Saturday, 01 August 2015 14:54

የኦባማ ንግግር ይሄን አስታወሰኝ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የሰላም ጓዶች አስደማሚ ጋብቻ
   ፕሬዜዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው ሐምሌ የማርያም ዕለት ከሰአት በኋላ   በአፍሪካ ህብረት ኔልሰን ማንዴላ  አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ በመላው አፍሪካ ከተሰማሩት የአሜሪካ የሰላም ጓዶች  ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት  ናቸው ማለታቸው እውነታቸውን ነው፡፡ ከእነኝህ ወጣት አሜሪካዊያን  የሠላም ጓዶች  መካከል አንዱ የሥራ ባልደረባዬ ነው፡፡ ታዲያ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን  ንግግር ስሰማ፣ ይኸ የሠላም ጓድ  እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ከአገሩ ልጅ ጋር  ያደረገው የጋብቻ ስነ ሰርአት ትዝ አለኝ፡፡
ይህ  ባልደረባችን  ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ አንድ እሮብ ከሰአት በኋላ እያንዳንዳችን ጋ እየመጣ “ተነገ ወዲያ አርብ ሠርጌ ነው፤ ስለዚህ በ12፡30 ከኢድናሞል ወረድ ብሎ በሚገኘው--- ሬስቶራንት እንገናኝ፤ አለባበስ ቀለል ያለ ይሁን፤ሱፍና ክራቫት አስፈላጊ አይደለም” ብሎ ነገረን፡፡ እኛም ˝..ጥላኝ ሄደች በሀምሌ ጨለማ..˝ በሚባልበት የክረምት ወራት የሚደረግ  የፈረንጅ ሰርግ ላይ  ለመታደም   በሶሻል ኮሚቴአችን አማካኝነት መጠነኛ ስጦታ አዘጋጅተን የእራት ግብዣው ቦታ ተገኘን፡፡ ሙሽሮቹ እስኪመጡም ቢራችንን እየጠጣን ጠበቅናቸው፡፡
ወደ አመሻሹ ላይ ሙሽራው ሻሩናስና  ሙሽሪት ኤሪካ  እግብዣው ቦታ ሲደርሱ ደስታ በፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር፤  ይፍነከነካሉ፤ያገኙትን ሁሉ መሳም ፤አብሮ ፎቶ መነሳት፤የሰርግ እለት ወሎአቸውን ማስረዳት፤በደረሱበት ጠረጴዛ ሁሉ መጠጥ ማስቀዳት፤ብቻ ምን አለፋችሁ ደስታቸው መጠን ያለፈው ሆነ፡፡ ሙሽሮቹ በተናጠል እያንዳንዱ ጠረጴዛ ላይ እየሄዱ  የሰርጋቸውን አዋዋል ይነግሩን ገቡ፡፡ የሙሽሮቹን  የሠርግ ቀን  ውሎ  እስቲ ላስቃኛችሁ፤
ሙሽሪትና ሙሽራው አዘውትረው በርገር ወደሚበሉበት ካፌ ሄደው ቁርስ ከበሉ በኋላ ዘወትር እንደሚያደርጉት ሁሉ ወደሚያውቁት ሊስትሮ ሄደው ጫማቸውን በማስጠረግ የሠርግ ቀናቸውን ጀመሩ
ወደ ውጪ ጉዳይ ሚ/ር  በመሄድ የጋብቻ ሰርተፊኬታቸውን  ለማግኘት  የሚያስችለውን  ወረቀት አገኙ
ወደ ጉለሌ ክ/ከተማ የወሳኝ ኩነቶችና የኗሪዎች አገልግሎት ጽ/ቤት ሄደው የጋብቻ ፊርማቸውን  በማኖር፣ የጋብቻ ሰርተፊኬታቸውን ተቀበሉ፤የቀለበት ስነሰርአታቸውንም በዛው አካሄዱ
