Saturday, 01 August 2015 14:28

በ“ጳጉሜ 6” ላይ ለቀረበ ተቃውሞ ማፍረሻ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

 በፋሲል ጣሰው ታደሰ፤ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምርት ክፍል

   1. መግቢያ
ይህ መጣጥፍ “ጳጉሜ ስድስት” ሥለየትኛው ዘመን መቁጠሪያ ነው የሚናገረው? በሚል ርዕስ በአቶ ሰሎሞን አበበ ቸኮል ተፅፎ ጥቅምት 23, 2006 ዓ.ም በአዲስ አድማሰ ህብረተሰብ አምድ ስር ለቀረበው ተቃውሞ ማፍረሻ የቀረበ ነው፡፡
በአጠቃላይ “ጳጉሜ ስድስት” ሥለየትኛው ዘመን መቁጠሪያ ነው የሚናገረው? በሚል ያነሱት የመከራከሪያ ርእስ ራሱ የሚያስተላልፈው ጠቃሚ መልእክት ነው፡፡ በመሆኑም ጳጉሜ 6 የተሰኘውን አዲስ የጊዜ መጽሐፍ የሚያነብ ሰው ስለ ኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የሚያገኘው አዲስ ጭብጥ ከመጸሐፉ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን የሚገልጽ መልእክት ነው፡፡ ስለዚህ የመረጡት ርእስ ጳጉሜ 6 ስለ ጊዜ ፍጹም የሚናገር መጽሀፍ መሆኑ የመጀመሪያ ማረጋገጫ ውጤት ነው። ምክንያቱም በየ4 አመት አንዴ ብቻ በሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድረ ሰማይ በመከሰት በእጅ ሰዓትና በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ላይ የሚመዘገበውን የጳጉሜ 6 እለት በጥንታዊው ሐሳበ ዘመን አስተምህሮት ዘዴ ውስጥ በፍጹም አለመታወቁን በሚመለከት (በተቃውሞ ስም) በጽሁፍ እንዲመሰከሩበት  ማስገደድ በመቻሉ  ነው።
እንዲሁም ጳጉሜ 6፣የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የማን ነው? የተሰኘው መጽሐፍ በእኔ ኢኮኖሚክስ መምህሩ ፋሲል ጣሰው መቅረቡን፣ ስለቀን መቁጠሪያው የማያጠያይቅ ደገኛ ሃሳብ ይዤ ማጥናቴንና መመርመሬን፣ በእጅጉ የለፋሁበትና አብዝቼ የተጠበብኩበት መሆኑንና የአመትና ወራቱንም እርዝማኔወች በማጥናት ጠለቅ ያለ አድካሚ ምርመር ማድረጌን ያረጋገጡበት የምስክርነት ቃል የሚያስመሰግኖዎት ቢሆንም በሌላበኩል (የተቃውሞ ፅሁፍ እንዲፅፉ የተገደዱበት) ጳጉሜ ስድስት መፅሀፍ በጭራሽ ስለኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያ ነው ለማለት የሚከብድ የምርምርና የጥናት ስራ ነው ማለትዎ በእርግጥም ካለጥናትና ምርመር ዘዴ ባልገባዎት እና ባላወቁት ጉዳይ ወደ ክርክር መግባትዎን ያሳያል፡፡
ስለዚህ እጅግ ቀላል ነገር ግን ፍፁም አዲሱን አንጻራዊ የጊዜ የጥናትና ምርምር ስራ ውጤት የሆነውን ጳጉሜ 6 መፅሀፍ ደጋግመው ቢያነቡት ኖሮ የተከተልኩትን ዘመናዊ የጥናትና ምርምር አሰራር ዝርዝር ስልቶች (ጥናቱ የሚፈታቸው መሰረታዊ ተድጋራቶች፣ አላማው፣ ግቦቹ፣ ጊዜ ሽፋኖች፣ መረጃ አይነቶችና ምንጮች፣ የጥናቱ ግኝቶችና ትንተናዎች ወዘተ) ስለሚያውቁና ስለሚገባዎት ባልተቃወሙ ነበር ወይም መፍረስ የሚችልም ከሆነ የማፍረሻ መንገዱን ያውቁት ነበር፡፡
ስለዚህ ያደረጉት ክርከር በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ መረጃ ላይ የተመሰረተ ባይሆንም ከዚህ ቀጥሎ በተመለከቱት 2 ነጥቦች ላይ መልስ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ (1ኛ) በጳጉሜ 6 መፅሃፍ የቀን መቁጠሪያ ወሮች ትችታዊ ዳሰሳ ክፍል ስር ባለመካተቱ የተመሰከረበት ባህረ ሐሳብ፣ (2ኛ) የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ተግባራዊ ጥቅም አውርደን ተጠቀምን ማለት የሚቻለው መቼ ነው?
