Monday, 24 August 2015 09:51

አንጎለላ፡- ተዘክሮ ልደት ምኒሊክ ወ ጣይቱ…!

Written by  ጥላሁን አበበ (ወለላው) tilahun.ab23@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

‹‹የመድሃኒት ጥቂት ይበቃል እያለች
የምኒሊክ እናት አንድ ወልዳ መከነች››
(ሰርጉ ሃብለስላሴ)
‹‹የሸዋው ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ‹ምኒሊክ› በሚባል ስም ሊነግሱ ሲሉ አንድ መነኩሴ ‹በዚህ ስም አትንገስ፣ መጥፎ አጋጣሚ ያመጣብሃል፡፡ ይህ ስም የሚስማማው ከመጀመሪያ ልጅህ ከኃይለ መለኮት ለሚወለደው ነው። ይህም ስም የሚወጣለት የልጅ ልጅህ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ትልቅ ንጉስ ይሆናል…›› ይል ነበርና ክብረ ነገስቱ፣ ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ‹ምኒሊክ› በመባል የመንገሳቸውን አሳብ ተዉት፡፡ ይህ ከሆነ ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ የአንኮበር ቤተ ክርስቲያን አለቃ የነበሩት የመምህር ምላት ገረድ፣ እጅጋየሁ ለማ አዲያሞ፣ የተባለች ሴት አንድ ቀን ጠዋት ‹‹ዛሬ በህልሜ ከብልቴ ፀሃይ ስትወጣ አየሁ…›› ብላ ብትናገር፣ ወሬው ከአለቃ ምላት ይደርስና ‹‹ወደ ላይ ቤት ትሂድ›› ተብላ ለንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ሚስት ወ/ሮ በዛብሽ ተሰጥታ የቤተመንግስቱ ገረድና የልጆች ሞግዚት ትደረጋለች፡፡
ይህን ወሬ የሰሙት ወ/ሮ በዛብሽ፣ ያ በህልም የታየው ፀሃይ ከልጃቸው እንዲወለድ ስለፈለጉ አብዝተው ለሚወዱት ለሰይፉ ሳህለ ሥላሴ እጅጋየሁን ‹አጥበውና አጥነው› ወደ ሰይፉ መኝታው ይሰዷታል፡፡ ወሬውን ቀድሞ የሰማው ሰይፉ፣ የሚወዳት ሌላ ሴት ነበረችውና፣ ወንድሙን ሃይለ መለኮትን ‹‹እባክህን ሌላ ሴት ከሌለህ እሜቴ የላኳትን ያቺን ገረድ ውሰድልኝ›› ብሎት ተስማሙና፣ እጅጋየሁ በዚያች ምሽት ከሃይለ መለኮት ትፀንሳለች፡፡
የእርግዝናዋ ወሬ ይፋ ሲሆን ወ/ሮ በዛብሽ ከሰይፉ ሳይሆን ከሃይለ መለኮት በማርገዟ፣ ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ደግሞ ልዑሉ ልጃቸው ገረድ በማስፀነሱ ሁለቱም ተናደዱ፡፡ እጅጋየሁም ከነቅሪቷ የንጉስ ሳህለ ሥላሴ እርስት ወደ ነበረው ወደ አንጎለላ ሄዳ በግዞት እንድትቀመጥ ተፈረደባት፡፡
ቅዳሜ ነሐሴ 12፣ 1836 ዓ.ም እጅጋየሁ በአንጎለላ ቤቷ ወንድ ልጅ ተገላገለች፡፡ እዚያው እቤቷ ጓሮም የልጇ እትብት ተቀበረ፡፡ ይህን የሰሙት ንጉስ ሳህለ ሥላሴም፣ ‹ልጄ አዋርደኸኛል፣ እንግዲህ ሸዋ ምን ትለኝ ይሆን…?› በሚል መሳይ ቁጭት የልጁን ስም ‹‹ምን-ይልህ-ሸዋ›› ብለው ጠሩት፡፡
ኋላም አንድ ቀን በህልማቸው ከዚህ ብላቴና ጋር አብረው ቆመው ሳለ፣የልጁ ጥላ ከሳቸው ጥላ ገዝፎ ይታያቸዋል፡፡ መሬት የረገጠው የእግሩ ምልክት፣እሳቸው ከረገጡት በላይ ረዝሞ ቢያዩት ጊዜና ከእንቅልፋቸው ሲነቁ፤‹‹ምኒሊክ የኔ ስም ሳይሆን የሱ ነው፡፡ ይህንን ልጅ ስሙን ‹ምኒሊክ› በሉት ብለው አዘዙ፡፡›› ይለናል ጳውሎስ ኞኞ፣ አጤ ምኒልክ በሚለው መፅሃፉ ላይ፡፡
ይህ ከሆነ ከ171 ዓመታት በኋላ ነሐሴ 12 ቀን 2007 ዓ.ም የታሪክ ፀሃፊና ተመራማሪ በሆነው ወጣት ዳንኤል በላቸው ፊታውራሪነትና በገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ ገጣሚ ደምሰው መርሻና በጋዜጠኛ/ገጣሚ ባንቺአየሁ አለሙ ደጀንነት፣ ምኒሊክ ወደዚህ ዓለም የመጡባትንና እትብታቸው የተቀበረባትን ኩርባ መሬት፣ በልደት ቀናቸው ለመዘከር፣ ራሳቸውን ጨምሮ 15 ሰዎችን በማሰባሰብ፣ ከጠዋቱ 1፡30 ላይ ጣይቱ ሆቴል በር ላይ ለጉዞ ተዘጋጅተው ነበር፡፡  
