Saturday, 26 March 2016 11:14

ትዝታ ነው የሚርበን?

Written by  አስፋ ጫቦ Corpus Christi,Texas USA
Rate this item
(6 votes)

ትዝታ ነው የሚርበን
 ላናገኘው ላያጠግበን...
ብሏል ወዳጄ የነበረው ጸጋዬ ገብረ መድኅን፡፡
ለመሆኑት ትዝታ ምንድነው? ዘፈን ነው? እንጉርጉሮ? ኩርኮራ? ማላዘን? ሐሳብ ልጓም የለውምና እንዳሻው ወደ ላይ ወደ ታች፤ ወደ ውስጥ ወደ ውጭ፤ ወደ ፊት ወደ ኋላ፣ ወደ የሚታይ ወደ ሊታይ ወደ ማይቻል ይሔዳል፤ ይጓዛል፤ ይተናል፤ ይበናል፤ ይመላለሳል፣ ይመለሳልም። “ማን አለኝ ከልካይ!” መሆኑ ነው።
ከዚህ ውስጥ
አንድ ጊዜ፤ አንድ ወዳጄ በፊት ከኖርኩበት፤ ከሎስ አንጀለስ (Los Angeles, California)፣ ደውሎልኝ የልጆቹን ጤንነት ጠያይቄ “አያት አደረጉህ ወይ!?” አልኩት። “እረ የለም!” አለ። ”ምነው?” ብለው “ሚስት/ባል የሚሆን አጥተው!” አለኝ። “ምነው ከዚያ ሞልቶ ከተረፈው ኢትዮጵያዊ!?” ስለው ችግሩን ነገረኝ። ”በልጅነታቸው ለማቀራረብም ሲባል ይህች/ይሔ የአጎትህ/የአክስትህ ልጅ (your nephew, your niece) ብለን አስተዋወቅን:: አሁን ተጋቡ ሲባሉ “እንዴት ተደርጎ የአጎቴን የአክስቴን ልጅ (my nephew, my niece) አገባለሁ; ሆነና ችግር መጣ አለኝ።
“በልጅነት የተነገረ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኖ ያድጋልና ተለዋጭ ማስረጃ ቢኖርም /ቢታይም ተቀባይነቱ ውሱን ነው” አልኩት። የሰፈር የስነልቡና ሊቅ (psychiatirist) መሆኔ ነው። አሁን በምን/ለምን አስታወስኩት?
*   *   *
ይሔ ደግሞ በ1983 ክረምት የሆነ ነው። የዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ምክር ቤት አባል ነበርኩ። ዘመኑን ሳስበው የጥንት ታሪክ ይመስለኛል። የሽግግር የተባለው ያኔም ዛሬም ያሳስበኛል። ድልድይ እንደ መሻገር ብለን ብንወስደው ያው በድልድዩ ላይ፤ ወደ ምስራቅ፤ ወደ ጸሐይ መውጫ፤ ወደ ምእራብ፣ ወደ ጸሐይ መጥለቂያ መሻገርም ነው። መሆኑ ነው!!
የዚያን ጊዜ አነጋግራቸው የነበሩ ወያኔዎች መለስን ጨምሮ በጣም ጥቂት ነበሩ። ከእነዚህ አንዱ ስዬ አብርሐ ነበር። ብቻ “አውቆታለሁ” ብሎኝም ሊሆን ይችላል። ትንሽ ወንድሙ አብሮን ማእከላዊ ታች ግቢ ነበር። ጥሩ ልጅ ይመስለኛል። ማእከላዊን ለማሻሻል ገንዘብ ስንሰበስብ የስዬ ወንድምና አቶ በየነ በርኸ በጣም ተባባሪ ነበሩ። አቶ በየነ በርኸ አሁን ከኛ ጋር የሉም። ማእከላዊን ሊታመን በማይችል መልኩ አሻሽለነው ነበር። ቴሌቪዥን ሁሉ ገዝተን!!
ታዲያ ስዬን ሳየው የደቡብ ሰው የሚመስለው ነገር አለው። ማእከላዊ በቂ የትግራይ ተወላጆች ስለነበሩ የትግሬዎችን ባህርይና ስነልቡና ደህና አድርጎ ለመታዘብ እድሉ ነበረኝ። ሌላውንም እንደማደርገው ሁሉ! ከዚያ ሞዴል፣ ስዬ ወጣ ይላልና ነው የደቡብ ሰው ይመስላል ያልኩት። የሰራው፣ የተሰራበት፣ የተሰራለት እንደተጠበቀ ሁኖ ግልጽና ጮክ ብሎ የሚናገር ነው። እንደ ዶርዜዎቹ! ዶርዜ ተሰብስቦ ሲነጋገር ያየ፣ እየተጣሉ ነው ሊል ይችላል፤ቋንቋውን ካላወቀው!
