Monday, 04 April 2016 07:48

ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ! ?

Written by  ታሁን ሄራሞ (ኬሚካል መሐንዲስ)
Rate this item
(0 votes)

      መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደሆኑ የጠቀሱ ፀሐፊ (ተመስገን ካሳዬ) ቀደም ሲል “በዕውቀቱና ድፍረቱ” በሚል ርዕስ በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ላቀረብኩት መጣጥፎቼ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ አቶ ተመስገን ጊዜአቸውን ሰውተው  የበኩላቸውን አስተያየት በመስጠታቸው ምሥጋናዬ የላቀ ነው፡፡
መጣጥፎቼን በተመለከተ በየትኛውም የዕውቀት እርከን ካለ አንባቢ የሚቀርቡትን አስተያየቶች ለማስተናገድ ዝግጁ ብሆንም ከወደ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ለሚመጡ ትችቶች ደግሞ ልዩ ትኩረት አለኝ፡፡ በተለይም ተቺው ከሥነ ጽሑፍ ዲሲፕሊን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ከሆነ ትችቱን ለማንበብ ያለኝ ጉጉት በእጅጉ ይጨምራል፡፡  ለምን ቢባል በዘርፉ ላይ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ ከሚሰራ ሰው የሚፈልቅ አስተያየት ለቀጣይ መጣጥፎቼ ብስለትንና ጥንካሬን ይጨምራል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡
ሆኖም ግን አቶ ተመስገን የሰጡትን አስተያየቶችን ደጋግሜ ባነባብኩ ቁጥር ምንጫቸው ከወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስለመሆኑ እንድጠራጠር ተገድጄአለሁ። አቶ ተመስገን ካሳዬ ዩኒቨርሲቲውን ይወክላሉ የሚል ጅምላ-ጨራሽ ፍረጃ ባይኖረኝም ቢያንስ የአስተያየቱ ከፍታ ይፋ የተደረገልንን  የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ አባልነት የሚመጥን ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ምናልባትም አስተያየት ሰጪው ከስማቸው ግርጌ “ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ” የሚል ቅጥያ ባያስቀምጡ ኖሮ ለቀረበው አስተያየት ምላሽ ለመስጠት መድከም ባልነበረብኝ ነበር። ሆኖም ግን አስተያየቱ ከዩኒቨርሲቲ ግቢና ከሥነ ጽሑፉ ዘርፍ ሰፈር ስለተወረወረ ብቻ ልክ ለሚመስላቸው አንዳንድ አንባቢያን ስል ምላሽ መስጠቱን መርጬአለሁ። በዚሁ ትይዩ ምላሼ የዩኒቨርሲቲዎቻችንን የትምህርት ጥራት ውድቀትን  በተመለከተ ብዙዎች በሚያነሱበት በአሁኑ ወቅት በመጠኑም ቢሆን ግብዓት ሊሆን የሚችል አንድምታዊ መረጃንም ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡፡       
