Saturday, 15 August 2015 16:16

ነጋዴ ጸሐፍት እና ጥበበኞች ምንና ምን ናቸው?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

   እንደ በልግ አዝመራ፣ እንደ መስቀል ወፍ ወቅትን ጠብቀው ሽሚያ ውስጥ የሚገቡ ደራሲያንን መመልከት ከጀመርን ሰነባበትን፡፡ ለእዚህም ማሳያ ሰሞኑን ከክረምቱ ካፊያ ጋር ብቅ ብቅ ያሉትን የጥበብ ሥራዎች አንድ ሁለት ብሎ መቁጠር ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ በከተማችን አውራ ጎዳና ላይ በተንቀሳቀስን ቁጥር ከመጽሐፍ አዟሪ ክንድ ላይ እራስ በራስ የተደራረቡ ክረምት-አፈራሽ መፃህፍት ጋር ዓይን ለዓይን መጋጨታችን የማይቀር ነው፡፡
ጥበብ ለመሸት፣ የደራሲው ምናብ ለመወበራየት የግድ ወርኃ ክረምት መጠበቅ አለበት ተብሎ የተደነገገ ይመስል ልክ ሰኔ ግም ሲል ቆፈን ያረበበበት የመጽሃፍ ገበያ ጉራማይሌ ገጽታን በተላበሱ የጥበብ ሥራዎች መፍገግ ይጀምራል፡፡
ይህ ዓይነቱ እሽክርክሪት (vicious circle) መለስ ቀለስ ማለት ከለመደ ዓመታት ነጎዱ፡፡ ጥበብ እንደ ሸቀጥ ቀን ተቆርጦለት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ገበያው ሲደራ መመልከት ለእውነተኛ ጥበብ አፍቃሪ ሠላም የሚሰጥ ትዕይንት አይደለም፡፡
በእርግጥ የመጽሃፍት ገበያው በአብዛኛው ክሽፈት በተጣባቸው ሰሞነኛ ሥራዎች ቢወረርም ለአመል አልፎ አልፎ ጣል ጣል ያሉ ዘመን ተሻጋሪ እንቁ የጥበብ ፍሬዎች ከግርግሩ መሃል አይታጡም፡፡ ቁጥራቸው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ የመፃህፍት ገበያው ውጥንቅጥ የተደራሲያኑን አዕምሯዊና ስነልቦናዊ አቋም ጠፍጥፎ በማበጃጀት በኩል የሚጫወተው ሚና  የላቀ ነው፡፡ ነጋዴ ጸሐፍትና ጥበብ ከዋኒዎች አሻራቸው ያረፈበትን የምናብ አብራክ ክፋይ በየፊናቸው ለገበያተኛው አውደ ርዕይ ያቀርባሉ። ሁለቱም ግን የሚዋሰኑበት ድንበር የለም፡፡ በመሃከላቸው እንደ በርሊን ግምብ የተገተረ ግርዶሽ አለ፡፡ አንዱ ለዝና፣ ለንዋይ ደፋ ቀና ሲል፤ ሌላው የጥበብ ሃድራን እያጫጫሰ ነገር አለሙን ይረሳል፡፡
የጥበበኞች መለያ ጠባይ /No-mind state/
የጥበብ ግዛትና ድንበር ከአእምሮ ንፍቀ ክበብ ውጪ ነው፡፡ አእምሮ ሲሰንፍ ጥበብ ታንሰራራለች። ጥበብ ባለማሰብ-ማሰብ ሒደት ውስጥ የምትዘወር ፈትል ናት። ነገሩ ወለፈንዲ ይመስላል፡፡ በማውጠንጠን ፋታ ላይ ብቅ ያለ ፈጠራን ቤት ለእንግዳ ለማለት መልሶ መላልሶ ማብሰልሰልን ይጠይቃል፡፡ ላለማሰብ ስንፈቅድ ሁሉም ነገር ጥረት አልባ ሆኖ ይከወናል፡፡ ሂንዱዎች “be like a hollow bamboo” የሚሉት ለእዚህም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቀርከሃ ጥዑም ዜማ ያፈልቅ ዘንድ ውስጡ ኦና መሆን አለበት፡፡ ኦና ሲሆን ዜመኛው እስትንፋሱን እንደ ልብ ለመልቀቅ እክል አይገጥመውም፡፡ እስትንፋሱን በቀርከሃው ሆድ እቃ ሲያንጀረጅረው ለጆሮ የሚጥም ዜማ በእዛው ልክ ይንቆረቆራል፡፡
ጥበበኛም እንደ ቀርከሃው ኦና አእምሮን ሲላበስ መጠበቡ እንደ መተንፈስ ይቀለዋል፡፡ ጥበብ በውስጡ ትንፎለፎል ዘንድ ግርዶሹ ተገፏልና፡፡ ያን ጊዜ በምናቡ እንደ ሽል የሚገላበጠው ፈጠራ ለዓይነ ሥጋ ለመብቃት አፍታ አይወስድበትም፡፡
ነፍስ ቦርቃ፣ አእምሮ አሸልቦ የተከወነ ጥበብ ተቀዳሚ ግቡ መተንፈስ፣ መገላገል ነው፡፡ ለግብ፣ ለስኬት አይባትትም፡፡ ትርፍ፣ ኪሳራው ላይ ዳተኛ ነው፡፡ ጥበበኞች ገበያው ላይ ያለው ሞቅታ ምናቸውም አይደለም፡፡ “They prefer to be art maker than business maker.” የጥበበኞች የእጅ ሥራ እንደ ሸክላ ረጋ ብሎ ነው የሚግለው። ለጊዜው ሲዳፈን የከሰመ ይመስላል፡፡ ሲውል ሲያድር ግን  ቅኔን እየመነዘረ፣ ንቃትን እያበረታ፣ ወጋገኑን እየገፈፈ ይሄዳል፡፡  
ልክ ጆን ዴዌይ የተባለው አሜሪካዊው ፈላስፋ ምስክርነት እንደሰጠው፡
“It is meaningless to ask what an artist really means by his product; he himself could find different meanings in it in different days and hours and different stages of his own development.”
ሒሳብ እያወራረዱ የሚጽፉ ብዕረኞች /Mind-dominated state/
ሒሳብ እያወራረዱ የሚጽፉ ነጋዴ ብዕረኞች በጥድፊያ የተሞሉ ናቸው፡፡ ከውስጥ ይልቅ ለውጪው፣ ለታይታው ይባዝናሉ፡፡ ጭቦ-ሰብእናቸው ሁለንተናቸው ላይ ይሰለጥናል። ለአዕምሮ፣ ለደመነፍስ ሹክሹክታ ቀልባቸውን ያውሳሉ፡፡ በአእምሮ ብቻ የተከወነ የጥበብ ሥራ ደግሞ ግብ አልባ ሊሆን አይችልም፡፡ ስሪቱም አይፈቅድለትም፡፡ ትርፍ ኪሳራን በማውጠንጠኑ ረገድ በደንብ የተዋጣለት ነው፡፡ የገበያውን አሰላለፍ፣ ውጣ ውረዱን በቅጡ ለመረዳት ተገቢውን ዕቅድ ይነድፋል፡፡
ነጋዴ ፀሃፍት የአንባቢን ቀልብ ለመግዛት መዘየድ የሚጀምሩት ገና በልባሳቸው፣ በሚመርጡት አርዕስት ነው፡፡ ወቅታዊ ትኩሳትን ለማድመጥ ስልጡን ጆሯቸውን ወደ ገበያው ግርግር ያነቃሉ፡፡ ወሲብ፣ ፖለቲካ፣ ኃይማኖት ሁሉም ላይ አክሮባት ከመስራት የሚያግዳቸው አንዳች ነገር የለም፡፡
