Saturday, 13 February 2016 10:57

የአሜሪካ ነባር ፓርቲዎችን የሚያናጋ የምርጫ ዘመቻ

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(8 votes)

ነባር የፓርቲ መሪዎችና አንጋፋ ፖለቲከኞች፣ ግራ ተጋብተዋል - ዘጋርዲያን
የነውጡ ሦስት ተዋናዮች (ዶናልድ ትራምፕ፣ ቴድ ክሩዝ፣ በርኒ ሰንደርስ)

ዶናልድ ትራምፕ (ቢሊዮነር)
በፓርቲ ውስጥ አልነበሩም። ለንግግራቸው አይጠነቀቁም። ከወረት ሆይሆይታ በኋላ፣ ተዋርደው ከምርጫ ዘመቻው እንዲወጡ ቢጠበቅም፤ “ስደተኞች አባርራለሁ፤ ከአረብ አገር ለሚመጡ ቪዛ አልሰጥም” በማለት ገናና ሆነዋል።
ቴድ ክሩዝ (ከኩባ ስደተኞች የተወለዱ)
“ሪፐብሊካኖች፣ ለግለሰብ ነፃነትና ለካፒታሊዝም በፅናት መቆም ትተዋል” በማለት በፓርቲያቸው ላይ ያመፁ የነፃ ገበያ አርበኛ ናቸው። ከአንጋፋ ፖለቲከኞች ድጋፍ ስላላገኙ፤ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተስፋ የላቸውም ቢባልም፤ ጎልተው ወጥተዋል።
በርኒ ሰንደርስ (ከፖላንድ ቤተእስራኤላዊያን ስደተኞች የተወለዱ)
“ዲሞክራቲክ ፓርቲ ወኔ ቢስ ለዘብተኛ ሆኗል፣ በሃብታሞች ላይ ከ50% በላይ ታክስ መጫን አለበት” በማለት በፓርቲው ላይ ያመፁ የሶሻሊዝም አፍቃሪ ናቸው። ከቁብ የቆጠራቸው አልነበረም። ዛሬ ግን፣ የሂላሪ ክሊንተን የጎን ውጋት ሆነዋል።
ባለፉት ጥቂት አመታት፤ የአውሮፓ ፖለቲካን እያቃወሱ የመጡ ሦስቱ የቀውስ ምንጮች፤ ዘንድሮ የአሜሪካ ፖለቲካን መፈታተን ጀምረዋል። ነባሮቹ ፓርቲዎች እየተናጉ መሆናቸውን ያልዘገበ የሚዲያ ተቋም ለማግኘት ያስቸግራል። በሰሞኑ የታይም መፅሔት ላይ የወጡ ሁለት ዋና ዋና ዘገባዎችን መመልከት ይቻላል። ዘገባዎቹ እንደሚገልፁት፤ የሪፐብሊካን እና የዲሞክራቲክ ፓርቲ አንጋፋ መሪዎችና ፖለቲከኞች፤ የሚያደርጉት ነገር አጥተዋል። የዘንድሮው ምርጫ እንደወትሮው ሊሆንላቸው አልቻለም። ዘጋርዲያን በበኩሉ፤ የሰሞኑ የማጣሪያ ምርጫ፣ ነባሮቹን ፓርቲዎች የሚያብረከርክ እንደሆነ ፅፏል።
የኤንቢሲ የፖለቲካ ዜና ዋና አዘጋጅ ቼክ ቶድ በበኩላቸው፣ የማጣሪያ ምርጫው ሁለቱን ነባር ፓርቲዎች የሚያናውጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ የማጣሪያ ምርጫን ተመልከቱ። የሂላሪ ክሊንተን ዋና ተቀናቃኝ ሴናተር በርኒ ሰንደርስ፤ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባልነታቸውን የሰረዙና ራሳቸውን ‘ሶሻሊስት’ ብለው የሚጠሩ ናቸው።