ምንተስኖት ማሞ (ገጣሚ)፣ አሌክሳንደር በየነ (ገጣሚና የዋሊያ ቢራ ባልደረባ)፣ ብሩክ ሞገስ (ኢንጂኒየር)፣ መስፍን አይንካው(የአማኑኤል የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤትና የመጪው ዓመት ጉዞ ስፖንሰር)፣ ዘላለም አበራ (የካሜራ ባለሙያ)፣ ብርሃኑ አየለ (ገጣሚና የማስታወቂያ ባለሙያ)፣ ሰናይት አዱኛ (የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ባለሙያ)፣ ጌቱ ኦማሂሬ (ድምፃዊ)፣ ተወልደ ብርሃን ኪዳኔ (ሰዓሊ)፣ ጌታቸው እሸቱ (መምህር) እንዲሁም እኔ ጥላሁን አበበ የተጓዥ ቡድኑ አባላት ነበርን፡፡
ጉዞአችን በምኒሊክና በሌሎች ጠለቅ ባሉ ታሪካዊ ውይይቶች እንደታጀበ ነበር ረፋዱ ላይ ሸኖ ከተማ የደረስነው፡፡ ለቡና እረፍት እያደረግን ሳለ ግን አንድ ያልጠበቅነው መጥፎ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የተሳፈርንበት ኮስትር-ሚኒባስ የቴክኒክ ብልሽት ገጠመውና ጉዞአችን የተስተጓጎለ መስሎን ብዙዎቻችን ተጨነቅን፡፡ የጭንቀታችን ዋናው ምክንያት፣ የዚያን ቀን ማታ በ11፡00 ሰዓት ላይ በፑሽኪን አዳራሽ የገጣሚ አደም ሁሴን መፅሐፍ ስለሚመረቅና እኔን ጨምሮ ቢያንስ 4 ገጣሚያን የመድረኩ አጋፋሪዎች ስለነበርን ነው፡፡ ጌታቸው እሸቱ ደግሞ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ስለነበር ብቸኛው አማራጭ በሚኒባስ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ብቻ ሆነ፡፡ ወዲያው ግን ከፍተኛ ቅናሽ አድርጎ የተባበረን የመኪናው ባለቤት፣ ሙሉ ክፍያችንን መልሶልን በሌላ ሚኒባስ ኮንትራት እንድንሄድ ስላስቻለን፣እሱን እያመሰገንን ጉዞአችንን በደብረ-ብርሃን አድርገን ወደ አንጎለላ ቀጠልን፡፡
ከቀኑ 6፡00 ገደማ ላይ ጭር ካለ አካባቢና ዙሪያ ገባውን የተሰበጣጠሩ ነዋሪዎች ካሉባት አንጎለላ መንደር ስንደርስ አይናችንን የሳበው፣ አንድ እንደነገሩ በሽቦ የታጠረ የጤና ጣቢያ ግቢ ውስጥ ያለ የድንጋይ ማማ ነው። በማማው አናት ላይ ደግሞ ከወገብ በላይ የተቀረፀና ሻሽ የጠመጠመ የምኒሊክ ሃውልት ከነምኒሊካዊው ግርማ ሞገሱ ጉብ ብሏል፡፡ የቡድኑ መሪ በሰጠን ማብራሪያ መሰረት፣ ያቺ ሀውልቱ የተሰራባትና የቆምንባት መሬት፣ የወ/ሮ እጅጋየሁ የግዞት ጎጆ የተቀለሰባት፣ብሎም ምኒሊክ በንግስና ዘመኑ ‹‹ማርያምን…!›› ብሎ አገርን አንድ ከማድረጉ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፁን በልቅሶ ያሰማባት እንደሆነች ስንረዳ በሁላችንም ውስጥ አንዳች ኩራት ሞልቶን ነበር፡፡  
የጉዞአችንን መርሃ ግብር ለማከናወን፣ ለምኒሊክ ውልደተ ክብርና ዝክር የገዛነውን አበባ በማስቀመጥና ሻማ በማብራት ጀምረን ስናበቃ፣የተወሰንነው ስነፅሁፋዊ ሥራዎችና ታሪካዊ ስነ-ቃላት አጠር አጠር አድርገን አቀረብን፡፡