የፀሐፊውን አስተያየት ካነበብኩ በኋላ ሰውዬው በማያውቁት ጭብጦች ላይ አስተያየት ለመስጠት ሞክረዋል ወይም ሆን ብለው ምላሽ ለመስጠትና የወጉን ለማለት ያህል ብቻ በጋዜጣው አምድ ላይ ብቅ ብለዋል ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡ በተለይም በማያውቋቸው ጭብጦች ላይ እንደጻፉ ፍንጭ የሰጠኝ የራሳቸው መግለጫ ነው፡፡ አቶ ተመስገን በመጣጥፎቼ ውስጥ ያነሳኋቸውን ሐሳቦች በተመለከተ ያላቸው መረዳት ሦስት ዓይነት (የተስማሙባቸው፤ያልተስማሙባቸውና የማያውቋቸው) እንደሆነ ነግረውናል፡፡ በእኔ አተያይ የዛሬ ሳምንት በአስተያየት መልክ ያሰፈሯቸው ሐሳቦች ከላይ ካስቀመጡት ውስጥ ለሦስተኛው ዓይነት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ምክንያቶቼ፦
ጽሑፎቼ ውስጥ ምላሹ እያለ እንደገና ማንሳታቸው
አቶ ተመስገን ጽሑፎቼን በቅጡ አንብበውት ቢሆን ኖሮ ለሚያነሱአቸው ጥያቄዎች ምላሹን እዚያው መጣጥፌ ውስጥ ያገኙት ነበር፡፡ የተሰጠው ምላሽ በቂ ካልሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ መጠየቅም መብታቸው ነበር፡፡ ምንም ምላሽ እንዳልተሰጠ አድርጎ  ጥያቄዎችን ለመደርደር መትጋት ግን ምናልባት ካላይ ወዳስቀመጥነው ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ አቅም ይሰጠናል፡፡
ለምሳሌ አቶ ተመስገን የግምገማው ዓላማና ትኩረት በመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ ቢሆን ኖሮ… የሚል ዓይነት ክርክር አንስተዋል፡፡ ለዚህ ጥያቄአችው ምላሽ ሊሆን የሚችል ገለጻ “በዕውቀቱና ድፍረቱ” ክፍል 1 ላይ በእንደዚህ ዓይነት መልክ  ማስፈሬን አስታውሳለሁ፡፡….”…ከጭብጦቹ ብዛት አንጻር ደራሲው ለተደራሲያኑ ሐሳቡን ለማስቃኘት የመረጠው ቅርጽ ቀጥተኛ ሳይሆን ባለ ብዙ መስኮት (Multiple frames) ነው፡፡ በዚህ ቅርጽ አማካይነትም በመጽሐፉ ጥቂት ገጾች ውስጥ አያሌ ክፍልፋይ ተረኮች (Fragmented stories) ሰፍረዋል፡፡ በክፍልፋይ ተረኮች ላይ የተጠነሰሰ ድርሰትን መገምገም ደግሞ ግምገማውንም ክፍልፋይ ማድረጉ የማይቀር ነው፡፡ ሐያሲው በደራሲው ከቀረቡለት ተረኮች ውስጥ አንዱን ብቻ መዝዞ ሊገመግም ይችላልና፡፡ ይህ ደግሞ በአንባቢያን ዘንድ ለገምጋሚው አተያይ  አሉታዊ ትርጉምን አላብሶ የሂሱን ደረጃ ወደ  ፀጉር ስንጠቃነት አሊያም ስህተት አነፍናፊነት ሊያወርደው ይችላል፡፡”
ውድ አቶ ተመስገን፦ አጠቃላይ ግምገማ የሚሰጠው የጭብጦቹ ይዘት ወጥነት ኖሮት በቀጥተኛ የትረካ/የገለፃ ቦይ ውስጥ ለሚፈሱ ሥነ ፅሑፋዊ ቅርጾች (Linear narratives) መሰለኝ! የበዕውቀቱ “ከአሜን ባሻገር” መጽሐፍ በቅርፅ አንፃር ወደ ድህረ ዘመናዊው የሚያደላ ነው፡፡ ድህረ ዘመናዊነት ደግሞ “አጠቃላይ” የሚባል ቋንቋ አይመቸውም፡፡ ስለዚህም ከተከፈቱልን አያሌ የምልከታ መስኮቶች ውስጥ የተመቸንን መርጠን መምዘዝ መብታችን ነው! ለምሳሌ እኔ የበዕውቀቱን ሃይማኖታዊ ምልከታ ለመቃኘት ሞክሬአለሁ፡፡ በታሪክና ፖለቲካ ቀመስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ግምገማውን ለማካሄድ ዝግጅቱ ስለሌለኝ የቤት ሥራውን ለዘርፉ ባለሙያዎች ክፍት ማድረግ መርጫለሁ፡፡ አቶ ተመስገን ደግሞ በተቃራኒው ስለ ፖለቲካውና ስለ ታሪኩ ለምን አልጻፍክም? የሚል ቀጭን ትዕዛዝ የሚያስተላልፉ ይመስላሉ፡፡ ይህ ጥያቄ ከድህረ ዘመናዊ የሥነ ፅሑፍ ውጤቶች ጋር ትውውቅ ከሌላቸው  አንባቢያን የሚመነጭ  ነው፡፡   