የሪፐብሊካን ፓርቲ፣ የማጣሪያ ምርጫስ? ምርጫውን እየመሩ የሚገኙት ቢሊዮነሩ ዶናልድ ትራምፕ፣ በፓርቲው ውስጥ በአባልነት ተሳትፈው ያውቃሉ? ‘አዲስ መጤ ፖለቲከኛ’ ናቸው።  የ30 ዓመታት ሰነዶችና መዝገቦችን ብንፈትሽ፤ የትራምፕን የፓርቲ ተሳትፎ የሚያሳይ አንድም ምልክት አናገኝም ብለዋል ቼክ ቶድ። ከዶናልድ ትራምፕ በመቀጠል በሪፐብሊካን ፓርቲ ማጣሪያ ምርጫ ላይ፣ ደህና ውጤት ማስመዝገብ የጀመሩት ሌላኛው ተፎካካሪ ማን እንደሆኑም ተመልከቱ። ቴድ ክሩዝ ናቸው። የፓርቲያቸውን መሪዎች፣ ሌት ተቀን በትችት በመሸንቆጥ ማንም አይስተካከላቸውም።
ዶናልድ ትራምፕና ቴድ ክሩዝ፣ በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ፤ እንዲሁም በርኒ ሰንደርስ በዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ፤... ‘የዛሬን አያድርገውና’፤ ለወራት አይደለም ለሳምንታት እንኳ ጎልተው መውጣት አይችሉም ነበር። ዛሬ ግን፣ ‘አዲስ መጤ ፖለቲከኛ’ና፣ በፓርቲያቸው ላይ ያመፁ ‘አፈንጋጮች’፣ በማጣሪያ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ውቴት እያስመዘገቡ ነው። ቴድ ክሩዝ፣ በአየዋ ግዛት (ክልል) በተካሄደው በመጀመሪያው የሪፐብሊካን የማጣሪያ ምርጫ ላይ፣ አሸናፊ ሆነዋል - ዶናልድ ትራምፕን በማስከተል። ሌሎች ነባር ፖለቲከኞች (የቀድሞው የፍሎሪዳ አስተዳዳሪ ጀብ ቡሽ፣ የኒው ጀርሲ አስተዳዳሪ ክሪስ ክሪስቲ ወዘተ...) ውራ ሆነዋል። በኒው ሃምፕሸር ክልል፣ ማክሰኞ እለት በተካሄው ሁለተኛው የማጣሪያ ምርጫ ደግሞ፣ ዶናልድ ትራም በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል። የዲሞክራቲክ ፓርቲ ማጣሪያ ምርጫ ላይ፣ በአየዋ ክልል ከሂላሪ ክሊንተን ጋር አንገት ለአንገት የተፎካከሩት በርኒ ሰንደርስ፤ ኒው ሃምፕሸር ላይ፣ በሰፊ ልዩነት አሸናፊ ሆነዋል።
በእርግጥ፣ ሁለቱ ነባር ፓርቲዎች በየፊናቸው የሚያካሂዱት የማጣሪያ ምርጫ፣ ገና ተጀመረ እንጂ አልተጋመሰም። ገና በአራት ደርዘን ግዛቶች ይቀጥላል። የሁሉም ተደማምሮ ነው፤ ከየፓርቲው ማንና ማን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ የሚታወቀው።
እንዲያም ሆኖ፤ በነባር ፓርቲዎች ላይ ያመፁ፣ “መጤ ፓለቲከኛና አፈንጋጮች” የዚህን ያህል ጎልተው መውጣታቸው፣ የነባሮቹ ፓርቲዎች ተአማኒነት ምንኛ እንደተሸረሸረ ያሳያል ብለዋል - የኤንቢሲው ቼክ ቶድ።
ምን ተፈጠረ?        
የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ ልዩ እንደሆነ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ቢሊዮነሩ ዶናልድ ትራምፕ፤ መራጮችንም ብዛት ስንመለከት፣ በታሪክ ታይቶ አይታወቅም ብለዋል። ንግግራቸውን ቀጠሉ ትራምፕ። ብዙ አሜሪካዊያን፣ ለማጣሪያ ምርጫ እንዲህ በብዛት የተነቃነቁት ለምንድነው? “በኔ ምክንያት ነው ልል አልፈልግም። ግን በኔ ምክንያት ነው” ብለዋል - ትራምፕ።
እንዲህ አይነት አነጋገር፣ ለዶናልድ ትራምፕ የተለመደ ዘይቤ ነው።
ባለፈው ሰኔ ወር፣ የምርጫ ዘመቻቸውን የጀመሩት፤ “11 ሚሊዮን የሜክሲኮ ህገወጥ ስደተኞች አባርራለሁ” በማለት ነበር። ሃይማኖት አክራሪዎችና የአይሲስ ታጣቂዎች በየቦታው የሚፈፅሙት ጥቃት ሲበራከት ደግሞ፤ “ከአረብ አገራት የሚመጡ ስደተኞች፣ ቪዛ እንዳያገኙ አግዳለሁ” የሚል ጨመሩበት። ለወትሮ፤ እንዲህ ብሎ የሚናገር ሰው፤ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖረው እድሜ አጭር እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ይሄ ግምት፣ ዛሬ እየሰራ አይደለም። ጭራሽ፤ የትራምፕ ዝናና ተቀባይነት ጨመረ - የንግግር ዘይቤያቸውም እንዲሁ።  
“የሜክሲኮ ሰዎችን እወዳቸዋለሁ” በማለት የጀመሩትን ንግግር፤ “የሜክሲኮ ፖለቲከኞችም እነ ኦባማን ማሞኘት የሚችሉ ብልጦች ናቸው። ወንጀለኞችን በገፍ ወደ አሜሪካ እየላኩ፣ አገራችንን በአደንዛዥ እፅ አጥለቀለቋት” በማለት ይደመድሙታል። “ህገወጥ ስደተኞችን በሙሉ አባርሬ፣ የአሜሪካን ድንበር በግንብ አጥራለሁ” ካሉ በኋላም፣ “የግንባታውን ወጪ የሜክሲኮ መንግስት እንዲሸፍን አደርጋሉ” ሲሉ አውጀዋል።
“ፖለቲከኞቻችን ሞኞችና ደካሞች ስለሆኑ፤ አገራችን በቻይ ስትዘርፍ ቁጭ ብለው ያያሉ” በማለት ቅስቀሳ የሚያካሂዱት ትራምፕ፤ “እኔ ግን ብልጥ ነኝ። ለቻይኖች ትልቅ ሕንፃ እያከራየሁ፣ ብዙ ትርፍ እሰበስባለሁ። እኔ ፕሬዚዳንት ስሆን፤ አሜሪካ ታተርፋለች” ብለዋል - በተደጋጋሚ።
“የኢራቅን ጦርነት ከመነሻው በመቃወም ቀዳሚ ነኝ። በሺ የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ሕይወታቸውን ያጡበትና ትሪሊዮን ዶላሮችን የከሰርንበት ጦርነት ነው” ካሉ በኋላ፤ እኔ ፕሬዚዳንት ስሆን በወታደራዊ ሃይል ከአሜሪካ አጠገብ የሚደርስ አይኖርም በማለት ቃል ይባሉ። “አሸባሪዎችን እናሸንፋቸዋለን። አይሲስን በአንድ አመት አጠፋዋለሁ። የነዳጅ ማውጫዎቹን ነጥቄ እወስዳለሁ። አሜሪካ፣ በአለም ዙሪያ የተገፈፈው ክብሯን እንደገና ታስመልሳለች” በማለትም ያበስራሉ።
“የምናገረው ነገር በሙሉ ይሳካል” ባይ ናቸው ሰውዬው። እንዴት ተብለው ቢጠየቁ፤ ምላሽ አላቸው። “የስኬት ሰው ነኝ። ትልቅ ኩባንያ ለመመስረትና የ10 ቢሊዮን ዶላር ጌታ ለመሆን በቅቻለሁ። አሜሪካም እንደገና ስኬታማና ታላቅ አገር ትሆናለች”... ይሄ የዘወትር መፈክራቸው ነው።
በቢዝነስ ሥራ ስኬታማ መሆናቸው፤ ትልቅ ቁምነገር መሆኑ አይካድም። በፖለቲካም ስኬታማ እየሆኑ ነው። ነገር ግን፤ ለዋና ዋና ችግሮች፣ ሁነኛና ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብና መርህ ስለያዙ አይደለም። እዚህና እዚያ ሲረግጡ እንጂ፣ ጥንቅቅ ያለ ትክክለኛ ሃሰብና መርህ ሲያቀርቡ አይታይም። ይልቅስ፤ አብዛኛውን ሰው እያስጨነቁ የሚገኙ ዋና ዋና ችግሮችን፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አጉልተው ሳይሸፋፍኑ መናገር መቻላቸው ነው ትልቁ ስኬታቸው።
ሦስቱ ዋና ዋና የአለም ቀውሶች
የሃይማኖት አክራሪነትንና አሸባሪነትን የሚገታ ሁነኛ መፍትሄ ለማበጀት አለመቻል አንደኛው የቀውስ አይነት ነው።የቢዝነስ ስራን በሚያዳክሙ እልፍ አእላፍ አላስፈላጊ ቁጥጥሮች፣ በድጎማ እና በታክስ ጫና እየተባባሰ የመጣ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ደግሞ፤ ሁለተኛው ፈተና ነው።
የግለሰብ ማንነት አጥብቆ እንደመያዝ፤ “የብሔረሰብ ማንነትና የባሕል እኩልነት” በሚሉ መፈክሮች፣ መቧደንንና የጅምላ ፍረጃን የሚያበረታታ ግራ ዘመም ፖለቲካ እየነገሰ፤ ከዚሁም ጎን ለጎን፤ የፋሺዝምን ቅኝት የተከተለ የብሔረተኝነት ፖለቲካ እየጎላ መምጣቱ፤ ሦስተኛው ቀውስ ነው።
አሜሪካ ከቀውሶቹ ተርፋላች ወይስ?