የነጋዴ ጻሃፍት “ፖፕላሬ” ሥራ በሃገር በምድሩ ለመብዛት ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ እንደ ብረት ምጣድ ተፋፍሞ ይግልና ፈጥኖ ይከስማል፡፡ በአንድ ሰሞን ሆያሆዬ ገጽታቸው አደባባይ፣ ስማቸው ከአፍ የማይጠፋ ዝነኛ ጸሐፊ ተብለው ለሽልማት ይታጫሉ፡፡ ከጥበብ በብዙ ሺ ክንድ ርቀው የእውቅና ካባ ይደርባሉ፡፡  
ታዋቂው ጣሊያናዊ ጥበበኛ ማይክል አንጅሎ ያነጸውን ግሩም ሃውልት አንድ ክልፍልፍ ወፈፌ ዶግ አመድ ለማድረግ ቅጽበት ነበር የወሰደበት፡፡ ወፈፌው ይህን ለምን እንደአደረገ ሲጠየቅ፡-
”ከዚህ ቀደም የተቀኘኋቸውን ግጥሞች የሕትመት ብርሃን ሊለግሳቸው የፈቀደ አንድም አካል አላጋጠመኝም፡፡ ጭራሽ ከእነመፈጠሬም ነበር የተዘነጋሁት። አሁን ግን ይኸው ይህንን ኃውልት በማፍረሴ የሀገር ምድሩ መነጋገሪያ ሆንኩኝ፡፡ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች የእኔን ፎቶ ከፊት ገፃቸው ላይ ለመለጠፍ ተሽቀዳደሙ፡፡” ብሎ አረፈ፡፡
የነጋዴ ጸሐፍት ግብር ከወፈፌው ጋር ኩታገጠም ነው፡፡ መዳፋቸው ጥበብን አፈር ድሜ የሚያበላ መዶሻ እንጂ ነፍስን የሚያለመልም ብዕር አልጨበጠም። ነጋዴ ጸሐፍትን ፊት የሚነሳ አንባቢ እስከሌለ ድረስ ይህ የአጥፍቶ ጠፊ ምግባራቸው ከመናኘት ወደ ኋላ አይልም።
ነጋዴ ጸሐፍትን እቅፍ ድግፍ አድርገው በንዋዩም፣በእውቅናውም ጣምራ ስኬት ላይ የሚያወጧቸው በአብዛኛው የማኅበራዊ ሚዲያ አንባቢዎች ናቸው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ነጋዴ ጸሐፍት በጭቦ-ስብእናቸው ባበጃጁት መረብ የሚያጠምዱት ዓሳ በብዛት የሚዋኝበት ክትር ነው።
የሚዲያ ባለሙያዎች የማኅበራዊ ሚዲያ አንባቢዎችን በሚከተለው መልኩ ይገልጿቸዋል፡-
“የማኅበራዊ ሚዲያ አንባቢ ልክ የሴት ጓደኛው ወደ ቀጠረችው ተናፋቂ ቦታ ፈጥኖ ለመድረስ  ባቡር ከሚጠባበቅ ኮበሌ ጋር ይመሳሰላል።”
ይህ ልቡ የተንጠለጠለ ኮበሌ  ቀልቡን የሚሰርቀው የጥበብ ሥራ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ስክነት በነጠፈበት፣ ቶሎ ለመፈገግ  በሚጣደፍ አንባቢ ሚዛን ተሰፍሮ አዋቂነት ሲታወጅ ጥበብ ምን ያህል እንደምትኮሰምን ለማወቅ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡
ነጋዴ ጸሐፍት የምናወቀውን፣ የሰለቸንን መልሰው እንደ ገደል ማሚቱ እያስተጋቡ ሲያደነቁሩን፣ ጥበበኞች በተቃራኒው ባልተሞከረና  ባልተለመደ ጎዳና ላይ ይነጉዳሉ፡፡
“Creater goes always in the wrong direction because the right direction has already discovered by everbodyelse.”

Read 1911 times