Saturday, 11 July 2015 11:50

የአልፋን ችግሮችና መፍትሔዎች መሸፋፈን መዘዝ ያስከትላል

Written by  ሺፈራው ተስፋዬ (ባለአክሲዮን)
Rate this item
(0 votes)

    አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ ሰኔ 13 ቀን 2007 ባወጣው እትሙ፤ “የአልፋ ባለአክሲዮኖችና አመራሮች እየተወዛገቡ ነው” በሚል ርዕስ ከአልፋ የትምህርትና ስልጠና አ.ማ ቦርድ ሰብሳቢ፣ የተሠጡትን የተሳሳቱና አደናጋሪ መረጃዎችን ማረም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዚህም መሰረት ከትርፍ፣ ከተማሪ መቀነስና ከትምህርት እንዲሁም ከካፒታልና ከሕንፃ ግንባታ ጋር በተያያዘ አጭር በመረጃ ላይ የተደገፈ ግምገማ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡  
በ2006 ዓ.ም የማህበሩ የተጣራ ትርፍ ተብሎ 4,679,586 ብር በሪፖርት ላይ ቢገለጽም 8 ሚሊዮን ብር የአያት ኩባንያ እዳ በስሌቱ ውስጥ ቢገባ ኖሮ፣ ይህን ያህል ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ (loss) በቀረበ ነበር፡፡
እውነታው እንዲህ ቢሆንም የቦርዱ ሰብሳቢ፤ “ትርፍ በአስጊ ሁኔታ እየቀነሰ አይደለም፣ ቅነሳው አያሳስበንም፣ የኪሳራና የውድቀት ስጋት የለብንም፣የባለአክስዮኖች ቅሬታ በፊት ሲገኝ ከነበረው ትርፍ በመቀነሱ ነው” በማለት አለአግባብ በማጣጣልና በማናናቅ ተናግረዋል፡፡ ይኸም ችግሩን ለመደበቅ እና ለመሸፋፈን የታለመ ነው፡፡
ከቢዝነስ አንጻር አንድ የንግድ ተቋም ኢንቨስት ካደረገውና ሠርቶ ሊያገኘው ከሚገባው ወይም ካሰበው በታች ትርፍ ካገኘ ኪሳራ (loss) ደረሰ ይባላል፡፡ በዚህ መልኩ በአልፋ ላይ የደረሰው ኪሣራ በነበሩት ሕንፃዎች ካለ ኪራይ የነበሩትን የድርጅትና ሌሎች ሐብቶች በነፃ ተጠቅሞ የነበረውንም የቢዝነስ ዕድል ባለመጠቀሙ በመሆኑ ኪሣራው እጅግ የላቀ ይሆናል፡፡ መፍትሔም ስላልተገኘለት እጅግ ያሳስባል፡፡ በሌላ በኩል ተቋሙ በየጊዜው መክፈል ያለበትን እየከፈለና ስራውን እየሠራ መቀጠል ካቃተው ተንገራግጮ ቆሟል ማለት ነው። ይህም በንግድ ህጉ መሠረት ኪሳራ (bankruptcy) ሲባል፣ ኪሳራውም በፍርድ ቤት መታወጅ አለበት። በርግጥ አልፋ ሁለተኛውና የመጨረሻው ደረጃ ላይ አልደረሰም፤ ሆኖም በተለይ ሕጋዊ መጠባበቂያ ገንዘቡ ሕንፃ እየተገነባበት ስለሆነ ትንሽ ችግር እንኳን ቢፈጠር ለዚህ ዓይነት ኪሣራ ሊጋለጥ ይችላል፡፡ የባለአክሲዮኖቹ ትግልና ጭንቀት ወደዚያ እንዳይደርስና አጠቃላይ ውድቀት እንዳይከተል ነው፡፡ ባለፉት አመታት የታየው ሂደት ከቀጠለና በወሳኝ መልኩ ካልተቀለበሰ ደግሞ አይቀርለትም፡፡
በሌላ በኩል በአልፋ እጅግ አስደንጋጭ የተማሪ ቅነሳ የታየበት ቢሆንም ምንም ዓይነት መፍትሔ ካለመቀየሱም በላይ የቦርዱ ሰብሳቢ በቅነሳው አልተደናገጥንም ብለዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ያልተደናገጠ መሪ መፍትሔም ስለማይፈልግ ችግሩ እንዳለ ቀጥሏል፡፡ በዲግሪና በተለይም በ2ኛ ዲግሪ ደረጃ የፕሮግራሞቹን ሕልውና የሚፈታተኑ ችግሮች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መደማመጥ ከተቻለ ችግሮቹንና መፍትሔዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
