Saturday, 08 August 2015 09:16

ቀልድ እና ፖለቲካ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(6 votes)

    ገጣሚው መምህሬ ደበበ ሰይፉ፤ ዝርው መሰል አንድ ግጥሙ እንዲህ ይላል፤
‹‹የላሊበላን ህንፃ ማን ገነባው?
የታሪክ ፀሐፊዎች ንጉሦች ናቸው ይላሉ፤
ግን ንጉሦች ድንጋይ ይሸከማሉ?››
የጠቀስኩት የደበበ ግጥም ርዕዮተ ዓለማዊ መነሻ ያለው ነው፡፡ ገጣሚው፤ ‹‹ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው›› ከሚል ሶሻሊስታዊ አመለካከት ተነስቶ የቋጠራቸው ስንኞች ናቸው፡፡ ይህ ተርጓሚ የማያሻው ሐቅ ሆኖ የተሰማኝን ያህል፤ ግጥሙን የጠቀስኩት በትውስታ ተመስርቼ በመሆኑ፤ ግጥሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩበትን አውድ በእርግጥ ማስታወስ አለመቻሌ ወንጃ እንድል አድርጎኛል፡፡ ደበበ በጥናት ሥራዎቹ ውስጥ እንዲህ ያሉ ግጥሞችን ይጠቅሳል፡፡ ስለዚህ ‹‹ያነበብኩት በአንዱ የጥናት ሥራው ውስጥ ይሆን እንዴ?›› የሚል ጥርጣሬ ፈጥሮብኝ፤ ግጥሙን ከደራሲው የተገኘን ሐሳብ መሠረት አድርጌ ለመተርጎም አለመቻሌ ትንሽ እንዳመነታ አደረገኝ እንጂ፤ የጠቀስኩት ግጥም ‹‹ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው›› ከማለት የወጣ ትርጉም ሊኖረው አይችልም።
‹‹ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው›› የሚል አቋም ፍፁም የተደላደለ መሠረት ያለው አቋም መሆኑ ቢሰማኝም፤ ግለሰቦች በታሪክ ሂደት ያላቸው ሚና እጅግ ወሳኝ መሆኑን ለመቀበል ከሚገፋፋ የተቃራኒ አቋም ስበት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ አለመቻሌን አውቃለሁ፡፡ ደበበ ‹‹ግን ንጉሦች ድንጋይ ይሸከማሉ?›› ሲል መጠየቁ፤ ድንጋይ ያልተሸከመን ሰው ህንፃ ገነባ የሚል ታሪክ በስሑት ብዕር የተፃፈ ነጭ ቅጥፈት መሆኑን ለመናገር ነው፡፡
ደበበ እውነቱን ነው፡፡ ንጉሦች ድንጋይ አይሸከሙም። ግን ከድንጋይ የከበደ እና የከበረ ውድ ሐብት አላቸው -ሥልጣን፡፡ የስልጣን መንትያ ወንድም ሐብት ነው፡፡ ሁለቱ ዘወትር እንደ አካል እና ጥላ አይለያዩም፡፡ እነዚህን ሁለቱን ሐብቶች የያዘ ሰው፤ ሲናገር ይደመጣል፤ ቃሉም በአክብሮት ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ ቃሉ የህግን ያህል ጉልበት ይኖረዋል፡፡ እርባና የሌለው ድርጊት እና ክንውኑ ሁሉ ዜና የመሆን አቅም ያገኛል፡፡ ከእርሱ ጋር መተዋወቅ ባይቻለን፤ ስለ እርሱ ለማወቅ እንጓጓለን፡፡ ፊርማውን ማግኘት አኩሪ ገድል ሆኖ ይታያል፡፡ አንዳንዴ ዝና፣ ሥልጣን እና ሐብት የማሰብ አቅማችንን ሰልበው፤ ከፍ ያለ ሥልጣን፣ ሐብት ወይም አኩሪ ሥራ በመስራቱ ዝና ያተረፈ ሰው፤ ሰብዐዊ ፍጡር መሆኑን ወደ መዘንጋት ያደርሰናል፡፡
