Saturday, 19 March 2016 11:25

ቤት፣ መሬትና አዲሳቤ

Written by  ዒዛና ዓብርሃ
Rate this item
(3 votes)

በአለም ላይ ጣራና ግድግዳ በሚሊዮኖች የሚሸጥባት አገር አዲሳባ ብቻ ትመስለኛለች!
         ጆሮ አልሰማ አይል፡፡ በቅርብ የማውቃቸው ሠዎች አዲስ አበባ የሚገኝ መኖሪያ ቤታቸውን በ25 ሚሊዮን ብር ቸብ አድርገው፣ አሁን ቀለል ባለ ዋጋ ሌላ መኖሪያ ቤት እያፈላለጉ ናቸው አሉ፡፡ ቀለል ያለ ዋጋ ስንት ነው ብለው እራስዎትን አያድክሙ፣ ከአምስት እስከ አስር ሚሊዮን መሆኑ ነው፡፡ ደሞ’ኮ ስሙ ቤት ተባለ እንጂ ጮክ ብለው ሲያወሩ የሚደረመስ፣ ሳርና አሉ የተባሉ ቅጠላ ቅጠሎች ከቤቱ ይልቅ ዘለግ ብለው የሚታዩበት ዓይነት ነው፡፡ ግን ቤቱ ምንም ይምሰል ምን ቁም ነገሩ ያለው ከቦታው ነው፡፡ ያዲሳባ ደላላ…እነ አባ መላ…ሁሉን ያስተካክሉታል፡፡
ለነገሩ የተባለው ቦታ ወይም ቤት ይኽንን ያህል ዋጋም ላያወጣ ይችላል፡፡ የሰማኋት ወሬ ጨው ቢጤ አታጣም። ያው የአበሻ ነገር…እንተዋወቃለን አይደል፡፡ ለጠላትም ለወዳጅም ሲባል ትንሽ ቆለል ይደረጋል፡፡ መቼም ስንት ዓመት የኖሩበትን፣ስንት እትብት የቀበሩበትን፣ ስንት ደግና ክፉ ያሳለፉበትን ቀዬ ጥለው ሲሄዱ ጠንከር ያለና ራስንም ሆነ ሌሎችን ማሳመኛ ዘዴ ያሻል፡፡ ብቻ ከቦታው ዐይነት አንፃር አንድ አስራ አምስት ሚሊዮን አያጣም ባይ ነኝ---ምንም ከነ አባ መላ ጋር ባልውል መቼም ልገምት፡፡ ታዲያ ወዳጆቼ አስራ አምስት ሚሊዮን ብር  አንሶባቸው ነው ትንሽ ንፋስ ቢጤ የሰጡት?  ከመሬት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ካልሆነ በቀር   ተራ ያዲሳባ ነዋሪ ሚሊዮንን እንደ ቆሎ መዝገን ይችል ነበር እንዴ? ጉድ እኮ ነው እግዜር በፈጠረው መሬት አንዱ ከእቅፉ በላይ ያፍስበታል፣ሌላው ወር ሙሉ አፈር ድሜ በልቶ ያገኛትን ደሞዝ ለቤት ኪራይ ያፈስሰዋል… አስራ አምስት ሚሊዮን ብር አጠቃቀሙን ላወቀው ስንት ስራ ይሰራል እኮ፡፡ ያው የኛ ነገር ሲገኝም ሆነ ሲታጣ አናውቅበትም እንጂ። ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ምሳሌ ባነሳስ? አሁን በቅርቡ አንድ የቤት ምርቃት ስታደም፣ ባለቤት ደረቱን ነፍቶ ክፍሎቹን እያዞረ አስጎበኘን፡፡ ወጪውን በሚሊዮን  ሲጠሩት ይዘገንናል፣ ባለ አራት ፎቅ ነው፡፡ ይሄ መኝታ ቤት፣ የልጆች መኝታ ቤት፣ ዕቃ ቤት፣ ባኞ ቤት፣ … አያችሁልኝ ሲኖር እንኳ እንደማናውቅበት፡፡ የተዘረዘሩት ሁሉ ያው ሰልፍ ማሳመሪያ ናቸው፣ ሰዎች ቤት ሰሩ ሲባል መካተት ያለባቸው የክፍል ዓይነቶች ማለቴ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ለቤተሰቡ ምን ምን ዓይነት ክፍሎች ያስፈልጋል ተብሎ የሚሰራ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ ልጆች ነገ ተነገ ወዲያ ሳሎን ካለው መመገቢያ ጠረጴዛ ላይ የቤት ስራ ሲሰሩ፤ “በሉ እናንተ ወደ መኝታ ቤት እንግዳ አለብኝ” ይባላል፡፡ መኪናዋ እንኳ መቆሚያ ሲሰናዳላት ለቤተሰቡ የሚሆን ምቾት ያለው ማንበቢያ ክፍል ማንም አላሰበው። ልክ ነዋ ባንድ ግዜ አልጋው ላይ ሆኖ በጣራ ቀዳዳ ኮኮብ ቆጣሪ የነበረ ሠው ፣ ወደ ሚሊዮን ብር ቆጣሪ ሲቀየር፣ ደሞኮ ተነብቦ፣ተለፍቶ አይደለም የተቆጠረው … ያው ከሁላችን ድርሻ ላይ ብድግ ተደርጎ እንጂ፡፡ የኛ ገንዘብ ለጊዜው ይምሰል እንጂ…በአዲሱ ባቡር ስንጓዝ ስቴዲዬሙ ጋ ያሉትን አሮጌ ሕንፃዎች ማየት ይበቃል፡፡ እነ ጌቶች ገነቡት፣ ገነቡት…ወይ እነሱ፣ ወይ ልጆቻቸው፣ ወይ የልጅ ልጆቻቸው አልኖሩበት፡፡ (እንደው እንደ ግርጌ ማስታወሻ ትቆጠርልኝና፣ እነዚህ የኮንዶሚኒዬም ቆጣሪዎች በነካ እጃቸው እንደእነዚህ ዓይነት የኪራይ ቤቶችንም ቢቆጥሩና ለእነማን እንደተሰጡ፣ ዜጎችስ እንደዚህ ዓይነት ቤቶችን ለማግኝት ምን ማድረግ ይገባቸው እንደሆነ ቢያሳውቁን?)
የመሬት ነገር ገና ብዙ ታስተዛዝበናለች፡፡ በሕገ መንግስቱ የሕዝብና የመንግስት ንብረት ትባላለች። በተግባር ግን የሻጭ፣ የገዢና የደላሎች ናት፡፡ ደላላ ስል እንግዲህ በሁለት እንደሚከፈል ይታወቃል - የመንግስትና የግል፡፡ መቼም ብልጦች የሚኖሩባት አገር አይደለች፣ መንግስት ጥቅሙ እንዳይቀርበት በሊዝ አሰራር መሰረት መሬቱን፣ ባለቤት ደግሞ በውስጥ አሰራር መሰረት ጣራና ግድግዳውን ለገዢ ያስተላልፋሉ። የሁለት ብልጦች አገር ማለት አሁን ነው፡፡ በአለም ላይ ጣራና ግድግዳ በሚሊዮኖች የሚሸጥባት አገር አዲሳባ ብቻ ትመስለኛለች፣ ዕድሜ ለእነ አባ መላ፡፡ ለዚያውም’ኮ እንደ በጋ መሬት የተሰነጣጠቀ ግድግዳና እንደ ድንች መፋቂያ የተዘነጣጠለ ቤት---ቆርቆሮውማ…በስብሶ እንደ በሶ ፍርክስ የሚለው ወራጅ ላይ ዜግነቱን ከቆርቆሮ ወደ አፈር የቀየረ ስም የለሽ ነው እንጂ፡፡ በእነዚህ ቤቶች የተነሳ በአንድ ወቅት The Chocolate roof city  ተብለናልም አሉ፡፡  
