Saturday, 05 September 2015 09:53

“...ዝምድና የሚታመንበት ጊዜ አይደለም...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

አለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ቁጥራቸው ወደ 20%  የሚጠጋ ሴቶች እንዲሁም 5-10%  የሚደርሱ ወንዶች በልጅነት እድሜያቸው የፆታ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡  በፈረንጆቹ በ2010 በ The United Nations Population Fund is an international development agency (UNFPA) እና Population Council የጋራ ትብብር በሀገራችን በተደረገ ጥናት አስገድዶ መድፈር ተፈፅሞባቸው የህክምና አገልግሎት ያገኙ ሴቶች ቁጥር በገጠር 1.9% እንዲሁም በከተማ 5.7%  ብቻ ናቸው፡፡ የሕግ ድጋፍ ያገኙ ደግሞ በገጠር 0.2%  በከተማ ደግሞ 7.4%  ሲሆን የስነልቦና ባለሙያ ድጋፍ ወይም የምክር አገልግሎት ያገኙት ደግሞ በከተማ 1.9%  እንዲሁም በገጠር 1.1%  እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡2013 በአለም የጤና ድርጅት በተደረገ ጥናት በአለም ዙሪያ የሚገኙ ቁጥራቸው 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች የዚህ ችግር ተጠቂዎች ናቸው፡፡
ባለፈው እትም በጎንደር ሆስፒታል ውስጥ በኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የተቋቋመውን ሞዴል ክሊኒክ የስራ እንቅስቃሴ ለመመልከት በተገኘንበት ወቅት በጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶችን እና የህግ እና የህክምና ባለሙያን ሀሳብ አስነብበናችሁዋል፡፡ በዚህ እትም አንዲት የአስራ አንድ አመት ሕጻን አባት እና የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያን እንዲሁም ከተለያዩ መረጃዎች በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን እውነታ እናስነብባችሁዋለን፡፡
//////////////
ጥ/    የተገናኘነው በጎንደር ሆስፒታል በሞዴል ክሊኒክ ነው፡፡ ለምን?
መ/    በጎንደር ሆስፒታል ውስጥ ወደሚገኘው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሴቶች ከሚታከሙበት ክሊኒክ የ11 አመት ሕጻን ልጄን ይዤ የተገኘ ሁበት ምክንያት ልጄ ጥቃት ስለደረሰባት ነው፡፡ ልጅትዋ እናትዋ ስለሞተችባት የምትኖረው ከእኔና ታናሽ ወንድምዋ እንዲሁም ዘመድ ከሆነ ልጅ ጋር ነው፡፡ እኔ     ልጆቼን ለማሳደግ በማደርገው ሩጫ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ አልገኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ያለውን ክፍተት ተጠቅሞ እቤቴ እማኖረው ዘመዴ ጥቃቱን በቤት ፈጸመባት፡፡
ጥ/    ልጅቷ ተገድዳ ስትደፈር የተመለከተ ሰው ነበር? ወይንስ?
መ/    ልጁ አስገድዶ በሚደፍራት ጊዜ ማንም አልደረሰላትም፡፡ እሱዋም እናትዋ ስለሞተች መደፈሬን አባቴ ቢሰማ እሱም ይጎዳብኛል በማለት አርቃ በማሰብዋ ከአንድ ቀን በላይ ዝም ብላ ነው የተኛቸው፡፡ በሁዋላም ምክንያትዋ ምን እንደሆነ ስጠይቃት     በቃ ...እገሌ     እንዲህ አድርጎኝ ነው ብላ ነገረችኝ፡፡ እኔም ወዲያውኑ ወደ ሕክምናና ወደ ህግ     መጥቻለሁ፡፡
ጥ/    የሕክምናው ውጤት እንዴት ነው?
መ/    የህክምናው ውጤት መደፈሩዋን ተደፍራለች፡፡ ሌላውን ሕክምና ግን በአስቸኳይ እየተደረገላት ነው፡፡ የደፈራት ልጅ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ልጅቷም በቫይረሱ እንዳትያዝ ሐኪሞቹ የተቻለውን ሁሉ እያደረጉላት ነው፡፡ ልጁም     በህግ ቁጥጥር ስራ ውሎአል፡፡
ጥ/    ለህብረተሰቡ የምታስተላልፈው መልእክት አለ?
መ/    እኔ የማስተላልፈው መልእክት ...ሴት ልጆችን በሚመለከት ዘመድ ምናምን እያሉ ማመን አያስፈልግም፡፡ በቃ፡፡ ዝምድና የሚታመንበት ጊዜ አይደለም፡፡ ሴት ልጆች ገና አፋቸውን ሲፈቱ ጀምሮ ሁኔታውን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወንዶች የሚሰሩትን የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ወላጆች እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ክትትሉን አጠንክሮ እንደነዚህ ያሉ አጥፊዎችን ወደ ህግ እንዲቀርቡ በማድረጉ በኩል አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ እመክራለሁ፡፡
/////////////
የፆታ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ለአጭር ወይም ለእረዥም ግዜ የሚቆይ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡
ከእነዚህም መካከል፡-
ጥቃቱ የደረሰባቸው ግለሰቦች በሌሎች ላይ ግድያ ሊፈፅሙ ወይም እራሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡
ከሀይል ድርጊቱ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች ሊደርስባቸው ይችላል፡፡
በአስገድዶ መድፈር ምክንያት ከሚፈጠር ያልተፈለገ እርግዝና ጋር በተያዘዘ ለውርጃ እንዲሁም ኤችአይቪን ጨምሮ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች እና የማህፀን ህመሞች ይዳረጋሉ፡፡
በጎንደር የነበረን ቆይታ ማጠቃለያ የሚሆነው ከጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስቱ ዶ/ር ጌታቸው ሽፈራው ጋር ያደረግነው ውይይት ነው፡፡
ዶ/ር እንደሚሉት፡-
“...ጎንደር ውስጥ የሴቶች ጥቃት በተለይም መደፈርን በሚመለከት ድርጊቱ አለ ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከሆስፒታሉ ጋር በመነጋገር ይህንን ሞዴል ክሊኒክ የከፈተው፡፡ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሴት ልጆች በቀን ውስጥ ሁለት ሶስት ያህል የሚመጡ ሲሆን ተገደው የተደፈሩት በወር እስከ ሀያ እና ሰላሳ በሚደርስ ቁጥር ለሕክምና ይቀርባሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ቁጥር በከተማዋ ወይንም በአካባቢው በጠቅላላ የሚፈጸመው ይህ ነው በሚል ለማመላከት አይረዳም፡፡ ወደ ህብረተሰቡ ስንዘልቅ ጉዳዩን ወደ ህግ ወይንም ሕክምና ሳያደርሱ በቤታቸው ደብቀው በሽምግልና የሚደራደሩትን ሳይጨምር ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ችግሩን ለፍትሕ ወይንም ለሕክምና የማያቀርቡት ሰዎችን ምክንያት ስንመረምር ከእውቀት ማነስ ወይንም ከፍርሀት አለዚያም የራስን ክብር ከመጠበቅ አንጻር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡”
ዶ/ር አክለውም ስለአካባቢው ልምድ ሲመሰክሩ “...በጎንደርም ይሁን በብዙ አካባቢዎች አስገድዶ መድፈር ያልተለመደ ድርጊት የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ወንጀሉ እየተለመደ እና እየሰፋ በመምጣቱ የህብረተሰቡንም የህግ አስፈጻሚ አካላትንም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በእርግጥ በቀድሞው ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የለም የሚያሰኝ ነገርም የለም፡፡ ምክንያቱም እንደአሁኑ በግልጽ ጉዳቱን ለመናገርና ወደ ፍትህ እንዲሁም የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ወደ ጤና ተቋም የመምጣት ልምድ ባልነበረበት ወቅት ተዳፍነው የቀሩ ብዙ ወንጀሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አይጠረጠርም፡፡” ብለዋል፡፡   