ስዬን ባገኘሁት ቁጥር “ይህ አዲስ አበባ፤ አራት ኪሎ ነው!” እያልኩ ትከሻው ላይ መታ መታ አደርገው ነበር። ነገሩ “ከጫካው ወጥታችሁ አዲስ አበባ ገብታችኋል፣ እኔም የአራት ኪሎ ነዋሪ ነኝና ተረጋጉ” ለማለት ነበር። በቀና መንፈስ! ያንን ያሰኘኝ ጥበቃ ስር ያሉ፤ የሚጠባበቁም፤ ገልመጥ ገልመጥ ብሎ የመቃኘት ሁኔታ በሁለንተናቸው (Body Language) ይታይ ስለነበር ነው። ታዲያ አንዱን ቀን ስዬ ጮኸብኝ፤“አቶ አሰፋ፤ እኛ ሰዎች ነን፤የዱር አውሬ አይደለንም; አለኝ። በከፊልም ቢሆን አልተረዳኝምና ይቅርታ ጠየኩ። በኔ ቤት ማረጋጋቴ ነበር!
ስዬን አንድ ቀን ታምራት ላይኔ ቢሮ ውሰደኝ አልኩት። ቀጥሮኝ ነበር። ወይም “ሲመችዎት ምንም ጊዜ ብቅ ይበሉ” ብሎኝ ስለነበር ይመስለኛል። ታምራት ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር። “አውቆታለሁ፤ የሚጽፉትንም አነባለሁ፤ ገጣሚም ነኝ…..” ያለኝ ይመስለኛል። ስዬ በመኪናው ይዞኝ ሔደ። ነገሩ ከፓርላማ በእግርም ቢሆን ቅርብ ነበር። የታምራት ቢሮ የሆነውን በፊት አላውቀውም። እኔ ማእከላዊ ከውረድኩ በኋላ የተሰራ ነው። ከዚህ፤ ከአቧሬ በኩል ወደ ፓርላማው የሚያመጣው አቀበት ላይ ነው። ከአጥሩ ታምራት ቢሮ እስኪደረስ የሆነች ርቀት ያለው አጥር ግቢ አለ። አንድ አራት አምስት የሚሆኑ፤ ጠመንጃ ያነገቡ አጥሩ በር ላይ አስወርደውን፤ ከስዬ ጋር የሆነ ነገር ተነጋግረው ፈተሹንና አለፈን። አንድ 50 ሜትር እንደሔድን እንደገና ያው ተደገመ። ሌላ 50 ሜትር ያክል እንደሔድን ያው ተደገመ። ታምራት ቢሮ እስክንደርስ ድረስ አራቴ ይሁን አምስቴ ወርደን ተፈተሽን። ነገሩ “ዲሞክራሲያዊነት”ም የሚያጣ አይመስለኝም። ስዬ፤ የመከላከያ ሚኒስትሩ፤ግንባር ቀደም ወያኔውም ልክ እንደኔው ነበር የሆነው።
ታምራት ቢሮ ስደርስ ደግሞ ያልጠበቅሁት ገጠመኝና ደነግጥኩ። ቢሮው ውስጥ ስድስት ሰባት የሚሆኑ፣ ጠመንጃ የያዙ በየቦታው፣ በየሶፋውና ወንበሩ ቁጭ ብለው ይጨዋወታሉ። ይሳሳቃሉም!! ታምራት “ቁጭ ይበሉ!” ብሎኝ፤የመጣሁት ለመጎብኘት እንጅ የተለየም ስለአልነበር #በል እንግዲህ ሌላ ቀን እመለሳለሁ” ብዬ ወጣሁ። ገረመኝ! ወይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲህ ይሆን? አልኩኝ፤ለራሴ! ከዚያ ስንወጣ “ለመሆኑ ይህ ሁሉ ምንድነው?” ብዬ ስዬን ጠየኩት። ”የሜዳው ህግ ነው። ወጥቼ፤ ተፈትሼ፤የዕለቱን/የሰአቱን ምስጢራዊ ቃል (code) ካልነገርኩ አያሳልፉም፣ ወይም እያዛለሁ አለኝ። ይህ አሰራር እስከ መቼ ቆይቶ ይሆን እላለሁ።
የኬላና ፍተሻ ነገር ሲነሳ አንድ ሌላ ገጠመኝ አስታወሰኝ። ከማእከላዊ በወጣሁ በወሩ እኔና ባለቤቴ፤ እህቴና ባለቤትዋ ከአንድ ሾፌር ጋር ሆነን አርባ ምንጭ ወርደን ነበር። አርባ ምንጭ ከአማሮ ኬሎ የሚመጣ ቅባታማ ቡና አለ ተባለና፣ አንድ 20 ይሆን 30 ኪሎ ገዛን። ሻሸመኔ ላይ በ”ቡና የኮንትሮባንድ ነጋዴ!”ነት ተያዝን። ዘመነ ደርግ ነበርና ፍተሻ እንደ ልብ ነው፡፡ ታዲያ ከፈታሾቹ አንዱ የኔን መታወቂያ ሲያይ፤ “አሰፋ የቡና ኮንትሮባንድ ነጋዴ አይደለም!” ያለ መሰለኝ፤ተለቀቅን። አንድ ሰው እኔን በስምም ቢሆን ማወቁ ተነግሮናልና!
