከማስተዋወቁ ጋር በተያያዘ፣ ይህንን ምስልም ተመልካቾችንና ሸማቾችን ለማሳሳትና ሽያጩን ለማሳደግ ባልተገባ ሁኔታ እንደተጠቀመበት ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ ለእሱ ሊወስንለት እንደሚችል ተነግሯል፡፡

Read 1714 times