Monday, 24 August 2015 10:23

“...ብዙ አማራጮች ቀርበዋል...”

Written by  ዮዲት ባይሳ (ከኢሶግ)
Rate this item
(32 votes)

  ከስምንቱ የምእተ አመቱ የልማት ግቦች ወይም Millennium Development Goals መካከል የእናቶችን ጤና ማሻሻል በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህም በዋናነት የእናቶችን ሞት በግማሽ መቀነስ እንዲሁም የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለሁሉም እናቶች ተደራሽ ማድረግ ላይ ያተኩራል፡፡ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን በተገቢው መንግድ ተደራሽ ማድረግ እና ሁሉም እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማድረግም በዚሁ እቅድ ስር የሚካተት ነው፡፡
የተለያዩ የእግዝና መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም የቤተሰብን ቁጥር ከመመጠን ባለፈ በአሁኑ ሰአት እጅግ አሳሳሲ ከሚባሉት የማህበረሰብ ጤና ችግሮች አንዱ የሆነውን የእናቶችን ሞት በእጅጉ ለመቀነስ ያስችላል። ለዚህም በየአመቱ ፅንስ በማቋረጥ ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሴቶችን እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡
ለዚህ ነው የተለያዩ የእርግዝና መከላከያ ምርቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእናቶችን ጤና በመጠበቅ እረገድ የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው የሚባለው፡፡
በአለማችን ላይ ያለው የእርግዝና መከላከያ ምርቶች ተጠቃሚ ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን የአለም የጤና ድርጅት በግንቦት ወር 2015 ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡ በዚህም የእስያ እና የላቲን አሜሪካ ሀገራት ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ ከሰራ በታች ያሉት የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ በተቃራኒው በዚህ እረገድ ያላቸው ተጠቃሚነት እጅግ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነም መረጃው ይጠቁማል፡፡
በአጠቃላይ ግን አለምአቀፍ ደረጃ ያለው የዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ምርቶች አጠቃቀም ላይ ከግዜ ወደ ግዜ መሻሻሎች እንደታዩ ለዚህም እንደማሳያ የሚጠቀሰው በፈረንጆቹ 1990 53% የነበረው የተጠቃሚዎች ቁጥር በ2014 ወደ 57.4% ማደጉ እንደሆነም በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
በፈረንጆቹ ከ2008-2014 ባለው ግዜ ውስጥም እድሜያቸው ከ15-49 የሆኑ የዘመናዊ የእርግዝና መቆጣጠሪያ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ቁጥር በእጅጉ እንደጨመረ እና በአህጉራችን አፍሪካም ከ23.6% ወደ 27.6% ማደጉን ይህ በያዝነው በፈረንጆቹ 2015 የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
አሁን ያለንበት የሀያአንደኛው ክፍለ ዘመን ብዙ ለውጦችን እያስተናገድን ያለንበት ዘመን እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በስራችን ወይም በእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ እንጠቀምባቸው የነበሩ ነገሮች በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተተክተው አንዳንዶቹም በፊት በነበረው ላይ እሴት ተጨምሮባቸው የሚስተዋሉ በመሆኑ ነው፡፡ በሁሉም የሙያ ዘርፎች ሊባል በሚችል ደረጃም አዳዲስ አሰራሮች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ታይተዋል፡፡ ግዜው ካዘመነልን ነገሮች መካከል ያልተፈለገ እርግዝናል ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የወሊድ መከላከያ ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ገነት ዳንኤል በሃያዎቹ መጨረሻ ላይ የምትገኝ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ነች፡፡ ለስራ ጉዳይ ወደ አንድ በከተማችን የሚገኝ የግል ሆስፒታል በሄድኩበት ወቅት ነበር የገኘኋት፡፡ በቅድሚያ ነዋሪነቷ በሀዋሳ ከተማ 06 ቀበሌ እንደሆነ እና አዲስ አበባ የመጣችው ለህክምና መሆኑን አጫወተችኝ፡፡ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኗን ጠይቄ ከተረዳሁ በኋላ የትኛውን የወሊድ መከላከያ እንደምትጠቀም ጠየኳት...
