Monday, 04 April 2016 07:41

ሰው መጽሐፍ ነው

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

(23 ምዕራፎች ያሉት)
                       
        ረጅም ጉዞ ላይ ነኝ፡፡ በጎዞዬም የማነበው የማት ሪድለይን (Matt Ridley) መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ የታተመው የዛሬ 17 ዓመት በ1999 ዓ.ም (እኤአ) ነበር። መጽሐፉ 23 ምዕራፍ አሉት፡፡ ደራሲው 23 ምዕራፍ እንዲኖረው ያደረገው በምክንያት ነው፡፡ የጻፈው መጽሐፍ የሰውን ‹‹ጅን›› ይተነትናል፡፡ ሰው ደግሞ በ23 ጥንድ ጅኖች ቅንብር የተገነባ ፍጥረት ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ 23 ምዕራፍ እንዲኖሩት አድርጓል፡፡ በእያንዳንዱ ምዕራፍም አንዳንዷን ክሮሞዞም ይዘክራል፡፡
ክሮሞዞሞች በመጠን ይለያያሉ፡፡ ትልቁ ‹‹ክሮሞዞም አንድ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ትንሹ ‹‹ክሮሞዞም ሃያ ሁለት›› ይባላል፡፡ የሰው ልጅ ከ30 እስከ 80 ሺህ ጅኖች እንዳሉት ይገመታል፡፡ አብዛኛው የሰው ልጅ ጅን ተጠንቶ፤ ተግባሩ ለይቶ ታውቋል፡፡ ደራሲው ሪድለይ፤ ‹‹ይህን መጽሐፍ መጻፍ በጀመርኩ ጊዜ፤ የሰው ልጅ ‹ጀኖሜ› (Genome፤ የተሟላ የ23 ጥንድ ክሮሞዞሞች ቅንብር ነው) ገና ብዙ አልታወቀም፡፡ አሁን ተለይተው የሚታወቁት ስምንት ሺህ የሰው ልጆች ጅኖች ብቻ ናቸው›› ብሎ ነበር፡፡ ሆኖም፤ እርሱ መጽሐፉን መጻፍ በጀመረ በአንድ ዓመት ገደማ አብዛኛውን ጅን የመለየቱ ከባድ ሥራ ተጠናቅቆ ነበር፡፡
በዓለም የተለያዩ ሐገራት የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት የሰውን ልጅ ‹‹ጀኖሜ›› ጠንቅቀው አነበቡት፡፡ ‹‹ጀኖሜ›› ሃያ ሦስት ጥንድ ሆኖ የሚገኝ የተሟላ የሰው ‹‹ጅን›› ነው። የሳይንስ ሊቃውንት፤ በጀኖሜ ውስጥ ያለውን ይዘት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለይተው አውቀው ጻፉት፡፡ አሁን የሰውን አካል ለመገንባት እና ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለውን ሙሉ መመሪያ ለማንበብ ችለዋል፡፡  
በ1998 ዓ.ም (እኤአ) አንዳንድ ሊቃውንት፤ ‹‹በሰባት ዓመታት ጊዜ ሁሉንም የሰው ልጅ ‹‹ጀኖሜ›› ለይተን ማወቅ እንችላለን›› የሚል ትንበያ ነበራቸው፡፡ በወቅቱ 10 በመቶ ያህሉ እንኳን አይታወቅም ነበር፡፡ አንድ ክሬግ ቬንተር (Craig Venter) የተባለ ደፋር ተመራማሪ ‹‹200 ሚሊየን ፓውንድ ካገኘሁ፤ በ2001 ዓ.ም (እኤአ) ሁሉንም ነገር ጠንቅቄ እችላለሁ›› ሲል ዝቶ ነበር፡፡ የቬንተር ዛቻ ከንቱ አልነበረም፡፡ በ1991 ዓ.ም (እኤአ) የሰውን ‹‹ጅን›› በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል አዲስ ዘዴ ለመፍጠር ቻለ፡፡ ቬንተር የሰራው ነገር፤ ብዙዎች ሊሰራ አይችልም ብለው ያስቡት የነበረውን ነገር ነው፡፡ ግን ከእርሱ በፊት ሌሎች ሥራውን አጠናቀቁት፡፡
