Saturday, 20 February 2016 09:26

“የያዝነው በግ እንጂ ውሻ አይደለም”

Written by  ገመቹ ካቻ ዋ/ኢ/ር የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን
Rate this item
(3 votes)

ሌላው በሃይማኖት ደረጃ አሳ መዝነብ አለመዝነቡ ሊመዘን ይገባው ነበር የሚል ሃሳብም አንስተዋል፡፡
ሃይማኖቱ ምን ይላል የሚለውን ለመመለስ ያህል ግን ኢንተርቪው የተደረጉ የሃይማኖት አባቶች ያሉትን
እንጥቀስ፤ “ድሬዳዋ አሳ መዝነቡ የድሬዳዋ መጪ ጊዜ በበረከት መሞላትን፣ ጥጋብን ያመለክታል” የሚል
ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ከሃይማኖት አንጻር ብዙ ሊባል ቢችልም ለሚዛናዊነት ያህል ይሄ ይበቃል፡፡

  የፍቅር ከተማ ከሆነችው ድሬዳዋ ጥር 20 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ተኩል ገደማ በተለምዶ መናኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አሳ መዝነቡን አስመልክቶ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የፌስ ቡክ ፔጅ ላይ ዜናውን ማስፈሩ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በርካታ ግለሰቦች ዜናውን ተመልክተው ለማመን ሲቸገሩ፣ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡ በርካታ ሃሳቦችም ተሰንዝረዋል፡፡ እንዲህ አይነት ሃሳቦች መሰንዘራቸው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና አንድ ድርጊት እውነት ነው አይደለም ለማለት በርካታ መመዘኛዎች ቢኖሩትም የቀረበው ድርጊት እውነት አይደለም ብሎ ሽንጥን ገትሮ ለመከራከር በቂ እውነት የሆኑ መረጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡
ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች ማንንም ምንም ሳይጠይቁ ድርጊቱ ሊፈጸም የማይችል የውሸት ቁልል ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሁንም እውነት ነው ውሸት ነው ክርክሩ የቀጠለ ሲሆን አዲስ አድማስም የካቲት 5 ቀን 2008 ዓ.ም “የጋማ ከብቶች” በሚል ርእስ ስር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጻፈው ጽሑፍ፤ “ይሄ የጋማ ከብቶች ወሬ ነው” ካለ በኋላ “ያንን የዘገበ ዘጋቢ ዓሳ ሊያዘንብ የሚችል ታሪካዊ፤ ሳይንሳዊ፤ ሃይማኖታዊ፤ አየር ንብረታዊ፤ ሌላም ምክንያት መኖር አለመኖሩን ሳያጣራ በየቦታው ተዘዋውሮ ሳያረጋግጥ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በህሊናው መዝኖ ከግምት በላይ ሳያልፍ እንዴት ለዘገባ ያበቃዋል? “ይኸ ጋማ ከብትነት ይባላል” ብሏል፡፡ ጉዳዩ ግለሰባዊ ከሆኑ ጥያቄዎች ከመሆን አልፈው ወደ ብዙሃን ሃሳብ እንዲሻገሩ በሚመስል መልኩ ለቀረቡት ትችቶች ግን ምላሽ መስጠት የግድ ይላል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጄ የሰጠው አስተያየት ነው ብሎ ያቀረበው ጽሑፍ፤ እውነት እነዚህ ጥያቄዎች ይጠየቁ ምንም ግምት ሳይኖረው እንዳልተጠየቁ በመደምደም፣ ሳይመነዠኩ የተሰራ ዜና ነው በማለት ጽሑፉን ይጠቅሳል? በርግጥ ያልተመነዠከውስ የማን ሃሳብ ነው?
