Saturday, 11 July 2015 12:55

የተማሪዎች የክረምት ፌስቲቫል ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዘንድሮ የትምህርት ጊዜ ማብቃትን ምክንያት በማድረግ “ኑ እናንብብ” የተሰኘ የተማሪዎች የክረምት የመፅሃፍ ንባብ፣ የባህልና የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ሐምሌ 11 እና 12 በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ከ30 በላይ በመፅሀፍ ህትመትና ሥርጭት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችና ከ20 በላይ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በሁለት ቀን ፌስቲቫሉ ላይ አንጋፋና ወጣት ደራስያን፣ አርቲስቶችና ምሁራን ለህፃናትና ወጣቶች መፃህፍት የሚያነቡ ሲሆን የህፃናት ቴአትሮች፣ መዝሙሮች፣ ፊልሞች፣ የፖፔት ትዕይንቶች እንዲሁም የባህልና ታሪክ የማስተዋወቂያ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሥነ - ፅሁፍ፣ የስዕልና የተሰጥኦ ውድድሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡
የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ተማሪዎች የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተጋበዙ ስኬታማ እንግዶችም የህይወት ልምዳቸውንና የንባብ ጠቀሜታን በተመለከተ ተመክሮአቸውን ለተማሪዎች እንዲያጋሩ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡
የተማሪዎች የክረምት ፌስቲቫሉን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን “የኢትዮጲስ ጊዜ” የተሰኘ የህፃናት ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው አማራጭ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት ከአዲስ ምዕራፍ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1691 times