Saturday, 24 October 2015 10:11

“ኢትዮጵያ ለእኔ ሁለተኛዋ ኢየሩሳሌም ናት…”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

• ተልዕኮዬ የጃንሆይን ትምህርት ለዓለም ማሰራጨት ነው
• Ethiopia is calling - የሚለውን እንዴት አቀነቀነው?

    ጃማይካውያን ለኢትዮጵያና ለቀድሞው ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያላቸው ከአምልኮ ያልተናነሰ ፍቅርና ክብር በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው፡፡
የሬጌ አቀንቃኙ ሲዲኒ ዊን ሳልማንም፤ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ እንዲሁም በጃንሆይ ፍቅር በእጅጉ መማረኩን ይገልፃል፡፡ ተልዕኮዬ የአባባ ጃንሆይን
መልእክት ለዓለም ማሰራጨት ነው ይላል፡፡ ከፍቅሩ ብዛት እምነቱን ሳይቀር ወደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቀይሯል፡፡ በቋሚነት የሚኖረውም እንደ
ሁለተኛዋ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም፣ በሚቆጥራት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በዚያ ላይ ኢትዮጵያዊት ሚስት አግብቶ ልጆች አፍርቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 የኒውዮርክ መንትያ ህንፃዎች በአልቃይዳ በተመቱ ጊዜ “Babilon is falling Ethiopia is calling” (ባቢሎን እየፈረሰች ነው፤
ኢትዮጵያ እየተጣራች ነው እንደማለት) የሚል ዘፈን ማቀንቀኑን ይናገራል፡፡ የዛሬ 14 ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ፣ የእረፍት
ስሜት እንደተሰማው ይገልፃል፡፡ እንዴት? ምን ዓይነት እረፍት? ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ፍቅርና ቁርኝት ምስጢሩ ምንድነው? አርቲስት ሲዲኒ ሳልማን
ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ሁሉንም በስፋት አውግቷታል፡፡ በ20 ዓመቱ ከጃማይካ ወደ አሜሪካ የተሻገረበትን ምክንያት በመግለፅ
የሚጀምረው አቀንቃኙ፤ ስለህይወቱና ሙያው በተለይም አዲስ ስለሚያወጣው የሙዚቃ አልበሙ ይነግረናል፡፡



ለምን ነበር ወደ አሜሪካ የሄድከው?
በዚያን ጊዜ እናትና አባቴ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ አሜሪካ በመሻገራቸው ነው እኔም  ከቤተሰቤ ጋር የሄድኩት፡፡ እዚያ እንደሄድኩ የኮሌጅ ትምህርት ጀመርኩኝ፡፡ በብሩክሊን ከተማ ብሩክሊን ኮሌጅ ውስጥ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አጠናሁ፡፡ ድምፅና ጊታር ያጠናሁት ግን  በሞንሮው ኮሌጅና ኢሮኖቲካስ ኮሌጅ በመሳሰሉት ውስጥ ነው፡፡…
በስንት ዓመትህ ነው ማንጐራጐር የጀመርከው?
የ12 አመት ልጅ ሆኜ ጃማይካ ውስጥ በትምህርት ቤት የተሰጥኦ ውድድር ላይ ተሳተፍኩ፡፡ በማመልክበት ቤተ-ክርስቲያንም እዘምር ነበር፡፡ በዚያን ሰዓት ድምፅህ አሪፍ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይሰጡኝ ነበር፡፡ በፕሮፌሽናል ደረጃ መዝፈን የጀመርኩት ግን ኒውዮርክ ውስጥ ነው፡፡ ከኮሌጅ ምርቃቴ በኋላ ማለት ነው፡፡ ከዚያም እምነቴን ወደ ኦርቶዶክስ ቀየርኩኝ፡፡ ሃይማኖቴን ኦርቶዶክስ ካደረግሁ በኋላ በሙሉ አቅሜና ችሎታዬ ስለ ኢትዮጵያና ፍትህ ስለተነፈጉ ድሆች ለመዝፈን ወሰንኩና መዝፈን ጀመርኩኝ፡፡
እምነትህን ለምንድነው ወደ ኦርቶዶክስ ሃየማኖት የቀየርከው?
