Monday, 11 January 2016 11:15

የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የሙስና ወግ

Written by  የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
Rate this item
(14 votes)

“አይነኬዎች በተፈጠሩበት ሙስናን መታገልም ዝም ማለትም አገር ያፈርሣል”
ባለፈው እሁድ መኢአድ በፅ/ቤቱ በዲሞክራሲና ሙስና ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ሲሆኑ በመግቢያቸውም የተለያዩ ዕውቅ ፈላስፎች ስለሙስና የተናገሩትን በመጥቀስ ሙስናን ለመተንተን ሞክረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ተገኝቶ የነበረው አዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ንግግራቸውን ለጋዜጣ እንደሚመች አድርጎ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ መልካም ንባብ!!!

“…ለግሪካውያኑ ፈላስፎች ለእነ አርስቶትልና ፕሌቶ ሙስና አገር የሚያፈርስ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ አርስቶትል፤ “ሙስና የፍትህ ስርአት ነፀብራቅ ነው፤ ፍትህ የሁሉም ነገር አያያዥ ሰንሰለት ነው” ይላል፡፡ ለአርስቶትል ፍትህ ማለት ማህበረሰቦች እንደየተፈጥሮአቸውና ይዘታቸው የራሳቸውን ድርሻ ብቻ ሲወጡ ነው፡፡ ሙስና የሚመነጨውም የማህበረሰቡን ውህደትና ሰላም ከማደፍረስ ነው ይላል አርስቶትል፡፡ ይህ ማለት ሙስና በሰፈነበት ሀገር ባለስልጣናት ከግላዊ ጥቅም ብቻ በመነሳት የማህበረሰብን ጥቅም በመንካት ሀገርን የሚያፈርሱ ናቸው ማለት ነው፡፡
የጣሊያኑ ፈላስፋ ጁሊያስ ሲሴሮም ስለ ሙስና የሚያስቀምጠው ትርጉም ተመሳሳይ ነው፡፡ “የሙስና ተቀዳሚ መሰረት የሚሆነው ማህበረሰቡን ለማስተዳደር በኃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች በፍቅረ ንዋይ እየተነዱ ከዋና ተግባራቸው ሲወጡ ነው” ይላል፡፡ ይህ ባለስልጣናት ከነጠላ ጫማ ወደ ሀመር መኪና በአንዴ ሲሸጋገሩ እንደማለት ነው … ፈላስፋው ከዚህ አይነት ችግር መውጣት የሚቻልበትን አቅጣጫ ሲያስቀምጥ፤ የፖለቲካ አመራሩን ገርቶና ኮትኩቶ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መመለስ መቻል ብቻ ነው ይላል፡፡
የሮማው የታሪክ ፀሐፊ ሌቪ በበኩሉ፤ የተወሰኑ ሰዎች (ማህበረሰቦች) ብረት ያነግቡና ሰራዊት ያቋቁሙና በጦርነት አንድን ሀገር ይወራሉ፣ ከወረሩ በኋላ ምቾት፣ ቅንጦት፣ ድሎት ሲበዛ ወደ ሙስና ቁልቁለት ውስጥ ይገባሉ ሲል ይገልፃል፡፡ እውነት ነው፡፡ የመሳሪያ ድልና ሙስና የተያያዙ ናቸው፡፡ ሙስና የተንሰራፋበት ስርአት ዝም ብለው ቢተዉት ወደ ማይቀረው ውድመት መውረዱ አይቀርም፤ በአንፃሩ ደግሞ የተስፋፋውን ሙስና ለመግታት ቢሞክር፣ ለማስተካከል በሚደረገው ግብ ግብ ስርአቱ አይቀሬ ይሆናል፤ ይላል ይህ የሮማ ታሪክ ፀሐፊ፡፡ አሁን እኔ ይሄን በጥያቄ ነው የማልፈው፡፡ በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ገብተናል ወይ? ሙስና መኖሩን መንግስትም ተቀብሎታል፡፡ መንግስት ሙስና መኖሩን ከተቀበለ ዘንዳ ዝም ብሎ ቢተወው ስርአቱን ይንደዋል፤ እናስተካክል ቢልም ስርአቱን ይንደዋል፡፡ ዋናው ጥያቄ አሁን የቱ ጋ ነን የሚለው ነው፡፡