የወረቀት ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሙሽሮቹ ቀደም ሲል  በተደጋጋሚ  ወደተዝናኑበት  አንዲት መኪና ተከራይተውና ፎቶግራፍ የሚያነሳውን ጓደኛቸውን ይዘው  ወደ  እንጦጦ ተራራ አቀኑ፡፡ እንጦጦ ተራራ ላይ ከሚኖሩ  ሀጻናት ጋር  በተለይ ሙሽሪት ˝ እቴ እሜቴ የሎሚ ሽታ ˝ ን  ተጫወተች ፤ሙሽሮቹ እከብቶች ግጦሽ ሜዳ ላይ ተንሸራሸሩ፤ፎቶ ተነሱ፤ተሳሳሙ፤ታስሮ እንደተለቀቀ እምቦሳ ቧረቁ፤ አንድ ጎጆ ቤት ገብተው የሚወዱትን ጠላ ጠጡ፤ የእንጦጦ ህጻናት ˝መልካም ጋብቻ˝ በማለት እቅፍ አበባ አበረከቱላቸው
ከእንጦጦ መልስ እግረ መንገዳቸውን ሽሮ ሜዳ የአገር ልብስ መሸጫ ሱቅ ወዳለው  ጓደኛቸው  ጎራ ብለው ሰርጋቸውን እያከበሩ መሆናቸውን በመንገርና በማስደመም  ጓደኛቸው  ሱቅ ውስጥ ፎቶ ተነሱ፤ተያይዘውም በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጠጅ ቤት ሄደው ጠጅ ጠጡ፤ ጠጅ ቤት ለነበሩት መሸተኞች ሙሽሮች መሆናቸውን በመግለጥ መሸተኛውን የሰርጋቸው ደስታ ተካፋይ አደረጉ፤ ፎቶም ከመሸተኛው ጋር ተነሱ፡፡
 ከዛም ሙሽራው በተደጋጋሚ ምሳ ወደሚበላበት ሬስቶራንት ሄደው በኢትዮጵያዊ ጉርሻ የታጀበ እንጀራ በወጥና ፒዛ በሉ
ወደ አዲስ አበባ መሀል ከተማ መስቀል አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት አንድ በግ ተራ በመሄድ ከበግ ሻጮች፤ ገዢዎችና ከበጎቹ  ጋር ፎቶ ተነሱ
መስቀል አደባባይ እንደደረሱ አላፊ አግጋዳሚውን ሰብሰብ በማድረግ ጮክ ብለው  ˝ “ወዳጆቻችን ፤ዛሬ ሰርጋችን ነው!˝ ብለው ገለጻ ቢጤ አደረጉ፤ከዛም ሙሽሪት የያዘችውን እቅፍ አበባ ወደ ሰማይ በተነችው፤ የተሰበሰበው ጥቂት  ተመልካችም አበባውን እየተሻማ ተቀራመተው
ከዛ ወደ ቤታቸው በመሄድ እረፍት አድርገው እራት ወደተዘጋጀበት ሬስቶራንት አመሩ
እኛ ታዳሚዎች ዘመን የማይሽረውን ˝ ሙሽራዬን˝ እያዜምን ተቀበልናቸው፤ቁጥራችን ከ35 አይበልጥም ነበር
የምግብና መጠጥ መስተንግዶው ቀጠለ፤ከሁሉም አገሪቱ ማዕዘናት  ያሉ ባህላዊ  ጨዋታዎች ድምጻቸው  ከፍ  ብሎና ከቀደምት የእንግሊዝኛ ዘፈኖች ጋር ተቀላቅሎ   ተደመጡ፤እስክስታ ተመታ፤ዳንሱ ቀለጠ
 በመጨረሻ የኬክ መቁረሱ ሥነስርአት ተከናወነ፤ እሱንም ተከትሎ ከዚህ በታች የምታዩት የሙሽሮቹ ፎቶግራፍ በጥሩ ፍሬም ሆኖ  በስጦታ መልክ  ተበረከተላቸው፡፡ እኛ ስጦታውን ስናበረክት ከእኛ ቀድሞ ይህ  ምስልና  የሙሽሮቹ የሰርግ  ቀን ውሎ በፌስ ቡክና በኢንስታግራም ተለቆ ነበር ፡፡
 በሰርጉ ማግስት  ከሙሽራው ጋር ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡
˝ሻሩናስ ፤ሰርግህን  አስመልክቶ አንድ ጽሁፍ ብጽፍ ፈቃደኝ ነህ?”