መሬቱን በገፍ ወስዶ መሰረት ብጤ ብቅ አድርጎና ፌሮ ገትሮ ምናምን ሚሊዮን የሚባልበት አገር ስጠን ካለችሁ፣አዲሳባን እነሆ፡፡ እንደኔ አይነቱ አንድ ስኒ ቡና ጠጥቶ፣ ስድስትና አምስት ብር ሲከፍል ፊቱን ኮሶ ያስመስለዋል፡፡ እንደዚህ ሲጠሩት አፍ ላይ የሚከብድ ብር አውጥተው የአዲሳባ ብሌን ላይ ጉብ የሚሉ ሰዎች ግን ብሩን ሲያወጡት ምን ይመስላቸው ይሆን? ምድሩ አፍ ቢኖረው ሳያሽሟጥጣቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ይኽንን ያህል ገንዘብስ ከወዴት አመጡት ብሎ መጠየቅ ምቀኛ ያሰኝ ይሆን…ማለቴ’ኮ እኛም ገባ ወጣ፣ብለን በዓመትም በስድስት ወርም እንደ እነርሱ እንኳ ባይሆን በመቶ ሺዎች ዘብ ማድረግ ከቻልን ብዬ ነው፡፡ አለበለዚያ አዲሳባ ላይ መሬትና ቤት መመኘት አይደለም  ፍጥጥ ብሎ ማየትም ጉድ ሊያፈላ ይችላላ፡፡ ልክ ነዋ ሰው በሚሊዮን የገዛውን ንብረት ዱዲ ሳያወጡ መገላመጥ አግባብ ይሆናል እንዴ?
የሚገርመኝ ግሩም መስተ-ሃልይ (Mind ለሚለው የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ግሩም ፍቺ ናት) ያላቸው- የቴክሮሎጂ ፈጣሪዎች እንኳ ስማርት ፎኑን፣ ፌስ ቡኩንና የመሳሰሉትን እየፈጠሩ እንዳዲሳቦቹ ቱጃሮች ሚሊዮኗን እንደ ቀልድ ፍርጥ አድርገው የአዲስአባ ባለቤት መሆን የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ደግሞ እነርሱ ቢያደርጉም የሐብታቸው ምንጭም ሆነ መከተሪያው ግልጽ ነው፡፡ የኛዎቹ’ኮ እንኳን እንደዚህ ያለውን ለሰው ልጅ በጎ ገፅታ ያለው ነገር ሊፈጥሩና አብዛኛዎቹ ስልካቸው ላይ ካሉት አፕሊኬሽኖች ውስጥ መደወልና መልዕክት መቀበል ላይ ብቻ ያተኮረ አነስተኛ ደረጃ ክሂሎት ባለቤት ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች ለዓለም ማቅረብ የሚችሉት ገፀ-በረከት የለም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ምናልባት ምርጥ የሽቦ አልባ ስፔሻሊስቶች ስለሆኑ ይኽንኑ በመፅሃፍ ወይም በሲዲ ማሰራጨት ይችላሉ፡፡ ታዲያስ አየር ባየር አይደል‘ንዴ ጨዋታው፡፡ አደራ ይኽ ጉዳይ ለፍተውና ሰርተው ያገኙትን አያካትትም፡፡ አስቡት እስቲ ድጎማ የሚደረግበትን ላምባ ከቤንዚን ጋር የሚቀላቅሉ፣ OPEC ይኽንን ቢያውቅ የዚህን ድብልቅ ዋጋ ለመወሰን ስብሰባ የሚቀመጥ አይመስላችሁም፡፡ ሌላ ደግሞ በተመሳሳይ ዋጋ ከተመሳሳይ ኩባንያ  የተገዙ ሲቲ እስካን