እኛ ሀገር ያለው ሙስና የሚነሳው ከፖለቲካ ነው። በዚህ ላይ መተማመን ላይ ከተደረሰ ሙስናው ስርአታዊ ነው ወይንስ ከግለሰቦች የመነጨ? እነ እገሌ በሞራል ስለላሸቁ ነው ወይንስ ስርአቱ ራሱ ሞሳኝ ስለሆነ ነው? ሙስና ወይም ምዝበራ የፖለቲካ ትንታኔ ሆኖ ሲቀርብ መጀመሪያ መነሳት ያለበት ጥያቄ፣ በስርአትና በግለሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በቅዱሳት መፅሃፍት በመጀመሪያ ቃል ነበር ተብሏል፡፡ በፖለቲካ ትንተናም በመጀመሪያ ስርአት ነበር፡፡ ስለዚህ ሙስና የግለሰብ የሞራል መበስበስን የሚያሳይ ቢሆንም መነሻው ከስርአት ጋር የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በሌላ አባባል በኛ ሀገር ያለው ሙስና መነሻው ስርአት ነው፡፡
ምን አይነት ስርአት ላይ ነው ያለነው?
 የኢህአዴግን ጉዳይ ከፖለቲካ አኳያ ውስብስብ የሚያደርገው፣ ስርአቱ የፖለቲካ ህይወቱን የጀመረው ህገ መንግስት አዘጋጅቶ ከማቅረብ ነው፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ ከህገ መንግስቱ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ከህገ መንግስቱ አኳያ ስንመለከት፣ ሙሉ ለሙሉ ህገመንግስቱን ጥሎ፣ አውሮፓውያን “ቄሳራዊ” እንደሚሉት ፈላጭ ቆራጭ ስርአት አልተመሰረተም፡፡ ከዚህ ይልቅ የኢህአዴግ አካሄድ ህገ መንግስቱን በከፊል እየሻረ ሲያሻው ደግሞ እያከበረ የሚንቀሳቀስ፤ ስልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ የተከማቸና መሪዎች የህግ ማዕቀብ ሳይጣልባቸው የፈለጉትን የሚያደርጉበት ስርአት መሆኑ ነው፡፡ በህገ መንግስቱ ላይ ፍፁማዊ የበላይነትን የተጎናፀፈ ስርአት ነው፡፡
እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስኩት ስርአቱ ሁለት መሰረታዊ ጥሪዎችን ማስተናገድ አለመቻሉን ተመልክቼ ነው፡፡ በአንድ በኩል የዲሞክራሲ ጥሪን ማስተናገድ አልቻለም፤ በሌላ በኩል የሊበራሊዝም ጥሪንም ማስተናገድ አልቻለም፡፡ የዲሞክራሲ ጥሪው የስልጣን ክፍፍል ላይ ነው፡፡ ሊበራሊዝም የሰውን መብቶችና ነፃነቶች የሚያካትት ነው፡፡ አሁን ላለፉት 14 እና 15 ዓመታት የምየናው በዲሞክራሲና ሊብራል እሴቶችና በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረግ ፍልሚያን ነው፡፡
በዚህ በኩል የዲሞክራሲ ጥሪ አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት አለ፡፡ አሁን ሁለቱ እየተጋጩ እየተመለከትን ነው። ሁለቱ በተጋጩ ጊዜ አሸናፊው ማን እንደሚሆንም ግልፅ ነው፤ ዲሞክራሲ የታጠቀ ኃይል የላትም፣ በአንፃሩ በስልጣን የመቆየት ፍላጎት በሚገባ የታጠቀ ሀይል አለው፡፡ ሁለቱ ሲጋጩ አሸናፊው ወይም ጨፍላቂው ግልፅ ነው፡፡ በዚህ መሃል ዜጎች ሰለባ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
የኢህአዴግ ጥንተ አብሶ (The original sin) የሚነሳው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን መነሻ አድርጎ የሚሄድ ስርአት ካለመሆኑ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር፤ “ኢህአዴግ ማን ሀብታም ማን ድሃ መሆን እንዳለበት የሚወስን ድርጅት ነው” ይላል። ቁጭ ብሎ ይህቺን ሰውዬ ሀብታም እናድርጋት እንዴ? ይህቺ እንኳ ድሃ ትሁን እያለ የሚወስን ነው። ለዚህ ነው ትናንት በእግሩ ሲኳትን የነበረ ዛሬ ሰው፣ የ2 ሚሊዮን ብር መኪና እየነዳ ገርምሟችሁ የሚያልፈው፡፡ የኔ አባት ነጋዴ ነው፡፡ 20 ሺህ ብር ትርፍ ለማግኘት 40 ዓመት ነው የሰራው፡፡ አሁን አንድ ወጣት ሀብታም መሆን ከፈለገ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት ወደ መንግስት መጠጋት ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኛ መሆን አንድ ሀብታም የመሆኛ መንገድ እየሆነ ነው፡፡
