Saturday, 24 October 2015 10:10

የሶፕ ኦፔራ ጣጣ!!

Written by  ከጉማራ ዙምራ zmtm1229@yahoo.com
Rate this item
(4 votes)

እኛንም የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል

   ጆአን የዋረን አፍቃሪ ናት፡፡ ዋረን ባለቤቱን ሲንዲን የሆስፒታል ህክምናዋን ተከታትላ እንደጨረሰች በህግ ሊፈታት ወስኗል፡፡ ነገር ግን የሲንዲ ዶክተር ጆአንን ክፉኛ ስለሚያፈቅራት በሆስፒታል ውስጥ የምታገኘውን ህክምና በማዘግየት፣ ከሆስፒታል መውጫ ጊዜዋን ለማራዘም ወጥኗል፡፡ ዶክተሩ ለራሱ ደግሞ አንድ ውጥንቅጥ ጉዳይ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ ሳንድራ የተባለቸው ነርስ ባልደረባው አርግዤልሀለሁ እያለችው ነው፡፡ ሩዲ የጆአን ባለቤት ሲሆን እርሷ ከዋረን ጋር የጀመረችውን የፍቅር ግንኙነት አውቋል፡፡ በመሆኑም የሜርቼዲስ መኪናዋን ፍሬን በማበላሸት በምሽት በምትወጣበት ወቅት አደጋ እንዲገጥማት አሲሯል፡፡
ነገሮችን ለማወሳሰብ ሩዲ የጆአንን ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ለመበቀል ከአመት በፊት እግር ኳስ ጨዋታ ተመልክታ ወደ ቤቷ ስትመለስ በነውጠኛ ወጣት ጥፋተኞች ከተፈጸመባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ካላገገመችው የ13 ዓመት ሴት ልጃቸው ጋር ወሲብ ለመፈጸም ፈልጓል፡፡ እውነት ከዚህ ሁሉ ዝብርቅርቅ የፍቅር ጉዞ በኋላ ዋረን እና ጆአን አብረው በአንድ አልጋ ይተኙ ይሆን? ሲንዲስ ከህመሟ አገግማ ከአልጋ ትነሳ ይሆን? ሩዲ ከገዛ ልጁ ጋር ሊፈጽመው ያቀደውን ወሲብና ሚስቱን ለመግደል የወጠነውን ሃሳብ ሰርዞ ለኑዛዜ ሞት ይበቃ ይሆን? ዋረንስ ጸጸት ተሰምቶት ከሆስፒታል አገግማ የምትወጣውን ሚስቱን ይቅር በይኝ በድያለሁ ይላት ይሆን? ጆአንን ለዶክተሩ ገጸበረከት እንድትሆን ይፈቅዳል? ነርሷ ሳንድራስ ጽንሱን ታቋርጠው ይሆን? ትእይንቱ ምላሽ በሌላቸው ውስብስብ ሴራዎች ታጭቋል፡፡
ይህ ሁሉ የተወሳሰበ የሰዎች የፍቅር ህይወት ግንኙነት የሚታየው በሀገረ አሜሪካ በሚገኙ የቴሌቪዥን ኔትወርኮች ላይ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ተከታታይ የቲቪ ፊልሞችን ሶፕ ኦፔራ ይሏቸዋል፡፡ ሶፕ ኦፔራ የመዝገበ ቃላት ትርጉሙ እንዲህ ይለዋል፡- ሶፕ ኦፔራ ማለት የአንድን ቤተሰብ ወይም ማህበረሰብ የእለት ተእለት ውጣ ውረድና ችግር በፊልም/ድራማ መልክ እየተዘጋጀ በየእለቱ ወይም በየሳምንቱ በሬድዮ ወይም በቴሌቪዥን የሚሰራጭ ፕሮግራም ማለት ነው፡፡