ሌላው የአቶ ተመስገን  መከራከሪያ  ነጥብ ግምገማው የተካሄደው በእግረ መንገድና ቅንጥብጣቢ ጉዳዮች ላይ ነው የሚል ነው፡፡ ለዚህኛው ደግሞ በክፍል 2 ጽሑፌ እንደዚህ ብዬ ነበር፡፡ “….በገጽ 40 እና 59 የተቀመጡትን የደራሲውን ዐረፍተ ነገሮች በወፍ በረር ስናያቸው የእግረ መንገድ ንግግሮች ስለሚመስሉን በጉዳዩ ላይ ጊዜ ወስዶ ማጤን አስፈላጊነቱ አይታየን ይሆናል፡፡ ግን እያንዳንዱ የእግረ መንገድ ንግግር ከኋላችን ትተን የመጣነው የህይወት ናሙና ነፀብራቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው በፍካሬ ስነ ልቦና ምሁራንና በፖሊሶች ዘንድ የእግረ መንገድ ንግግር ተብሎ የሚጣል የመረጃ ቅንጥብጣቢ የሌለው!”   በነገራችን ላይ የሥነ-ተረክ (Narratology) ጠበብት አንድ ተረክ ከሁለት ዓይነት ሁነቶች (Events) እንደሚዋቀር ይነግሩናል፡፡ የመጀመሪያው ትረካውን ወደ ፊት የሚያስፈነጥር ዋናው ሁነት ሲሆን ሁለተኛው አጋዥ ሁነት ነው:: አንዳንዶች ለዋናው ሁነት “constituent” አሊያም “nucleus” የሚል የእንግሊዘኛ ስያሜ ሲሰጡ ለአጋዡ ሁነት ደግሞ “Supplementary” ወይም “catalyzer” የሚለውን ይመርጣሉ፡፡ ብዙዎቻችን እግረ መንገድ፤ ቅንጥቢጣቢ ወዘተ እያልን ያለነው አጋዡን ሁነት ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ የአጋዡ ሁነት ሚና ከዋናው ሁነት አንጻር ሲታይ ወሳኝ የሆነ ሚና ላይኖረው ይችላል። ከተረኩ ውስጥ ተቆርጦ ቢጣል እንኳን የተረኩ (story) ማዕከላዊ ሀሳብ አይናጋም፡፡ ሆኖም ግን በአጋዥ ሁነት ተቆርጦ መጣል ትረካዊ ሐቲቱ (Narrative discourse) በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ሮላንድ ባርቴዝ ይህን በተመለከተ እንደዚህ ይላል፡- “A nucleus (constituent) can not be deleted without altering the story ,but neither can a catalyzer (supplementary event) without altering the discourse”
ይህን በተመለከተ በክፍል 2 መጣጥፌ ወደ ዝርዝር ጉደይ ሳልገባ በምሳሌ ብቻ አስቀምጬ ነበር፡፡ በትረካው ሐቲት ጎዳና ተኣማኒነት የጎዳላቸው ዋናም ሆነ አጋዥ ሁነቶች መከሰት የንባቡን ሂደት የቱን ያህል ሊያደናቅፉ እንደሚችሉ በመኪና መንገድ ላይ ከተደነቀረው እንቅፋት ጋር አመሳስዬ ለማብራራትም ሞክሬ ነበር፡፡ አቶ ተመስገን ደግሞ በአስተያየታቸው ውስጥ መንገድህ ከተዘጋ ለምን ሌላ አማራጭ መንገድ አትፈልግም? የሚል ምክር ቢጤ ነገር ጣል አድርገዋል፡፡ ይህ ማለት የአጋዥ ሁነቶች አመክንዮኣዊ መሠረት ጥያቄ ላይ ቢወድቅ እንኳን ነገሩን ችላ ብለህ በሌላ አማራጭ መንገድ ሸውደህ እለፍ እንደማለት ነው፡፡ ውድ አቶ ተመስገን፦  አንባቢ የሐቲቱን ጎዳና የመቀየር ሥልጣኑም ዕድሉም የለውም፡፡ ደራሲው እኮ የሕይወት ልምዱን ሊያካፍለን የተረኩን የሐቲት መዋቅር መርጦና  ለሕትመት አብቅቶ  ለአንባቢው አቅርቧል፡፡ በንባቡ ሂደት አንባቢያን በቀረበው ሐቲት ላይ የሚጎረብጣቸው ነገር ሲያገጥማቸው ጥያቄ ማንሳትና ሂሳዊ ሐሳቦችን መሰንዘር መብታቸው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ  ተለዋጭ  መንገድ ብሎ ነገር የለም! ሆኖም ግን በትርጓሜ አሰጣጥ (Interpretation) ወቅት አንባቢው በተለይም ድህረ ዘመናዊ መጣጥፎችን በመሰለው መንገድ የመተርጎም ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አሁን ባለንበት ዘመን የትኛውም መረጃ ደቂቅ ነው ተብሎ አይጣልም፡፡ ለዚህም የ”Chaos theory” በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ንድፈ ሐሳብ በአዳም ረታ የልብ ወለድ ሥራዎች ውስጥ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በእርሱ ልብ ወለዶች ውስጥ ጥቃቅንና የእግረ መንገድ የሚመስሉ ትረካዎች (እርሱ ወሽመጥ የሚላቸው) እጅግ ብዙ ናቸው። አንዳንዶቹም በግርጌ ማስታወሻ ሰፊ ግዛት ይዘው ሲንፋላሰሱ ማየት የተለመደ ነው፡፡
 ስለዚህም የአንድ ሐሳብ ጥልቀት በቃላት ብዛት ወይም ማነስ ላይ የተመረኮዘ አለመሆኑን ማስመር ከዘመኑ ጋር አብሮ እንደመሄድ ይቆጠራል፡፡ ይህን በዕውቀቱም የሚያጣው አይመስለኝም፡፡ ቀደም ሲል ሶስትና አራት ገፅ ድረስ የሚሄዱ የግጥም ሥራዎችን ወደ ሁለትና ሶስት ስንኝ በማሳጣሩ በምሳሌነት ከሚጠቀሱ ገጣሚያን አንዱ ነው፡፡ ሆኖም ግን የእርሱ ባለሁለት ስንኝ ግጥሞች ፍልስፍናዊ ዳራቸው ቢዘረዘር አንድ ጥራዝ መጽሐፍ ሊወጣላቸው ይችላል፡፡ ይህ የገጣሚነት ሚናው በበጎ ጎኑ በመጣጥፎቹ ውስጥ መንፀባረቃቸውን መካድ አይቻልም፡፡ በሌላው ዓለም ለግጥም ብቻ ሳይሆን  ለልብ ወለዶችም ዕምቅ ይዘትን አላብሶ በጣም በተወሰኑ ቃላት ማስቀመጥ የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም በአስረጅነት ባለ 34 ቃላቱንና Revenge of the Lawn መጽሐፍ ውስጥ በአራት መስመር ብቻ ያለቀውን የሪቻርድ ብራውትጋንን  “The Scarlatti Tilt”ን (አንዳንዶች በግጥም-መሰል ልብወለድነት የፈረጁትን) እንደሚከተለው ላስቀምጥ፦
“‘It’s very hard to live in a studio apartment in San Jose with a man who’s learning to play the violin.’ That is what she told the police when she handed them the empty revolver.”  ይህ እንግዲህ መጽሐፉ ውስጥ ከተካተቱት አጫጭር ልብወለዶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ልብ ወለዱ “ሚጢጢ” ቢመስልም ልክ እንደ ጉንዳን ከራሱ ክብደት በላይ የሆኑ ትንታኔዎችን ያዘለ በመሆኑ ብዙዎች በሰፊው ጽፈውበታል፡፡