እንዲህ ያለ ሰው በዝና ወይም የታወቀ ይሆናል። ግን እንደማይታወቅ ሰው ማንነቱ በተለያየ (በጎ ወይም መጥፎ) የፈጠራ ታሪክ ይታጠራል፡፡ ይከበር - ይታፈር ይሆናል። ግን የቀለድ ማዳወሪያ ሊደረግ ይችላል፡፡ ከዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች መፈጠር እና መስፋፋት ጋር ተያይዞ፤ ግለሰቦች በህብረተሰብ አስተሳሰብ እና ድርጊት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ይሰማኛል፡፡ የአንዳንድ ግለሰቦች ውሳኔ፣ ምርጫ፣ ሙገሳ፣ ወቀሳ፣ ድርጊት፣ እንቅስቃሴ ወዘተ እንደ መሬት ዑደት ያለን ቋሚ የተፈጥሮ ስርዓትን እንኳን ማዛባት የሚችል መስሎ ይታየን ጀምሯል፡፡ ለዚህ ለምናገረው ሐሳብ አስረጂ ሊደረግ የሚችል ትኩስ እና ቅርብ የሆነው ምሳሌ፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ነው፡፡ የዚህ ፅሑፌ መነሻ የሆኑት እርሳቸው ናቸው፡፡ ባራክ ኦባማ አንድ ሰው ናቸው፡፡ ግን ዓለምን በፈለጉት መንገድ ለመንዳት እና የታሪክን የጉዞ አቅጣጫ ለመወሰን የሚችሉ አንድ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ ታሪክን መስራት የሚችሉ ናቸው፡፡ ‹‹ሉኣላዊ ነኝ›› ከሚሉ የዓለማችን መንግስታት የሚበዙት፤ በኦባማ ግልጽ እና ስውር ዱላ በቀላሉ መሠረታቸው ሊናጋ ይችላል፡፡ እንኳን ቁጣ እና ኩርፊያቸው፤ ትንሽ ጮህ ያለ ሰላምታቸው፤ የመሬት መንቀጥቀጥ የመፍጠር ኃይል ያለው ይመስላል፡፡
ይህን ያህል ኃያል ሆነው ሳለ፤ ለማንም ሰው ጉልቶ የሚታየው (‹‹ሐበሻዊ››) ልዩ ትህትናቸው ነው። የኢራንን ኒዩክለር የመሳሰሉ እጅግ አሳሳቢ በርካታ የሐገር ቤት እና የዓለም ጉዳዮች የሚያሳስቧቸው መሪ ሆነው፤ የመቀለድ ዕድል ሲፈጠር ዝም ብሎ ለማሳለፍ የማይፈልጉ ሰው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ጉብኝታቸው፤ በተደጋጋሚ ፈገግታ የሚያጭር ንግግር ሲያደርጉ ሰምተናል፡፡ በዚያው ልክ፤ በእርሳቸው ጉብኝት ላይ የሚያጠነጥኑ ቀልዶች (በአሜሪካ፣ በኢትዮጵያ እና በኬንያ) ተነግረዋል፡፡ ይህን በማስተዋል በፖለቲካ እና ቀልድ (በኮሜዲ) መካከል ምን ዝምድና ይኖር ይሆን? ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ከዚህ በታች ያለው ጨዋታ፤ ለጥያቄዬ ምላሽ የምፈልግበት ነው፡፡                     
ፖለቲካ እና ቀልድ
ማልኮልም ሙጌሪጅ (Malcolm Muggeridge)፤ ‹‹ቀልድ፤ የነፃነት አንድ ገፅታ በመሆኑ፤ ነፃነት በሌለበት ቦታ፤ ቀልድ ወይም ዋዛ ከቶ ሊኖር አይችልም›› ይላል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ፤ ‹‹የአሜሪካ ዲሞክራሲ ልዩ መገለጫ ቀለም የመቀለድ እና የመሳቅ ነፃነት ነው›› ሲሉ ፅፈዋል፡፡ ይህን ሐሳባቸውን ለማሳየትም ከ9/11 የሽብር ጥቃት በኋላ በአሜሪካ የተፈጠረውን በንፅፅር ያነሳሉ። ‹‹የሽብር ጥቃቱ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የሥነ- ልቦና ቁስል እና ቀውስ አስከትሏል›› ለማለት የሚያመነቱ አሜሪካውያን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ጥቃቱ፤ የአሜሪካ ዲሞክራሲ መለያ ባህርይ በተባለው የመሳቅ (የመቀለድ) ስሜት እና ነፃነት ላይ ጉልህ ጉዳት መድረሱን ሁሉም ሰው ያምናል፡፡