በሃገራችን ኢትዮጵያም በኤፍ.ኤም ራዲዮ እና የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለቁጥር አታካች የሆኑ የሶፕ ኦፔራ ይዘት ያላቸው ፊልሞችና ድራማዎች በቴሌቪዥንና በራዲዮ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም በሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ ውስጥ በዚህ አመት ብቻ ለሰባት የግል ኤፍ.ኤም የራዲዮ ጣቢያዎች ፍቃድ የሚሰጥ ሲሆን  ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ደግሞ ለ20 የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ ሃላፊው ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የግል ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ለማቋቋም ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ከወዲሁ ተመልካችን የሚስቡ፣ የሚማርኩና የሚያስተምሩ ተከታታይ ፊልምና  ድራማዎችን እያዘጋጁ እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ የማስታወቂያ ገቢ ከማመንጨት ጋር ተያይዞ ፊልም እና ድራማዎቹ የሚያስገኙት ጥቅም የማያከራክር ቢሆንም ፊልሞቹ ለድራማና ፊልም አላማ ብቻ ከመሰራታቸውና ከመብዛታቸው ጋር ተያይዞ በአሜሪካን አገር ያደረሱትን ጉዳት በተመለከተ “TOUGH TALK about TOUGH ISSUES” በሚል ርእስ ቦብ ላርሰን የተባሉ ጸሃፊ፤ስለ SOAP OPERA የጠቃቀሷቸውን ጉዳዮች ለዜጋም ሆነ ለባለ ድርሻ አካላት የሚያስተምር ከሆነ ብዬ ላነሳሳው ፈቀድኩ፡፡
ታሪኩ ካቆምኩበት ቦታ ቀጠለና እንዲህ ፈሰሰ፡-
“ይህ አይነቱ ውስብስብ የወሲብ ሴራ በሶፕ ኦፔራ ላይ የተለመደ ትእይንት ነው፡፡ ወሲብ ላይ ያጠነጠኑ ትእይንቶችን ስንፈትሻቸው ሶፕ ኦፔራ አንዳችም ለዜጋም ሆነ ለትውልድ ጠብ የሚያደርገው ነገር የለም” ይላሉ-፤ፀሀፊው፡፡ ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ ያካሄደው ጥናት እንዳረጋገጠው፤ በሶፕ ኦፔራ ውስጥ ወሲባዊ ድርጊቶች በአንድ ሰዓት ውስጥ 6.58 ጊዜ የሚደጋገሙ ትእይንቶችን ለተመልካች ያቀርባሉ ይላል፡፡ ዶ/ር ብራድሊ ግሪንበርግ የተባለ ተመራማሪ በሚቺጋን ስቴት ዩንቨርሲቲ ባካሄደው ጥናት እንዳሰፈረው፤ ወሲባዊ ግንኙነቱን ሲፈጸም የሚያሳዩት ትእይንቶች ባብዛኛው ባገቡና በቅድመ ጋብቻ ጎዳና ላይ ባሉ ሰዎች ነው ይላሉ፡፡ 49% ፈጻሚዎች ፍቅረኛሞች፣ 29% ደግሞ ተያይተው በማያውቁ ሰዎች የሚፈጸም ወሲብ ትእይንት ሲሆን፤ ባለ ትዳር የሆኑ ፍቅረኛሞች የሚፈጽሙት የወሲብ ትእይንት ግን 6% ብቻ ናቸው ይላሉ፡፡ ሶፕ ኦፔራ ተመልካቾች ሳይወዱ በግዳቸው የሚደርሱበት ማጠቃለያ ነገር ቢኖር ይላሉ ተመራማሪው፤ “ባለትዳር ተጣማሪዎች ፍቅርን ለመፈጸምና ነጻ ወሲብን ማድረግ እንደማይችሉ ፤ በተቃራኒው ደግሞ ያላገቡ ሰዎች ወሲብን ሁልጊዜ በደስታ ነጻ ሆነው የሚያከናውኑት ድርጊት ነው ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