˝አዎ ግርማ ደስተኛ ነኝ ፤ሰርጋችንን ወደድከው?”
˝አዎ በጣም ወድጀዋለሁ፤ለእኛ  ወጣቶች እንደ ሞዴል ጋብቻ አድርጌ ስለአየሁት በሰርጋችሁ ላይ አንድ ጽሁፍ  ጋዜጦች ላይ አወጣ ይሆናል ˝
˝ግርማ በጣማ ደስተኝ ነኝ፤ የሰርጉን ፎቶዎች በሙሉ ሰርቨር ላይ እጭናቸዋለሁ ፤ በተጨማሪም  አንድ ጓደኛዬ ፖስት ያደረገውንም እልክልሃለሁ˝
˝በጣም ጥሩ፤ፎቶዎቹ ለጽሁፌ መነሻ  ይሆኑኛል˝
በመጨረሻም በሚቀጥለው ጥቅምት 2008 ላይ 23ተኛ አመቴን የማከብረውን፤ ከሽማግሌ መላክ እስከ ቅልቅል ድረስ ያለውን ኮተተ ብዙ የአበሻ ሰርግ ሁደት  እያሠብኩ፤
˝ሻሩናስ ፤አንድ ጥያቄ  ልጠይቅህ ከወላጆቻችሁና፤ ከዘመዶቻችሁ እርቃችሁ ሰርጋችሁን ለምን በኢትዮጵያ ምድር  ላይ  ለማድረግ  ወሰናችሁ?
˝ ግርማ፤ ለእኔና ለባለቤቴ ኤሪካ ኢትዮጵያ ልዩ ቦታ አላት፤ ስለሆነም  ሰርጋችንን  እዚሁ  በህይወታችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ ካላቸው ወዳጆቻችን፤ ከህጻናት ጋር ፤የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ስሜት የያዘ፤ አዘውትረን  የምንሄድባቸውን ቦታዎችና ጓደኞቻችንን  የሚያስታውስ ፤ ኢትዮጵያዊ  ስሜት ያለው   እንዲሆንልን  ስለፈለግን ነው˝ ብሎ መለሰልኝ!!
ወጣት ፍቅረኞች  እናንተስ? እኔ መቼም  ይህን ሰርግ ወድጄዋለሁ፤ ከተለመደው ኮተተ ብዙ  የአበሻ  ሰርግ ይልቅ ይኸ ቅልብጭ ያለ የሰላም ጓዶቹ  ሰርግ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ሰርጉ ቀላል፤ አሳታፊና ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ  ባለፈው የማሪያም ዕለት በንግግራቸው የጠቀሷቸው  የሰላም ጓዶች በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል  ከንግድና  ኢንቨስትመት  ትስስሩ ጎን ለጎን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ላይ ናቸው፡፡ በላእላይ መዋቅር ደረጃ  በእምዬ ምኒልክ ጊዜ የተጀመረው  የኢትዮ-አሜሪካ መልካም ግንኙነት፣ በታህታይ መዋቅሩም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሲጠናከር መሰረተ ሰፊና ስር የሰደደ ይሆናል፡፡
ሰለዚህ  ፕሬዚዳንት ኦባማ ሆይ፤ እባክዎትን ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩልንን  የሰላም ጓዶች   የወንድና የሴቱን ቁጥር ባመጣጠነ መልኩ ከፍ ያድርጉልን፤ እኛ ከዚህ እያጋባን እንልካቸዋለን! 

Read 2640 times