Saturday, 23 January 2016 13:38

ከንብ ጋራ ኑሮ

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(39 votes)

“የማትናደፍ ንብ ከፈለግህ ከዝንብ ጋር ተጋባ”
     በገድለ ወለተ ጴጥሮስ ላይ እንዲህ የሚል ታሪክ አለ፡፡ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ወደ ዋልድባ ገዳም በገባች ጊዜ ለአንዲት እናት ረድእ ሆነች፡፡ እኒህ እናት ፈጽሞ ጠባይ የሚባል ያልፈጠረባቸው ነበሩ፡፡ አሁን የተናገሩትን አሁን ይሽሩታል፣ በሆነው ባልሆነው ይቆጣሉ፤ ከእርጅናቸው ብዛት የተነሣ ይነጫነጫሉ፤ ትእዛዛቸው ሁሉ ውኃ ቀጠነ ነው፡፡ በዚህ ዐመላቸው የተነሣ ማንም ከእርሳቸው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ከእርሳቸው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ ሆና ለረዥም ጊዜ ያገለገለቻቸው ወለተ ጴጥሮስ ነበረች፡፡
አንድ ቀን መነከሳዪያቱ ተሰባስበው፤ ‹እንዴት ከእኒህ እማሆይ ጋር ለዚህን ያህል ዘመን አብረሽ ለመኖር ቻልሽ? እንዴትስ ታገሥሻቸው? እንዴትስ መሮሽ ጥለሽ አልወጣሽም?› ሲሉ ጠየቋት፡፡ ወለተ ጴጥሮስም ‹ንብ ታውቃላችሁ? እኒህ እናት ንብ ናቸው፡፡ ከእርሳቸው የሚገኝ ብዙ ዕውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ልምድ፣ ብዙ ታሪክ፣ ብዙም ጸጋ አለ፡፡ ነገር ግን እናንተ መናደፋቸውን ብቻ ነው የምታዩት፤ ስለዚህም ማሩን ከእርሳቸው ልትቆርጡ አልቻላችሁም፡፡ ንብ ትናደፋለች፣ ነገር ግን ማር የሚገኘው ከምትናደፈው ንብ ነው፡፡ የማትናደፈው ዝንብ ቆሻሻ እንጂ ማር የላትም፡፡ እኔ ግን ከንብ ጋር እንዴት እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ ከንብ ጋር እየኖርኩም ማሩን እቆርጣለሁ› አለቻቸው ይባላል፡፡
ትዳር ማለትም እንዲሁ ነው፡፡
‹አበባው አበበ ንቡም ገባልሽ
እንግዲህ አልማዜ ማር ትበያለሽ›
የሚለው የሠርግ ዘፈን ከዚህ ጋር ይስማማል፡፡ አፍንጅም ከጋብቻ በኋላ ያለውን ጫጉላ ‹ማር ጨረቃ› ሲለው ይኼ ታይቶት እንደሆነ እንጃ፡፡ አንዳንዶቹ የትዳር ንድፊያው ብቻ ስለሚታያቸው ወይ ትዳር ሳይመሠርቱ ወይም የመሠረቱትን ትዳር ሲፈቱ ይታያሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የትዳር በጎነቱን ብቻ ስለሚያውቁት እስኪገቡበት ሲጓጉ፣ ከገቡበት በኋላ ደግሞ፤
ስሳል እንዳልኖርኩኝ አንቺን እስካገኝ
