Saturday, 19 December 2015 10:42

አሴዋ ሁሌም በልባችን ነህ!!

Written by 
Rate this item
(20 votes)

አይረሴ ራዕይ
እኛማ እንቆጥራለን
ዛሬም ሙሉ ሳቅክን
ያልተሸራረፈ ሙሉ ፈገግታህን
እንዳቀፍን አለን በየምላዳችን የነገ ሰብልህን
አሴ ኩራ ኩራ፣ ባለህበት ኩራ
ብርሃኑ ያዘምራል፣ ያሳብህ ተራራ
ዓመቱማ ያልፋል ወደፊት ገፍትሮን
ዘመኑ ቢሸብት፣
አይረሴ ራዕይ፤ ነጭ ፀጉር የለው
ከቶ መች ይረሳል
ህልምህ የወይን ጠጅ ሲነጋ ይበስላል፡፡
የነበረህና የነበረን ሀሳብ፣ እያደር ይጠራል፡፡
ስምህ ማዘርዘሩ፣ መንፈስህ መብቀሉ
ዕምነት ፍልስፍና ውልና ፈትሉ
ዕውቀትና ትጋት ብርሃን ፊደሉ
ሩቅ እንዳሰብነው ሩቅ ነው ገድሉ
ዛሬም አለ ቃሉ፣
ያውም በርቶ ፈክቶ፣ እስከማዕዘኑ፡፡
አውቃለሁ ታውቃለህ
የመከረኛ አገር መከሯ እስኪገባ
መከራ መብዛቱ
ዕውን ቢሆን እንኳ
ራዕይህ አለ ምስክር ይቆማል፤ ቀኑ ለመንጋቱ፡፡
አይቆምም ጉዟችን ባይቆምም ሥጋቱ
አይደለም ራዕይ ብሳና ዛፍ ግንድ
ሽበት አይወርሰውም፤ የዕድሜ ዘመን ግርድ
አይረሴ ራዕይ የቸገንክበትን
የፍል ዕውቀት እርሻ፣ የዓለም አሂዶህን
ታያለህ ማሳውን፡፡
አሴ ኩራ ኩራ
ብርሃን ያዘምራል ያሳብህ ተራራ
የራዕይ ተራራ !!
(ለአቶ አሰፋ ጎሳዬ ሙት አመት መታሰቢያ)
ነ.መ


Read 6586 times