Saturday, 16 January 2016 10:03

የረሃብ አደጋው እርዳታ፣ 80% የአሜሪካና የእንግሊዝ ነው

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(8 votes)

አንዳንዴ፣ ባለውለታን ብናመሰግን ምናለበት?

  በረሃብ የተጠቁ ኢትዮጵያውያንን ለማገዝ፣ በዓመት ውስጥ 530 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደተለገሰ የዩኤን መረጃዎች ይገልፃሉ (ካለፈው ዓመት የተሻገረ ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር ሳይካተት)።
ለመጠባበቂያ የተያዘ፣... እንዲሁም ባለፈው ወር ቃል የተገባ ተጨማሪ እርዳታ ሲታከልበት፣ ከለጋሾች የተገኘው  እርዳታ 700 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል።
ከዚህ እርዳታ ውስጥ፣ $560 ሚሊዮን ያህሉ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ መንግስት የተሰጠ እርዳታ ነው።
ታዲያ፣ የውለታቸውን ያህል፣ ትልቅ ምስጋና አይገባቸውም? ይገባቸዋል። እስካሁን ግን፣ ብዙም የምስጋና ድምፅ አላሰማንም። እንዲያው፣... የውለታቸውን ያህል፣ እጅጉን ከፍ አድርገን ማመስገን ባይሆንልን እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ አንዳንዴ... “እናመሰግናለን” እንበል እንጂ (በተለይ፣ ለአሜሪካና ለእንግሊዝ)።
በእርግጥ፣ እርዳታው፣ እንደ wfp በመሳሰሉ የዩኤን ተቋማት በኩል፣ ወይም በሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች አማካኝነት የሚመጣና የሚከፋፈል ሊሆን ይችላል። ዋናዎቹ የእርዳታ ምንጮች ግን፣ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ናቸው - ከሁሉም በላይ ደግሞ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግስታት እርዳታ ከፍተኛ ነው።
ባለፈው ሳምንት፣ Humanitarian funding analysis በሚል ተዘጋጅቶ በዩኤን የተሰራጨውን መረጃ ማየት ይቻላል።
በረሃብ ለተጠቁ ኢትዮጵያዊያን ከተለገሰው እርዳታ ውስጥ፣ ግማሽ ያህሉ የአሜሪካ መንግስት እርዳታ እንደሆነ ይገልፃል ሪፖርቱ። ቀደም ሲል፣ 260 ሚሊዮን ዶላር የለገሰው የአሜሪካ መንግስት፣ ባለፈው ወር ደግሞ፣ ተጨማሪ ዘጠና ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብቷል። እርዳታው ተጠቃልሎ ሲደርስ፣ የዓመቱ የአሜሪካ እርዳታ፣ 350 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሆነ የዩኤስኤይድ ገልጿል - ከሦስት ሳምንት በፊት ባሰራጨው መግለጫ። ይሄ፣ እስከ ጥር ወር ድረስ ብቻ ነው። በዚያ ላይ፣ ለረሃብ ተጠቂዎች ብቻ የተመደበ እርዳታ ነው። (በየዓመቱ፣ ለትምህርት፣ ለጤናና ለመሳሰሉ ዘርፎች የሚመጣ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ መደበኛ እርዳታን አይጨምርም።)
ሌላኛው ትልቅ ለጋሽ፣ የእንግሊዝ መንግስት ነው። እስካሁን፣ በቀጥታ የተሰጠ፣ በአውሮፓ ህብረት እና በዩኤን በኩል፣ ለኢትዮጵያ የተለገሰው የእንግሊዝ እርዳታ፣ 110 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል (በእርግጥ፣ 43 ሚ ዶላሩ ዩኤን ለመጠባበቂያ ይዞታል)። ባለፈው ወር፣ ቃል የተገባላቸው ተጨማሪ የ100 ሚ ዶላር እርዳታዎች ሲታከሉበት፣ የእንግሊዝ መንግስት እርዳታ፣ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል። (በየዓመቱ፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለግብርናና ለመሳሰሉ ዘርፎች የሚመጣ፣ 300 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መደበኛ የእንግሊዝ እርዳታን፣ እዚህ ስሌት ውስጥ አይካተትም)።
የማይናቅ እርዳታ የለገሰና ቃል የገቡ ሌሎች አገራትም አሉ። የአውሮፓ ህብረት አገራትን መጥቀስ ይቻላል። እርዳታው፣ በደፈናው በ“አውሮፓ ህብረት” ስም ቢመጣም፣ ዋናዎቹ የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ምንጮች አምስት ናቸው - ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ኔዘርላንድ። እናም፤ በአውሮፓ ህብረት ስም ከመጣው ሰማኒያ ሚሊዮን ዶላር ውስጥ፣ ትልቁ ድርሻ የጀርመን ነው - ወደ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት። የፈረንሳይ፣ የጣሊያንና የእንግሊዝ ድርሻ፣ በየፊናቸው ሲሰላ ወደ 15 ሚሊዮን ዶላር ይጠጋል። ሌሎች የአውሮፓ አገራትም (ኔዘርላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድንና አየርላንድ)፣ እንዲሁም፣ ካናዳና ጃፓን፣ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር እስከ ሃያ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እርዳታ ለመለገስ ቃል ገብተዋል። የእነዚህ አገራት እርዳታ የሚናቅ አይደለም።
እንዲያም ሆኖ፣ ወደ ሰማኒያ በመቶ ያህሉ እርዳታ፣ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ የሚመጣ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በእርግጥም፣ እስከ ጥር ድረስ፣ በዓመት ውስጥ ለኢትዮጵያ የለገሱት እርዳታ፣ ትልቅ ውለታ ነው።
ነገር ግን፣ በሚቀጥሉት ወራትም፣ ተጨማሪ እርዳታ የሚጠበቀው፣ ከእነዚሁ አገራት ነው።  
እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ፣ እርዳታና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው፣ የረሃብ ተጠቂና ችግረኛ ኢትዮጵያዊያን፣ 18 ሚሊዮን ያህል ናቸው - በደንብ ባይገለፅም።
ስምንት ሚሊዮን ችግረኞች፣ “የምግብ ዋስትና” (ወይም ሴፍቲኔት) በተሰኘው መደበኛ የእርዳታ አሰራር፣ ይደጎማሉ።
ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ፣ አጣዳፊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የረሃብ ተጠቂዎች ናቸው። ለእነዚህ ነው፣ 15 ሚሊዮን ኩንታል የምግብ እርዳታ ያስፈልጋል የተባለው።

Read 2360 times