በአባባ ጃንሆይ ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ለሰው ልጆች ስላላቸው ፍቅር በልጅነቴም እሰማ ነበር፡፡ ወደ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ ከኢትዮጵያዊያን ጋር የመገናኘት እድል ስለገጠመኝ የበለጠ ሰው ወዳድነታቸውን፣ ለሃይማኖታቸው ያላቸውን አክብሮት በተግባር ለማየት ቻልኩ፡፡ እንደምታውቂው ምዕራባዊያን ሁሌ ወከባ፣ ሁሌ ለአለማዊ ነገር ግርግር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ለመኖርና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ለመሆን በቃሁ፡፡ የኢትዮጵያ ባህልና እምነት የህይወት ልምዴ አንዱ አካል እንዲሆን መረጥኩ፡፡
“Babilon is falling Ethiopia is calling” የሚለውን ዘፈን ያቀነቀንከው ለዚህ ነው?
አዎ፡፡ ግን ይሄ አልበም የተሰራው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2001 ዓ.ም ኒውዮርክ ውስጥ የሚገኙት ሁለት መንትያ የቢዝነስ ህንፃዎች በአልቃይዳ በተመቱ ወቅት ነው፡፡ የሚገርምሽ የኔም የስራ ቦታ እነዚያ ህንፃዎች ውስጥ ነበር፡፡ በቃ እንደዛ ህንፃዎቹ ተመትተው ሲወድቁ “Babilon is falling Ethiopia is calling” የሚለው ዘፈን መጣልኝ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያኖች ይህን ዘፈን ያውቁታል፡፡ ከዚያም አልበሙ እንደወጣ (ከ14 አመት በፊት ማለት ነው) ሰሞን ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማህ ስሜት ምን ነበር?
እዚህ እንደመጣሁ የተሰማኝ እረፍት ነው፡፡ ምንም እንኳን ለአገሪቱ አዲስ ብሆንም እረፍት ተሰምቶኛል፡፡ ምክንያቱም በኖርኩበት ኒውዮርክ ሁሌም ወከባ ነው፤ ያለሽን 95 በመቶ ጊዜ የምታሳልፊው በስራ ነው፡፡ ለመኖር… ለቤት ኪራይ… ለሶሻል ሴኪዩሪቲ… ለሁሉም መስራት አለብሽ፡፡ ይህን ሁሉ ለማሟላት ገንዘብ ያስፈልግሻል፡፡ አሜሪካ ውስጥ አንድ ቀን እንኳን ስራሽን አጣሽ ማለት ውው….ው በቃ ህይወትሽ ተመሳቀለ ማለት ነው፡፡ እኔም በዚህ ህይወት ውስጥ ስለኖርኩ ስልችት ብሎኝ ነበር፡፡ እዚህ ስመጣ አዲስ ህይወት… እረፍት… ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያን በክርስቶስ ፍቅር ውስጥ ተረጋግቼ የመኖር ፍላጐት አደረብኝ፡፡ በቃ ኢትዮጵያ እንደገባሁ እረፍት ነው የተሰማኝ፡፡
ህዝቦቹም እንግዳን እንደ ህፃን ልጅ በፍቅር ነው የሚንከባከቡት፡፡ አየሩም… ሁሉም ነገር ለእኔ በጣም ተስማሚ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቼ አማርኛ መናገር ስጀምር፣ እየሳቁ ያበረታቱኝና ሞራል ይሰጡኝ ነበር፡፡ ብቻ ኢትዮጵያ ፍቅር… የፍቅር አገር ናት፡፡ ከዚህ ፍቅር ደግሞ እኔ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፡፡ ኢትዮጵያን እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደባት ቅዱስ አገር፣ እንደ ኢየሩሳሌም ነው የማያት፡፡ ለእኔ ሁለተኛዋ ኢየሩሳሌም ናት ማለት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ኢየሩሳሌም እስራኤል ውስጥ ጦርነት አለ፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በሰላም በኩል ከኢየሩሳሌም ትበልጣለች፡፡
ኢየሩሳሌም ኖረህ ታውቃለህ?
በፍፁም! ኢየሩሳሌምን በመፅሀፍ ቅዱስ ነው የማውቃት፡፡ ነገር ግን በፍፁም የምረሳት አገር አይደለችም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዋናው ስራህ ምንድን ነው? ሙዚቃ? ንግድ ወይስ?
ዋናው የእኔ ተልእኮ የመፅሃፍ ቅዱስን ትምህርት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅርና መልእክት መስበክና ማሰራጨት ነው፡፡ የአባባ ጃንሆይን መልእክትና ትምህርት ለዓለም ማሳወቅ ነው፡፡ አባባ ጃንሆይ የአለም ህዝቦች ፣ በዘርና በቀለም ሳንለያይ በፍቅር እንድንኖር አስተምረውናል፡፡ የእኔም ዋና ስራ እነዚህን ነገሮች ማስተማር ነው፡፡ ትምህርቱን የማስተላልፈው ደግሞ በሙዚቃ ነው፡፡ ስለዚህ ዋና ስራዬ ሙዚቃ ነው ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊት አግብተህ ሁለት ልጆች ማፍራትህን ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለትዳርህ አጫውተኝ?