በስተመጨረሻም ዶ/ር ጌታቸው ሺፈራው ስለሕክምና አሰጣጡ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ “...አንዲት ልጅ ተደፍራለች ተብላ ወደ ሕክምና ማእከላችን ስትደርስ ከኢትጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የተሰጠንን ፕሮቶኮል ተጠቅመን ለፍትሕ አካላቱ የምንሰጠው ምስክርነት አለ፡፡ በእርግጥ ተደፍራለች አልተደፈረችም የሚል ቃል በቀጥታ አንጠቀምም፡፡ ነገር ግን በሰውነቷ ላይ ያየነውን ጉዳት በመከተል በቅርብ ጊዜ የተፈጸመ ወይንም የቆየ መሆኑን በዝርዝር በስእል ጭምር አስደግፈን እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ሌሎች ሕክምናዎች ኤችአይቪ... ጉበት... እርግዝና... የአባላዘር በሽታዎችን በሚመለከት ተገቢው ምርመራ ለልጅቷ ይደረግላታል፡፡ በእርግጥ ይህ ክሊኒክ ገና አንድ አመት ገደማ የሚሆነው ሲሆን በሂደት ሁሉንም አገልግሎች ማለትም የህክምና፣ የምክር አገልግሎት፣ የፍትህ እና የስነልቡና ሕክምናን በአንድ ቦታ እንዲያገኙ የሚቻልበት መንገድ ይመቻቻል የሚል ተስፋ አለን፡፡”
“...ወንድ ሴትን የሚደፍርበት ምክንያት ብዙ ጊዜ የስርአተ ጾታ ክፍፍል ልዩነቱ ወይንም ጀንደር ከሚለው ሁኔታ ጋር ይያያዛል፡፡ ሴት እንዲህ ነች ወንድ ደግሞ እንዲህ ነው የሚለውን ህብረተሰቡ የሚያምንበትና ተግባራዊ እያደረገው ካለው ጋር በተያያዘ አስገድዶ መድፈሩ ብዙ ጊዜ ይፈጸማል፡፡ ምክንያቱም ህብረተሰቡ ለወንድ ልጅ ኃይል ወይንም አቅም እንዳለው እየነገረ ስለሚያሳድገው ወንዱ በተፈጥሮው ካገኘው ጥንካሬ ባሻገር በአስተሳሰብም ኃይል እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ ከዚህም በተለየም በልጅነታቸው የመደፈር ወይንም የመገለል እንዲሁም የተለያዩ ጥቃቶች የደረሰባቸው ከሆነ አስገድዶ መድፈርን እንደ እልህ መወጫ ይጠቀሙበታል፡፡ አንድ ወንድ እንደዚህ ያለ ጉዳት እየደረሰበት ያደገ ከሆነና እሱም ጥቃቱን መፈጸሙ በሳይንሳዊው መንገድ ሲተረጎም አእምሮው በሚያድግበት ሰአት የተለያዩ ኢንዛይሞች ማለትም ነርቭ ከነርቭ የሚገናኝበት መልእክት የማስተላለፊያ ኬሚካሎች በደም ውስጥ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ አእምሮው እያደገ ሲመጣ ኬሚካሉ ግን እየቀነሰ መምጣቱ በሚያድጉበት ሰአት ላይ ይህንን ወሲባዊ ጥቃትም ሆነ ማንኛውንም ወንጀል እንደሰው መግደል የመሳሰሉትን ጨምሮ የመፈጸም እድላቸው የሰፋ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ አስገድዶ መድፈር የሚፈጽሙ ሰዎች ከአንድ ሰው ጋር ወይንም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ጥሩ አይነት ግንኙነት መመስረት የማይችሉ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ከአስተዳደግ ወይንም ከተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎች ሊሆን ይችላል፡፡ በተረጋጋ ሁኔታ ከሰዎች ጋር መኖር ካልተቻለ ወይንም ህብረተሰቡ የሚጠብቀውን ደረጃ ማሟላት ካልተቻለ እንደመሸሻ የሚቆጠረው የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን የመሳሰሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ
የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት

Read 2290 times