ጁን 26፣ 2000 ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንና የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር (በየራሳቸው ሐገር)፤ የሰዎች ጀኖሜ የመጀመሪያ ረቂቅ ተጠናቅቆ መቅረቡን ይፋ አደረጉ፡፡ በተመሳሳይ ሰዐት ዜናውን አወጁ፡፡ ይህ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ድንቅ የሚባል ክንውን  ነበር፡፡ በህይወት ኢቮልዩሽናዊ ጉዞ ውስጥ አንድ ፍጥረት ከምን ከምን ተቀናብሮ እንደ ተሰራ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማወቅ ቻለ፡፡ የሰው ልጆች ‹‹ጀኖሜ››፤ የሰው አካል እንዴት እንደተገነባና ሥራውን ሊያከናውን እንደሚችል የሚያስረዳ መመሪያ የያዘ ነው፡፡
የሰው ጅን የማጥናቱ ሥራ ዋና ግብ፤ እንደ ካንሰርና ልብ ድካም ያሉ፤ እንዲሁም ለሌሎች በዘር ለሚወረሱ በሽታዎች መድኀኒት ለመፈለግ ነው፡፡ ግን ስለ ‹‹ጅን›› ማወቃችን ያለው ፋይዳ በሽታን በማዳን የሚወሰን አይደለም፡፡ በጅን ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ከሰው ወደ ሰው ሲተላለፍ የነበረን ምስጢራዊ መልዕክት ለማግኘት ይቻላል፡፡
እንደ ሳይንቲስቶቹ ሐሳብ፤ የፍጥረት መነሻ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሆኖም በፕላኔት መሬት እንደ ሰው ልጅ ያለ ውስብስብ ሥነ ህይወታዊ ማሽን አይገኝም፡፡ በዘይቤ ማውራት ከፈለግን ማሽን ከማለት መጽሀፍ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ‹‹መጀመሪያ ቃል ነበር›› የሚለው አነጋገር በሳይንሳዊ መነጽር ሲታይ ትክክል ነው፡፡ የሰው ልጅ ከ100 ትሪሊየን ሴሎች የተገነባ ነው፡፡ አንዷ ሴል ወደ ጎን ስትለካ የአንድ ሚሊሜትር፤ አንድ አስረኛ የሚሆን ስፋት ያላት ናት፡፡ በእያንዳንዷ ሴል ውስጥ አንድ ጥቁር ነቁጥ አለ፡፡ ይህ ነቁጥ ኒውክለስ ይባላል፡፡ በእያንዳንዷ ሴል ሁለት የተሟሉ ጀኖሜዎች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ስፐርምና በእንቁላል ውስጥ አንድ ኮፒ ብቻ ነው፡፡
‹‹ጀኖሜ››ን እንደ መጽሐፍ አስቡት፡፡
23 ምዕራፎች አሉት - ክሮሞዞም ይባላሉ፡፡ በእንያንዳንዱ ምዕራፍ በርካታ ሺህ ታሪኮች አሉ- ጅን ይባላሉ፡፡ እያንዳንዱ ታሪክ በአንቀጽ የተከፋፈለ ነው። እነኚህ አንቀጾች ኤክሶን (Exons) ይባላሉ፡፡ አንቀጾቹ፤ ኢንትሮን (Introns) በሚባሉ ማስታወቂያዎች ይቋረጣሉ፡፡ እያንዳንዱ አንቀጽ በቃላት የተዋቀረ ነው- ኮንዶን (Condons) ይባላል፡፡ እያንዳንዱ ቃል በሆሄያት የተዋቀረ ነው- ቤዝ (Base) ይባላል፡፡