ታይም እንደዘገበው፣ ብዙ አሜሪካዊያን፣ የአገራቸው ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል፤ ከዓለም ዙሪያ በሚሰሙት የቀውስ ዜናም ደስተኛ አይደሉም። ነገር ግን፣ እንደሌላው ጊዜ ከፖለቲካ ከመራቅ ይልቅ፤ ይበልጥ መከታተል ጀምረዋል ይላል -የታይም።
የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ
የአሜሪካ ኢኮኖሚ፣ ከሌሎች አገራት... ከአውሮፓና ከነ ጃፓን የተሻለ ቢሆንም፣ እንደወትሮው አይደለም። ሦስት እና አራት በመቶ የኢኮኖሚ እድገት፣ የድሮ ትዝታ እየሆነ ነው። የመንግስት ድጎማ እየተስፋፋ ከመምጣቱ የተነሳ፤ ከሱፐርማሪኬት አስተናጋጅ ይልቅ፤ ያለ ሥራ ድጎማ የሚቀበሉ ሰዎች፣ የተሻለ ገቢ ሲያገኙ ይታያል።
በታክስ ጫናና ቁጥር ስፍር በሌለው የቁጥጥር ደንቦች የተነሳ በርካታ ኩባንያዎች እየተዳከሙ ናቸው። አንዳንድ ኩባንያዎች ግን፣ “ታዳሽ ሃይል ያመነጫሉ፤ የኤሌክትሪክ መኪና ይሰራሉ” ተብለው በቢሊዮኖች የሚቆጠር የድጎማ ገንዘብ እየወሰዱ ይከስራሉ። እዳው የመንግስት ይሆናል።
የዲሞክራቲክ ፓርቲው ባራክ ኦባማ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ፤ አስር ትሪሊዮን ዶላር የነበረው የመንግስት ብድር፣ ዛሬ ከ18 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል። ሸክሙ ዞሮ ዞሮ በአምራች ዜጎች ላይ ነው - የመንግስትን እዳ ለመክፈል፣ ተጨማሪ የታክስ ጫና ይሸከማሉ።
በእርግጥ፤ ይሄ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ፤ በአሜሪካ የተፈጠረ ልዩ በሽታ አይደለም። ከአሜሪካ በፊት፣ በብዙ እጥፍ ከቻይና እስከ ራሺያ፣ ከብራዚል እስከ ግሪክ፣ ከጣሊያን እስከ ጃፓን... የአብዛኞቹን አገራት ኢኮኖሚ እያዳከመና እያቃወሰ የቆየ የአመታት በሽታ ነው - ሁሉንም እያዳረሰ የሚገኝ አለማቀፍ ቀውስ። ነባር ፓርቲዎች፣ ለዚህ ቀውስ ሁነኛ መፍትሄ ማበጀት ተስኗቸዋል።
መፍትሄ ያልተበጀለት የሃይማኖት አክራሪነትና ሽብር
አሜሪካና አውሮፓ፣ የሃይማኖት አክራሪዎችን ለመግታትና የአሸባሪዎችን ጥቃት ለማስወገድ ያልቻሉት፣ በአቅም እጦት ነው? ወይስ የፍላጎት እጦት?
የአሜሪካ አውሮፕላኖች፣ በአሸባሪው ቡድን በአይሲስ ላይ የአውሮፕላን ድብደባ ከጀመረች ከአመት በላይ ሆኗታል። ነገር ግን፣ የአይሲስ ወታደራዊ ሃይልና የገንዘብ አቅም ሲብረከረክ፣ የሽብር ጥቃትና ግድያ ሲቀንስ አይታይም። ለምን?