የታሪክ ባለሙያው ዳንኤል በላቸው፤ለምን ይህንን ልዩ ጉዞ እንዳዘጋጀ ካቀረበልን ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ሶስቱን ስንመለከት፡- 1)በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተወለደበት (ብሎም እትብቱ የተቀበረበት) እና በሞት ያረፈበት ቦታ በትክክል የሚታወቅ ንጉስ አፄ ምኒሊክ በመሆኑ፡፡ 2)ላለፉት 171 ዓመታት፣ ምናልባት የመካነ መቃብሩ ቦታ እንጂ ይህ የውልደት ቦታው አንዴም በገሃድ ያልተጎበኘ በመሆኑ፡፡ እንዲሁም 3) በአጠቃላይ ምኒሊክ እንደ ትንቢቱ ኢትዮጵያን አንድ በማድረግ ብቻ ሳይገታ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ባለው የላቀና ታሪካዊ አስተዋፅዖው ምክንያት እንደሆነ አስረድቶን ሲያበቃ፣ወደፊትም በየዓመቱ ጉብኝቱ ከአሁኑ በበለጠ ሁኔታ በስፋት እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡  
ባንቺአየሁና ሰናይት፣ አፄ ምኒሊክ ከተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች መካከል ለእቴጌ ጣይቱ የፃፉትን ፍፁም ፍቅር አዘል ደብዳቤዎች ሲያነቡልን፣ምኒሊክ ለሚስታቸው የነበራቸው ፍቅርና አክብሮት ምን ያህል ጥልቅ እንደነበር በግልፅ ለመረዳት ችለናል፡፡ ብርሃኑና አሌክሳንደር፤ በምኒሊክ ላይ ከተፃፉት የታሪክ መጻህፍት መካከል ከአንደኛው ላይ ጥቂት አንቀፆችን ያነበቡልን ሲሆን ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ በጣም ከምናውቀውና ከተወደደለት ‹‹የምኒሊክ አናት›› የተሰኘ ግጥሙ ላይ የተወሰኑ ስንኞችን በቃሉ ሲወርድልን፣ሁላችንም በውስጣችን የምኒሊክ መንፈስ አድሮብን ነበር፡፡
እኔም ‹ምኒሊክ አሁን ከሞት ተነስቶ ቢያይ…› በሚል ጭብጥ በቅርቡ እየፃፍኩት ከነበረውና  ከምኒሊክ የሙት መንፈስ ጋር ካደረግኩት ውይይት ላይ ጥቂት አንቀፆችን ያነበብኩ ሲሆን  ምኒሊክ በሞት የተቀጡ ወንጀለኞችን ለመግደያ እንዲሆን ከአሜሪካ ካስመጧቸው 3 ወንበሮች መካከል አንዱን ለራሳቸው መቀመጫ ዙፋንነት ያገለግል ዘንድ የመውሰዳቸውን ነገር ስገልጽ፣ የጉዞው አባላት በሳቅ ዘና ብለው ነበር፡፡   
በመቀጠልም፣ከሃውልቱ በግምት 50 ሜትር ገደማ ወረድ ብለን የምኒሊክ እትብት የተቀበረባትን ቦታ ተመለከትን፡፡ ቦታዋ ለምልክት ያህል የድንጋይ ካብ ተከምሮባታል፡፡ እዚህ ሥፍራ ከ171 ዓመታት በፊት የአገር ንጉስ እትብት፣ መሬት ጫር ጫር ተደርጎ መቀበሩን  ስናስብ፣ሁላችንም ለዚህ ዕድል በመብቃታችን ከፍተኛ ደስታን ፈጥሮብን ካቧ ላይ ቆመን ፎቶ ተነሳን፡፡
በመጨረሻም፤ተሞጋግሰንና ተመራርቀን እንዲሁም ከዚህ በኋላ ሁላችንም ራሳችንን እንደ መስራች ኮሚቴ ቆጥረን፣ በየዓመቱ ይህንን መልካም አርዓያነት ሳናስተጓጉል ከዚህ በላቀ ሰፊ ስነ-ስርዓት እንደምናከብር ቃል በመግባት፣የመልስ ጉዞአችንን ጀመርን፡፡ ደብረብርሃን ላይ ምሳችንን በልተን በቀየርናት ሚኒባስ ሸኖ ከመግባታችን ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ የኮስትር- ባሱ ሹፌር መኪናውን በወጉ እንዳሰራው ስለጠቆመን፣ ባለ-ሚኒባሱን ሸኝተን በመጀመሪያው መኪናችን ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሆነ፡፡
 ማለዳ የተነሳንበት ጣይቱ ሆቴል በር ላይ የደረስነው 11፡30 ሲሆን በፑሽኪን አዳራሽ በሚካሄደው የወዳጃችን የመጽሐፍ ምርቃት ሥነስርዓት ላይ ለመታደም በቂ ጊዜ ነበረን፡፡
ዘንድሮ በ15 ተጓዦች የተጀመረው ተዘክሮ ልደት ምኒሊክ ወ ጣይቱ፤ወደፊት በብዙ ሰዎችና ግብሮች ታጅቦ እንደሚከናወንና ታሪካዊ ቦታውም የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት፣ የቱሪስት መስህብነቱ ከፍ እንደሚል መላ የጉዞ አባላቱ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

Read 2811 times