በዚህ መጽሐፍ አንድ ቢሊየን ቃላት አሉ፡፡ ይህም 800 መጽሐፍ ቅዱስ ይወጣዋል፡፡ በአንድ ሰከንድ አንድ ቃል ብናነብ፤ መጽሐፉን አንብቦ ለመጨረስ አንድ መቶ ዓመት ይፈጃል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር በዓይን ሊታይ በማይችልና በስፒል ጭንቅላት ላይ ለመቀመጥ በሚችል አንድ ኒውክለስ ውስጥ የሚገኝ መረጃ ነው፡፡
አንዳንድ የአማርኛ ቃላት አራት ወይም አምስት ሆሄያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ሁሉም ጀኖሜዎች ባለሦስት ሆሄያት ናቸው፡፡ ቃላቱም የሚመሰረቱት ሦስት ፊደሎችን በመጠቀም ነው፡፡ ፊደላቱ A፣ C፣ G፣ T ናቸው። ‹‹A›› Adeninenን የሚወክል ነው፡፡ ‹‹C›› Cytosineን የሚወክል ነው፡፡ ‹‹G›› Guanineን የሚወክል ነው፡፡ ‹‹T›› Thymineን የሚወክል ነው፡፡ ታዲያ እነኚህ ፊደላት የሚጻፉት በጠፍጣፋ ወረቀት ሳይሆን በረጅም የስኳር ሰንሰለትና በፎስፌት የ‹‹DNA›› ሞሎኪዩል ላይ ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ክሮሞዞም ረጅም የ‹‹DNA›› ሞሎኪዩል ነው፡፡ ታዲያ ‹‹ጀኖሜ›› ሰልጠን ያለ መጽሐፍ ነው፡፡  ራሱን ማንበብ እና ፎቶኮፒ ማድረግ የሚችል መጽሀፍ ነው፡፡ ‹‹ጀኖሜ መጽሐፍ ነው›› ሲባል ዘይቤ አይደለም፡፡ በእውነትም መጽሀፍ ነው፡፡  
ሰው ባለ 23 ምዕራፍ መጽሐፍ ነው፡፡ በ3 ሆሄያት በሚቀመሩ ቃላት የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፡፡ ግን 23 ምዕራፍ እንዳለው የታወቀው በኋላ ነው፡፡ መጀመሪያ ባለ 24 ምዕራፍ መጽሐፍ መሆኑ ይታመን ነበር፡፡ ሁሉም ሳይንቲስቶች፤ ‹‹ሰው 24 ጥንድ ክሮሞዞም አለው›› ይሉ ነበር፡፡ ከ1955 ዓ.ም በፊት በነበሩት ሦስት አስርታት፤  ሁሉም የሳይንስ ሊቃውንት የሰው ልጅ ባለ 24 ጥንድ ክሮሞዞም ፍጡር መሆኑን ያስረዱ ነበር፡፡
በ1921 ዓ.ም፤ ቲዮፊለስ ፔይነተር (Theophilus Painter) የተባለ ተመራማሪ ከሦስት ‹ያልታደሉ› ሰዎች (ሁለት ጥቁር እና አንድ ነጭ) ቆለጥ (Testicles) ቀንጥቦ ወስዶ ጥናት አድርጎ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች አዕምሯቸው የታወከና ‹‹ራሳቸውን የመጉዳት ዝንባሌ›› (Self-abuse) ስለነበራቸው እንዲመክኑ ተደርጎ (Castrated) ነበር። ስለዚህ ከቆለጣቸው ናሙና ቀንጥቦ ወስዶ ጥናት ለማድረግ ተፈቀደለት፡፡ ቀንጥቦ የወሰደውን ሥጋ በኬሚካል ውስጥ አስገብቶ ካደረቀ በኋላ በአጉሊ መነጽር ሲመለከት፤ 24 ክሮሞዞም መኖሩን እንዳረጋገጠ ተናገረ። ‹‹እኔ  በጣም እርግጠኛ ነኝ ቁጥሩ ከ24 አያንስም - አይበልጥም›› ብሎ በመተማመን ተናገረ፡፡ ሌሎች አጥኚዎችም ከእርሱ የተለየ ነገር አልተመለከቱም፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ጥያቄ የማይነሳበት ሐቅ ሆኖ ታይቶ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የጀመሩትን ጥናት አቋረጡ፡፡ ለሠላሳ ዓመታት ያህል ይህን ሳይንሳዊ ሐቅ የሞገተ ሰው አልተገኘም፡፡ ጥንድ ክሮሞዞሞችን መለያየት የሚያስችል አዲስ የምርምር ዘዴ ያገኙ ሌሎች ሳይንቲስቶች፤ ነገሩን አይተው-አጥንተው 24 መሆኑን ተናገሩ፡፡ ነገሩ በዚህ ተደመደመ፡፡