እውነቱ ይሄ ነው፡፡ አሳው ዘነበ በተባለ እለት መረጃው የደረሰው ክፍላችን በቦታው በመሄድ ወዲያውኑ በተቻለ መጠን የዘነበውን አሳ በካሜራችን የማስቀረት ስራ የተሰራ ሲሆን የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጅ እንደገመቱት ሳይሆን እንዴት አሳው ዘነበ፤ ልክ ሲዘንብ በቦታው የነበሩ ግለሰቦች ድንገት የአሳ መአት እላያቸው ላይ ሲዘንብ ተደናግጠው እንደሮጡ፣ የአካባቢው ህብረተሰብ የዘነበውን አሳ ለመወሰድ ሲሻማ እንደነበርና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ከተወሰዱ በኋላ በቦታው የነበሩ የፖሊስ አባላትም የነበረውን ሁኔታ በማያሻማ መልኩ በኢንተርቪው አስረድተዋል፡፡ እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ ሳይመነዠክ፤ ሳይጠየቅ፤ ሳይመዘን ብሎ ሃሳብ መስጠት ለዛውም ባልጠየቁት መረጃ ማን ነው ያላመነዠከው? እኛ ወይስ በግምት ሃሳብ የሚሰጡት የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጅ?
በዋናነት አሁን ማመን አለማመን የግለሰቡ ጉዳይ ሆኖ ነገር ግን ይሄንኑ ሃሳብ እውነት አይደለም በሚል ወይም መረጃው ያልተብላላና ያልተመዘነ ነው ብሎ መረጃ መስጠት ትክክል አለመሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ዲያቆን ዳንኤልም ይሄንን የወዳጃቸውን መላምት እንደ መረጃ ከመጠቀማቸው በፊት እውነታውን አመንዥከው ቢወስዱት ኖሮ እሳቸውንም ወዳጃቸውንም ከአጉል ግምት ይታደጓቸው ነበር የሚል ግምት አለን፡፡ ክፍላችን ለሰጠው መረጃ መቼም ቢሆን እውነታውን በእርግጠኝነት የሚናገረው በስማ በለው ሳይሆን ቦታው ድረስ በመሄድ በአይን አይቶ መረጃውን በመመዘን ነው፡፡ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጅ ሊመዘን ይገባ ነበር ባሏቸው መስፈርቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዜናዊና ፖሊሳዊ ጥያቄዎች ተፈትሸው የቀረቡ እንጂ ሳይመነዠኩ አይደለም፡፡
በተጓዳኝ ሊመዘንበት ይገባል ተብለው ከቀረቡት መስፈርቶች አንዱ አሳ ዘነበ የሚለው ዜና በታሪካዊ ሚዛን ሊመዘን ይገባው ነበር የሚለውን ሃሳብ በተመለከተ፣ የእሩቁን ጊዜና ብንመለክት እንኳን በበርካታ የአለማችን ከተሞች አሳ፤ እንቁራሪት፤ ጓጉንቸር፤ ጂሊ ፊሽና ሎበስተር እንደዘነበ በታሪክ መጠቀሱን የቁምነገር መጽሔት የየካቲት 2008 ዓ.ም እትም ገጽ 20 መመልከት ይበቃል፡፡ እዛው መጽሔት ላይ በቅርቡ በሃዋሳ ከተማ አሳ ዘንቦ እንደነበርም ጨምሮ ያወሳል፡፡ በእርግጥም በተለያዩ ምክንያቶች አሳ ሊዘንብ እንደሚችል ታሪክ ይጠቁማል፡፡ ስለሆነም ድሬዳዋ አሳ ቢዘንብ ከታሪክ አንጻር ሊገርመን የሚገባ ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለና የነበር ጉዳይ ስለሆነ፡፡
ሌላው በሃይማኖት ደረጃ አሳ መዝነብ አለመዝነቡ ሊመዘን ይገባው ነበር የሚል ሃሳብም አንስተዋል፡፡ ሃይማኖቱ ምን ይላል የሚለውን ለመመለስ ያህል ግን ኢንተርቪው የተደረጉ የሃይማኖት አባቶች ያሉትን እንጥቀስ፤ “ድሬዳዋ አሳ መዝነቡ የድሬዳዋ መጪ ጊዜ በበረከት መሞላትን፣ ጥጋብን ያመለክታል” የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ከሃይማኖት አንጻር ብዙ ሊባል ቢችልም ለሚዛናዊነት ያህል ይሄ ይበቃል፡፡
አሳ ዘነበ የሚለው ዜና ሳይንሳዊ በሆነ ሚዛን ሊመዘን ይገባው ነበር የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡ አሳ ሊዘንብባቸው የሚችልባቸው ምክንያቶች ከታሪክ ጋር አጣቅሰን የት ቦታ እንዴት ሊዘንብ እንደቻለ መረጃውን ለጠየቁ አካላት ሰጥተናል፡፡ አሁንም ለመስጠት ያህል ከውቂያኖሶችና ከባህር በከፍተኛ ንፋስ የሚነሱ አውሎ ንፋሶች በከፍተኛ ግፊት ከውሃ ውስጥ አሳዎችን እንቁራሪቶችን፤ ጊንጦችን ይዞ በመሄድ ሩቅ ሥፍራ ላይ ወደ ምድር ሊዘንብ እንደሚችል ሳይንስ ያስቀምጣል፡፡ ድሬዳዋ የዘነበው አሳ ከየትኛው ውቅያኖስ፣ ከየትኛው ወንዝ ነው ተነስቶ የመጣው የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ ግልጽ ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የጅቡቲ ባህር እንደሆነ ባለሙያዎች ግምት አስቀምጠዋል፡፡ ተጨማሪው ትንታኔ ከባለሙያዎች ቢደመጥ መልካም ይመስለናል፡፡