2.. በጳጉሜ 6 መፅሃፍ የቀን መቁጠሪያ ወሮች ትችታዊ ዳሰሳ ክፍል ስር ባለመካተቱ የተመሰከረበት ባህረ ሐሳብ
“በ1990ዎቹና ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ብቻ አስር የሚጠጉ ጽሑፍች በመጽሐፍ በድረ ገጽ እና የምርምርና ጥናት ሥራዎች፣ዓውደ ጥናቶችና ዓውደ ርዕይ ቢቀርቡበትም አለቃ ያሬድ ፈንታ ካሳተሙት ባህረ ሐሳብ መጽሐፍ በስተቀር ሁሉም እንክን አላባቸው”
ከላይ በጥቅስ የተመለከተው የአቶ ሰለሞን አበበ ድምዳሜ፤ ጳጉሜ 6፣ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የማን ነው? የተሠኘውን አዲስ ሳይንሳዊ የጊዜ መጽሃፍ በተቃውሞ ስም እጅግ ተቀባይ መሆኑን ለማረጋገጥ የቀረበ ደጋፊ ክርክር ሁኖ ተወስዷል፡፡ ምክንያቱም የመሰከሩበት ባሕረ ሐሳብ የተሠኛው የአለቃ ያሬድ ፋንታ መፀሃፍ በጳጉሜ 6 መፅሐፍ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ወሮች ትችታዊ ዳሰሳ ክፍል ውስጥ ባለመካተቱ ብቻ ሳይሆን ራሱ ያሉት ባሕረ ሐሳብ መጽሐፍ ጳጉሜ 6ን ስለማያውቅ ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም  መከራከሪያ ሐሳቡ ቀጥለው የተመለከቱት አበይት እንከኖች አሉበት፡፡
ሀ). ከዚህ በፊት በቀን መቁመሪያው ዙሪያ የተደረጉት ሁሉም ጽሁፎች ውስጥ የሚታየው እንከን  የርሶዎ ግኝት አይደለም
ባለፋት 16 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ በሚመለከት ወደ 10 ጽሁፎች በመፀሃፍ፣ በድረገፅ ፀዘተ ቢቀርቡበትም ከአንዱ መፀሃፍ በስተቀር ወደ ዘጠኝ ያህሉ ውድቅ ናቸው፤ የሚለው ሀሳብ የፀሃይ ቀን መቁጠሪያ እውቀት ፈጣሪና አረጋጋጭ ባለሥልጣን የሆኑ ያስመሥልብዎታል፡፡
እንዲሁም ከዚህ በፊት በቀን መቁመሪያው ዙሪያ የተደረጉት ሁሉም ጽሁፎች እንከን አለባቸው በሚል የሞገቱ መሆኑን አላሳወቁም፡፡ ስለዚህ የጳጉሜ 6 መፅሐፍ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ወሮች ትችታዊ ዳሰሳ ክፍል ውስጥ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ቀን መቁመሪያው ዙሪያ የተደረጉት ጽሁፎች እንከን ያለባቸው መሆኑን በተጨባጭ መረጃና ትንተና መረጋገጡን መጠቆም ሲገባዎት፤ “ከዚህ በፊት በቀን መቁመሪያው ዙሪያ የተደረጉት ሁሉም ጽሁፎች እንከን አለባቸው” በማለት ጉዳዩን የእርስዎ ግኝት አስመስለውታል፡፡
ለ.  የተመሰከረበት ባህረ  ሐሳብ፤
ለመከራከሪያ መሠረት ነው ብለው የመሰከሩበት ባህረ ሐሳብ የተሠኘው የአለቃ ያሬድ ፋንታ መፀሃፍ፤ በጳጉሜ 6 መፅሐፍ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ወሮች ትችታዊ ዳሰሳ ክፍል ውስጥ ባለመካተቱ ነው። ምክንያቱም በእርስዎ ጥቆማ መሰረት፤ መጽሀፉን አግኝቼ ስመለከት ማስተዋል የቻልኩት መጽሐፉ የተጻፈው የኢትዩጵያ ወሮች በአመት ውስጥ የሚያሳዩትን የሞቃት ምድር አጭር ቀንና ለሊት ልዩነት ሰአቶች እና 4ቱን መካከለኛ ወቅቶች መነሻና ማብቂያ እለት መረጃዎች መሰረት አድርጎ ሳይሆን ልክ እንክን አለባቸው እንደተባሉት ሌሎቹ ፀሀፊዎች ሁሉ ማሳየት የማይችሉትን