Friday, 11 September 2015 09:25

የዓመቱ አነጋጋሪና አሳዛኝ ክስተቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

       አሮጌ ብለን የምንሸኘው የ2007 ዓ.ም በርካታ አነጋጋሪ፣ አሳዛኝና አስደሳች ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ ጥቂቶቹን እንቃኛቸው፡፡
“ሃና ላላንጐ…”
በአመቱ ብዙ ኢትዮጵያውንን ካሳዘኑ አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የ16 ዓመቱ ወጣት ሃና ላላንጎ ላይ የተፈፀመው ዘግናኝ ጥቃት ነው፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ሃና፣ በአምስት ወጣቶች ተደፍራ ህይወቷ አልፏል፡፡ ደፋሪዎቹም፣ ከ17 አመት እስከ እድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ድርጊቱ በጥቅምትና በህዳር ወር አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በበርካታ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ተዘግቧል፡፡
እልቂትና የስደተኞች መከራ
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በያሉበት፤ በሀገር ቤት ያሉትም በሃዘንና በቁጭት የተንገበገቡበት መርዶ የተሰማው በሚያዚያ ወር ነው፡፡ 30 ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ አሰቃቂ ግድያና ጭፍጨፋ የተፈፀመው፣ ‹አይኤስ› በተሰኘው አሸባሪ ቡድን ነው፤ በሊቢያ፡፡
የሰቆቃ ጊዜ ነበር፡፡ የስደት መከራ ሳያንስ በሰው ልጅ ዘንድ ለማመን የሚከብድ ጭካኔ ተፈፀመባቸው፡፡ በዚያው  ሰሞን 900 ገደማ አፍሪካውያን ስደተኞችን ጭና፣ ከሊቢያ ወደ ጣሊያን የምትጓዝ ጀልባ ሰጥማ፣ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል፡፡ አዲስ አድማስ ይህንን አሳዛኝ ክስተት በመከታተልና የሟች ቤተሰቦችንና ወዳጆችን በማነጋገር ተገቢውን የዘገባ ሽፋን ሰጥታለች፡፡ 17 ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ህይወታቸውን በዚህ አደጋ አጥተዋል፡፡
በወርሃ ሚያዚያ፣ በሃይማኖት አክራሪነት የሚፈፀም ዘግናኝ ድርጊትንና በስደት ሳቢያ የሚከሰት አሳዛኝ አደጋን ብቻ ያየንበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የዘረኝነት ሰለባ የሆኑበትም ወር ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ የውጭ ዜጐችን አላማ ያደረገ ዘረኝነትን (ዜኖፎቢያን) የሚያራግቡ ቡድኖች በኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ላይ የጥቃት ዘመቻ አካሂደዋል፡፡ 3 ኢትዮጵያውያን በዚሁ ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና የበርካቶች ንብረት ወድሞ ከኑሮ መፈናቀላቸው ተዘግቧል፡፡
በአመቱ የኢትዮጵያውያን የስደት ህይወት በአሠቃቂ ክስተቶች የተሞላ ሆኖ አልፏል፡፡
የድርቅ አደጋ
እያሰለሰለ በሚከሰተውና ኤልኒኖ በተሰኘው አለማቀፍ አየር ፀባይ መዛባት ሳቢያ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተው የዝናብ እጥረት የሚሊየኖችን ኑሮ አናግቷል፡፡ የተዘሩት እህል በቡቃያነቱ የጠወለገባቸው፣ በመኖ እጦት የቤት እንስሳት የሞቱባቸው 4.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል፡፡ የተጎጂዎች ቁጥር እስከ 6 ሚሊዮን ይደርሳል የሚሉ የእርዳታ ድርጅቶችም አሉ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጉብኝት
ባራክ ኦባማ፣ በኢትዮጵያና በአሜሪካ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን የጎበኙ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ድጋፍና ተቃውሞንም ያስተናገደ ነበር፡፡ ከአመት በፊት ከታሰሩ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች መካከል 5ቱ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁት በፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዋዜማ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ ከእስር የተፈታችውም በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ ትችትና ድጋፍ ባስተናገደው ጉብኝት ላይ፣ ባራክ ኦባማ ያስተላለፉት መልእክት አንድ ወጥ አልነበረም፡፡ የፓርላማ ምርጫ በሰላም መካሄዱን ደግፈው፣ ነገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የጋዜጠኞች እስርን ወይም ወከባን ማስቀረት፣ የፖለቲካ ነፃነትን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዋና ትኩረታቸው ግን፣ የኢትዮጵያ ጦር አሸባሪነትን የመዋጋት ብቃት አለው በሚለው ነጥብ ላይ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአባታቸው ሃገር ኬንያንም ጐብኝተዋል፡፡