ማሽኖች ሁለት የተለያየ ሆስፒታል ሲገቡ…አንደኛው ሆስፒታል አስር አመት ሲገለገሉበት፣ ሌላኛው ጋር በሳምንቱ ሲበላሽስ… ካምፓኒው ይኽንን ጉድ ሲሰማ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል… በቃ ማሽኑን በአንድ ሳምንት ውስጥ በደካማ ጎኑ ገብተው ክራክ ስላደረጉለት ሽልማት ሲያንበሸብሻቸው አይታያችሁም፡፡ እንደው እምኑ ላይ ቢመቱት ነው በሳምንት ፀጥ ማድረግ የቻሉት፡፡ ሌላ ደግሞ አየር ባየር፣ ከእስካንዴኒቪያን አገራት በዕርዳታ የገቡ መድሃኒቶች፣ ጎረቤት አገራት ሲቸበቸብስ… እና ሚሊዮን ምናምን ለነዚህ የአየር ባየር ስፔሻሊስቶች ምንድን ናት…ከነርሱ ጋርስ ተጋፍቶ አዲሳባ ላይ መኖር እንዴት ይቻላል፡፡
ስለዚህ ተስፋችን አሁንስ ምንድን ነው፡፡ ኮንዶሚኒየም አልነበረምን፡፡ እሷም ጉድ አፈላቻ፡፡ የቆጠራው ውጤት ባይደርሰንም፣ ግን’ኮ ያ ታክሲ ላይ የሚፅፈው ልጅ ምነው በዚህ ረገድ ዝምታን መረጠ፡፡ ኮንዶሚኒየም ሲረከቡ፣ ባስረካቢው ፊት ቆጥረው ይውሰዱ ቢልስ፡፡ “ቆጥሮ ያልሰጠም ሆነ ቆጥሮ ያልተረከበ ሁለቱም …ናቸው” ቢጨምር መልካም ሳይሆን አይቀርም፡፡ የተሰራውንና ለተጠቃሚ ያስረከበውን እንዲሁም ቀሪውን ለይቶ ያልመዘገበ ቢሮ ነበረ ማለት ነው ወይስ እንዴት ነው… አሉባልታው ብዙ ነው፡፡ የተዘጋውን ሰብሮ ሲያከራይ ኖረ፣ ከጎኑ የነበረን ለቀም አድሮጎ መኝታ ቤት አደረገ፣ አስር ግዜ ዕጣ የወጣለት ተገኘ (ይኼ መቸም እናቱ “…”ን የሳመችው መሆን አለበት፣አራትና አምስት ግዜ የተሸጠ ቤት ገዝቶ የሚኖር ግለሰብ መጀመሪያ ዕጣው የደረሰውን ግለሰብ ትራክ ሲያደርግ ከረመ፣ እነ አባመላም ሽቀላውን ሲያጧጡፉ ከረሙ፣…ያው መረጃ በቀጥታ ከስር ከስር ለሕዝብ ይፋ ካልተደረገ ኢ-መደበኛ የሆኑ መረጃዎች እንደ ልባቸው መንሸራሸራቸውን አይቀሬ ያደርጓል፡፡ በርግጥ ስለዚህ ለመናገርም ሆነ ለመተቸት ግዜው ገና ነው፡፡ ግን አሁንም ነቃ ካልተባለ የአየር ስፔሻሊስቶቹ ፊት-ባየር ተከርብተው ሠዎቹን የኮንዶሚኒየም ሳይሆን የሺ ብሮች ቆጣሪዎች አድርገው ሊመልሷቸው ይችላሉ። ለነገሩ ቆጠራው ወደ መጠናቀቁ ነው፡፡
