Saturday, 12 March 2016 11:18

የነዳጅ ዋጋ ለመንግስት ተስማምቶታል

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(15 votes)

በአመት፣ ከቤንዚንና ከናፍጣ፣ 15 ቢሊዮን ብር፣ የመንግስት ኪስ ውስጥ ይገባል?

   በአለም ገበያ፣ የነዳጅ ዋጋ በጣም ወርዷል። በሰኔ 2006 ዓ.ም፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል፣ 112 ዶላር ነበር። ዛሬ ከ40 ዶላር በታች ነው። የአገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ግን፣ እላይ እንደተሰቀለ ቀርቷል፡፡ “ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥሉ፣ የአለም ገበያን እየተከተልኩ፣ በየወሩ የችርቻሮ ዋጋዎች ላይ ማስተካከያ አደርጋለሁ” ሲል የነበረው የንግድ ሚኒስቴር፤ ምን ነካው?
ዛሬኮ፤ መንግስት፤ “የአለም ገበያ” የሚባለው ነገር ከነስሙ ያስጠላው ይመስላል። “እንቅስቃሴዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥሉ፣ የችርቻሮ ዋጋዎች ባሉበት ይቀጥላሉ” የሚል መግለጫ ያወጣል በየወሩ። ዓመት ሙሉ፣ ለ12 ወራት... ይህንኑ ነው ሲነግረን የዘለቀው - “የችርቻሮ ዋጋዎች ባሉበት ይቀጥላሉ”።
ለመሆኑ፣ መንግስት እንዲህ በማናለብኝነት እንዳሻው የሚሆንብን ለምንድነው? ነዳጅ ከውጭ ማስመጣት፣ ለመንግስት ካልሆነ በቀር ክልክል ስለሆነ ነዋ። አማራጭ የለንም። ተፎካካሪ የለበትም። ተፎካካሪ እንዳይመጣብኝ ብሎ እንኳ አይሰጋም። ስለዚህ፣ የችርቻሮ ዋጋውን፣ እንዳሰኘው መወሰን ይችላል - ጡር ካልፈራ በቀር።
የሆነስ ሆነና፣ ዋጋውን ከጣራ በላይ ሰቅሎ፣ ከዜጎች ስንት ብር እየወሰደብን ይሆን?
ያው፣ በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ምን ያህል እንደወረደ ሲታይ፤ ብዙ ብዙ ገንዘብ እየወሰደ እንደሆነ፣ ጥያቄ የለውም። በትክክል ምን ያህል ብር፣ የመንግስት ኪስ ውስጥ እንደገባ ‘እቅጩን’ ለማወቅ ግን፣ በርካታ መረጃዎችን መሰብሰብና ማስላት የግድ ይሆናል። ከዚያም፣ በቀላሉ ለመረዳት በሚያስችል አቀራረብ፣ ውጤቱን ለማሳየት መሞከር ያስፈልጋል። እንሞክር።
የመጀመሪያው ጥያቄ - ድፍድፍ ነዳጅና ቤንዚን ምንና ምን ናቸው?
ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ነዳጅ፣ ሙሉ ለሙሉ የተጣራ ነዳጅ ነው። ድፍድፍ ነዳጅ ተገዝቶ አይመጣም። ማጣሪያ የለንም። (አሰብ ላይ የተተከለው ማጣሪያ፣ የድሮ ታሪክ ሆኗል። ለነገሩ፣ ያኔም ቢሆን፣ እንደብዙዎቹ የመንግስት ተቋማት፣ የአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ፣ አክሳሪ እንደነበር መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ወጪውና ብክነቱ ከበዛ ምን ይደረጋል? ድፍድፍ ነዳጅ ገዝቶ ከማጣራት ይልቅ፣ የተጣራ ነዳጅ መግዛት የተሻለ ይሆናል ማለት ነው።)
እናም፣ ተገዝተው የሚመጡት፣… ናፍታ፣ ቤንዚን፣ የአውሮፕላን ኬሮሲን የመሳሰሉ የተጣሩ የነዳጅ ውጤቶች ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአለም ገበያ፣ “የነዳጅ ዋጋ አሻቀበ፣ አሽቆለቆለ” የምንለው፣ የድፍድፍ ነዳጅ አማካይ ዋጋ በመመልከት ነው - የለንደን የገበያ ዋጋን በመንተራስ።
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፤ “የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወረደ ማለት፣ የቤንዚን ዋጋ መውረዱን ያሳያል ወይ?” የሚል ነው። አዎ ያሳያል። መጠኑ ቢለያይም፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ፤ የናፍጣ፣ የቤንዚንና የኬሮሲን ዋጋም ይቀንሳል። ይህንን በጥቂት መረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል።