የግንቦቱ ምርጫ
በአመቱ አነጋጋሪ የነበረው ምርጫ፣ ከዝግጅቱ እስከ ውጤቱ ድረስ አከራካሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፓርላማና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን መቶ በመቶ፣ ማሸነፋቸው አንዱ አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ከምርጫው ቀደም ብሎ በተለይ በአንድነት ፓርቲ መሪዎች መካከል እንዲሁም የመኢአድ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ላይ፣ ምርጫ ቦርድ ያሳለፋቸው ውሣኔዎችም በርካታ ትችቶችን ያስከተሉና በማህበራዊ የሚዲያ መድረኮች ያከራከሩ ጉዳዮች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡
የመቀሌው የኢህአዴግ ጉባኤ
ከመቀሌው የኢህአዴግ ጉባኤ ቀደም ብሎ፣ አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች የየራሳቸውን ጉባኤ አድርገው በኃላፊነት ላይ የነበሩ መሪዎችን በዚያው እንዲቀጥሉ ወስነዋል፡፡ በኢኮኖሚ መስክ ኢንዱስትሪና ኤክስፖርት አለማደጋቸው አሳሳቢ ነው፤ በፖለቲካው መስክ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች አሳሳቢ ናቸው፡፡ የሚሉ ሃሳቦች ተደጋግመው በተነሱበት የመቀሌው የኢህአዴግ ጉባኤ፣ የዘረኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት አደጋዎችም አስጊ እንደሆነ መክረንበታል ብለዋል የድርጅቱ ቃል አቀባይ፡፡  ጉባኤው የተወሰኑ ነባር አመራሮቹን ከስራ አስፈፃሚነት አሰናብቷል፡፡
ተመርቆ የቀረው የባቡር ፕሮጀክት
የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ያቃልላል ተብሎ ከ3 አመት በፊት የተጀመረው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተገኙበት ተመርቆ ወደ ሙከራ ስራ መግባቱን ያበሰረው በየካቲት ወር ነው፡፡ ከ3 ወር ሙከራ በኋላ የህዝብ አገልግሎት ይጀምራል ቢባልም፣ በኤሌክትሪክ ሃይል እጦት ሳቢያ፣ ሙከራውን ማጠናቀቅ ተስኖታል፡፡ ምናልባት በአዲሱ አመት ስራ ይጀምራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የበርበሬና የምስር ዋጋ
መፍትሄ ከናፈቃቸው የዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የስኳርና የመሳሰሉ እጥረቶች በተጨማሪ፣ የመረጋጋት አዝማሚያ የነበረው የዋጋ ንረት፤ ከዓመቱ አጋማሽ ወዲህ ከ10% በላይ እያሻቀበ መምጣቱ፣ አነጋጋሪ ሆኖ ከርሟል፡፡ የበርበሬና የምስር ዋጋ በእጅጉ መናሩን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በርበሬ ኪሎ እስከ 180 ብር የተሸጠበትና ምስር በኪሎ እስከ 70 ብር የደረሰበት ዓመት ነው፡፡ መንግስት ኋላ ላይ በርበሬ በድብቅ ወደ ውጪ እየተላከ መሆኑን አረጋግጫለሁ፤ እርምጃም እወስዳለሁ ሲል ቢደመጥም፤ የበርበሬ ዋጋ ከተሰቀለበት ሳይወርድ አይቀመሴ ሆኖ ወደ አዲሱ አመት ተሻግሯል፡፡
የቢራ አብዮት
በ2007 መግቢያ ላይ፣ ሄኒከን ኩባንያ “ዋሊያ ቢራ መልካም አዲስ አመት” በሚል፣ አዲስ የቢራ ምርቱን ሲያስተዋውቅ፤ አቃቂ አካባቢ የተገነባው ፋብሪካውም በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡ በአመቱ የቢራ ገበያውን የተቀላቀሉት ራያ ቢራ እና ሐበሻ ቢራ የአብዮቱ አካል ሆነዋል፡፡ አመቱንም ከቀደሙት አመታት በተለየ የቢራ አብዮት የተቀጣጠለበት ዓመት ያደርገዋል፡፡ የሜታ ቢራ ባለቤት የፈረንሳዩ ኩባንያ ዲያጆ፣ ‹ዘመን› የተሰኘ ቢራ ያስተዋወቀ ሲሆን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ አምራች ቢጂአይ እንዲሁም ዳሽን ቢራ በማስፋፊያና በማስተዋወቁ ፕሮጀክት የተጠመዱበት ዓመት ሆኗል፡፡

Read 5090 times