Saturday, 18 July 2015 11:22

በእኛ ጊዜ ልጅ ቢያጠፋም ባያጠፋም ይቀጣል!

Written by  ተዓምር ተክለብርሃን
Rate this item
(1 Vote)

የቅጣት ነገር ሲነሳ ትዝ የሚለኝ ጥዋት ጥዋት ሰንደቅዓላማ ለመስቀል ትምህርት ቤት የምንሰለፈውን ሰልፍ ማታ ማታ ለመገረፍ ቤት ውስጥ የምንደግመው ነገር ነው ። ብሄራዊ መዝሙር የተከፈተ ይመስል አባታችን ፊት ያለምንም ንቅናቄ ቀጥ ብለን ባልተዛባ ሰልፍ ቆመን እንገረፋለን። ተራችንን እንኳ አናዛባም።  ብቻ የኔ ትውልድ ከድንጋይ ዘመን ከአፍ ያለ የዱላ ዘመን ትውልድ እስኪመስለኝ ድርስ እናት፣ አባት፣ ጎረቤት በተጨማሪም መምህር ቀጥቅጦ ያሳደገው ነው። ዝናብ ሲመታን “ዝናብ ያሳድጋል” ይሉናል እንጂ ማለት የነበረባቸው “ዱላ ያሳድጋል “ ነበር። ከዝናብ ይልቅ የቀጠቀጠንም ያሳደገንም ዱላው ይመስለኛል።
ከቤት ስጀምር እናቴ ስትቆነጥጠኝ ፊቴ ላይ ያስቀመጠችው የራይት ምልክት ለናይክ የጫማ ፋብሪካ እንደግብአት በማገልገሉ በአሁኑ ሰዓት ታዋቂ የጫማ ማርክ ሆኖዋል ። (እኔን ማስረጃ ይዛ የፈጠራ ውጤቱ ባለቤትነቷን እንድትጠይቅ ብጎተጉታት ጥሩ ይመስለኛል) ሴት የቤተሰቡ አባላት አጭር ቀሚስ እንዳያደርጉ፣ ወንዶቹ በጃፖኒና በቁምጣ እንዳይዘንጡ ማን አስተጓጎላቸው ? እሷ አጠቃላይ ሰውነታችነን ላይ በሰራችው ዲዛይን ምክንያት አይደለምን? “ አርክቴክት ባልሆንና  የህንፃ ዲዛይን ማሰፍርበት ቦታ በሀብት እጥረት ምክንያት ባይኖረኝ ሰፊ ገላ ያላቸው ልጆች አሉኝ” ብላ ተጫወተችብን።
አቤት! በቁንጥጫ ያላስቀመጠችብን ምልክት አለ እንዴ? ህፃን ብትሆንና ለእንቁጣጣሽ ብትሰጠን በስመ አብ በእንቁጣጣሽ አበባ ሽያጭ የከበረች ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ትሆን ነበር። ምን ያደርጋል እሷም ህፃን አልሆነች እኛም ሰው ሆንባት።
የአባቴ መግረፊያ ጉማሬ የሰንጠረዥ አይነት አሳውቆናል። የኔን ዘልዬ የእህቴን ግርፋት ልንገራችሁ። ቤታችን ውስጥ የተከሰተውን ቁጣ ሸሽቼ እሁድ መዝናኛ ለማየት ጎረቤት ሄድኩ ።
እህቴ ሆዬ እያየሁት ያለሁት እሁድ መዝናኛ አነሰኝ ያልኩ ይመስል፣ ሌላ እሁድ መዝናኛ ይዛልኝ መጣች ። እሷ ስትገረፍ ነበር ወጥቼ የመጣሁት። እሷ ግን ለምን ይቅርበት ብላ ዝንቅ በጆሮዋ ላይ ተሸክማ መጣች። ያበጠ ጆሮዋን ስመለከት ዝንቅ ላይ “ሶስት ጆሮ ያላት የሰው ፍጡር” ብሎ ያቀረቧት መሰለኝ። ጆሮዋ ቅርፁን ሳይለቅ በእብጠቱ እራሱን ደግሟል። የታችኛው ጆሮዋን ይዤ የአዲሱ ጆሮዋን መስማት መቻል ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር። እንዴት ልሳቅ? አይኗ ቀልቷል። የሚያምሩኝ ከንፈሮቿ ይዞታቸውን ለቀው የኔን መስለዋል። ለምን መጣች?  ብቻ በሰዓቱ መሳቅም ማልቀስም አልቻልኩም፡፡ ዓይን ዓይኔን ታያለች፤ የታፈነው ሳቄ አፌ ስለተዘጋበት ነው መሰለኝ አፍንጫዬን ያነቃንቀዋል። እንደ ደህና ነገር ሰው ጎረቤት ድረስ መገረፉን ሪፖርት ሊያደርግ ይመጣል?