ታሪክ የተቀየረው በ1955 ዓ.ም ነበር፡፡ ታሪክ ቀያሪውም ጆይ-ሂን ቲጂዮ (Joe-Hin Tjio) የተባለ ኢንዶኔዢያዊ ተመራማሪ ነበር፡፡  ጆይ-ሂን ቲጂዮ በጊዜው በስፔን ነዋሪ ነበር፡፡ እናም አልበርት ሌቫን (Albert Levan) ከተባለ ተመራማሪ ጋር ምርምር ለማድረግ ወደ ስዊድን አቀና፡፡ ሁለቱ ተመራማሪዎች ቀድሞ ከነበረው የምርምር ዘዴ የተለየ አሰራር ተጠቅመው ባደረጉት ጥናት የተለየ ነገር ተፈጠረ፡፡ ‹‹የሰው ልጅ 23 እንጂ 24 ጥንድ ክሮሞዞም የለውም›› አሉ፡፡ 24 ጥንድ ክሮሞዞም ያላቸው፤ ችምፓንዚና ጎሪላ የተባሉ የዝንጀሮ ቤተሰቦች ናቸው፡፡
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ እኛ (ሰዎች) ከዝንጀሮ ወገን የምንመደብ ነን፡፡ እናም ከዝንጀሮ ቤተሰብ 23 ጥንድ ክሮሞዞም ያለው ሰው ብቻ ነው፡፡ እንደ ሳይንቲስቶቹ ሐሳብ፤ የእኛ ክሮሞዞም ከወገኖቻችን ተለይቶ 23 ሊሆን የቻለው፤ አንዷ ቅንጣት በኢቮሉሽን ጉዞ በመንገድ ጠፍታ ሳይሆን፤ በዝንጀሮ ወገን ከሚገኙ 24 ክሮሞዞሞች ሁለቱ ተጣምረው አንድ ቅንጣት ስለሰሩ ነው፡፡ በመጠኑ የሁለተኛ ደረጃን የያዘው የሰው ክሮሞዞም፤ ‹‹ክሮሞዞም 2›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ክሮሞዞም፤ መካከለኛ መጠን ከነበራቸው ሁለት የዝንጀሮ ክሮሞዞሞች የተቀናበረ ነው።
ይህ የሳይንስ ትንታኔ ከሐይማኖት ጋር የሚጣላ ነው፡፡ ሆኖም ከ12 ዓመታ በፊት (ኦክቶበር 22፣ 1996) በ‹‹Pontifical Academy of Science›› ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሮማው ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ አንድ አስታራቂ የመሰለ ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ እንዲህ አሉ፤ ‹‹የሰው ወገን በሚባሉት ዝንጀሮዎችና በሰው ልጅ መካከል የነበረው የዝምድና ገመድ አንድ ቦታ ተቋርጧል (There was ontological discontinuity)፡፡ ይህ ዝምድና የተቋረጠውም እግዚአብሔር በእንስሳው ውስጥ የሰው ነፍስ ባስገባበት ጊዜ ነው›› በማለት ቤተክርስቲያናቸው ከኢቮልዩሽን ጋር እንድትታረቅ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡  
እንደነገርኳችሁ አሁን ረጅም ጉዞ ላይ ነኝ፡፡ እዛው አዲስ አበባ ስመለስ፤ ስለፍጥረታችን ተጨማሪ ነገር አጫውታችኋለሁ፡፡         

Read 2296 times