 አቶ ተመስገን በተደጋጋሚ ስለ ሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ማንሳቴን እንደ ቀላል ነገር ሊቆጥሩት መከጀላቸው ሌላው ያስደመመኝ ነገር ነው፡፡ በመሠረቱ እኔ ስለ ሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ያነሳሁት ከእኔ ቀድሞ የመፅሐፉ ደራሲ እንደ ከርሞው በየፌርሜታው በማንሳቱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ደራሲው ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የቱን ያህል ትኩረት እንደሰጠ ያመለክታል፡፡ በዕውቀቱ በጉዞ፤በታሪክና በፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቹ ውስጥ ስለ ሃይማኖት አንስቷል፡፡ ዛሬ ኢ-አማኒያንም ሆኑ አማኒያን ፈላስፎች ስለ ዘርፉ ጥልቅ ምርምር ለማድረግ በ”Philosophy of Religion” ዲሲፕሊን ሥር ለማጥናት መጠለላቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ዲሲፕሊን ደግሞ በአሁኑ ወቅት በጣም እያበበ ያለ ዘርፍ ስለመሆኑ በክፍል 1 መጣጥፌ ውስጥ ጠቅሼአለሁ። እኛ ዘንድ ግን ስለ ሃይማኖት አንስቶ መነጋጋርን ያለ አቅማችን እንደ ዋዛ አይተነው ለማለፍ መሞከሩ የኮሚኒዝም ዘመን ትቶት ያለፈው ጠባሳ ያመጣው ጣጣ መስሎ ይታየኛል፡፡
የትርጉም ጉዳይ
  አቶ ተመስገን በትርጉም አሰጣጥ ላይ የሰጡት አስተያየት ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም ባሻገር ጥሩ አንባቢ እንዳልሆኑም የሚጠቁም ነው፡፡ በክፍል 2 ጽሑፌ ውስጥ የፍሮይድን አጠቃላይ ሐሳብ በራሴ አባባል ስገልጸው እንደዚህ ብዬ ነበር..ይህም ዕውን ሆኖ ከተገኘ የሰው ልጅ በዕውቀት ከመመራት ይልቅ በደመ ነፍስ መመራትን ስለመረጠ ምልከታዬን ፉርሽ አድርጉት ብሎናል፡፡… ይህ ቃል በቃል የተተረጎመ አባባል ባለመሆኑ በመጣጥፌ ውስጥ በትምህርተ ጥቀስ ውስጥ አላስቀመጥኩትም። አቶ ተመስገን ይህን ለመተቸት ሲያመቻቹ በራሳቸው ሥልጣን ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ እንዳስቀመጥኩ አድርገው ትርጉሙን ቃል በቃል እንግሊዘኛው ውስጥ መፈለጉን ተያያዙት፡፡  የፈለጉትን ሲያጡ ጊዜ ጽሑፌ ተኣማኒነት እንደሚጎድለው ነግረውን አረፉ፡፡ ይህን በተመለከተ ብዙ ማለት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያልተቀመጠን ሐሳብ ይዞ ትርጉሙን ቃል በቃል በእንግሊዘኛው ውስጥ መፈለግ ልክ አለመሆኑን ለማስረዳት የ8ኛውን ክፍል “Direct” እና “Indirect speech” ህግጋትን መጥቀሱ በቂ ነው፡፡
3. ኪኒኑን በፈቃዱ ቢያቆመውስ?