ጥቃቱ ካስከተላቸው የተለያዩ ተፅዕኖዎች መካከል በደንብ ጉልቶ የታየ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም፤ ማንም ሳያዛቸው የአሜሪካ ሚዲያዎች የቀልድን እና የሳቅ ዝግጅቶች ለተወሰነ ጊዜ የመዝጋታቸው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ ዘግናኝ እና አስደንጋጭ ክስተት ማግስት፤ በአሜሪካውያን ዘንድ የታየው ቀልድ የመስማት እና የመናገር ጉልበት ማጣት ወይም ቀልድን እንደ ነውር ነገር የማየት ልዩ የስሜት መሳሳት (ስሱነት)፤ በሽብር ጥቃቱ የተፈጠረውን ትራጄዲያዊ ድባብ ይበልጥ እንዲጠናከር ያደረገ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ ‹‹የ9/11 ክስተት አንዳንድ የቀልድ ዓይነቶች ከአሜሪካ ህብረተሰብ ዘንድ ጨርሶ እንዲጠፉ ምክንያት የሆነ ክስተት ነው›› እስከማለት ደርሰው ነበር። ለምሣሌ፤ ‹‹የኒውስደይ›› (Newsday) አምደኛ ጀምስ ፒንከርተን (James Pinkerton)፤ ‹‹ክስተቱ፤ ምፀት፣ ሽርደዳ እና ልግጫ (hipness) ከአሜሪካ ምድር እንዲጠፉ ምክንያት የሆነ ሽንፈትን የፈጠረ ነው›› ሲል ፅፎ ነበር:: በእርግጥ፤ ቀደም ሲል (በ1986 ዓ.ም) ቻለንጀር የተሰኘችው መንኩራኩር ሰማይ ላይ በጋየች ጊዜ ለጆሮ የሚከብዱ አላጋጭ ቀልዶች ወዲያው መነገር ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም፤ በ9/11 የሽብር ጥቃት ማግስት፤ አንዲት ቀልድ አልተሰማም። ለወትሮው፤ በአሜሪካ (የእሳት ቃጠሎን የመሰሉ) ከባድ አደጋዎች ሲከሰቱ፤ ወዲያው በርካታ ቀልዶች ይፈለፈላሉ፡፡ ሆኖም በ9/11 ያ የተለመደ የአሜሪካውያን ባህርይ አልታየም፡፡
በተቃራኒው፤ በጥቃቱ ማግስት በነበሩት ጥቂት ሣምንታት፤ የዴቪድ ሌተርማን (David Letterman) እና የጃይ ሌኖ (Jay Leno) የምሽት የቴሌቪዥን ዝግጅቶች ተቋርጠው ነበር፡፡ ቆይተው ዝግጅቶቹ መቅረብ ቢጀምሩም፤ በፕሮግራሞቹ መክፈቻ ይቀርቡ የነበሩት መነባንቦች ቀርተው ነበር።
በእርግጥ፤ አሜሪካውያን በቀልድ እና በዋዛ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ጊዜያዊ ነበር፡፡ ለምሳሌ፤ ከክስተቱ ሁለት ሳምንት በኋላ የታተመውና ‹‹The Onion›› የተሰኘ ምፀታዊ ጋዜጣ፤ በሴፕቴምበር 26፣ 2011 ዓ.ም እትሙ የፊት ገጽ፤ ‹‹እግዚአብሔር ‹አትግደል› የሚለውን ህጉን በቁጣ አብራራው (“God Angrily Clarifies ‘don’t kill’ rule”) በሚል ጉልህ ርዕስ መጣጥፍ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ አንድ ወር ገደማ ካለፈ በኋላ በኦክቶበር 2011 ዓ.ም አደባባይ ወጥተው ለኒውዮርክ ከተማ ህዝብ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ሩዶልፍ ጊዩሊያኒ (Rudolph Giuliani)፤ ‹‹ሰዎች መሣቅ ጀምሩ›› የሚል ግልጽ ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡
ከንቲባ ሩዶልፍ ጊዩሊያኒ፤ በአንድ የበጎ አድራጎት ዝግጅት ተገኝተው በቦታው ለተሰበሰቡት የከተማዋ ነዋሪዎች ንግግር ሲያደርጉ፤ ‹‹እኔ ዛሬ ከመሐላችሁ የተገኘሁት፤ የመሣቅ ፈቃድ ልሰጣችሁ ነው፡፡ ትዕዛዜን በማክበር ካልሣቃችሁ፤ ሁላችሁንም እስር ቤት እከታችኋለሁ›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ቀስ በቀስ፤ አሜሪካውያን መሳቅ ጀመሩ። መሳቅ፤ በጥቅሉ የአሜሪካውያንን፤ በተለይ ደግሞ የኒውዮርክ ነዋሪዎችን የማይሰበር መንፈስ የሚያመለክት ተምሳሌት ተደርጎ ታየ፡፡ በእርግጥ፤ የመሳቅ ነፃነት የአሜሪካ ዲሞክራሲ ልዩ ባህርይ ተደርጎ የሚታይ ከሆነ፤ ከሽብር ጥቃቱ በኋላ የታየው ሣቅ፤ የህዝቡ የመንፈስ ጥንካሬ ተምሣሌታዊ መግለጫ ሆኖ መታየቱ ተገቢ ነው፡፡ የደስታ፣ የልዩነት፣ ራስን በነፃነት የመግለጽ መብት እና ‹‹የመጀመሪያው የህግ ማሻሻያ›› (First Amendment) ልዩ ትርጉም ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ሣቅ (ቀልድ)፤ የአሸባሪዎቹ ልዩ መገለጫ የሆነውን ሣቅ የመጥላት ባህርይን እና አክራሪ ቀኖናዊነት በመቃወም ፀንቶ ሊቆም ይገባል።
አሜሪካዊው ኮሜዲያን ሌዊስ ብላክ (Lewis Black)፤ ‹‹አሸባሪዎች ከቶም ቀልድ የማያውቁ ሰዎች ናቸው›› ማለቱ እዚህ ሊጠቀስ ይገባል፡፡ ሆኖም፤ በሌዊስ ብላክ አስተያየትም ሆነ ከፍ ሲል በተጠቀሱት ሐሳቦች ዙሪያ ጥያቄዎች ሊነሳ ይችላል፡፡ መነሳት ከሚገባቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ፤ ‹‹ለመሆኑ፤ እንደ ልብ ለመሳቅ ወይም ለመቀለድ በመቻል እና በነፃነት የመኖር መብት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖር ይሆን?›› የሚለው ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ አገላለፅ፤ በነፃነት እና በቀልድ ወይም በዋዛ (በስላቅ፣ በሽሙጥ፣ በልግጫ፤) መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? በአጭሩ፤ ፖለቲካ ኮሜዲን (ቀልድን) እንዴት ይመለከተዋል? እንግዲህ አመለካከት እና ዝምድናቸው ምን እንደሚመስል ለማየት፤ ታሪክን በምስክርነት እየጠራን ነገሩን እንመርምር፡፡
የሳቅ ፈላስፋ
በሆሬስ አመለካከት፤ ‹‹ኮሜዲ እውነትን በፈገግታ አዋዝቶ የማቅረብ ጥበብ ነው፡፡›› በሌላ በኩል፤ ቀልድ እና ኮሜዲ ሁሌም በፖለቲካ መሳባቸው አይቀርም፡፡ ገና ከመነሻው፤ ኮሜዲ በፖለቲካ እና የመንግስት አሰራር ጉዳዮችን ወይም የባለስልጣናትን ጉዳይ በማንሳት ይታወቃል፡፡  ‹‹የኮሜዲ አባት›› የሚባለው ፀሐፌ ተውኔቱ አሪስቶፋነስ ነው። አሪስቶፋነስ፤ ብዙውን ጊዜ በኮሜዲ ሥራዎቹ የሚተችና የሚጎነተለው፤ ክፉኛ የሚያብጠለጥል - የሚጎነትለው የአቴናን ታዋቂ ፖለቲከኞች እና ፖሊሲዎቻቸውን ነው፡፡