“...በአሁኑ ሰአት በገበያ ላይ ለአጭር ወይም ለእረዥም ግዜ የሚሆኑ በጣም ብዙ የወሊድ መከላከያ አማራጮች አሉ ...እኔ ግን የምጠቀመው ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ነው። እንደነገርኩሽ ሁለት ልጆች አሉኝ ...እና እነሱን በሚገባ ተንከባክቤ ማሳደግ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ከባለቤቴ ጋር ተነጋግረን ባለሙያም አማክረን የወሰነው ነገር ነው፡፡...”
የፅሁፌ መነሻ ሀሳብ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ምርቶች ላይ ያለውን መሻሻል ከተጠቃሚዎች አንደበት ለመስማት ነውእና ቀጣይ ጥያቄዬ በዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ምርቶች ላይ ያለውን መሻሻል እንዴት ታይዋለሽ? የሚል ነበር፡፡
“...በእኔ እይታ... በጣም ትልቅ ለውጥ ነው የመጣው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም በፊት ግዜ ገበያው ላይ የነበሩት የወሊድ መከላከያ መድሀኒቶች በጣም ውስን እና ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ግን አማራጩ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ...ለምሳሌ እኔ የመጀመሪያ ልጄን ከወለድኩ በኋላ የምታጠባ እናት የምትወስደውን ነበር የምጠቀመው፡፡... በእንክብል የሚወሰዱ፣ በክንድ ላይ ተቀብረው እስከ አራት ወይም አምስት አመት እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ ሌሎችም ብዙ አማራጮች ቀርበውልናል፡፡ ...አሁን አንዲት ሴት ተገዳ ብትደፈር ወይም ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ ፈፅማ ቢሆን እርግዝና እንዳይፈጠር የሚያደርግ በ72 ሰአት ውስጥ የሚወሰድ መድሀኒትም አለ፡፡ ስለዚህ ከድሮው ጋር ስናወዳድረው አማራጩ በጣም ብዙ ነው... እና አሁን ላይ ያለን ሴቶች በጣም እድለኞች እንደሆንን ይሰማኛል...”  
ሌላዋ እናት ሉአም ትባላለች፡፡ የአንድ ወንድ ልጅ እናት የሆነችው ሉአምም የአጭር ግዜ የወሊድ መከላከያ ተጠቃሚ ነች፡፡ በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ያለው የዘመናዊ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ላይ ብዙ መሻሻሎች መታየታቸውን እና አቅርቦቱም ጥሩ የሚባል እንደሆነ ትናገራለች፡፡  
“...አሁን ያለው ሁኔታ ከድሮው ጋር በጣም ልዩነት አለው፡፡ ...ድሮ እናቶቻችን ወሊድን የሚቆጣጠሩት በባህላዊ መንገድ ከዛም በኋላ በጣም ጥቂት በሚባሉ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒቶች ነው፡፡ አሁን ግን በጣም ብዙ አይነት የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ልክ እንደ ብዛታቸው ሁሉ አይነታቸውም አጠቃቀማቸውም የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ ከእኛ የሚጠበቀው መርጦ መጠቀም ብቻ ነው፡፡...”
በሀገራችን የተለያዩ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎቶችን ወይም ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያችስችሉ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች በማድረስ ላይ የሚገኙ ሀገር በቀል እንዲሁም አለም አቀፍ ድርጅቶች አሉ፡፡ በዚህ ስራ ላይ ከተሰማሩት  አለምአቀፍ ድርጅቶች መካከል ዲኬቲ ኢትዮጵያ አንዱ ነው፡፡
ዲኬቲ ኢትዮጵያ በሀገራችን አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት በፈረንጆቹ 1990 ጀምሮ በዘርፉ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን እና ህብረተሰቡን የዘመናዊ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ በዲኬቲ ኢትዮጵያ ቴክኒካል ዲፓርትመንት ውስጥ በስራ ላይ የሚገኙት አቶ ሙሉጌታ አስጨናቂ ይናገራሉ፡፡
“...ዲኬቲ ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት ከጀመረበት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1990 አመተምህረት ጀምሮ በዘርፉ በርካታ ስራዎችን ስንሰራ 25 አመታትን አስቆጥረናል። ...ዲኬቲ ኢትዮጵያ ከሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ እና ዋናው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉ መድሀኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ...እንደሚታወቀው የፕሮግራሙ ዋና ባለቤት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው፡፡ እኛ ደግሞ አገልግሎቱ ተደራሽ ያልሆነባቸው ቦታዎች ላይ በመድረስ እንደ አንድ አጋር ሆነን የመንግስትን ፕሮግራም በማገዝ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ዲኬቲ በሀገራችን ውስጥ ያለው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሽፋን እንዲጨምር ወይም እንዲሻሻላ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ያለ ድርጅት ነው፡፡...”