ከዚያ በወሩ ይሁን እንዲያ ወዳጄ የነበረው የሐገር ደህንነት ሚኒስትሩ፤ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ፣ እቤቱ ራት ጋብዞኝ በጫወታ ላይ ይህንኑ፤የሻሸመኔውን ነገርኩት። ”አሰፋ፤ የሚገርመው ነገር ኬላው ሁሉ እንዲነሳ መመሪያ ከተላለፈ ቆይቷል፤እኔ ነኝ ያስተላለፍኩት፤ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ይቻላል?” አለኝ። ”መመሪያ ማስተላለፍና ተፈጻሚ ማድረግ ሁለት የተለያዩ ነገሮች አይመስሉህም?” አልኩትና ተሳሳቅን። በደርግም በወያኔም ውስጥ መደማመጥ የለም/ አልነበረም ልበል?
*   *   *
የታምራት ላይኔ ነገር ከተነሳ አንድ ነገር ልጨምር መሰለኝ። መለስ ዜናዊ እንዳለው ከሆነ፤ “ወራዳ ሌባ!” ተብሎ፤ በዚህም ፍርድ ቤት ፈርዶበት፣ ወህኒ ማቆ ነበር የወጣው። ሰረቀ ወይም ጉቦ ተቀበለ የተባለው ገንዘብ ወደ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ነበር። ታምራት ደግሞ ዛሬ የጴንጤ ሰባኪ ሆኗል። 20 ሚሊዮን ያለው ደግሞ ነጋዴ እንጂ ሰባኪ አይሆንም የሚል ግምት አለኝ። ዘረፈ፤ ጉቦ፤ ተቀበለ ወይም በማንኛቸውም ሌላ ተስማሚ ስም ይሁን ይህንን አካበተ የተባለዉን ገንዘብ መልሶ መንግስት ካዝና አስገብቷል የሚል አልሰማሁም፤ አላነበብኩም።
ብቻ፤ ለሁሉም ለሁሉም ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ነበር። እዚያ ውስጥ ኢትዮጵያም አለችበት። ከማርክሲዝም እስከ መጽሐፍ ቅዱስ መንገዱ ሩቅ ይመስለኛል። ፍርድ ቤት ቀርቦ ተፈርዶበታል። እዚህ ሁሉ ውስጥ እውነት የትኛው ነው? ለመሆኑ እውነት የሚባልበት ነገርስ አለ? ጋዜጠኞች አነፍንፈው ቢያወጡ ጥሩ ንባብ የሚሆን ይመስለኛል። የቅርብ ታሪካችን ወይም የቅርብ ጊዜ ጉዳችን መሆኑ አይደል!!
የዚህ መሳይ፤ አልፎ አልፎ ብቅ-ጥልቅ የሚልብኝ አይጠፋምና እመለስበታለሁ።
ድምጻዊት በዛወርቅ አስፋውን እወዳታለሁ። አዲሱን ትዝታዋን ደግሞ የበለጠ እወደዋለሁ፡፡
እስላም ክርስቲያኑን እንዲህ ያዋሐደው፤
ማተቡን ከጥንት አብሮ የገመደው ነው ---- ትላለች።
ኢትዮጵያ አመቱን ሙሉ የአመት በአል አገር ናትና፤መልካም የአመት በአል!!

Read 4563 times