ካገኘሁሽ ወዲያ እላለሁ አውጣኝ
…እያሉ ያንጎራጉራሉ፡፡
ምናልባትም ደግሞ በሠርግ ላይ የሚዘፈነው፤
ማን ፈርሚ አለሽ፣ ማን ፈርሚ አለሽ
በተወለወለው በአለንጋው ጣትሽ
…የሚለው ዜማ፤ ‹ትንቢት ይቀድሞ ለነገር› ዓይነት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ትዳር ግን ሁለቱም ብቻ አይደለም፡፡ ትዳር ከንብ ጋር መኖር ነው፡፡ ንብ ሁለት ጠባይ አላት፡፡ አንዱ ያስደስታል፤ ሌላኛው ያስከፋል፡፡ አንዱ ጤና ይሆናል፣ ሌላኛው ግን ያማል፡፡ አንዱ ይጣፍጣል፤ ሌላው ግን ይመራል፡፡ አንዱን ይቆርጡታል፣ ሌላውን ግን ይከላከሉታል፡፡
ትዳርም እንዲሁ ነው፡፡ ሁለት ጠባይ አለው፡፡ አንደኛው ያስቃል አንዱ ያሰቅቃል፤ አንዱ ያስደስታል፣ ሌላው ያሳዝናል፡፡ አንዱ ግቡ ግቡ ሌላው ውጡ ውጡ ያሰኛል፡፡ አንዱ ይናደፋል፣ አንዱ ይጣፍጣል፤ አንዱ ጤና ሌላው ሕመም ይሰጣል፡፡ አንደኛው ግን ያለ ሌላው አይገኝም፡፡
ይኼን ለመድኃኒት፣ ለብርዝ፣ ለጠጅ፣ የምናደርገውን ማር የምትሰጠው ንብ ናት የምትናደፈው፡፡ ያቺ ስትናደፍ ፊት የምታሳብጠው፣ ውስጥን የምትመርዘው፣ የምትጠዘጥዘው፣ ንብ ናት ማሩን የምትሰጠው፡፡ በትዳርም ውስጥ ሁለቱም አሉ፡፡ ጭቅጭቁ፣ ንዝንዙ፣ ጠቡ፣ ኩርፊያው፣ አንዱ ለሌላው የግድ መታዘዙ፣ አንዱ የሌላው አገልጋይ መሆኑ፣ አንዱ ያለ ሌላው ለመወሰን አለመቻሉ፤ የሌላውን ጠባይ፣ የሌላውን ዐመል የግድ መታገሡ፤ ከሚታገሡት ሰው ጋር አብሮ መኖሩ፤ ይኼ ነው የንቧ ንድፊያ፡፡
ሰው የወለደውን አያገባም፡፡ ያሳደገውን አያገባም፣ የተዛመደውን አያገባም፡፡ የቤቱን ሰው አያገባም፡፡ ሰው ደግሞ በዐመልም፣ በፍላጎትም፣ በአመለካከትም ይበልጥ የሚቀራረበው አብሮት ከኖረና ካደገ ሰው ጋር ነበር፡፡ እምነቱና ባሕሉ ግን ጋብቻን እስከ ሰባት ቤት አርቆ ለባዕድ ይሰጠዋል፡፡ አብረነው ላልኖርነው፣ አብረን ላላደግነው አብረን ላልተወለድነው፣ ላልተዛመድነው ሰው፡፡ ከሌላ ተወልዶ፣ ሃያ ሠላሳ ዓመት ሌላ ቦታ ኖሮ፣ ከሌላ ጋር አድጎ፣ ሌላ ጠባይ ነሥቶ፣ በሌላ መንገድ መጥቶ ያገኘነውን ሰው ነው የምናገባው፡፡ ይኼንን ሰው ወይም ይህችን ሴትዮ በዕውቅ አላሠራናትም፣ አላሠራነውም፡፡ ዐመሉ እንዲህ፣ ሐሳቡ እንዲያ፣ መንገዱ እንዲህ፣ እምነቱ እንዲያ፣ ዕውቀቱ እንዲህ፣ ምግባሩ እንዲያ ብለን ዝርዝር ሰጥተን አላስመረትነውም፡፡ ‹ሬዲ ሜድ› ነው ያገኘነው፡፡ ዓይተን እንመርጣለን እንጂ፣ መርጠን አናሠራም፡፡