በአሁኑ ሰአት በርካታ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አማራጮች በተለያየ መንገድ ለተጠቃሚዎች ቀርበዋል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ አማራጮች የትኞቹ ናቸው? አቶ ሙሉጌታ ለዚህ ምላሽ አላቸው፡፡
“...እነዚህን የወሊድ መቆጣጠሪያ ምርቶች በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ አንደኛው ጥምር የወሊድ መከላከያ የምንለው ነው፡፡ ...እነዚህ ጥምር ወይም (Combined oral contraceptives) የምንላቸው መድሀኒቶች በሁለቱ ማለትም ኤስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን በተባሉት ሆርሞኖች መልክ ሰው ሰራሽ በሆነ መልክ የሚሰሩ መድሀኒቶች ናቸው፡፡ ...ሁለተኛው አይነት ደግሞ Mono ወይም ነጠላ የምንላቸው መድሀኒቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ወርሀዊ የሆኑ በእንክብል መልክ የሚወሰዱ እንዲሁም በመርፌም የሚሰጡም አሉ፡፡ ...ለምሳሌ ኮንፊደንስ የምንለው በየሶስት ወሩ በመርፌ የሚሰጥ መድሀኒት አለ፡፡ ሌላ ደግሞ በ72 ሰአት ውስጥ የሚወሰድ Postpill የተባለ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ መድሀኒትም አለ፡፡ ...በተጨማሪም በአምስት  የተለያየ ቃና የተዘጋጁ ኮንዶሞች አሉ፡፡ ኮንዶም ጠቀሜታው ሁለት ነው፡፡ አንድም ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይፈጠር ያደርጋል በሌላበኩል ደግሞ የኤች አይቪ ቫይረስ እንዳይተላለፍ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ለተወሰነ ግዜ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ መድሀኒቶች ናቸው።...”እነዚህ ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ምርቶች እርግዝናን በግዜያዊነት ለመከላከል የሚያስችሉ ሲሆኑ ማርገዝ በሚፈለግበት ግዜ መድሀኒቶቹን በማቆም ብቻ እርግዝና እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላል፡፡ ግዜያዊ መባላቸውም በዚሁ መነሻነት እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ይገልፃሉ፡፡  
ሌላኛው አማራጭ እርግዝናን በቋሚነት ለመከላከል የሚያስችሉ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች ናቸው። እነዚህ መድሀኒቶች ጭርሱን እርግዝና እንዳይፈጠር የሚያደርጉ ሲሆን ተጠቃሚዎች ይህን አይነት መድሀኒቶችን ከመውሰዳቸው በፊት በቂ የባለሙያ ምክር ማግኘት እንደሚኖርባቸውም ይናገራሉ፡፡
እነዚህ በርካታ አማራጮች መብዛታቸው የህብረተሰቡን መርጦ የመጠቀም እድል እንዲሰፋ እና የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥርም እንዲጨምር ያደርጋል ይላሉ፡፡   
“...በሀገራችን ደረጃ የተለያዩ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን እያበዛን በመጣን ቁጥር ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን እና ከጤናቸው ጋር የሚስማማውን ዘዴ መርጠው የመጠቀም እድላቸው በጣም ይሰፋል፡፡ በተመሳሳይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ...በሀገሪቷ ውስጥ ያለው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሽፋን ከፍ እያለ ይመጣል፡፡ ...ዛሬ እድሜ ለቴክኖሎጂ ብዙ አይነት አማራጮች ቀርበዋል፡፡ ተጠቃሚዎችም ከድሮ የተሸለ ግንዛቤ አላቸው፡፡ ...ይህ ትልቅ እመርታ ነው፡፡...”
እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ይላሉ አቶ ሙሉጌታ፡-
“...እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ሁሉም የቤተሰበ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የትኛውንም አይነት መድኒት ከመውሰዳቸው አስቀድሞ የባለሙያ ምክር እና እገዛ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡...”

Read 36574 times