የሰሜን ቀዝቃዛ ምድረ ሰማይ ረጅም ቀንና ለሊትሰዓት ልዩነት  እና ከፍተኛ ወቅቶች መረጃዎችን ነው፡፡ ከዚያም በላይ ጳጉሜን በአጭር ቀንና ለሊት ሰዓት ልዩነት፤ በአመት 12ኛ ወር  እና 94 እለት በሚሸፍነዉ 4ኛዉ ወቅት (በሰሜን ሞቃት ክረምት እና በደቡብ ሞቃት በጋ) ውስጥ መገኘቱን ባለመካተቱ ምክንያት  አቶ ሰለሞን ጳጉሜ 6 የተሰኘውን አዲስ የጊዜ መጽሐፍ አልቀበልም በሚል አላግባብ ለሙግት የተጋለጡበትን ምክንያት ያሳያል፡፡
ሐ. ከፀሀይ አመት የተሰሩ 7ት ተግባራዊ የጊዜ መለኪያ አሐዶች፤
“በሐሳበ ዘመኑ ትምህርት ዘዴ ሰባት አዕዋዳት ውስጥ ሶስቱ በእለታት (ዐውደ እለት፣አውደ ወርሃና ዐውደ ዓመት) እና 4ቱ በአመታት (አውደ እበቅቴ፣ዓውደ ፀሃይ፣ዓውደ ማህተም እና አወደ ቀመር) መቆጠራቸውን፣ የአውደ አመት አሃድም (unit) እለት መሆኑን እና ሐሳበ ዘመኑ በአሐዶች እንኳን ልዩ ጥንቃቄ የሚያደርግ ነው”
የሚለው መከራከሪያ ሐሳብ ጳጉሜ 6 መፅሐፍ የጊዜ መለኪያ አሐዶችን አልተጠቀመም የሚል ይመስላል፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ እየተባለ እዚህ ተሸሽጎ የሚገኘውን ቀን መቁጠሪ ከጠባብ ቀዝቃዛ ምድር አገሮቹ የግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ ጋር በማገናዘብ የሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር አገሮች ቀን መቁጠሪያ መሆኑን ያረጋገጥኩት በአመት ውስጥ የሚገኙትን 7 ተግባራዊ የጊዜ መለኪያ አሃዶችን በመጠቀም ነው። ከፀሀይ ዓመት የተሰሩት 7 የጊዜ መለኪያ አሃዶች በሁለት የተከፈሉ ናቸው፡፡ በእጅ ሰዓት ላይ በ12 ሰዓት ቀን እና በ12 ለሊት ተከፍለው የሚመዘገቡት  ሶስት ትናንሽ የጊዜ መለኪያ አሃዶች ማለትም (1ኛ) ሠከንድ (የደቂቃ አንድ 60ኛ ክፍል)፣ (2ኛ) ደቂቃ (60 ሰከንድ) እና(3ኛ) ሰዓት (60 ደቂቃ) ሲሆኑ፡ በቀን መቁጠሪያ ላይ የሚመዘገቡት 4 ትላልቅ የጊዜ አሃዶች፡- (4ኛ) እለት (24 ሰዓት)፣(5ኛ) ሳምንት (7 እለት) ፣(6ኛ) ወር 30፣35 እና 36 እለት (የኢተዮጵያ) እና 28፣29፣30 እና 31 እለት (የግሪጎሪያን) እና (7ኛ) ዓመት (365 እና በየአራት አመት 366 እለት) ናቸው፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የሚመዘገቡት የዓመተ ምህረት አመታት፣ ወራት፣ ሳምንታት፣ እለታት እና የየእለቱ አጭር የቀንና ለሊት ልዩነት በግሪጎሪያኑ ቀን መቁጠሪያ ከሚመዘገቡት የአመተ ምህረት ዓመታት፣ ወራት፣ሳምንታት፣ እለታት እና የየእለቱ እጅግ ረዥም የቀንና ለሊት ልዩነት የተለዩ መሆናቸውን በተጨባጭ ማስረጃና በአንጻራዊ የጊዜ ሂሳብ ትንተና ዘዴ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህም በጳጉሜ 6 መፅሐፍ ውስጥ በጥልቀትና በዝርዝር ቢገኝም እርስዎ አልገባኝም ያሉበት ምክንያት ከላይ ጥንቃቄ ያደርጋል ያሉት ጥንታዊው የሐሳበ ዘመኑ ትምህርት አስተምሮት ዘዴ በዓመት ውስጥ ከሚገኙት 7ተግባራዊ የጊዜ መለኪያ አዕዋዳት ውስጥ 4ቱን መሰረታዊ የጊዜ መለኪያ አሀዶች ማለትም ሳምንት፣ሰዓት፣ደቂቃ እና ሰከንድን አካትቶ ባለማስተማሩ የተነሳ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ወሮች እና በግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ ወሮች መካከል ያለውን ልዩነት አጢኖት ስለሚያውቅ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡
መ. በጳጉሜ 6 ቀን ፡5999 ዓመተ ዓለም፡
የጳጉሜ 6 ጥያቄ የርስዎም ጥያቄ ነው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ጳጉሜ 6 የማትታወቀው የክርክር መሰረት ነው ብለው በጠቀሱት የአለቃ ያሬድ ፈንታ “ባህረ ሐሳብ” መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን  በንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ “ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት” በተሰኘው መጽሐፍ ጭምር ተጽፎ የሚገኘው ጳጉሜ 5 ብቻ ነው፡፡
“በኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት፤ እንዲሁም … ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከድንግል ማርያም የተወለደበት ጊዜ፡ በጳጉሜ 5 ቀን ፡5500 ዓመተ ዓለም፡ ከለሊቱ 6 ሰዓት ሞልቶ፡ አንዲት ካልዕት ለማትሞላ አፍታ፡ጥቂት እልፍ ብላ በነበረችው ቅጽበት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ መስከረም 1 ቀን፤ 1 ዓመተ ምህረት ተብሎ የዓመተ ምህረት ዘመን አቆጣጠር የጀመረው በዚያች፡ የዓመተ ኩነኔ፡ ወይም የዓመተ ፍዳ ማብቂያ ከሆነችው፡ ጳጉሜ 5 ቀን ፡5500 ዓመተ ዓለም፡ ከለሊቱ 6 ሰዓት በኋላ ከነበረችው ቅጽበት ጀምሮ ኾኗል፡፡” ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ (1997፡306)፡፡
ስለዚህ ስለርሱ ከተጻፉት ውስጥ አንዳችም ስህተት የሌላቸው ስንቶቹ ይሆኑ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ የጳጉሜ 6ን እለት ሳያካትቱ አጠቃላይ የጻፉት በስህተት የተሞላ ብቻ ሳይሆን ውጤቱም ያልተሟላ ነው፡፡ ከዚያም በላይ በእነርሱ ዘንድ በፀሐይ አመት 365.25 እለት ንድፈ ሐሳብ እና ይህንን ንድፈ ሐሳብ ወደ መሬት ባወረደው የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ጋር ያለመተዋወቅ መሰረታዊ ተግዳሮት መኖሩን ያሳያል፡፡
ስለዚህ ከላይ በጥቅስ ውስጥ የተመለከተው ሀሳብ ሦሥት መሰረታዊ እንከኖች አሉበት፡፡ (1ኛ) ጳጉሜ 6ን አያውቀውም በዚሁ ምክንያት የ6ኛ ሺህ ማብቂያ 5999 ዓመተ ዓለም መሆኑን አላወቀም፡፡ (2ኛ) በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ህግ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከድንግል ማርያም የተወለደበት ጊዜ ለሊት ሳይሆን ጧት ነበር፡፡ (3ኛ)  በሦሥት ምድብ አራት ዓመት የፀና ዙር መሰረት የመጀመሪያው ዙር አራት ተከታታይ ዓመተ ምህረት ዓመቶች 0 ምድብ አንድ፤1 እና 2 ምድብ ሁለት እና 3 ምድብ ሦሥት