አቶ ተመስገን በዕውቀቱ በፈቃዱ ኢ-አማኒ ከሆነ ፍሮይድ ደስታውን አይችለውም ብለውናል፡፡ በመሠረቱ ፍሮይድ ሰው እምነቱን በሁለት ምክንያት ሊተወው እንደሚችል ገልጾአል፡፡ የመጀመሪያው በክልከላ ሲሆን ሁለተኛው በክርክር ተሸናፊ ሲሆን ነው፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው የፍሮይድን መጽሐፍ አንብቦ እምነቱን ቢተው ምክንያቱ ክርክር ነው የሚሆነው! ማለትም ክርክሩ በአንባቢው ዘንድ ሳይንሳዊ ሚዛኑን ደፍቶአል ማለት ነው፡፡ በሳይንስ የተረጋገጠ ነገር ደግሞ የማንንም ፈቃድ አይጠይቅም፡፡ አቶ ተመስገን ደግሞ ፈጽሞ ሊገባን በማይችል መልኩ በዕውቀቱ በፈቃዱ እምነቱን ቢተው  ፍሮይድ ደስታውን አይችለውም ይሉናል፡፡ ምናልባት ፍሮይድ ደስ የሚለው ሰዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በተረጋገጠ ንድፈ ሐሳብ እምነታቸውን ሲቀይሩ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ጋ ፈቃድ ብሎ ነገር ቦታ የለውም፡፡ “The future of an illusion” ውስጥ የሰፈሩ መከራከሪያ ሐሳቦች ደግሞ ሳይንሳዊ መሰረት እንደሌላቸው ፍሮይድ እራሱ ይፋ ያደረገው እውነት ነው፡፡  
የበዕውቀቱ አድናቂዎችን በተመለከተ
ከበዕውቀቱ ደጋፊዎች የተሰነዘሩትን አስተያየቶች በተመለከተ ማንሳት የፈለኩትን  ሐሳብ አቶ ተመስገን አልተረዱትም ወይም ሆን ብለው አቅጣጫውን ለማሳት ጥረት አድርገዋል፡፡ የኔ ትኩረት ሙሉ በሙሉ በደራሲ ዙሪያ የተሰባሰቡት አድናቂዎችን የአስተሳሰብ ደረጃ መፈተሽ ስለ ደራሲው የጥበብ ማዕድ የሚሰጠን ጥቆማ ሊኖር እንደሚችል ማሳየት ነበር፡፡ አቶ ተመስገን ግን እኔ ያነሳሁትን ይህን የመነሻ ሐሳብ ከቁብ ሳይቆጥሩ  እኔ ከደጋፊዎቹ ጋር ብሽሽቅ እንደገጠምኩ፤ የእነርሱ ስድብ የሂሱን ተጨባጭነት እንዲያረጋግጥልኝ መፈለጌን፤ ሂሱ የተሰጠው በስድብ ለሚያምኑ ደጋፊዎች እንደሆነ ወዘተ በፅሑፋቸው አስፍረዋል፡፡  ሰውዬው ይህን ሁሉ ማስረጃ የሌለውን ሐተታ ከየት አምጥተው እንደጻፉት ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባት ሐተታውን የዘጉት በ”ይመስላል” መሆኑ የራሳቸው ግምታዊ ምልከታ እንደሆነ ጠቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር በጽሑፌ ውስጥ ከደጋፊዎች ጋር ብሽሽቅ የገጠምኩበትን፤ ወይም ተሳዳቢዎቹ ሂሱን እንዲያረጋግጡልኝ ስሞታ ያቀረብኩበትን አንዷን ሐረግ እንኳን ማሳየት ቢችሉ መልካም ነበር፡፡ ግን ግን  በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ላልተቀመጠ ሐሳብ የቃል በቃል ትርጉም ከሚፈልግ ተቺ፤  ከድህረ ዘመናዊ መጣጥፎች ጥላ ሥር አጠቃላይ ጭብጥን ከሚፈልግ አስተያየት ሰጪ፤ የደራሲውን የሐቲት ጎዳና በሌላ ተለዋጭ ጎዳና ለመቀየር ሐሳብ ከሚሰነዝር ሞጋችና፤ ሳይንሳዊ ምልከታዎች በሰው ልጅ ፈቃድ ላይ የተመሰረቱ እንደሆነ ከሚያምን ምሁር ይልቅ ጎራቸውን የለዩ  አክራሪ የበዕውቄ ደጋፊዎች ሳይሻሉ ይቀራሉ?   

Read 1481 times