Saturday, 06 February 2016 11:10

የአቡነ ጴጥሮስ ሁለቱም ሃውልቶች ይተከላሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“እኔ ለሃገሬና ለሃይማኖቴ ሞትን አልፈራም”

  የታላቁ ኢትዮጵያዊ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ለባቡር ግንባታ በሚል ከተነሳበት ቦታ በነገው ዕለት ተመልሶ በክብር የሚቆም ሲሆን የሃውልቱ የምረቃ ስነ ስርአት ይከናወናል፡፡  
የኢትዮጵያዊ ጳጳስ ቅርፅ አይመስልም በሚል ተነስቶ የነበረው በ1933 የተተከለው ሃውልትም፤ አቡኑ ደማቸው በፈሰሰበት ትክክለኛ ቦታ ላይ ከዋናው ሃውልት ጎን ለጎን ተመልሶ ይተከላል ተብሏል፡፡
ሃውልቱ ተመልሶ የሚተከልበትን ቦታ በልዩ ዲዛይን የመንገባት ኃላፊነቱን የወሰደው አሰር ኮንስትራክሽን፣ አጠቃላይ ስራውን ማጠናቀቁን ኃላፊዎች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡ የሃውልቱ ተከላ በነገው እለት ከተከናወነ በኋላም ቦታውን የማፅዳትና የማስዋብ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ታውቋል፡፡  
የአሰር ኮንስትራክሽን ኃላፊ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ኩባንያው የዋናውን ሃውልት ስራ በኮንትራት ክፍያ እየሰራ እንደሚገኝና የገንዘብ መጠኑ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚገለፅ ጠቁመው በ1933 ዓ.ም አፄ ኃይለ ሥላሴ ያስቀረፁትን የመጀመሪያውን ሃውልት አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት በተቀበሉበት፣ ደማቸው በፈሰሰበት ትክክለኛ ቦታ ለማስቀመጥ የሚከናወነውን ግንባታ በነፃ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  
አቡነ ጴጥሮስ በሰንሰለት ታስረው አጠገባቸው መድፍ ተወድሮ የሚያመለክተው ነጩ ሃውልት፣ ከስር የሚያልፈው ባቡር ንዝረት እንዳይሰማው በከፍታ ማማ ላይ እንደሚቀመጥ ያስረዱት የምህንድስና ባለሙያዎች፤ሃውልቱ አረንጓዴ ቦታን ጨምሮ የውሃ ፏፏቴ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡
ሃውልቱ የሚያርፍበት ቦታ አጠቃላይ ስፋት 715.5 ስኩዬር ካሬ ሜትር የሚያካልል ቦታ እንደሆነ የጠቆሙት ባለሙያዎቹ፤ 9.56 ዳያሜትር ስፋት ያለው የውሃ ፏፏቴን ጨምሮ ከ3 ሜትር በላይ ስፋት ያላቸው ዙሪያ ጥምጥም ሁለት የአረንጓዴ ቦታ ቀለበቶች እንዲሁም  ከ3 ሜትር በላይ ስፋት ያላቸውና በእብነ በረድ የተነጠፉ ሁለት የእግረኛ መንገድ ቀለበቶች ይኖሩታል ብለዋል፡፡ የሃውልቱ ርዝመት ከ7-8 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ሲሆን የሃውልቱ መቀመጫ ውድ በሆነ ሞዛይክ የተለበጠ መሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቁመው፣በሃውልቱ ቅጥር ውስጥም 5 አትሮኑሶች መሰራታቸውን አስረድተዋል፡፡
ሃውልቱ አሁን በተዘጋጀለት ስፍራ ላይ ሲቀመጥ ከሁሉም የአደባባዩ አቅጣጫዎች በጉልህ ሊታይ እንደሚችልም ባለሙያዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡  
