Saturday, 13 February 2016 12:01

የግብጹ ፕሬዚዳንት ቀይ ምንጣፍ ተቃውሞ ገጥሞታል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በርዕሰ መዲናዋ ካይሮ አቅራቢያ የተሰራን የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት መርቀው በከፈቱበት ወቅት የተነጠፈላቸው እጅግ ረጅም ቀይ ምንጣፍ ሰፊ ተቃውሞ እንደገጠመው ዘ ዴይሊ ሜይል ዘገበ፡፡
4 ኪሎ ሜትር እርዝማኔ እንዳለውና 143 ሺህ ፓውንድ እንደሚያወጣ የተነገረለት የፕሬዚዳንቱ የክብር ምንጣፍ፣ በአገሪቱ ጋዜጦችና በማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ውግዘት እንደደረሰበት የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞ ለንባብ የበቃው አል ማቃል የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣም፣ አብዛኛውን የፊት ገጹን ምንጣፉን በሚተች ዘገባ መሙላቱን ጠቁሟል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአንድ አመት በፊት ያወጣው ሪፖርት ከሩብ በላይ ግብጻውያን ከድህነት ወለል በታች እንደሚገኙ መግለጹን ያስታወሰው ዘገባው፣ ለፕሬዚዳንቱ የክብር ምንጣፍ ይሄን ያህል ገንዘብ መውጣቱ ብዙዎችን ማሳዘኑንና ትችት ማስተናገዱን አስታውቋል፡፡ የአገሪቱ መንግስት የጦር ሃይል ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ኢሃብ አል አህዋጊ በበኩላቸው፤ አወዛጋቢው ምንጣፍ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የአብዱል ፈታህ አልሲሲ አስተዳደር የተገዛ አለመሆኑን በማስታወስ፣ ምንጣፉ ከሶስት አመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በመሰል ስነስርዓቶች ላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው ሲሉ ሊያስተባብሉ ሞክረዋል ተብሏል፡፡

Read 2618 times Last modified on Saturday, 13 February 2016 12:13