ከጥፋት የተረፉት አስራ አንድ የአርስቶፋነስ ሥራዎች በሙሉ፤ በዘመኑ ከነበሩ የአቴናውያን ተቋማትንና ከዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ጋር ተያያዥ በሆኑ ፖለቲካዊ ጭብጦች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እንዲሁም በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር የሚያያዙ ፖለቲካዊ ጭብጦችን የሚያነሱ ድርሰቶች በሩ፡፡
የእነዚህ የአርስቶፋነስ ሥራዎች፤ በዛሬው ዘመን በስም ማጉደፍ ክስ ሊያስጠይቁ የሚችሉ ጉዳዮችን የሚያነሱ፤ የመንግስት ባለስልጣናትንና የወታደራዊ መኮንኖችን እንዲሁም በስርዓቱ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ያላቸውን ግለሰቦች ስም በቀጥታ መጥቀስ የተለመደ የዘመኑ ኮሜዲ ሥራዎች መገለጫ የሆነ ባህርይ ነበር፡፡
 አሜሪካውያን ‹‹የሳቅ ፈላስፋ›› የሚሉት ጆን ሞሪል (John Morreal)፤ ቀልድ የሰው ልጆች ሁሉ በተፈጥሮ የታደሉት የማይዝል እና የማይረታ የግፍ እና የጭቆና መከላከያ ጋሻ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ‹‹መሳቅ እና መቀለድ የሚችልን ሰው መንፈስ ሙሉ በሙሉ ማንበርከክ እና መደፍጠጥ አይቻልም፡፡ አንድን ሰው እስር ቤት አስገብቶ ሊያስር የሚችለው መንግስት እንኳን፤ የሰውን የነፃነት መንፈስ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋው አይችልም›› የሚለው ሞሪል፤ ‹‹በፖለቲካ መስክ በሚታዩ ብልሹ አሰራሮች ላይ የማላገጥ እና የመሣለቅ ችሎታ ያለው ሰው፤ በዚያው መጠን በደሉን ቁልቁል የመመልከት ዕድል ይኖረዋል። ምናልባት፤ ወህኒ የወረወረው መንግስት የመንቀሳቀስ ነፃነቱን ሊገድበው ይችላል። ሆኖም፤ ቀልድ የነፃነት መንፈሱን በሆነ መንገድ ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ዕድል እና ችሎታን ይሰጠዋል›› ይላል፡፡
በሌላ በኩል፤ ጣሊያናዊው ሎርድ ሸፍስተበሪ (Lord Shaftesbury) በ1709 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በፃፈው አንድ መፅሐፍ ያሰፈረው ሐሳብ ከፍ ሲል ከጠቀስኩት የጆን ሞሪል ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹‹Sensus Communis›› በተሰኘው በዚሁ መፅሐፍ ያሰፈረው ሐሳብ፤ ቀልድ የማህበራዊ ፍትህ እጦት የሚያስከትለውን ቁጣ እና ቁጭት የማርገብ ብቃት እንዳለው ያመለክታል፡፡ እንደ ሸፍስተበሪ (Lord Shaftesbury) ሐሳብ፤ አንድ ሐገር ወይም የአንድ ሐገር ህዝብ ለኮሜዲ የሚኖረው ፍላጎት፤ በዚያ አገር ከሚታየው የፖለቲካ ጭቆና ጋር ቀጥተኛ ጉድኝት አለው፡፡ በሌላ አገላለፅ፤ ጭቆና ሲበዛ፤ በዚያው መጠን የህዝቡ የኮሜዲ ፍላጎት ይጨምራል ነው። ይህ ሐሳብ አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም፤ ፀሐፊው በጣሊያን ይፈፀም ነበር ስለሚለው ‹‹መንፈሳዊ ጭቆና›› (Spiritual Tyranny) ሲያትት እንደሚከተለው ይላል፤