ልክ ነው ሚስቴ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡ ለይላ ትባላለች፡፡ ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ሴት ልጆችን ከእሷ ወልጃለሁ፡፡ ምስጋናዬ ሲዲኒ እና መባፅዮን ሲዲኒ ይባላሉ፡፡ ምስጋናዬ ዘጠኝ አመቷ ሲሆን መባፅዮን የአራት አመት ልጅ ናት፡፡ በኑሮዬ፣ በልጆቼና በትዳሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
እስቲ ስለ ባለቤትህ ለይላ እና ስለተገናኛችሁበት አጋጣሚ አጫውተኝ…
ባለቤቴ ለይላ መኩሪያ ትባላለች፡፡ የተገናኘነው ናዝሬት ውስጥ ነው፡፡ እኔ ገና አዲስ አበባ እንደመጣሁ ኑሮዬን ለማመቻቸትና ስራ ለመስራት ወዲህ ወዲያ እያልኩ ሳለ ነበር ያገኘኋት፡፡ ናዝሬት አንድ ዝግጅት ነበረኝ፤ እዚያ ለስራ ስሄድ የፕሮግራሙ አደራጅ ነበረች፡፡ በዚያን ጊዜ የአዳማ ወጣቶች ልማት ላይ የመስራት ፍላጐት እንዳላት ነገረችኝ፡፡ እኔም ሻሸመኔ ውስጥ የሆነ ድርጅት አለን፤ ራስታዎች የምንሳተፍበት፡፡ አዳማና ሻሸመኔ ደግሞ ሁለቱም የኦሮሚያ ክልሎች እንደመሆናቸው ብዙ የልማት ስራዎችን አብረው ይሰራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አዳማና ሻሸመኔ ላይ ፌስቲቫሎች ተዘጋጀና እኔም በበጐ ፈቃደኝነት ስራዎቼን አቀረብኩኝ፡፡ ላይላ ባላት አቅም አገሯንና ህዝቧን ማገልገል የምትወድ ጐበዝ ሴት ናት፡፡ እንዲህ ተቀራርበን ነው ያገባኋት፡፡ ለይላ ለእኔ ጥሩ ሚስት ናት፡፡
የባለቤትህ ዋና ሙያ ምንድን ነው?
እሷ የተዋጣላት ማናጀር ናት፡፡ በማኔጅመንትና በእንግዳ አቀባበልና አያያዝ ዘርፍ ነው የተመረቀችው፡፡ አዳማ ትልቅ ሆቴል ውስጥ በስኬታማ ማናጀርነት ለረጅም ጊዜ ሰርታለች፡፡ አሁን ደግሞ በሙዚቃና ኢንተርቴይንመንት ዘርፍ ትልልቅ ዝግጅቶችን ታሰናዳለች፡፡
የመጀመሪያ ሚስትህ ናት ወይስ ከዚያ በፊት ትዳር ነበረህ?
አሜሪካ እያለሁ ሌላ ሚስት ነበረችኝ፤ ከእሷ ሁለት ትልልቅ ሴት ልጆች አሉኝ፡፡
“The Ultimate Challenge” (ታላቁ ፈተና) የተባለው ሁለተኛ አዲስ አልበምህ … ምን ላይ ደረሰ?
“ታላቁ ፈተና” አልበሜ አልቋል ግን አልተለቀቀም፡፡ በመጀመሪያ የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን ነጠላ ዜማ ለቅቄያለሁ፡፡ በመቀጠል ሶስት ነጠላ ዜማዎችን እለቅና ከዚያ በኋላ ታህሳስ ወር ላይ ሙሉ አልበሙ ይለቀቃል፡፡
“ታላቁ ፈተና” የተሰኘውን ነጠላ ዜማ በለቀቅህ ጊዜ የዘፈኑ መነሻ አባባ ጃንሆይ እ.ኤ.አ በ1963 በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ጀኔቫ ውስጥ ያደረጉት ንግግር እንደሆነ ገልፀህ ነበር…
ልክ ነው፡፡ አባባ ጃንሆይ ዓለምን ትልቅ ፈተና እንደገጠማት፣ በፍቅር መኖር ሰላምና አብሮነት እየጠፋ፣ የሰው ልጅ ፈተና ውስጥ መውደቁን ተናግረው ነበር፡፡ መነሻው ያ ንግግር ነው፤ እሳቸው ኢትዮጵያ የራሷ ባህል፣ ፈሪሀ እግዚአብሄር፣ መዋደድና መፋቀር ያላት አገር እንደሆነች በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ እኔም እዚህ ላይ አፅንኦት ሰጥቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ዋናው ስራዬ በሙያዬ ፍቅርና አንድነትን መስበክ ነው ብዬሻለሁ፡፡
በእሳቸው ንግግር መነሻነት ቦብ ማርሌይም ያቀነቀነ ይመስለኛል፡፡ ያንተ በምን ይለያል?