ለአይሲስ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ የሆኑት የነዳጅ ማውጫና ማከማቻ ማዕከላት፤ በአብዛኛው በአሜሪካ አውሮፕላኖች አልተደበደቡም። ለአውሮፕላን ድብደባ አስቸጋሪ ስለሆኑ አይደለም። “የነዳጅ ማዕከላት፣ በቦምብ ከተደበደቡ፣ ቃጠሎ ስለሚነሳ፣... የአለም ሙቀትን የሚያባብስ የአየር ብክለት ሊፈጠር ይችላል” የሚል ነው የኦባማ ጭንቀት። ‘የአካባቢ ጥበቃ’ ቡድኖች አስተሳሰብ፣ የዚህን ያህል ከመስመር የለቀቀ እንደሆነ ብዙዎች አይገነዘቡትም። ግን፤ ይሄውና፤ አይሲስ ነዳጅ እየሸጠ በሚሰበስበው ገንዘብ፤ ፈንጂዎች እንዲያጠምድና ሰዎችን እንዲፈጅ ሰፊ እድል አግኝቷል።
“በአየር ብክለት ሳቢያ፣ የአለም ሙቀት፣ ከመቶ አመት በኋላ፣ በግማሽ ሴንቲግሬድ ሊጨመር ይችላል” በሚል ጭንቀት፤ አሸባሪዎችን ከመዋጋት የሚቆጠቡ የመንግስት ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ሲያጋጥሟችሁ ምን ትላላችሁ? ዜጎች፣ በነባር ፓርቲዎችና ፓለቲከኞች ላይ የነበራቸው እምነት ይሸረሸራል።
መኪና ላይ መትረየስ ጠምደው የሚጓዙ የአይሲስ ታጣቂዎች ላይ፣ የአሜሪካ አውሮፕላኖች፣ ሚሳዬላቸውን አይተኩሱም። በቅድሚያ፣ ማስጠንቀቂያ ይተኩሳሉ። ወይም ከሄሌኮፕተር በድምፅ ማጉያ ያስጠነቅቃሉ። ለምን? ምናልባት፣ መኪናው ውስጥ፣ ሲቪል ሰዎች እንዳይኖሩ በማሰብ!
ሲቪሎችን ኢላማ አለማድረግና ሲቪሎች እንዳይጎዱ መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው። “ምናልባት፣ የጠላት ምሽግ ውስጥ፣ ሲቪሎች ሊኖሩ ይችላሉ” በሚል ስሜት፣ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ግን እብደት ነው። እንዴት ነው ነገሩ? ይሄ ነገር ጦርነትና ውጊያ ነው? ወይስ የወገኞች ትርዒት? በዚህ አካሄድ፣ የሃይማኖት አክራሪነትንና ሽብርን መግታት አይቻልም።
እንዲህ አይነቱ ጤና ያጣ የፖለቲካ ቀውስ፣ በአሜሪካ ላይ ብቻ የተፈጠረ አይደለም። እንዲያውም፣ ከአሜሪካ በፊት፣ ዋነኞቹ የበሽታው ተጠቂዎች አውሮፓውያን ናቸው።
“ዘረኛ ላለመባል፣ ስደተኞችን አትንኩ”
ከወር በፊት በፈረንጆቹ አዲስ አመት ዋዜማ፣ በኮሎኝ እና በሌሎች የጀርመን ከተሞች የተፈፀመውን አስደንጋጭ ድርጊት መጥቀስ ይቻላል። በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶች፣ በአንድ የባቡር መናኸሪያ ዙሪያ ከተሰበሰቡ በኋላ፣ በየአቅጣጫው ተከፋፍለው ተሰማሩ። ከዚያስ? ዘመቱ ቢባል ይሻላል። በየሄዱበት አቅጣጫ፣ መንገድ ላይ ያገኟትን ሴት መያዝ፣ ቦርሳዋን መንጠቅ፣ ልብሷን መቅደድ፣ መጎተት፣ መጎንተል... ወዘተ። ዘመቻው፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው።
አስገራሚው ነገር፤ ዜናው ወዲያውኑ አልተዘገበም። የተወሰኑ የሚዲያ ተቋማት፣ ውለው አድረው ነው የዘገቡት። በመንግስት በጀት የሚደብለት የሚዲያ ተቋም ደግሞ፣ ከነጭራሹ ዜናውን ሳይዘግብ ሰንብቷል። ለምን?