‹‹ጣሊያናውያንን የሚያስንቅ ወይም የሚያስከነዳ ቀልደኛ ህዝብ በዓለም ውስጥ አይገኝም፡፡ ጣሊያናውያን ቁጥር አንድ ኮሜዲያን ናቸው፡፡ በጽሑፋቸው፣ በተራ የቡና ወሬዎቻቸው፣ በቲያትር ቤቶች እና በጎዳናዎች ሁሉ ሳቅ እና ስላቅን እንደ ትልቅ ፋሽን ወደው ይዘውታል። መፈናፈኛ ያጡ ጎስቋላ ድሆች፤ ሐሳባቸውን በነፃነት ለመተንፈስ የሚችሉበት ቀዳዳ ቀልድ ሆኗል… የመከራው ሸክም በከበደ መጠን፤ መራራ ምፀቶች እንደ አሸን ይፈለፈላሉ፡፡ የባርነት ቀንበሩ ሲከብድ፤ በዚያው ልክ የቀልዶቹ ውበት እና ርቀት እየጨመረ ይሄዳል፡፡››
በእርግጥ፤ ቀልድን እንደ ተፈጥሯዊ የነፃነት መግለጫ አድርጎ የማቅረብ ነገር ችግር እንዳለው ይገባኛል፡፡ ስለዚህ፤ የሸፍስተበሪን ገለፃ ‹‹ትንሽ የኳሸ ነው -Over romanticized›› ብለው የሚተቹም አሉ፡፡ በእርግጥ በሳቅ እና ቀልድ ሊጽናና/ወይም ሊታገስ የማይችል መከራ እና ችግር ማሰብም ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሐቅ ፍንትው ብሎ ይታየኛል፡፡ ብዙ መንግስታት ያፀኑትን ሥርአት የማናጋት ጉልበት ያላቸው ቀልዶችን ለመቆጣጠር ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ሲከፋም በቀልድ የተነሳ ቅጣት የሚጥሉ መንግስታት መኖራቸውን ከተጨባጭ የታሪክ ሁነቶች መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ፤ ሰር ሮበርት ዋልፖል (Sir Robert Walpole) በመንግስቱ ላይ የሚሰነዘሩ ምፀታዊ ሽንቆጣዎችን ለመከላከል ያስችላል ብሎ፤ በ1737 አንድ ህግ አውጥቶ ነበር፡፡
በሌላ በኩል፤ አዶልፍ ሂትለር ልዩ ‹‹የቀልድ ችሎት›› (Joke court) አቋቁሞ ነበር፡፡ በሰርድሪክ ላይ ሊተኮስ የሚችለው የቀልድ አዳፍኔ ጥቃት ያስጨነቀው አዶልፍ ሂትለር፤ የቀልድ ችሎት ከማቋቋም አልፎ፤ ፈረሶቻቸውን ወይም ውሾቻቸውን ‹‹አዶልፍ›› ሲሉ የሰየሙ ጀርመናውያን እንዲቀጡ አድርጓል። በበርሊን የምሽት ክለቦች ቀልድ በማቅረብ የሚታወቀው ወርነር ፊንክ (Werner Finck)፤ የናዚ አገዛዝ ሐሳብን በነፃነት በመግለፅ መብት ላይ የጣለውን ገደብ በመቃወም አንድ የስላቅ ስዕላዊ ንድፍ (Sketch) ሰርቶ ነበር፡፡
በዚህ የተነሳ ወርነር በ1935 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ወደ ናዚ የማጎሪያ ካምፕ ተወስዶ ታስሮ ነበር።  በሩሲያም ተመሳሳይ ታሪክ መኖሩን እናያለን። በሩሲያ የኮሚኒስት ፓርቲ እና በአመራሩ ላይ ኪነጥበባዊ ስልቶችን ተጠቅሞ ትችት ማቅረብ ፈፅሞ የተከለከለ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ትችት ለመሰንዘር የደፈረ ሰው የግዴታ የጉልበት ሥራ የሚያሰሩ ወህኒ ቤቶች ይላክ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የነፃነት አርማ ተደርጋ በምትታየው አሜሪካ ተመሳሳይ የታሪክ ሁነቶችን እንመለከታለን፡፡ በዚህ ረገድ የሚጠቀሱት አሳፋሪ የታሪክ ቅርሶች የታዩት በ1950ዎቹ ነበር፡፡ ታዋቂው ሴናተር ጆሴፍ ማካርቲ (Joseph