Saturday, 17 October 2015 09:47

በደሌ ቢራ እናቶች አልጋ ላይ እንዲወልዱ አደረገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      ወ/ሮ ካሙላ ፊጣ ሦስት ልጆቿን በሰላም ነው የተገላገለችው፤ ሁለቱን በቤት አንዱን በጤና ጣቢያ፡፡ አራተኛው ፅንስ ግን ለመወለድ አልታደለም፡፡ 4 ወር ሲሆነው በሆዷ ሞቶ ደም ስለፈሰሳት ወ/ሮ ካሚላ ወደ ሰከቻ ክሊኒክ ተወሰደች፡፡ የክሊኒኩ ባለሙያዎች አይተው ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ፣ ሪፈር ጽፈው፣ አምቡላንስ ጠርተው ወደ በደሌ ሆስፒታል ላኳት፡፡ የሆስፒታሉ ባለሙያዎችም በሆዷ የሞተውን ሽል በመሳሪያ አውጥተውላት እፎይቷ ሰጧት፡፡
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ያማቱ ናስር፤ ወደ በደሌ ሆስፒታል የመጣችው አራተኛ ልጇን ለመገላገል ነው፡፡ ወ/ሮ ያማቱ እርግዝናዋን በአካባቢዋ ባለ ጤና ጣቢያ ስትከታተል ነበር፡፡ ምጥ ስለመጣባት ወደ ባሌ ከተማ ሆስፒታል መጥታ አልጋ ላይ ሆና መውለጃዋን እየተጠባበቀች ነው፡፡ በሆስፒታሉ የማዋለጃና የመቆያ ክፍሎች ብዙ እናቶች አሉ፡፡
ሁሉም ወላዶች አልጋ ላይ ተኝተዋል፡፡ በደሌ ቢራ ምስጋና ይግባውና ሁሉም እናቶች አልጋ ላይ መውለድ ችለዋል፤ ብለዋል - የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ወርቅነህ፡፡
አቶ ታመነ መንግሥት በበደሌ ከተማ ያሰራው ሆስፒታል 64 አልጋዎች እንዳሉት ጠቅሰው፣ የሆስፒታሉ አስተዳደር 20 ክፍሎች ጨምሮበት፣ የአልጋዎቹ ቁጥር 84 መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሆስፒታሉ አገልግሎት የሚሰጠው በ10 ወረዳ ለሚገኙ 710, 900 ሰዎች ስለሆነ በቂ አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት 1,652 እናቶች ናቸው በሆስፒታሉ የተገላገሉት፡፡
በአማካይ በየቀኑ 5 ሴቶች ይወልዱ ነበር ማለት ነው፡፡ ሁለትና ሦስት የሚወለድበት ቀን ቢኖርም 15 ሴቶች የሚወልዱበት ጊዜም አለ፡፡ አልጋ ሲጠፋ መሬት ላይ የሚወልዱ እናቶች ነበሩ፡፡ አሁን ማስፋፊያው ከተሰራ በኋላ መሬት የምትወልድ እናት የለችም፡፡ እናቶችን ከመሬት አንስተን አልጋ ላይ ማስተኛት ችለናል ብለዋል፡፡
በደሌ ቢራ አ.ማና ሄኒከን አፍሪካ ፋውንዴሽን በበደሌ ከተማ ሆስፒታል ውስጥ በ5.6 ሚሊዮን ብር ያሰሩት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ባለፈው ሳምንት የተመረቀ ሲሆን 12 አዲስ የእናቶች ማዋለጃና 24 የሕፃናት ማቆያ ክፍሎች ያላቸው ሁለት ብሎኮች በ3.1 ሚሊዮን ብር አስገንብቷል፡፡ ለህክምናና ለላብራቶሪ መሳሪያዎች፣ ለጨቅላ ህፃናት ማቆያ ኢንኩቤተር፣ ለሥልጠና፣ … 2.5 ሚሊዮን ማውጣቱን አቶ ታመነ አስረድተዋል፡፡ ቀደም ሲል ከክፍሎች ጥበት የተነሳ የቤተሰብ ምጣኔ፣ ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ፣ ክትባትና ከወሊድ በኋላ ክብካቤ የሚሰጠው በአንድ ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ የሄይኒከን ቢራ አ.ማ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚ/ር ጌሪት ቫን ሉ፤ “የማስፋፊያው ፕሮጀክት ለእናቶችና ከ5 ዓመት በታች ላሉ ህፃናት፣ የተሻለና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል እናምናለን” ብለዋል፡፡
ሚ/ር ቫን ሉ ባለፉት 4 ዓመታት ፋብሪካውን ለማዘመንና ደረጃውን ከፍ ለማድረግ 100 ሚሊዮን ብር ማውጣታቸውን ጠቅሰው፤ ለአንድ ሄክቶ ሊትር ቢራ ጠመቃ ያስፈልግ የነበረውን 11 ሊትር ውሃ ወደ 5.5 ሄክቶ ሊትር ማውረዳቸውን እንዲሁም ለቢራ ጠመቃ የተጠቀሙበትን ውሃ ለማጣራትና ከብክለት ነፃ ለማድረግ፣ 23 ሚሊዮን ብር ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ በደሌ ቢራ በቀረጥ ለመንግስት የሚያስገባው ገቢ በአራት እጥፍ ያህል ማደጉን የጠቀሱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ በ2000 ዓ.ም 71.9 ሚሊዮን የነበረው ታክስ፤ በ2006 ዓ.ም 280.9 ሚሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ለቢራ ጠመቃ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ገብስ 48 ከመቶ ከሀገር ውስጥ እንደሚያገኙ ጠቅሰው፣ በቀጣይ ዓመታት ከውጭ የሚመጣውን 20ሺህ ሜትሪክ ቶን ገብስ በአገር ውስጥ ለማምረት፣ ከ20ሺህ ገበሬዎች ጋር እየሰሩ መሆኑን ሚ/ር ጌሪት ቫሉ አስረድተዋል፡፡

Read 2680 times