ትክክል ነው፤ ቦብ በዚህ ላይ መዝፈኑን አስታውሳለሁ፡፡ እሱ የቆዳ ቀለም፣ የአይን ቀለም… ልዩነት የአለምን ህዝብ መለያየት የለበትም፤ ሁሉም የአለም ህዝብ እኩል ነው… የሚለውን ነው ማስተላለፍ የፈለገው፡፡ የእኔም ከዚህ ብዙ አይለይም፡፡ አሁንም ታላቅ ፈተና የሆነው ይኸው በዘር፣ በቆዳ ቀለም መከፋፈል… የሰው ልጅ አንድነትን ያለመቀበል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ እግዚአብሄርን በማመንና በእግዚአብሄር ፍቅር ውስጥ ሊፈታ የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ልቡን ወደ ፈጣሪ በማዞር፣ እርስ በእርስ መዋደድ እንዳለበት ነው ጃንሆይ በአፅንኦት የተናገሩት፡፡ እኔም በዚህ ላይ ነው ያተኮርኩት፡፡ ትንሽ ልዩነት ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ አባባ ጃንሆይ በንግግራቸው መጨረሻ፤ “ልባችሁን ክፈቱና ሌሎችን በፍቅር ተቀበሉ፤ ያን ጊዜ ታላቁ ፈተና ያበቃል” ነበር ያሉት፡፡
ባለፈው ወር የአልበምህን መምጣት ለማስተዋወቅና “ታላቁ ፈተና” የተሰኘ ነጠላ ዜማህን ለማስመረቅ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ኮንሰርት አዘጋጅተህ ነበር፡፡ የታዳሚው አቀባበል እንዴት ነበር?
በኮንሰርቱ ያገኘሁት ምላሽና የሰዎች አስተያየት ከጠበቅሁት በላይ አሪፍ ነበር፡፡ አልበሜ ውጤታማ እንደሚሆን አመላካች ኮንሰርት ነው፡፡
ከኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ጋር የመስራት እድል ገጥሞሃል?
ኦ…ው በጣም በጣም ከብዙዎች ጋር ሰርቼአለሁ፡፡
ለምሳሌ …?
ለምሳሌ ከፀሃዬ ዮሐንስ ጋር ሰርቻለሁ፤ “ሳቂልኝ ሳቂልኝ” የሚለውን ዘፈኑን ካስታወስሽ “ቆንጅዬ ደህና ነሽ” እያልኩኝ ፊቸሪንግ ሰርቻለሁ፡፡ መድረክ ላይ ከጆኒ ራጋ (ዮሐንስ በቀለ) እንዲሁም ከሃይሌ ሩት ጋር ሰርቻለሁ፡፡
ከብዙ ዓመታት በፊት ከቴዲ አፍሮ ጋር ሻሸመኔ ውስጥ አብረን ሰርተናል፡፡ በሻሸመኔ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚማሩበትና እኛ የምንረዳው ት/ቤት አለ፡፡ “ጃማይካ ራስተፈሪያን ደቨሎፕመንት ኮሚዩኒቲ” የሚባል ት/ቤት ነው፤ ወደ 800 ያህል ተማሪዎች አሉት፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በትምህርታቸው መቶ በመቶ ውጤታማ ናቸው፡፡
 በጥሩ ሁኔታ እንግሊዝኛ ይናገራሉ፤ ሻሸመኔ ብትሄጂ ብዙዎቹ ወጣቶች በትክክልና በአጥጋቢ ሁኔታ እንግሊዝኛ ይናገራሉ፡፡ ሌላው አካባቢ ይሄንን አታይም፡፡ ለማንኛውም እኔና ቴዲ አፍሮ በጋራ ኮንሰርት አዘጋጅተን፤ ለዚህ ት/ቤት አቅርበናል፡፡ ከጋሽ መሐሙድና ከሌሎችም ትልልቅ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ ክብርና ደስታ ይሰማኛል፡፡
እስቲ ኢምፔሪያል ማጀስቲክ ስለተባለው የሙዚቃ ባንድህ ንገረኝ…
ኢምፔሪያል ማጀስቲክ ባንድ ከተለያየ አለም በተውጣጡ ሙዚቀኖች የተዋቀረ ባንድ ነው፡፡ አብዛኞቻችን የተገናኘነው ሻሸመኔ በተደረገ የራስተፈሪያን ኮሚዩኒቲ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ መጀመሪያ እኔ፣ ጁዳ፣ አልተን፣ ዛብሌን የተባልን ሰዎች ነን ያቋቋምነው፡፡
ዋና ዋናዎቹ የባንዱ ሰዎች እኛ ነን፡፡ ከዛ በፊት ሌሎችም ሰዎች ነበሩ፤ ግን በቋሚነት ባንዱ ውስጥ የሚሰሩ አልነበሩም፡፡
ስንት አይነት የሬጌ ስልቶች አሉ?
