Saturday, 01 August 2015 14:18

በመተወንም ሆነ በመዘመር እያሳቅንም ሆነ እየገጠምን

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

  የውሃ ሀብታችንን እንጠብቃለን - አርቲስት ችሮታው ከልካይ
                               
      የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለሥልጣን ከግሪን ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ጋር በመተባበር በተፋሰሱ የሚገኙትን ሐይቆች ከጉዳት ለመከላከል “ሐይቆቻችንን መጠበቅ የቀን ተቀን ሕይወታችን ሲሆን ይገባል” በሚል መርህ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ የንቅናቄ ፕሮግራም ጀምሯል፡፡ ከንቅናቄ ፕሮግራም ዘዴዎች አንዱ አርቲስቶች ሐይቆቹ ያሉባቸውን ችገሮች ተረድተው በሙያቸው ኅብረተሰቡን እንዲያስተምሩና ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ ማድረግ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት ከትናንት በስቲያ በሀርመኒ ሆቴል ለግማሽ ቀን በተዘጋጀ ፕሮግራም አርቲስቶቹን በመጋበዝ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች አሁን ያለባቸውን ችግር፣ ወደፊት ሊደርስ ይችላል ተብሎ የተፈራውን ስጋት አሳውቋል፡፡ አርቲስቶቹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱን ከተከታተሉ በኋላ “ውሃ ሕይወት ነው” የሚለውንና ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚያውቁትን አባባል በዕለቱ በተደረገላቸው ገለፃ ከአባባልነት ባለፈ ውሃ በእርግጥም ሕይወት መሆኑን፣ እንስሳትም ሆኑ ዕፅዋት ያለውሃ ሕልውና እንደሌላቸው መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
እስከዛሬ ድረስ ስለሐይቆች ያለን ግንዛቤ መዝናኛነታቸው ነበር፡፡ በዛሬው ትምህርት ስለውሃ ብዙ ተገንዝበናል፡፡ ውሃ ሕይወት ነው ከሚለው የዘለለ ግንዛቤ አልነበረኝም ያለው አርቲስት ችሮታው ከልካይ ውሃ ለፍጡራን ሁሉ ያለውን ጥቅም፣ በሕይወት መኖርም ሆነ ዕድገት ከውሃ ውጭ በጭራሽ እንደማይታሰብ መገንዘቡን ተናግሯል፡፡ ውሃን ብንጠብቅ ሕልውናችን እንደሚጠበቅ ተረድተናል፡፡ ውሃ ስንል ለአንደበታችን ቀላል ይመስላል። ውሃ ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ሰዎች ለመኖር፣ ዕፅዋት ለማደግ፣ ገበሬው ለእኛ ለሚያቀርበው ምርት፣ ለሚያረባቸው እንስሳት፣ … ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን፣ ነገር ግን ለውሃ ትኩረት ባመስጠታችን የሚደርሰውን ጉዳት ተረድተናል ብሏል፡፡
ማንኛውም ሰው ውሃ እንዳያልቅ በአግባብ መጠቀም፣ እንዳይቆሽሽና እንዳይበከል ቆሻሻን በጥንቃቄና በተገቢው መንገድ ማስወገድ እንዳለበት ተረድቻለሁ ያለው አርቲስቱ፡፡
የውሃ መቀነስና መበከል ለትውልድ የሚተላለፈ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትል ተረድተናል፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ ማስተማርና መቀስቀስ ያስፈልጋል፡፡
እየተወንም ሆነ እየዘመርን፣ እያሳቅንም ሆነ እየገጠምን ውሃን እንጠብቃለን በማለት ገልጿል፡፡
የሐይቆች የመጥፋት አደጋ በሐሮማያ ላይ ብቻ የተከሰተ አለመሆኑን የገለፀው የቲያትር ደራሲው ውድነህ ክፍሌ ሌሎች ሐይቆችም ይኸው ጥፋት እንዳንዣበበባቸውና ትግራይ ውስጥም የጠፋ ሐይቅ መኖሩን ተናግሯል፡፡ ውሃው (ሐይቁ) የነበረበትን ዙሪያ ገበሬዎች እያረሱ ነው፡፡ አደጋ ከፊታችን ተደቅኗል ማለት ነው፡፡ በዓይናችን እያየን ያለው የገጸ ምድር ውሃ እየጠፋ ነው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ከአርቲስቶች ብዙ ይጠበቃል።