ሶፕ ኦፔራዎች የሚያሳዩት በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚፈጸሙ የወሲብ ትእይንቶችን ብቻ ነው ብላችሁ ደምድማችሁ ከሆነ በድጋሚ ማሰብ አለባችሁ ይላሉ ተማራማሪው፡፡ በቅርቡ ዶና ፔስኮው የተባለች አክትረስ ነውረኛ የተባለውን የቴሌቪዥን ሶፕ ኦፔራ ትእይንት ይግረማችሁ ብላ የLesbians (የሴት ግብረ ሰዶማዊ) ገጸባህሪ በመጫወት ነውሩን አሻሽላዋለች፡፡  “All My Children” የሚለው ፊልም አምራቾች የሰው ልጅ ኢ-ተፈጥሮአዊ የሆኑ ትእይንቶችን በማየት የሚሰማውን ትክክለኛ ሃዘን በማጣመም ጉዳዩን በበጎ መልኩ ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ ብሪያን ፍሮንስ የተባሉ የNBC ም/ፕሬዝደንት ስለ ሶፕ ኦፔራ ፊልሞች ሲናገሩ ፤ “ሶፕ ኦፔራ ፊልሞች በቅርቡ ተከታታይና በተደጋጋሚ የሚታዩ ግብረሰዶማዊ ትእይንቶች ይኖሩታል፡፡” ብለዋል፡፡
“Loving” የሚለው ሶፕ ኦፔራ ደራሲ ዳፍ ማርላንድ፤ “በግልጽ የሚታይ ግብረሰዶማዊ የፍቅር ታሪኮችን ይዤ ለመቅረብ አቅጃለሁ ብሏል፡፡ ማርላንድ ጨምሮ እንደገለጸው፤”ፊልሙ የሚታየው ተመልካቾች ግብረሰዶማዊነትን እንዲማሩ ሳይሆን እንደ እለት ተእለት የኑሮ ሁኔታ እንዲረዱት ለማድረግ ነው” ይላል፡፡ የሶፕ ኦፔራ ጸሃፊዎችና አምራቾች በግልጽ በሚነፉት ጉራ፣”ግልጽ እርቃንና ግብረሰዶማዊ ትእይንቶች በነጻነት የሚታዩት ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ቁጣዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲናዱ ነው፡፡” ይላሉ፡፡  
በእርግጥ ወሲባዊ የሶፕ ኦፔራ አደገኛ እንደምታው የፊልሙ ሱስ ድንገተኛ የወሲብ ስሜት ፈንቅሎ እንዲወጣ በማነሳሳት አድርግ- እመን (Make- Believe) የሚለውን ተግባር ለመፈጸም ወደ እውነታ የሚያስጠጋ መሆኑ ሲሆን ልጓም አልባ የወሲብ ዝሙት ለወራት ሲመለከቱ የቆዩ ለትዳራቸው ታማኝ የሚባሉና ፈጽሞ የማይጠረጠሩ ሴቶች ሳይቀር ሳያውቁት ለማመንዘር ፍቃደኛ ምልምል ሆነው ይገኛሉ፡፡ ለሴቲቱ በፊልሙ ላይ ውብ፣ ፈርጣማና የወሲብ ሊቅ ሆኖ የሚታየው ገጸ ባህሪ ፤ ከፈዘዘውና ፍላጎት አልባ ከሆነው ባሏ ልቆ ይታያታል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከጋብቻ ውጪ ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም ይገባዋል ወደሚል ማጠቃለያ ይወስዳቸዋል፡፡ የሶፕ ኦፔራ ሱስ ሴቶች ስለትዳራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ በማስገደድ በትዳር ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉትን እምነት ማጣትና ፍቺን ሳይፈሩ በድርጊቸው እንዲገፉበት ያበረታታቸዋል፡፡ ይላል ጸሀፊው ቦብ ላርሰን፡፡የሳይንስ ፊክሽን ኹነቶች፣ መውጫ መግቢያው የማይታወቅ የፍቅር ሴራ፣ ትንግርታዊ የሚመስሉ የህልም አለም ክስተቶችና የተጋነነ፣  የተከለከለ፣ ውለታ ቢስ፣ የታወከ ፍቅርን የማሳየት ይዘት ካለው እሱ ፊልም ሶፕ ኦፔራ ነው፡፡ እለታዊ አርእስቶች- ውርጃ፣ የቀዘቀዘ ወሲባዊ ስሜት፣ ህጋዊ ያልሆነ ግንኙነት፣ የትዳር ንትርክ ሶፕ..... ኦፔራ ውስጥ አይጠፉም፡፡ ሴቶች እርጉሞች ናቸው፤ወንዶች ደግሞ ለጥቅማቸው ነዋሪዎች፡፡ ከአምስት በላይ አሳሳቢ ጉዳዮች የገጠመው ቤተሰብ ታውቁ ይሆን? 4 ውርጃዎች፣ 3 ወሲባዊ ድሪያዎች፣ 2 ራስን ማጥፋቶች፣ 1 ቢያንስ በሳምንት ውስጥ የቤተሰብ አባል ላይ የሚፈጸም የወሲብ ጥቃት፡፡ እውን እያንዳንዱ አሜሪካዊ ቤተሰብ ይህን ይመስላል? ኢ-ሞራላዊነት ነግሷል፣ እንዲህ ያለ ቲቪ ሾው ተመልካቹን አደንዝዞት ይገኛል፡፡ ባጠቃላይ ሶፕ ኦፔራ ወራዳ ጠባይን የሚያበረታታ፣ ሰይጣናዊ ድርጊት በማህበረሰቡ ውስጥ አስርጿል፡፡የሶፕ ኦፔራን በመመልከት የደነዘዙት፣ ቡና ፉት እያሉ ፈታ እያሉ የሚውሉ የቤት እመቤቶች አይምሰላችሁ፡፡ ብዙዎቹ ተመልካቾች ወጣትና የተማሩ ሴቶች ናቸው፡፡
የኮሌጅ ተማሪዎችና እውቅ ባለሙያዎች ሶፕ ኦፔራን ይመለከታሉ፡፡ የተመልካቹን ውስጣዊ ፍላጎት ለማሟላት ትርክት ውስጥ የተማሩ ሴቶች፣ አናሳ የሚባሉ ሰዎች፣ የፋብሪካ የጉልበት ሰራተኞች እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ህገ ወጥ ግንኙነት፣ ማመንዘር፣ አስገድዶ መድፈር፣ በቤተሰብ አባል ላይ የሚፈጸም ወሲብ፣ ስም ማጥፋት፣ ስርቆት፣ግድያ --- እነዚህን ሁሉ የያዘ ሶፕ ኦፔራን መሸጥ ኢ-ሞራላዊ ነው ይላሉ ጸሃፊው፡፡
በአማካይ ሳምንታዊ ፊልሞቹን ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ያዩታል፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ከ18-49 እድሜ ያላቸው ሴቶች ናቸው፡፡ ይህን ያህል ተመልካች ማለት ለቲቪ ኔትወርክ ትልቅ ቢዝነስ ነው፡፡
ABC 40% የሚሆነውን ትርፉን የሚያገኘው ከሶፕ ኦፔራ ፊልሞች ነው፡፡ 13ቱ በዋና ዋናዎቹ ኔትወርኮች ለ55 ሰዓታት የሚተላለፉ ሶፕ ኦፔራዎች እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ ከማስታወቂያ ብቻ ያገኛሉ፡፡ የ30 ሰከንድ ማስታወቂያ 26,000 $ ገቢ ያመነጫል እንደ ማለት፡፡
 አንድ ኢሞራላዊ ተረቶችን መሰረት ያደረገ ትልቅ ቢዝነስ የማህበረሰብን የወል እሴት የማያፈርስ ይዘት ይኖረው ይሆን? “General Hospital” የሚል ሶፕ ኦፔራ ደራሲ ግሎሪያ ሞንቴ እንዳለችው፤ “ሶፕ ኦፔራ የተመልካቾችንንና የማህበረሰቡን ፍላጎት ለሟሟላት ጥረት ያደርጋል ብላለች፡፡” ነገር ግን በነውጠኛ ጎረምሶች አስገድዶ መደፈር የተፈጸመባት ልጁ ጋር ወሲብ ለመፈጸም የሚዳዳ አባት እንዲሁም የኑሮ አጋሩን በመኪና አደጋ ለመግደል የሚያሴር ቤተሰብ እንዲኖረው የሚፈልግ ማን ይሆን? በፍጹም፤ይላሉ ጸሃፊው፡፡ ሞራሊቲንና ጤናማ አስተሳሰብን ከማጎልበት አንጻር ሶፕ ኦፔራ ያበረከተው ትንሽ ነው፡፡ ዴቪድ ፊሊፕስ የተባለ የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር ስለ ሶፕ ኦፔራ ጥናት አካሂጄ ደረስኩበት ያለው መረጃ እንደሚያስረዳው፤ በሶፕ ኦፔራ ላይ ያለው ገጸ ባህሪ ራሱን በማጥፋቱ ምክንያት በማህበረሰቡ ውስጥ ራስን የማጥፋት ሙከራ በ3% ጨምሯል፡፡ ህይወት ቀጣፊ የመኪና አደጋዎች 14% ጨምረዋል፡፡
 ባጠቃላይ እንደ ፐሮፌሰር ፊሊፕስ ገለጻ ከሆነ፣ ነውጠኛ አስመሳይ የቲቪ ታሪኮችን ተመልክተህ ለመሞት ሙከራ እንድታደርግና ገዳይ አደጋዎችን ለመፈጸም የሚገፋፉ ናቸው፡፡
