Monday, 24 August 2015 09:48

አሉታዊ አስተሳሰቦችን ቀብሮ፣ በጎ በጎዎቹን ማጽደቅ!!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለፉት አስር አመታት የተለያዩ ራስን የማበልጸግና የአመራር ስልጠናዎችን ለመካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በመስጠት የሚታወቀው SAK የስልጠና ማዕከል፤በዘንድሮ ክረምት 80 ለሚሆኑ ህጻናትና ወጣቶች እራስን የማበልጸግ (Personal Development)  ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ፡፡  
ስልጠናው በዋናነት ህጻናትና ወጣቶች ከትምህርት እውቀታቸው በተጨማሪ በባህሪያቸው ታንጸው በራሳቸው የሚተማመኑ፣አላማ መር ህይወት የሚመሩና ሃላፊነትን የሚቀበሉ የነገ አገር ተረካቢዎች እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በሶስት ዙር በተሰጡት ስልጠናዎች ተሳታፊ የነበሩ ተማሪዎች እንዲሁም ወላጆች እርካታቸውን የገለጹ ሲሆን ስልጠናው በ10ኛው ቀን ሲጠናቀቅ የ“አልችልም አስተሳሰብ” የቀብር ስነስርዓት (“I can not do it; funeral) ይካሄዳል፡፡ የቀብር ስነስርአቱ ከመካሄዱ በፊት የሬሳ ሳጥን ይዘጋጅና ሁሉም ተማሪዎች ወደ ኋላ የሚያስቀሯቸው አስተሳሰቦች፣ ለምሳሌ - አልችልም፣ ይሉኝታ፣ ያበሻ ቀጠሮ፣ አይመለከተኝም፣ በጎ ነገሮችን ያለማድነቅ አባዜ፣ እኔ ብቻ ልጠቀም (win-Loss) ወይም ሁለታችንም አንጠቀም (Loss-Loss) ወዘተ---ተጽፈው በሳጥኑ ውስጥ ይገቡና ይቆለፍባቸዋል፡፡ በቀብሩ ስነስርዓት ወቅትም ተማሪዎች የደስታ ቀናቸው ስለሆነ፣ ሁሉም ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ መቃብሩ ይሄዳሉ። በጉዞውም ላይ ቻው ቻው አልችልም፣ ባይ ባይ አልችልም የሚል መዝሙር ይዘምራሉ፡፡
የቀብሩን ጉድጓድ ተማሪዎች የሚያዘጋጁ ሲሆን የቀብሩም ቦታ ላይ የአልችልም አስተሳሰብ የቀብር ሥነስርዓት በንባብ ይሰማል፡፡ ከዚያም ሳጥኑ በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ይቀበራል፡፡ በቀብሩ ስነስርኣት ላይም ተማሪዎች እነዚህን የቀበሯቸውን ኋላ ቀር አስተሳሰቦች በድጋሚ እንዳያስቧቸው ቃል ይገባሉ፡፡ በቀብሩ ላይ የተነበበው ንባብ፣ በሰልጣኞች መኝታ ቤት ውስጥ እንዲለጠፍና ሁልጊዜ ተማሪዎቹ እንዲያዩት ይደረጋል፡፡
ሳይረፍድ በልጆቻችን አስተሳሰብ ላይ ለውጥ በማምጣት የወደፊት የህይወት መሰረታቸውን አብረን እንጣል የሚል ጥሪ ማስተላለፉን ያስታወሰው ማዕከሉ፤ጉዞውን በዘንድሮ ክረምት በስልጠና  መጀመሩን አመልክቷል፡፡ ስልጠናው መደበኛ ትምህርት በሚጀመርበት አዲሱ አመትም የሚቀጥል ሲሆን ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በየቀኑ የየእለቱ ትምህርት ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚሰጥ ማዕከሉ ጠቁሟል፡፡
የ SAK የስልጠና ማዕከል ራስን የማበልጸግ ስልጠናው እንደ ማንኛውም ትምህርት በአገራችን የትምህርት ስርአት ውስጥ ተካቶ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተማሪ ከልጅነት ጀምሮ እንዲሰጥ ያለመ  ሲሆን ይህም ውጤቱ በእውቀትና በባህሪ የተገነባ ትውልድ ማፍራት ነው ይላል፡፡
የአልችልም አስተሳሰብ የቀብር ሥነስርዓት
እኛ ዛሬ እዚህ የተሰበሰብነው እራስን የማበልጸግ ሥልጠና የወሰድን ተማሪዎች፣ በዋናነት አልችልም የሚለውን አስተሳሰብና ሌሎችም እራስን ወደ ኃላ የሚያስቀሩ አስተሳሰቦችን ለምሳሌ፡-
እድለኛ አይደለሁም ብሎ ማሰብን
ለይሉኝታ መገዛትን
የአበሻ ቀጠሮ የሚባለውን ሰዓት የማርፈድ አስተሳሰብ
ሌላ ሰውን ለመምሰል የመፈለግ አባዜ
አይመለከተኝም የሚለውን አስተሳሰብ
አሉታዊ ጎኞች(Negative thinking) ላይ የማተኮር አስተሳሰብ
ድርድር ላይ መሸነፍ፣ መሸነፍ (Lose - Lose) የሚለውን ወይም የዜሮ ድምር አስተሳሰብ
ዛሬ ነሐሴ ----------/2007 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ቀብሬያቸዋለሁና ከዚህ በኋላ አነዚህ አስተሳሰቦች ከእኔ ጋር ቦታ የላቸውም፡፡ እነዚህ አሮጌ አስተሳሰቦች የአገራችን እድገት ጠንቅ በመሆናቸው በህይወት ዘመናችን ሁሉ ታግለን ከአገራችን ልናጠፋቸው ቆርጠን ተነስተናል፡፡ ዛሬ በቀበርናቸው አሮጌ አስተሳሰቦች ፋንታ የሚከተሉትን 10 አዲስ አስተሳሰቦች ለመተግበር ወሰነናል፡፡
እራሴን በቀጣይነት በእውቀት ለማሳደግ
እራሴን ተቀብዬ በማንነቴ ለመኩራት
በራሴ ለመተማመን
እችላለሁ በማለት በህይወቴ ለስንፍና ቦታ ላለመስጠት
በጎ አመለካከትን (Positive thinking) የህይወቴ መርህ ለማድረግ
የማድነቅ ባህልን የህይወት መመርያዬ ለማድረግ
ሃላፊነት መቀበልን ከህይወቴ ጋር ለማላመድ
የጋራ ተጠቃሚነትን ሁልጊዜ በህይወቴ ለመተግበር
ጊዜዬን በአግባቡ በመጠቀም ያበሻ ቀጠሮ የሚለውን አስተሳሰብ ለመሻር
ኑሮዩን በራይና በአላማ ለመምራት
ይህንንም የአልችልም አስተሳብ የቀብር ስነስርዓት ጽሁፍ፣ በመኝታ ቤቴ ግድግዳ ላይ ለጥፌ ሁልጊዜ ለማንበብ፤
ቃል እገባለሁ!
ቃል እገባለሁ!
ቃል እገባለሁ!

Read 3827 times