ነበሩ፡፡ 0፤1ና2 እያንዳንዳቸው ባለ 365 እለት ዓመት ሲሆኑ፤ 3 ዓመተ ምህረት ግን የመነሻ እምርታ አመት ባለ 366 እለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ 1996፤1997 እና 1998 እና 1999 በሦሥት ምድብ አራት ዓመት የፀና ዙር መሰረት 500ኛ ዙር አራት ተከታታይ ዓመተ ምህረቶች ነበሩ፡፡ እንዲሁም 2004፤2005 እና 2006 እና አሁን የምንገኝበት አመት 2007 502ኛው ዙር የሶስት ምድብ አራት አመተ ምህረቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ዓመተ ምህረት የመጀመሪያው ሦሥት ምድብ አራት አመት ሁለተኛ አመተ ምህረት (መስከረም 1 ቀን፤ 1 ዓመተ ምህረት) ላይ ሳይሆን መስከረም 1 ቀን 0 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እና ሰብቴምበር 12 ቀን 7 ዓ.ም በግሪጎሪያን ላይ ነዉ፡፡
በመሆኑም ከላይ በጥቅስ የተመለከተው የንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ ሐሳብ ከዚህ እንደሚከተለው መጻፍ ነበረበት፡፡
በኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት፤ እንዲሁም … ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከድንግል ማርያም የተወለደበት ጊዜ፡ በጳጉሜ 6 ቀን ፡5999 ዓመተ ዓለም፡ ከጧቱ 12 ሰዓት ሞልቶ፡ አንዲት ካልዕት ለማትሞላ አፍታ፡ ጥቂት እልፍ ብላ በነበረችው ቅጽበት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ መስከረም 1 ቀን፤ 0 ዓመተ ምህረት ተብሎ የዓመተ ምህረት ዘመን አቆጣጠር የጀመረው በዚያች፡ የዓመተ ኩነኔ፡ ወይም የዓመተ ፍዳ ማብቂያ ከሆነችው፡ጳጉሜ 6 ቀን ፡5999 ዓመተ ዓለም፡ ከጧቱ 12 ሰዓት በኋላ ከነበረችው ቅጽበት ጀምሮ ኾኗል፡፡
ሥለዚህ በጳጉሜ 6 እለት ተፈጥሮ መሰረት ጊዜ ማለት ዘላለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ የተገለጹት 7 ተከታታይ የጊዜ መለኪያ አሃዶች  ውስጥ 3ቱ  በእጅ ሰኣት እና 4ቱ በቀን መቁጠሪያ ላይ በቁጥር እየተሰፈሩ በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም በእጅ ሰኣት ላይ የሚመዘገቡትን የእለት አሀድ መሰረት የሆኑትን ሰዓት፣
ደቂቃ እና ሰከንድን እና በቀን መቁጠሪያው ላይ የሚመዘገቡትን የአመተ ምህረት ዓመት፡ 12 ወራት፤ 52 ሳምንት ከ 1 እና 2 እለት ሳይገነዘቡ ወደማይገባ ክርክር መግባትዎትን ያሳያል፡፡ በመሆኑም የ7ቱም ተግባራዊ የጊዜ መለኪያ አሃዶች  እና የሶስት ምድብ አራት አመት፤ 28 አመት እና ሚሊኒየም (1000 ዓመት) መሰረት ምንጭ የሆነችውን ጳጉሜ 6 ሳያውቁና ሳይቀበሉ፤ የሐሳብ ዘመኑ ትምህርት ዘዴ ሰባት አዕዋዳት አሉት የሚለውን የጨበጣ ሀሳብ መቀበል እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን መጠቆሙ አስፈላጊ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ተግባራዊ ጥቅም አውርደን ተጠቀምን ማለት የሚቻለው መቼ ነው?