McCarty) በአሜሪካ ምክር ቤት ያቋቋመው አንድ ኮሚቴ ነበር። ‹‹አሜሪካዊ ያልሆኑ ተግባራት መርማሪ ኮሚቴ›› በሚል የሚታወቀው ኮሚቴ፤ የኮሚኒስት ሥርዓት ወዳጆች ሆነው ወይም መስለው የታዩ ሰዎችን የመንቀል እና በሐገር መክዳት ሴራ ገብተው የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን ለማምከን ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡
በዚህ ወቅት፤ ሁኔታው ሥጋት የፈጠረባቸውና በማካርቲ የጥቁር መዝገብ የመስፈርና የእስር አደጋን ለመሸሽ የፈለጉ ኮሜዲያኖች ድምጻቸውን አጥፍተው ነበር፡፡ አሜሪካውያንን በሐፍረት የሚያሸማቅቀው የዚህ ዘመን ተግባር፣ቻርሊ ቻፕሊንን ከአሜሪካ አሳድዶታል። የማካርቲ የአፈና በትር ሰለባ ከሆኑ ሥራዎች መካከል ላይምላይት (Limelight) የተሰኘው የቻርሊ ቻፕሊን ፊልም አንዱ ነበር፡፡ ላይምላይት (Limelight) የፖለቲካ ይዘት ያለው ፊልም ባይሆንም፤ ሚሊየነሩ ቻርሊ ቻፕሊን ለሠራተኛው መደብ አባላት የበዛ ፍቅር እንዳለው ሊያመለክት የሚችል ድርሰት ነው፡፡
እንግሊዛዊው ቻርሊ ቻፕሊን፤ ለረጅም ጊዜ በአሜሪካ ቢኖርም ዜግነቱን አልለወጠም፡፡ አንዳንድ ምሁራን ‹‹የማካርቲ ዘመን›› (McCarty era) በሚል በሚጠቅሱት በዚያ ዘመን፤ ቻርሊ ቻፕሊን ከአሜሪካ ወጣ ብሎ ለመመለስ ሲሞክር ችግር ገጠመው፡፡ ‹‹የኢሚግሬሽን መርማሪ ቦርድ›› (Immigration Board of Inquiry) ከተባለ አንድ ኮሚቴ ፊት ቀርቦ፤ ለሚቀርቡለት ‹‹ከፖለቲካ እና ከሞራል ውድቀት›› ጋር ተያያዥ ለሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ክልከላ ተጣለበት። በዚህ የተነሳ፤ አሜሪካን ትቶ ወደ ስዊዘርላንድ በመሄድ መኖሪያውን በዚያ አደረገ፡፡ ከዚያ ክልከላ በኋላ ቻፕሊን ወደ አሜሪካ የሄደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም፤ በ1972 ዓ.ም የኦስካር ሽልማቱን ለመቀበል ያደረገው ጉዞ ነበር።
በመጨረሻ
ኮሜዲ፤ ሐሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት ጠበቃ የመሆን ታሪክ እንዳለው ሁሉ፤ በተቃራኒው ጭቆናን የመደገፍ ሚና ይዞ የሚታይበት የታሪክ አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ለምሣሌ፤  በአንዳንድ የኮሜዲ ሥራዎች ውስጥ የሚታየው ፆታ እና ዘርን መሠረት ያደረገ የማጥላላት ተግባር፤ የጥቃት ዒላማ የተደረጉት ማህበራዊ ቡድኖች፤ የራሳቸውን ማንነት ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረት ለማጣጣል ይሁነኝ ተብሎ የሚደረግ ‹‹የኃይል ትርክት›› (discourse of power) ተቀባይነት እንዲያገኝና እንዲጠናከር ሊያደርግ ይችላሉ፡፡ እንዲያውም፤ በአልበርት ኩክ (Albert Cook) አመለካከት፤ ‹‹ኮሜዲ በወቅቱ የሚገኘውን ህብረተሰብ የማነወር ሳይሆን የማሞካሸት ሚና ያለው ነው፡፡ ኮሜዲ ወግ አጥባቂ እንጂ ሊበራል አይደለም›› ይላል፡፡

Read 5262 times