አሳ ዘነበ የሚለው ዜና ከአየር ንብረታዊ ሚዛን ሊመዘን ይገባው ነበር የሚልም ሃሳብ ተነስቷል፡፡ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጅ እንደገመቱት ሳይሆን በወቅቱ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ድሬዳዋ የምትታወቅበት ደማቅ ፀሐይ ጠፍቶ፣ በደመና የሰነበተችበት ጊዜ ያ ሲሆን አልፎ አልፎ ካፊያ ይጥል ነበር፡፡ አሳው በዘነበበት ወቅትም ካፊያ ነበረ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አሳዎች ሊዘንቡ የሚችሉት በዝናብ ወቅት ሲሆን ዝናብ በሌለበት ወቅትም አሳዎችና የተለያዩ የባህር እንስሳት አብረው እንደሚዘንቡ ቢል ኢቫንስ፤ “Its Raining Fish and Spires” በሚለው መጽሐፉ ጠቁሟል፡፡
አሳ ዘነበ የሚለው ዜና እንደተሰማ በየቦታው ተዘዋውሮ ዘጋቢው ሳያረጋግጥ የሚል ሃሳብም ተነስቷል፡፡ ተዟዙሮ የሚለው ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ ከሆነ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ ቦታው ላይ በመገኘት መረጃ የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል፡፡
ስለሆነም የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጅ ሊመዘን ይገባል ባሉት ብቻ ሳይሆን ከዛም በዘለለ ነገሩን እውነት ነው ሀሰት ነው የሚለውን ለመመዘን ጥረት ተደርጓል፡፡ ምክንያቱም እንደተቋም የድሬዳዋ ፖሊስ ለሚያወጣው መረጃ ከአንድ መቶ ፐርሰንት በላይ እርግጠኛ መሆን ይገባናልና ነው፡፡ ምን አልባት የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጅ መረጃው በፌስ ቡክ መለቀቁ ባለቤት የሌለውና ምላሽ የሚሰጥ አካል የሌለ ከመሰላቸው ትልቅ ስህተት ነው የተሳሳቱት፡፡ እንደተባለው ሳይመነዠክ በአቡ ነሲብ የተሰጠ መረጃ ሳይሆን የተመነዠከ ዜና ነው፡፡ ታዲያ ያልተመነዠከው ምንድን ነው ላለ ጠያቂ ግልጽ ነው፡፡ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወዳጅ በግምት የሰጡት ሃሳብ ነው፡፡ በመጨረሻ ነገር በምሳሌ ሲሆን መልካም ነው፡፡ አንድ ሰው በግ ሊገዛ ወደ ገበያ ወጣ፡፡ በጉን ገዝቶ ሲመለስ መንገድ ላይ ሶስት ሌቦች በጉን ሊሰርቁት ፈለጉ፡፡ ፊት ለፊት መስረቅ ስላልፈለጉ አንድ ዘዴ አሰቡ፡፡ ዘዴውም በየመቶ ሜትሩ ላይ በመቆም ሰውየውን የማግኘት ዘዴ ነው፡፡ ሲያገኙት ግን ዝም ብሎ ማግኘት ሳይሆን እውነቱን በማስካድ በጉን መውሰድ ነው፡፡
የመጀመሪያው ሌባ ከመንገዱ ቆሞ በግ እየጐተተ የሚሄደውን ግለሰብ፤ “ምነው ጃል ዘንድሮ የማይታይ ነገር የለ ወይ ስምንተኛው ሺ … ውሻ በጠራራ ጸሐይ ለምን ትጐትታለህ” ሲለው ግለሰቡ ገርሞት “እኔ በግ እንጂ ውሻ አልጐተትኩም” ብሎ በነገሩ እየተገረመ ይሄዳል፡፡ በማስከተል ሁለተኛውም ሌባ ከመቶ ሜትር በኋላ ሌላው ሌባ ጓደኛቸው እንዳለው፤ “ለምን ውሻ በጠራራ ፀሐይ እንደሚጐትት” ሲጠይቀው፤ ግለሰቡ በመገረም “ዛሬ ሰው ሁሉ አብዷል” በማለት በግ እንጂ ውሻ አለመጐተቱን ነግሮ አልፎት ይሄዳል፡፡ አሁንም ከመቶ ሜትር በኋላ ሌላው ሌባ ጓደኛቸው ቀደም ሲል ጓደኞቹ የጠየቁትን ጥያቄ በግ እየጐተተ የሚሄደውን ሰው ይጠይቀዋል፡፡ አሁን ሰውየው ጉዳዩን ሊቀበለው በመቻሉ፤ “እውነትም ይሄ ነገር በግ ሳይሆን ውሻ ነው፤ እኔ ነኝ የተሳሳትኩት” በማለት በጉን ፈቶ ይለቀዋል፡፡ ይሄንን ሲጠብቁ የነበሩት ሌቦች በጉን ይዘውት ሄዱ፡፡ እኛ ግን አሁንም ደግመን እንላለን፤ የያዝነው በግ እንጂ ውሻ አይደለም፡፡ መልካም ሳምንት፡፡

Read 3185 times