አር ኤንድ ቢ ሬጌ አለ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጪ አንቺ ሆዬ፣ ባቲ፣ ትዝታ፣ አምባሰል ስልት ሬጌዎች አሉ፡፡ “ታላቁ ፈተና” የተሰኘው አልበሜም በነዚህ አራት የሙዚቃ ስኬሎች የተሰራ ነው፡፡
በአልበሜ ትዝታ ማይነር አንቺሆዬ፣ ባቲ ማይነር ተካተውበታል፡፡ ከበሮና ዋሽንትንም በተለያዩ ሙዚቃዎች ውስጥ አስገብቻለሁ፡፡ የጃማይካ ሬጌ ላይ ደግሞ ድራምና የሬጌን ስሜት የሚፈጥሩ መሳሪያዎችን አካትቻለሁ፡፡
በአልበሙ ላይ አማርኛ ዘፈኖች የሉህም?
“Ethiopia is calling” የተባለው የመጀመሪያ አልበሜ ላይ ሁለት የአማርኛ ዘፈኖች ነበሩ፡፡  “ስላሴ የነፍስ ዋሴ” እና “ኢትዮጵያ የኔ መመኪያ” የተሰኙ እንደውም “ስሜን የማታውቁ ካላችሁ፣ ሲዲኒ ሳልማን እባላለሁ ልንገራችሁ” እያልኩ ነው የዘፈንኩት፡፡
በአሁኑ አልበሜ ላይ አማርኛና እንግሊዝኛ እየደባለቅሁ እንጂ ብቻውን አማርኛ አልዘፈንኩም፡፡ ወደፊት ሙሉ በሙሉ የአማርኛ አልበም አወጣለሁ፡፡ ምክንያቱም የአማርኛ ቋንቋ ችሎታዬ እያደገ ነው፡፡ እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል አይደለም የሚባለው... (በሚያስቅ አማርኛ)፡፡
ከኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በጣም የምትወደው ምንድን ነው?
ለእኔ አንደኛ ዶሮ ወጥ ነው፤ ሽሮም ነፍሴ ነው፤ አልጫና ጥብስም እወዳለሁ፡፡ ዶሮና ሽሮ ወጥ ግን ለእኔ በጣም ተወዳጅ ምግቦች ናቸው፡፡
ሻሸመኔ የሚገኘው “Twelve Tribes of Israel” የተባለው ድርጅታችሁ አሁንም አለ?
አለ፡፡ እኔ በ2001 እ..ኤ ሀምሌ ነው ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣሁት፡፡ የመጣሁትም ይሄ ድርጅት ጋብዞኝ ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ለመኖር አፈልግ ሰለነበር በድርጅቱ ግብዣ ሀምሌና ነሐሴን እዚህ ቆይቼ ሁሉንም ነገር ካጠናሁ በኋላ መስከረም ላይ የሆነ ፕሮግራም ስለነበረኝ ለንደን ሄጄ፣ ከዚያ ወደ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ ነው ጠቅልዬ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት፡፡
 “ትዌልቭ ትራይብስ ኦፍ እስራኤል” በእየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ራስ ተፈሪያን ያቋቋሙት የእምነት ድርጅት ነው፡፡ አሁንም አለ፡፡
አሁን የት ነው የምትኖረው?
እዚሁ አዲስ አበባ ሰሚት ነው የምኖረው፡፡ ሻሸመኔ መኖሪያ ቤት ሰርቻለሁ፤ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ፡፡ ሻሸመኔ አለ ያልኩሽ “ጃማይካ ራስተፈሪያን ዴቭሎፕመንት ኮሙዩኒቲ” ት/ቤት ውስጥም አልፎ አልፎ አስተምራለሁ፡፡
    በገቢ በኩል ይሄም ያግዘኛል፡፡ ሚስቴ ጐበዝ ሰራተኛ ናት፤ በጣም ደስተኛ ህይወት እየኖርኩኝ ነው፡፡    

Read 3876 times