መቼም ዛሬ ላይ አንገትን ደፍቶ ማሕበረሰቡን የሚቀይር፣ ችግር ፈቺ ምርምር እያደረጉ በቤትና ገንዘብ እጦት ከመማረር፣ አየሮሎጂን በደንብ አጥንቶ መንቀባረር ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ ያው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከጮቤ ወደ ሸቤ እስኪዞሩ ድረስ፡፡ በርግጥ የተዘገነችውን በደንብ ከቆረጠሙ፣ ከሸቤ ሲወጡ ተጠቀሙ--- ለሆነላቸው ትንሽ እረፍት ብጤ አድርጎ እንደ መመለስ ይቆጠራል፡፡ ዕድሜ ልክ ሰርተው የማያገኙትን ሕንፃ ለዚያውም አዲሳባ ላይ ከገነቡ በኋላ ፣ አንድ አምስት፣ስድስት፣ ሰባት አመት እስር ጠጥቶ ቀሪውን ጊዜ ተረጋግቶ መኖር ከተቻለ ማለት ነው፡፡
ደግሞ’ኮ የአየሮሎጂ ስፔሻሊስቶች ስራቸውን ጀስቲፋይ ሲያደርጉት፣ ገንዘቡን ከአገር አላወጣነው፣ የስራ ዕድል ፈጠርንበት እንጂ ይሏታላ፡፡ በርግጥ እንደነ አሜሪካ ላሉ ግዙፍ አገራት ዝርፊያ ብዙ አገልግሏል። ደቡቡ ክፍል ጥቁር ሕዝቦችን እንደ ፍየል እየቸበቸበ፣ እንደ ከብት ጠምዶ እያረሰ፣ እንደ አህያ እየጫነ…ሲያሰራ ሰሜኑና ካፒታሊስቱ ደግሞ ኢንሹራንሱን፣ የገንዘብ ዝውውሩን… እያሳለጠ ዛሬ ሁላችን የምንቀናበትን፣ጥቁር ነዋሪዎቿ ደግሞ አሁንም የሚጎብጡበትን አገር ገንብተዋል፡፡ መቼም ይህቺን አገር የገነቡ ጥቁሮች ከትምሕርት ቤት ይልቅ ወደ እስር ቤት እየተነዱ፣ በአደባባይ በጥይት እንካ ቅመስ እየተባሉ  ጤነኛ ስርዓት አለ ማለት አይቻልም፡፡
ምኑን ከምኑ አያያዝከው እንዳትሉኝ…ያው መንፈሱ ዝርፊያ ስለሆነ አንድ ቦታ ላይ መቆራኘታቸው አይቀርም።  እንደዚህ ዓይነት የሕንፃ መስራት ሽቅድምድም በጤነኛ መስመር የሚሆን ስላልመሰለኝ ነው፡፡ የወንጀሉ አይነት ቢለያይም ግዙፍና ማራኪ ከተሞች ሁሉ አንድ ጉድ ከጀርባቸው  ሸፍነዋል፡፡
ያም ሆኖ ግን በገዛ ሕዝባቸው ላይ አይመስለኝም፡፡ የኛን ለየት የሚያደርገው ነገር ወንድም ወንድሙ ላይ ጉብ ብሎ ሐብት ማፍራቱ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የተገነባ ኢኮኖሚ እንዴት ፍትሃዊ ሊሆን እንሚችል አላውቅም፡፡ ታዲያ ይኽንን ጉድ ጠለቅ ብሎ ያላየ አንድ ኬንያዊ ፀሐፊ በቅርቡ፣አዲሳባ ከእንግዲህ ኋላ ቀር ከተማ አትባልም ብሎ ያበስረናል፡፡ አብላጫ ቁጥር ያላቸውን ነዋሪዎቿን በባቡሯ እፍን አድርጋ፣ጥቂቶቹን በዲፎርዲ የምታንቀባርረዋን፣አብዛኛውን ነዋሪዋን በቤት ኪራይ ናላውን እያዞረች ጥቂቶቹን በቤት ኪራይ ኪሳቸውን የምትሞላዋን አዲሳባ፡፡
በመሰረቱ ወፍ እንኳ ጎጆ አላት፤ለዚያውም ዝናብ ከመምጣቱ በፊት በሩ የሚቀየርለት፣ እነዚህ ወፎች ግን አይገርሙም? የራሳቸውን ቤት ይሰራሉ፡፡ ዛፉ በሙሉ የኔ ካልሆነ ብለው ክንፋቸው እስኪበጠስ፣ ላባቸው እስኪረግፍ ግን አይቧቀሱም፡፡ ቸር ይግጠመን!!

Read 2616 times