በ1928 “የጣሊያንን አገዛዝ አልቀበልም፤ የኢትዮጵያ ህዝብም እንዳይቀበል ገዝቻለሁ።” ማለታቸውን ተከትሎ ፋሽስት ኢጣሊያ ህዝብ በተሰበሰበበት በጠራራ ፀሐይ በጥይት ደብድቦ የገደላቸውን የታላቁን አቡነ ጴጥሮስ ታሪክ ለማስጠበቅ በስማቸው ከሁለት ዓመት በፊት ማህበር የተቋቋመ ሲሆን ማህበሩ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ሰብሳቢው መምህር ሙሉጌታ አማረ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ማህበሩ ከቅርስ ባለስልጣን ጋር በቅርበት በጉዳዩ ላይ እየሰራ መሆኑን ያወሱት ሰብሳቢው! በአቡኑ የትውልድ አካባቢ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም በስማቸው ተመስርቶ የተመረቀው ገዳም አካባቢ ማህበሩ የአፀደ ህፃናት ማቋቋሙን ጠቅሰዋል። በአሁን ወቅት በተቋቋመው አፀደ ህፃናት  178 ወላጅ አልባና የአቅመ ደካማ ልጆች እየተማሩ መሆኑን የጠቆሙት መ/ር ሙሉጌታ፤ በቀጣይ ት/ቤቱን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ቤተክርስቲያን አቡነ ጴጥሮስን “ሠማዕት ፅድቅ” በሚል ስያሜ እንደምትጠራቸው ያወሱት መምህሩ፤ይህም በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ የተሰጣቸው የቅድስና ስም ሲሆን ትርጉሙም  “ቅዱስ ሰማዕት” ማለት ነው ብለዋል፡፡ በስማቸው የተሰራላቸው ገዳምም ሆነ ት/ቤቱ “ሰማዕት ፅድቅ አቡነ ጴጥሮስ ገዳም እና ት/ቤት” ተብሎ መሰየሙን የጠቆሙት መ/ር ሙሉጌታ፤ አቡነ ጴጥሮስ ለዚህች ሃገር ከሰሩት ውለታ አንፃር በመንግስትም ሆነ በቤተ ክርስቲያኗ የተሰጣቸው ቦታ የሚመጥናቸው አይደለም ብለዋል፡፡
በስማቸው የተሰየመ ሆስፒታል፣ አውራ ጎዳና፣ ት/ቤት --- አለመኖሩን መምህሩ ጠቅሰው፣ ቤተ-ክርስቲያንም ተገቢውን ክብር እየሰጠቻቸው አይደለም፤ የበለጠ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደማቸው የፈሰሰበት ትክክለኛ ቦታ (መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ አጠገብ ያለው) የቆሻሻ መጠራቀሚያና ሽንት መሽኛ ሆኖ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን አካባቢው ጸድቶ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1933 ያሰሩላቸው ሃውልት እንዲተከልበት ይደረጋል ብለዋል፤ መምህር ሙሉጌታ።
አቡነ ጴጥሮስ በስዊድን ሃገር በኢትዮጵያውያን ምዕመናን አሳሳቢነት፣ በስዊድን መንግስት ድጋፍ “የኢትዮጵያ ጀግናና የሃይማኖት አርበኛ” በሚል በተባበሩት መንግስታት የባህል ትምህርትና ሳይንስ ማዕከልም በፈረንጆች ሚሊኒየም በአለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከነበሩና ለአላማ ከተሰው የክፍለ ዘመኑ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው መካተቱን መምህሩ አውስተዋል፡፡  
የጣሊያን ወታደሮች ሊገድሏቸው ሲሉ በጥቁር ጨርቅ አይናቸውን አስረዋቸው የነበረ ቢሆንም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ “እኔ ለሃገሬና ለሃይማኖቴ ሞትን አልፈራም” ብለው ከአይናቸው ላይ ጨርቁን አንስተው ሞትን ፊት ለፊት መጋፈጣቸው ይነገርላቸዋል፡፡

Read 1426 times