አይ እህቴ! እቺው እህቴ (እሷን አተኩሬ ምቦጭቅላችሁ አነስ ብላ ቀጠን ያለች ስለሆነች ቀለል ስለምትለኝ ነው) ዱላ ሰልችቷት የኢትዮጵያን ትምህርት ተግባር ተኮር ለማድረግ የጣረችው ነገር ትዝ ይለኛል። እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተደበደበች በኋላ ሰባተኛ ክፍል ስትደርስ የስነ ዜጋ ትምህርት ተጀመረላት። ማንም ማንንም የመምታት መብት የለውም ብሎ ሲደበደብ እዚህ የደረሰው መምህራቸው ብሶቱን ተማሪዎቹን ለአብዮት በሚያነሳሳ መልኩ አስተማራቸው።እሜቴ ሆዬ ከታላቅ አጠር ያለ ምክር ፈልጋ ይሁን እኛንም ወደ አብዮቱ ልታካትተን፣ ጉዳዩን መጥታ ለኔና ለታናሽ ወንድሜ አማከረችን፡፡ እኔና ወንድሜ ምንም ሴራ ማሴሪያ ሰዓት ሳያስፈልገን ፈገግ ብለን ከተያየን በኋላ ለአባታችን መንገር እንዳለባት ሹክ አልናት። የሚመጣውን ለውጥ ለማየት ሳይሆን የምትባለውን፣ ከከፋም ቅጣትዋን ለመስማት ጓጉተን ጅል እህታችንን ላክናት።
“ማንም ማንንም የመደብደብ መብት የለውም” እሱዋ ይሄን ስትናገር “የለውም” እያልን በመፈክር መልክ ብናግዛት ደስ ይለን ነበር፤ ግን ሀላፊነቱን እንደ አልቃይዳ ለሷ አሳልፈን ሰጥተን ኮሪደራችን ያለውን ጨለማ ተገን አድርገን የጉባኤው ተካፋይ ሆንን። አባታችን ሳቅ እንደያዘው ያስታውቃል ። ግንባሩን ጨምደድ አድርጎ ሳቁን ለመቆጣጠር ይጥራል። ተሳክቶለታል። ማንም ማን ነው? የሚል ጥያቄ እንዳይከተል የሰጋች ይመስል። የታላቅ ወንድማችንን ስም ትጠራና እሱም ቢሆን እኔን የመምታት መብት የለውም ። ሳጠፋ መምከር እንጂ እንደ አህያ ለምን ይቀጠቅጠኛል ? መልስ ስታጣ ድምጿ መርገብገብ ጀመረ። “የምሸሸግበት ጥግ አጣሁ እመብርሃን” ሳትል ትቀራለች። ለውጥ ባታመጣም በቅጣቱ ሂደት ላይ የማሻሻያ ስራ እንደሚሰራበት ቃል ተገብቶላት ወጣች። እኛም ባንዲራውን ከፍ አድርጎ እንዳውለበለበ ጀግና አቀባበል አደረግንላት። ይገባታል። ታሪክ መለወጥ ባትችል ታሪክ ለመስራት የሞከረች አዲስ ትውልድ!
እናታችን በቁንጥጫ፣ አባታችን በጉማሬ፣ መምህር በዱላ አሊያም በጎማ የሚገርፉን  ሁሌ አንድ አይነት ሆኖ እንዳይሰለቸን በአቅራቢያ ከሚገኙ ዛፎች ዘንጥፈን ወይም ዶቢ በአዲስ አበባ ስሟ ሳማ ቆርጠን ይዘን እንድንመጣ እንታዘዛለን። ያኔ እርግብ ነበርን፤ የታዘዝነውን ይዘን እንመለሳለን፡፡ ይሄን ሳስብ ቁራ ይገርመኛል። መገረፊያ ይዘህና አልተባለ፤ ሄደህ ውሃው መድረቁን አይተህ ና ለተባለው በዛው መቅረቱ! አሁን እንደው ዶቢ ይዘና ቢባል ምን ሊሆን ነው ? እስከነ አካቴው ምድር ላይ የቁራ ዘር ሊጠፋ ይችል ነበር። ብቻ ቁራ የኛ ቤት ነዋሪ ሊሆን የሚያስችል አንድም ባህሪ አላየሁበትም ።
ወላጅ ያኔ ገርፎ የሚደክመው እንጂ ቅጣቱ የሚወጣለት አይመስለኝም፡፡ መምህራኖችን ባገኘበት አጋጣሚ “እንደው አደራህን ልጄን እየቀጣህ” ብሎ ትእዛዝ ይሰጣል። ያም መምህር ተባለም አልተባለም መቅጣቱ ባይቀርም ትውውቅ እንዳለው ለማሳወቅ በትንሹም በትልቁም ዱላው እረፍት እንዳያገኝ ይሰነዝራል። ከኔ ዘመን ርቆ ያለው ትውልድ ከዱላ ጋር ብዙም እውቂያ ያለው አይመስለኝም። እንደኔ ለምን ሳይቀጠቀጥ ቀረ ብዬ አይደለም። ግን ሲያጠፋም ወላጅ አይቀጣውም፤ መምህር ምርር ብሎት “ይህን ትውልድ ለማነፅ ትንሽ ቅጣት ያስፈልጋል” ብሎ እጁን ቢሰነዝር፣ ወላጅ በነጋታው ይመጣና እሱ ግንባር ላይ አነስ ያለች “ፒስትል” ይሰነዝራል።





Read 2152 times