የፕሮግራሙ
አዘጋጆች እኛን ያስተማሩትና ያሳወቁን ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተን በሚረዳው ቀላል መንገድ ግንዛቤውን ከፍ እንድናደርግ ነው ያለው ደራሲ ውድነህ ክፍሌ ወደ ሐይቆቹ እየሄድን የተደቀነባቸው አደጋ የፈጠረብንን ውስጣዊ ስሜት በመግለጽ ውጤታማ የግንዛቤና ቅስቀሳ እንደምናደርግ እርግጠኛ ነኝ ብሏል፡፡  
አርቲስት አስቴር ዓለማየሁ በበኩላ፣ የሀሮማያ ሐይቅ መድረቅ በቴሌቭዥን ሲተላለፍ አይቼ በጣም አዝኜ ነበር። አሁን በተሰጠን ትምህርት ሌሎች ሀይቆችም ተመሳሳይ ዕጣ እየጠበቃቸው መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እንደዜጋና እንደሙያተኛ ኃላፊነት እንዳለብኝ ተስምቶኛል፡፡ ህዘቡ ይወደናል፣ ያከብረናል፡፡ ህዝቡ የሰጠንን የፍቅር ሀብት በመጠቀም ህብረተሰቡ ውስጥ ገብቼ በመቀስቀስና በማስተማር የዜግነት ድርሻዬን ለመወጣት ተነስቻለሁ በማለት ስሜቷን ገልጻለች፡፡
የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክር ዶ/ር ከበደ ካንቹላ ውሃ በህይወት ለመኖር አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ለዕድገትም አስፈላጊ መሆኑን ሲገልጹ፤ … የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፣ የቤቶች ግንባታ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ … ማንኛውም ግንባታ የሚሰራው ሲሚንቶና ውሃ ሲደባለቅ ነው፡፡ ዳንጎቴ፣ ሙገር፣ ደርባ፣ መሰቦ፣ … የፈለገው ዓይነት ሲሚንቶ ቢሆን ያለ ውሃ አንዳች የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ሲሚንቶ‘ኮ የተቃጠለ  አመድ ነው ያሉት በማለት አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ከበደ ስለውሃ ጠቀሜታ በስፋት ካስረዱ በኋላ ሐይቆቹ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ጠቅሰው፤ አደጋዎቹም የሐይቆች መበከልና የውሃ መቀነስ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ “የፍቅር ሐይቅ” የሚባለው የሀዋሳ ሀይቅ፣ ፍቅረኛሞች ሲዝናኑ ለመጠጣት ይዘው የሄዱትን ውሃ ሲጨርሱ የውሃውን መያዣ ፕላስቲክ ሐይቁ ውስጥ ስለሚጥሉና በሌሎችም ቆሻሻዎች መበከሉን፣ የዝዋይ ሐይቅ ደግሞ በመሬት መራቆት የተነሳ ደለል ስለሚገባበት እንዲሁም በምዕራብ ጎኑ ብቻ በ6 ሺ ፓምፖች ለመስኖ ውሃ ስለሚሳብ ውሃው እየቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በያዝነው በጀት ዓመት (2008) በዝዋይ - ሻላ፣ ሀዋሳ፣ አባያ - ጫሞ ሐይቆች በዘላቂና የተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ከብክለትና ከደለል ሙላት ለመከላከል ፕሮጀክት ቀርፀውና ለመንግሥት አቅርበው ከመደበኛ በጀት ሌላ 24 ሚሊዮን ብር እንደተፈቀደላቸው ተናግረዋል፡፡
ለእያንዳንዱ ሐይቅ ከአርቲስቶች አምባሳደር ይሾማሉ ያሉት ደግሞ የግሪን ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲል አስማማው፣ በየቴአትር ቤቶቹ ግንዛቤ እንዲፈጠር ሐይቆቹን እንደሚያከፋፍሉ፣ ከህብረተሰቡ ጋር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚሰሩ፣ … ገልጸዋል፡፡

Read 1422 times