ንብን እኛ ብናሠራት ኖሮ የርሷን መናደፍ ለዝንብ ሰጥተን፣ የዝንብን ጠባይ ለንብ በመለስንላት ነበር፡፡ ግን ንብን እንዲሁ ሆና አገኘናት፣ አላመድናት፣ ወደ ቀፏችን አስገባናት እንጂ አንድም አልፈጠርናት፣ አንድም አላስፈጠርናት፡፡ ንቧን ማርና ንድፊያ እንደያዘች ነው ያገኘናት፡፡ ሰው በውስጡ ማርና ንድፊያ አለው፡፡ የተገዛ የሱፐር ማርኬት ማር የሚበላ ልጅ ንብ፣ የምትባለውን የሚያውቃት በጣሳው ላይ ባለው ሥዕል ነው፡፡ መልኳን እንጂ ንድፊያዋን አያውቀውም፡፡ እርሱ እድሜ ልኩን በንብ እየተነደፈ ለጌቶቹ ማር ቆርጦ የሚሰጥ ገባርም፤ ንብ እንደምትናደፍ እንጂ ማር እንደምትሰጥ አያውቅም፡፡ ‹ጌቶች ምን ምን ቢላቸው ነው ይህን የቀፎ እንጀራ የሚያስገፈግፉኝ› አለ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
አንዳንዶች በሠርግ ዘፈን፣ በተረት፣ በሠርግ ሥነ ሥርዓት፣ በስብከት፣ በድራማና በፊልም ትዳርን ሲያዩ ምናልባት ማሩ ይሆናል የሚታያቸው፡፡ ያገኛቸውም ሰው ሁሉ፤ ‹ምነው አንተ አታገባም እንዴ› ይላቸዋል እንጂ ተጋብቶ ምን እንዳለ አይነግራቸውም፡፡
‹የዛሬ ዓመት፣ የዛሬ ዓመት፣
የእንትናዬ አባት
ሲወለድ ማሞ፣ ሲወለድ ማሞ
እንመጣለን ደግሞ፤
… ያሉት ሰዎች ደግመው ላይመጡ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶችም ማሞ ሲወለድ እንደማይመጡ እያወቁት የሚዘፍኑት ዘፈን ነው፡፡ ‹የዛሬ ዓመት የእንትናዬ አባት› መሆን ለሁሉ ያልተሰጠ መሆኑን የሚናገርም የለም፡፡ ይኼ ያልተነገራቸው የዋሐንም ናቸው ልጅ የለም ብለው የሚፋቱት፡፡
ሌሎች ደግሞ ትዳር ሲባል የንቧ ንድፊያ ነው ትዝ የሚላቸው፡፡
‹ታሠረች አሉ በትዳር፣
ከንግዲህ ቀረ መሽርቀር› የሚለው ዘፈንም ውስጠ ዘ አለበት፡፡
ትዳር ምን ዕዳ ነው ትዳር ምን ዕዳ ነው
ጉልቻው ስሙኒ ምጣዱ ብር ነው
… የሚለው ባሕላዊ ዜማ፤ የምጣዱና የጉልቻው ዋጋ ዛሬ ሰማይ በነካበት ጊዜ ቀርቶ ትናንትም በርካሹ ዘመን ትዳርን ‹ዕዳ› ነው እያለ የንቧን መናደፍ እየነገረን ነው፡፡
ትዳር ግን ሁለቱም ብቻ አይደለም፡፡ ትዳር ከንብ ጋር መኖር ነው፡፡ ለማሩ ስንል ንድፊያውን መታገሥ፡፡ ቆይተህ ደግሞ ንድፊያውን መልመድ፡፡ ገበሬ ቀፎ ሰቅሎ ንብ ሲያንብ፣ ንብ እንደምትናደፍ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ የማትናደፍ ንብ ከፈለገ በየደጁ ቆሻሻ ፍለጋ የምትጓዘው ዝንብ ነበረችለት፡፡ ዝንብ ምን ጠባይዋ ሸጋ ቢሆን፤ ጠብ የሚላት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ይህን ያውቃል ገበሬው፡፡ እያወቀም ንብ ያንባል፡፡ ማነብ ብቻ ሳይሆን