እስካለፈው መስከረም ድረስ፣ በሦስት ወራት ውስጥ፣ የድፍድፍ ነዳጅ አማካይ ዋጋ፣ ለአንድ በርሜል 50 ዶላር ነበር። በእነዚያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ፣ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቤንዚን፣ በስንት እንደተገዛም ይታወቃል። አንድ ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ለመግዛት፣ በአማካይ 560 ዶላር ወጪ እንደተደረገ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል። በእርግጥ በርሜል እና ሜትሪክ ቶን ለንፅፅር አይመችም። ግን ችግር የለም። “ለአንድ ቤርሜል ቤንዚን፣ 66 ዶላር” እንደማለት ነው። ከዚህ በኋላ አይከብድም።
የየሦስት ወሩን፣ የድፍድፍ ነዳጅ አለማቀፍ ዋጋ በአንድ ረድፍ፣ እንዲሁም ቤንዚን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባበትን አማካይ ዋጋ በሌላ ረድፍ፣ ደርድሮ ማየትና ማነፃፀር ነው። ቁጥሮቹን ከመደርደር ይልቅ ደግሞ፣ የዋጋ ውጣ ውረዱን ለማሳየት ወደሚያመች ምስል መቀየርም ይቻላል።
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በሚሊኒየሙ መባቻ፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 75 ዶላር ነበር። በዚያን ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቤንዚን ደግሞ፣ ለበርሜል 80 ዶላር ሂሳብ የተከፈለበት ነበር።
በዚያው ተረጋግቶ አልቆየም። የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከወር ወር እየናረ፣ የአመቱ መጨረሻ ላይ 121 ዶላር ደርሷል። ከዚሁ ጋር አብሮ፣ የቤንዚን ዋጋም ጨምሯል፤ ከውጭ ገዝቶ ለማስመጣት የሚከፈለው ዋጋ፣ የአመቱ መጨረሻ ላይ 126 ዶላር ነበር የደረሰው።
ግን፣ ከዚያ በላይ አልሄደም። ወዲያውኑ መውረድ ጀምሯል።
2001 ዓ.ም ከተጋመሰ በኋላም ነው፤ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 44 ዶላር፣ የቤንዚን ዋጋ ደግሞ ወደ 51 ዶላር ዝቅ ያለው። እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። በአለም ገበያ፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ሲንር፣ ከዚያ ጋር አብሮ፣ ቤንዚን ከውጭ ለማስመጣት የሚከፈለው ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል። ሲቀንስም እንደዚያው አብሮ ይወርዳል፡፡
ከ2003 ዓ.ም መጨረሻ እስከ 2006 መጨረሻ ደግሞ፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፣ በአመዛኙ ጣሪያ ላይ ተሰቅሎ የሚያንዣብብ ነበር ማለት ይቻላል - ለአንድ በርሜል፣ ከ100 እስከ 120 ዶላር። ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ቤንዚንም እንዲሁ፣ ለአንድ በርሜል፣ ከ108 እስከ 126 ዶላር ይከፈልበት ነበር። መራራ አመታት ነበሩ።
ከዚያ ወዲህ ግን፣ ዋጋው ረግቧል። በምስል 1 እንደምታዩት፣ በአለም ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ቁልቁል እየወረደ መጥቷል። ቤንዚን ወደ ኢትዮጵያ ተገዝቶ የሚመጣበት ዋጋም እንዲሁ፡፡ መስከረም ላይ ነው።
በአጭሩ፣ በአለም ገበያ፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከወረደ፤ ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ ኬሮሲን ለመግዛትና ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የሚከፈለው ዋጋም ይወርዳል።