መጀመሪያ በፓርቲ ይቧደናሉ። ማዘጋጃ ቤት ውስጥ የሆነ አስተዳደር ይሆናል፡፡ እንደምንም ብሎ 5000 ካሬ ሜትር ቦታ ካገኘ እሷን በሚሊዮን ብር ይሸጣል፡፡ በቃ ሀብታም ሆነ ማለት ነው፡፡ አንዱ የዘመናችን ሙስና መገለጫ ይሄ ነው፡፡ አሁን ያለው ጭንቀት ስርአቱን እናስተካክለው ቢሉት ሊፈርስ ነው፣ ዝም ብለው ቢተዉትም ሊፈርስ ነው። ስለዚህ አዙሪት ውስጥ ገብተናል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው አዙሪት ደግሞ አንድ ስርአት ዲሞክራሲና ሊበራሊዝም ሲጎድለውና በጥቂት ቡድኖች ሲመራ የህግና የፖለቲካ አይነኬዎችን ይፈጥራል፡፡ ከህግ በላይ የሆኑ በፖለቲካ የማይጠየቁ፣ ደፋር የሆኑ ሀብታሞችን ይፈጥራል፡፡
የአፄውንና የአሁኑን ስርአት በነዚህ አመክንዮዎች ካወዳደርን የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃሉ። በአፄው ዘመን፣ እነ ራስ፣ እነ ቢትወደድ፣ እነ ደጃዝማች… ስልክ እንኳ ዝም ብለው አይጠቀሙም። አንድ ጊዜ መኳንንቶቹ የስልክ ሂሳብ ሳይከፍሉ እዳቸው 5 ሺህ ብር ደረሰ። በወቅቱ የዘርፉ ኃላፊ የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ዲንቃ፤ “ቄሳርና አብዮቱ” በሚለው መፅሃፋቸው እንደገለፁት፤ የእነዚህን ከፍተኛ የሀገር አመራሮች ስልክ አስቆርጠዋል፡፡ የልኡላኖቹን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ባለስልጣናት እንዴት እንነካለን ሲሉ ለንጉሱ አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ንጉሱም ታዲያ “ምናችሁ ተነካ? ትክክል ነው የተደረገው፤ ለምን አትከፍሉም?” ብለው እንዲከፍሉ ተገደዋል፡፡ በወቅቱ እንግዲህ አይነኬዎች አልነበረም ማለት ነው፡፡
አሁንስ? የማንን ስልክ ማን ያስቆርጣል? አደገኛ ነው፡፡ በፊት በፊት እኛን መመርመር አይቻልም” ያሉ የዘመናችን የመንግስት ተቋማትን አይተናል፡፡ ይሄ እንግዲህ የፖለቲካ አይነኬዎች መፈጠራቸውን ያረጋግጥልናል፡፡ መሬት የዘረፉ እጃቸውን ቸብ ቸብ ተደርገው፣ ተቀጡ ተብለው ወዲያው ይለቀቃሉ፡፡ አንድ ሞባይል የመነተፈ ግን አደገኛ ቦዘኔ ተብሎ ከ2 ዓመት በላይ ይታሰራል፡፡ የፖለቲካ ኃይልና የዘረፋ ኃይል ውህደቱ ከፍተኛ ነው፡፡ “ይሄ የኔ ሰው ነው፤ አትንካው” የሚባልበት የአይነኬዎች ስርአት ነው የምለው ከዚህ አንፃር ነው፡፡
በንጉሱ ጊዜ የሆነ አንድ እውነተኛ ታሪክ አለ፡፡ አንድ የመንግስት ገንዘብ ያዥ 2ሺህ ብር ይሞስንና ዳኛ ፊት ይቀርባል፡፡ ዳኛው ጥፋተኛነቱን ካረጋገጡ በኋላ … “ሰማህ አንተ” ይሉታል (መዳፋቸውን ጨብጠው) “የመንግስት ገንዘብ እንደዚህ ነው የሚያዘው፤ ጨመቅ …. ጨመቅ ስታደርጋት ፍጭጭ እያለች በጣቶችህ መሃል ስትወጣ እሷን ላስ ታደርጋለህ እንጂ መዳፍህን ከፍተህ እንዴት በሙሉ ትገምጠዋለህ” አሉት፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር ተገምጦ አልቋል፡፡
በደርግም ሆነ በንጉሱ ጊዜ ሀብታምና ድሃው ልዩነቱ ግልፅ ነበር፡፡ ሀብታም የሚባለው ጫማ ያደርጋል፡፡ ቤቱ ቋንጣ፣ ጠጅ ምናምን ይኖራል፣ ወይም አንድ ሁለት ውሽማ አላቸው፤ ሌላ የላቸውም፡፡ አሁን ግን እንዴት እየኖርን እንደሆነም አይታወቅም፡፡
ዛሬ በዚህ ሀገር፤ “የ380 ሺህ ብር አልጋ አግኝቼ ልገዛ ነው” ፣… “እንዴት ርካሽ አልጋ አገኘህ!” እያሉ የሚያወሩ ሰዎችን እያየን እኮ ነው፡፡ በዚያው ልክ ቀን ከሌት ላቡን ጠብ እያደረገ አንዲት የማዳበሪያ ፍራሽ ለመግዛት በተስፋ የሚኳትን ደግሞ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ በዜጎች መካከል በእውነት ምን ያህል ልዩነት እንዳለ እኔም አይገባኝም ወይም ለመግለፅ ከብዶኛል…፡፡”     


Read 8263 times