ከንብ ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻልም ያውቃል፡፡ ንብ ትናደፋለች፤ ግን እንዳትናደፍ ማድረግም ይችላል፡፡ የምትወደውና የማትወደው ሽታ አለ፡፡ ስትቀርብህ ምን ማድረግ እና ምን አለማድረግ እንዳለብህ ገበሬው ያውቃል፡፡ በሀገራችን ንብ አትገደልም፡፡ ነውር ነው፡፡ ብትነድፍም አትገደልም፡፡ የንቧን ማር ለመውሰድም ንቧን ገድሎ፣ አጥፍቶ፣ ጎድቶ ወይም አሰቃይቶ ሳይሆን በጭስ ራሱን እየተከላከለ፣ ፊቱን በጨርቅ ሸፍኖ፣ ወደ ንቧ ቀፎ ገብቶ ነው ማሩን የሚቆርጠው፡፡ ንቧም ሳትጎዳ፣ ማሩም ሳይጠፋ፣ እርሷም ሳትናደፍ፡፡
ትዳርም እንዲህ ነው፡፡ አኗኗሩን ነው ማወቅ፡፤ የንቧን ንድፊያ የመቀነሻውን መንገድ ነው ማወቅ፣ የማሩን አቆራረጥ መንገድ ነው ማወቅ፡፡ ደግሞም‘ኮ አስገራሚው ገበሬው የሚከባከበው ይህቺኑ የምትናደፈውን ንብ መሆኑ ነው፡፡ የምትቀስመው አበባ ትፈልጋለች፣ ንጹሕ አካባቢ ትፈልጋለች፣ ከጉንዳንና ከአውሬ ነጻ የሆነ ቀፎ ትፈልጋለች፡፡ ግን ትናደፋለች፡፡ ደግሞም ማር ትሰጣለች፡፡ ትዳር አስደሳች ነገር ብቻ ሳይሆን አስመራሪ፣ አንገብጋቢ፣ አስጠሊታ፣ ጨጓራ አንዳጅ፣ አንጀት ቆራጭ፣ ልብ አቃጣይም ክፍል አለው፡፡ ይናደፋል፡፡ ግን ደግሞ ክብካቤም ይፈልጋል፡፡ ንጹሕ ልብ፣ ታማኝ ኅሊና፣ ቻይ አንጀት፣ ታጋሽ ሆድ፣ ጠቢብ አእምሮ፣ አሳላፊ ልቡና ይፈልጋል፡፡ ለምን ቢሉ? ማር ይሰጣልና፡፡
አንዳንዶች ቤት ካለችው ወይም ካለው ንብ ይልቅ ውጭ ያለቺውን ወይም ያለውን ዝንብ ሲያደንቁ ይሰማል፡፡ መቼም ከቀፎ ውጭ ምን እንደሚኖር የታወቀ ነው፡፡ ንብ ትናደፋለች ብሎ ንብ የማያነባ ገበሬ ስንፍናውን እንጂ የንቢቱን ክፋት ማንም አይረዳለትም፡፡ ጥበብ አልባ መሆኑን፣ ትዕግሥት አልባ መሆኑን፣ ተሸናፊነቱን እየተናገረ እንጂ የንቧን ጠባይ እየተናገረ አለመሆኑን ሁሉም ያውቅለታል፡፡ የትዳርን ችግር ብቻ የሚያወራ፣ በትዳር ተመርሮ ከቀፎው ውጭ የሚሄድም ስንፍናውንና ዐቅመ ቢስነቱን እንጂ የቀፎውን ችግር እየተናገረ አይምሰለው፡፡ ቀፎው ውስጥ ማር የምትሠራው ንብ እንዳለች ሁሉም ያውቃልና፡፡ ሌላው ቀርቶ ውጭ ያለቺው ዝንብም ይኼንን ታውቃለች፡፡   
አንዳንዶች ከንብ ጋር የመኖር ጥበብ ሲያንሳቸው የማትናደፍ ንብ ፍለጋ ይኳትናሉ፡፡ የማትናደፍ ንብ መፈለግ፣ ከመረቁ አወጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ እንደማለት ነው፡፡ ወይም የማትዞር መሬት እንደመፈለግ፡፡ የማትናደፍ ንብ ከፈለግክ ከዝንብ ጋር ተጋባ፡፡

Read 17420 times