“ቤንዚን፣ ናፍታ፣ ኬሮሲን ለማስመጣት የሚከፈለው ዋጋ”፣ ጂቡቲ ወደብ እስኪራገፍ ድረስ ያሉ ወጪዎችን በሙሉ ያጠቃልላል። ከዚያ በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ፣ ለማከፋፈልና ለመቸርቸር... የተለያዩ ወጪዎች ይጨመሩበታል። በአለም ባንክ ስሌት፣ እነዚህ የአገር ውስጥ ወጪዎች ሲደማመሩ፣ ለአንድ በርሜል ወደ 10 ዶላር ገደማ ይሆናሉ። አንድ ሊትር ከጂቡቲ አጓጉዞ፣ ለማከፋፈልና ለመቸርቸር፣ 1 ብር ከሰላሳ ሳንቲም ይፈጃል እንደማለት ነው።
መንግስት በስንት እያስመጣ በስንት ይቸበችባል?
ከውጭ አገር፣ በስንት ሂሳብ ተገዝቶ ጂቡቲ እንደሚደርስ ካወቅን፤ ከዚያም እስከ ችርቻሮ ድረስ ያለውን ወጪ ከጨመርንበት፣ ምን ቀረ? ምንም አልቀረም። ነዳጅ ለማስመጣት የሚውለውን ጠቅላላ ወጪ አሰላን ማለት ነው።
የችርቻሮ መሸጫ ዋጋውን ደግሞ እናውቃለን በንግድ ሚኒስቴር የሚወጣ ተመን ነው።
ነዳጅ ለማስመጣት በሚውለው ወጪ እና በችርቻሮ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት፤ ተጠቃልሎ የመንግስት ኪስ ውስጥ ይገባል። ይህንን ነው ለማስላት የምንሞክረው።
ለምሳሌ እስከ መስከረም ወር በነበሩት ሦስት ወራት፣ አንድ በርሜል ቤንዚን ለማስመጣት 66 ዶላር ፈጅቷል። በርሜሉን ወደ ሊትር ስንበትነው፣ ዶላሩንም በያኔው የምንዛሬ ምጣኔ ወደ ብር ስንዘረዝረው፤... ለአንድ ሊትር ቤንዚን 8 ብር ከ60 ሳንቲም ይሆናል። ይሄ እስከ ጂቡቲ ድረስ ያለው ወጪ ነው። ከዚያ በኋላ እስከ ችርቻሮ ድረስ ደግሞ፣ አንድ ብር ከሰላሳ ሳንቲም ወጪ ያስፈልጋል። ስንደምረው፣ የአንድ ሊትር ቤንዚን ጠቅላላ ወጪ፣ አስር ብር ገደማ ይሆናል።
የችርቻሮ ዋጋውስ? 17 ብር ከ40 ሳንቲም ላይ ድርቅ ብሏል።
ወጪውንና ሽያጩን ስናቀናንሰው፣ መንግስት ከእያንዳንዷ ሊትር፣ 7 ብር ከ40 ሳንቲም ወደ ኪሱ ያስገባል ማለት ነው የሚል ስሌት ላይ እንደርሳለን። በሦስት ወራት ውስጥ ከውጭ የገባው የቤንዚን መጠን፣ 72313 ሜትሪክ ቶን ነው፤ ማለትም 97 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን።
ስለዚህ፣ ከቤንዚን ብቻ፣ በሦስት ወራት (ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ መስከረም)፣ መንግስት 720 ሚሊዮን ብር አግኝቷል።
ከዚያ በፊትም፣ በሚያዚያ፣ ግንቦትና ሰኔ፣ ከቤንዚን 600 ሚሊዮን ብር አግኝቷል። ከዚያ በፊት፣ በጥር፣ የካቲትና መጋቢትስ? 700 ሚሊዮን!
ከዚያ በፊት በጥቅምት፣ ህዳርና ታህሳስ ወራት? 600 ሚሊዮን ብር!
በአጠቃላይ፣ በአንድ አመት ውስጥ፣ እስከ መስከረም ድረስ፣ ከቤንዚን ብቻ፣ መንግስት 2.6 ቢሊዮን ብር አግኝቷል። ገሚሱ፣ በታክስ መልክ የሚገባ ነው። ገሚሱ ግን፣ መንግስት ከአለም ገበያ ጋር የችርቻሮ ዋጋ በአግባቡ ለመቀነስ ስላልፈለገ፣ ከዜጎች የሚወሰድ ገንዘብ ነው።
ከናፍታስ?
የናፍታ በጣም ብዙ ነው። በአመት ውስጥ፣ ከውጭ የሚመጣው ናፍታ፣ ከቤንዚን በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ከዚሁ ጋር ወደ መንግስት ኪስ የሚገባው ገንዘብም እጅግ ብዙ ነው። በአመት (እስከ መስከረም ድረስ በነበሩ 12 ወራት)፣ መንግስት እስከ 13 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ አግኝቷል ከናፍታ። ያው፣ ገሚሱ በታክስ መልክ የሚሰበሰብ ነባር ገቢ ነው። ገሚሱ ግን፣ መንግስት የችርቻሮ ተመን ባለመቀነስ የሚያገኘው ገቢ ነው።
በቤንዚንና ናፍጣ፣ በአመት ውስጥ ወደ መንግስት ኪስ የገባው ገንዘብ 15 ቢሊዮን ብር ገደማ ይሆናል ማለት ነው።
ይሄ እስከ መስከረም ድረስ ነው። ከመስከረም ወዲህ ደግሞ፣ ወደ መንግስት ኪስ የሚገባው ገንዘብ ጨምሯል። ለምን? በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ፣ ይበልጥ አሽቆልቁሏል። የችርቻሮ ዋጋ ግን ቅንጣት አልቀነሰም ማለት ይቻላል።




Read 7735 times