ሶፕ ኦፔራን አዘውትረው የሚመለከቱ ሰዎች ከፍተኛ ድብርት፣ ፍርሀት፣ ግብ አልበኝነትና ርህራሄ አልባ ባህሪያትን ያሳያሉ፡፡ ሶፕ ኦፔራ መመልከት ለሴቶች ግለሰባዊ ክብር የሚያበረክተው አንዳችም ነገር የለም፡፡ አብዛኞቹ ሴት ተመልካቾች በቲቪ ስክሪኑ ላይ እንደምትታየው ተዋናይት ቆንጆ አይደሉም ወይም ውብ አለባበስ አይለብሱም፡፡
 የሶፕ ኦፔራ ገጸ ባህሪያት ብዙ ጊዜ የናጠጠ ሃብታም ሆነው በሁሉም አይነት ተግባራት ላይ ወሰን የሌለው ሀብትና  ጉልበታቸውን የሚያውሉ ናቸው፡፡
አልፎ አልፎ ብቻ ሳህን የሚያጥቡና ቤት የሚጠርጉ ገጸ ባህሪዎች ልታይ ትችላለህ፡፡ አስተዋይ የቤተሰብ ሃላፊነትና አርአያነት ያለው ወላጅነት ተረስተዋል፡፡ ሁሉም ሰው በስራ የተወጠረና ለልጆቹ በቂ ግዜ የማይሰጥ ነው፡፡ ሶፕ ኦፔራ ልጆች አዎንታዊ እሴቶችን እንዲኖራቸውና አምራች ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ አይመክርም፡፡
ሶፕ ኦፔራ ላይ የሚስተዋሉ ኢሞራላዊ ትእይንቶች ቢኖሩበትም ብዙ የቤት እመቤቶች ግን የሚመለከቱባቸው የራሳቸው ምክንያት እንዳለቸው ይናገራሉ፡፡
አንዳንዶቹ ትርፍ ጊዜ ሲኖራቸው፣ ብቸኝነትን ለመርሳት ወይም ከአሰልቺው የቤት ውስጥ ሃላፊነት ለማምለጥ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ሶፕ ኦፔራ የሌሎችን ሰዎች የወሲብና የግል ህይወት በግልጽ የማቅረብ ዘዴው ተስበው የሚመለከቱ ናቸው፡፡
 በሂደቱም ኢሞራላዊ ባሪያትን ተላብሰው ይቀራሉ፡፡በእኛም ሃገር የሶፕ ኦፔራ ባህሪ ያላቸው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች በተሟሟቀው የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ምን ያህል ወላጆች ነን ቲቪ የመመልከቻ ግልጽ ፕሮግራም ያለን? በፕሮግራም ሲታይስ የትኛው ፊልም ነው ከልጆች ጋር የሚታየው? የትኛውስ ነው ለልጆች የሚከለከለው? በትርፍ ጊዜያችንስ ቴሌቪዥን ብቻ ነው መመልከት ያለብን ወይ? ለምን መጽሀፍ አናነብም? ከ13 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት እንዳያዩት የተከለከለ ፊልም ሲባል ምን ማለት ነው? በየትኛው የነጠረ መመዘኛስ ነው ፊልሞቹ የሚመዘኑት? ብዙ ጊዜ እንዳስተዋልኩት ደም መፋሰስና ግድያ ያለባቸው ፊልሞችን እንጂ ከላይ በዝርዝር እንዳየነው ውርጃ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የወሲብ ቅሌት፣ስርቆት ዝሙትና የመሳሰሉት ትእይንቶችን ያካተተ ፊልም ሙሉ ቤተሰብ ተሰብስቦ የሚያያቸው ናቸው፡፡
የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች እነዚህ ፊልሞች በማህበረሰቡ ህይወት ላይ የሚፈጥሩትን ተጽእኖዎች ለመፈተሽና ጥናት ለማድረግ ሞክረው ይሆን? ፋይዳው፣ ጉዳቱ ምንድን ነው? ጥናት ተኮር የሆነውን የአሜሪካውያን አኗኗር ለማሳየት የሞከርኩት አንዳች ትምህርት ብናገኝበት ብዬ ነው፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡


Read 2527 times