ጥቃቱን የፈፀሙት ወጣቶች፣ ከአረብ አገራት የሄዱ ስደተኛ ወጣቶች ናቸው። በርካታ ጋዜጠኞች፣ “ዜናውን ከዘገብን፤ ዘረኛ እንባላለን” ብለው ይሰጋሉ። ወይም፣ “ዘረኛ” የሆኑ ይመስላቸዋል። እናም፣ ብዙዎቹ ዜናውን በፍጥነት ሳይዘግቡ ቀሩ። ግን ተደብቆ አልቀረም። በጀርመን አደባባዮች የተፈፀመውን የጥቃት ዘመቻ፣ በሰው ሰው የሰሙ ብዙ ጀርመናዊያን፣ አዘኑ። ዜናው አለመዘገቡ ደግሞ አስቆጣቸው። ያኔ ነው፤ ዘገባው የተሰራጨው።
ይሄ ብቻ አይደለም ችግሩ። እንደማንኛውም ሰው፤ በየጊዜው ወንጀል የሚፈፅሙ ስደተኞች መኖራቸው፣ ይታወቃል። ያው፤ ማንም ሰው፣ ስደተኛም ሆነ ዜጋ፣ በዘርና በተወላጅነት ምንም ሆነ ምን፣ ወንጀል ከፈፀመ በሕግ ተጠያቂ መሆን የለበትም? በርካታ የጀርመን ፖሊሶች ግን፣ ስደተኞች የፈፀሙት ወንጀል ሲያጋጥማቸው፤ በይፋ ሪፖርት እንዳያቀርቡ፣ ፖለቲከኞች ተፅእኖ እንደሚያደርጉባቸው ተናግረዋል። ጥፋት የፈፀሙ ስደተኞች፣ በሕግ እንዳይጠየቁ ሸፋፍኖ ማስቀርት ለምን አስፈለገ? “ስደተኞችን ካሰርንና ከከሰስን፤ ዘረኛ እንባላለን” የሚል ስጋት ስለሚያስጨንቃቸው ነው። ስለዚህ፤ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ሲፈፀም፣ በዝምታ ይታለፋል።የአውሮፓ በሽታ፣ የዚህን ያህል ስር የሰደደ ሆኗል። ጀርመናዊያን፣ እንዲህ አይነቱን ነገር በየጊዜው ይታዘባሉ በማለት የዘገበው ቢቢሲ፣ ዜጎች በአገሪቱ ነባር ፓርቲዎችና ላይ የነበራቸው እምነት እየተሸረሸረ ነው ብሏል። ደግሞም፤ በፍጥነት እየተሸረሸረ መሆኑ፣ ሚስጥር አይደለም። ስልጣን ላይ የሚፈራረቁ ነባሮቹ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፤ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስን ለመፍታት የነፃ ገበያ ስርዓትን ከማስፋፋት ይልቅ እዚያው መዳከርን የሚመርጡ ከሆነ፤...  የሽብር ጥቃትንና ወንጀልን የመከላከል ፈቃደኝነት ከጎደላቸውና ለመሸፋፈን የሚሞክሩ ከሆነ፣... ምን ማድረግ ይቻላል?
“እኛ አለንላችሁ” ብለው የሚመጡ፣ ሌሎች አይነት ፖርቲዎች አሉ - “ስደተኞች ጠላታችን ናቸው” የሚሉ ነውጠኛና ዘረኛ ፓርቲዎች፤ እንዲሁም ‘ወደ ሶሻሊዝም እንገስግስ’ የሚሉ “ዝርፊያ ናፋቂ ኮሙኒስቶች” እየገነኑ ይመጣሉ። ይህ የከፋ የጥፋት አደጋ፤ ቀስ በቀስ በአውሮፓ አገራት እየጎላ ሲመጣ እያየን ነው።አሜሪካ ትንሽ ትሻላለች። ገና፣ የአውሮፓ ያህል፣ ወደ ከፋ አደጋ አልተጠጋችም። አነሰም በዛ፤ ለነፃ ገበያና ለግለሰብ ነፃነት የሚከራከሩ ፖለቲከኞች ገና አልጠፉም። ቢሆንም፤ በሦስቱ አለማቀፍ ቀውሶች፣ የአገሪቱ ነባር ፓርቲዎች ፈተና ውስጥ እየገቡ እንደሆነ፣ የዘንድሮው የምርጫ ዘመቻ፣ አንድ ምልክት ነው።        

Read 4312 times