“አንፃራዊ ጊዜን /ዘመንን፣ እንደነ አልበርት እና ስቴፊንግ ሆውኪንግ ያሉ የሳይንስ ጭንቅሌዎች በ20ኛው መቶ ክ/ዘመን ከልደት ወዲህ ሊደርሱባት የቻሉትን የጊዜ ዘመን ፍቺ ከጥንት ጀምሮ ይዞ፣ ተግባራዊ ጥቅም ላይ በሚውልበት አያያዝ አውርዶ ሲጠቀምበት የኖረ የዘመንና የዓለም ሐሳብ ነው”
ከላይ በተገለጸው መከራከሪያ ሀሳብ መሰረት የአንፃራዊ ጊዜን ትርጉም  የሚያውቁ ከሆነ፤የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ለምን ጥንታዊ ብቻ አድርገዉ ደመደሙ የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለብዎት፡፡ጥንት ማለት ዛሬንና ነገን ማየት የማይችል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የአንፃራዊ ጊዜን ትርጉም ሳይረዱ ስለጊዜ መናገር ኢሳይንሳዊና ኢተፈጠሮዋዊ ነው፡፡ ማነጻጸር ማለት ምን ማለት ነው? ጳጉሜ 6 የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ከግሪጎሪያን ቀን መቁጠሪያ ጋር በ7 ተግባራዊ የጊዜ መለኪያ አሃዶች በግልጽና ለማንም በሚገባ ሁኔታ በማነጻጸሩ ምክንያት  የሚናገር መጽሐፍ ነው ብለው የምስክርነት ቃል አልሰጡምን?
ስለዚህ ከላይ  የገለፁት … ተግባራዊ ጥቅም ላይ በሚውልበት አያያዝ አውርዶ ሲጠቀምበት የኖረ የዘመንና የዓለም ሐሳብ ነው የሚለው ሐሰት ቢሆንም፤ የሚከተለውን አዲስ ጥያቄ በመፍጠሩ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ተግባራዊ ጥቅም አውርደን ተጠቀምን ማለት የሚቻለው መቼ ነው?  
የኢትዮጵያን ቀን መቁጠሪያ ተግባራዊ ጥቅም ላይ ልናውል የምንችለው በዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ከማንኛውም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እሴት የተዘለለችውን ጳጉሜን ማግኘት ብቻ ሳይሆን የግሪጎሪያኑን ቀን መቁጠሪያ ኢ-ተፈጥሮዊና ኢ-ሳይንሳዊ ጥቅም በማስቀረት በሰሜንና ደቡብ ሰፊ ሞቃት ምድር ውስጥ የሚከሰቱት መካከለኛ የተፈጥሮ ወቅቶች፣ አጭር ቀንና ሌሊት ሠዓት ልዩነት እና ማናቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥራዎች ሲመዘገቡበት ብቻ ነው፡፡ ስሊዚህ ይህን አዲስ ስራ የመተግበርና ማስተግበር አመራር በኛ ኢትዮጵኖች እጅ እና በመላዉ የአለም ህዝብ እጅ ላይ የወደቀ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡
በመጨረሻ የባሕረ ሐሳብ አስተምሮት ዘዴ በፀሐይ አመት 365.25 እለት ንድፈ ሐሳብ እና ይህንን ንድፈ ሐሳብ ወደ መሬት ባወረደው የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ጳጉሜ 6 ጋር ፍጹም ያለመተዋወቅ መሰረታዊ ተግዳሮት እንዳለበት በጉልህ እንዲታይ አድረገዋል፡፡ በመሆኑም ላደረጉበት የተቃውሞ ተሳትፎ አመሰግናለሁ፡፡

Read 7294 times