ሰብሳቢው እንዳሉት፤ የርቀት ትምህርትን በተመለከተ የገበያ ድርሻው የቀነሰው በተፎካካሪዎች መበራከት ሳይሆን የኩባንያው አመራር በተሻለ ሁኔታ ተወዳዳሪ ሆኖ ከገበያው የሚገባውን ባለማግኘቱ ነው፡፡ በጥራቱም በኩል በተሻለ ሁኔታ ላይ ቢሆን ኖሮ በተማሪ ብዛት ይጨናነቅ ነበር እንጂ በተማሪ “ድርቅ” አይመታም ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካፒታሉን ወደ 125 ሚሊዮን ብር አሳድገናል በማለት የቦርዱ ሰብሳቢ የተናገሩትን በተመለከተ፣ ካፒታሉ ያደገው በ1997 ዓ.ም ማለትም ከ11 ዓመታት በፊት ነው፡፡ የአልፋ ችግሮች የተከሰቱት በተለይም ከ2001 ዓ.ም በኋላ ነው፡፡ በነዚህ ዓመታት በስልጣን ላይ የነበሩት ቦርድና ማኔጅመንት ካፒታል የሚገነባ ስራ ባይሰሩም፣ ዘወትር የሚነግሩን ህንፃዎቹን እንደዘበኛ ጠብቀን በማቆየታችን አትከስሩም፣ እንዲያውም ሲሸጡ ትርፍ ታገኛላችሁ የሚል ነው፡፡ የባለአክሲዮኖቹ ክርክር ደግሞ ባለው ሀብት ሰርታችሁ ለደንበኛው አርኪ አገልግሎት፣ ለኛ ደሞ ጥቅም አላስገኛችሁም የሚል ነው፡ በሌላ በኩል ሰብሳቢው በተደጋጋሚ የገለጹት ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የግል ህንፃዎችንና ትምህርት ቤቶችን በየቦታው በመገንባት ቋሚ ንብረት እያፈራን ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እሳቸው እንዳሉት፤ በቅርብ ጊዜ ት/ቤቶችና ሕንፃዎች በትርፍ እየተገነቡ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል የአልፋ ችግሮች፣ መንስኤዎችና መፍትሔዎች በሕንፃ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፡፡ ችግሩ ያሉትንም ሐብቶች ወደ ውጤት ለመቀየር አለመቻል ነው፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ ከአመራር ድክመት የተነሣ፣ ተቋሙና ቢዝነሱ ለመሥራት አለመቻላቸው ነው፡፡
አልፋ በሥራውና በውጤቱ ማሽቆልቆል ከጀመረበት ጊዜ በተለይም ከ2003 ዓ.ም አንስቶ  ባለአክሲዮኖች ባለማሰለስ ችግሮችንና የመፍትሔ ሃሳቦችን አቅርበዋል። እንዲሁም ከ2005 ጀምሮ ከባለአክሲዮኑ 10% በማስፈረም፣ ችግሮችንና መፍትሔዎችን እንዲሁም የመመስረቻ ጽሑፍና የመተዳደሪያ ደንቡን ለማሻሻል የሚያስችል የመነሻ ሃሳብ ቢያዘጋጁም በወቅቱ በነበረው ቦርድ ሐሳቦቹ ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርበው ውይይት እንዳይደረግባቸው ሆነዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኩባንያችን እነሆ ዋጋ ለመክፈል ተገዷል፡፡ ችግሮቹንና መፍትሔዎችን መደበቅና መሸፋፈን ከቀጠለ ገና ብዙ ሊያስከፍል ይችላል። በጠቅላላ ጉባዔ የባለአክሲዮኖች አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ባቀረቡት ችግሮች ላይ የምርመራ ኦዲት እንዲሠራ ቢወሰንም፣ በወቅቱ የነበረው ቦርድ ውሳኔውን ወደ ማኔጅመንት ኦዲት ቀይሮት እሱም ተኮላሽቶ እንዲቀርብ አድርጐታል፡፡ በዚሁ በተኮላሸው የማኔጅመንት ኦዲት ውጤት ላይ ለመወያየት ታህሳስ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በጉባዔው ላይ በባለአክሲዮኖች ተጠይቆ ስምምነት ላይ በተደረሰው መሠረት፣ የአልፋ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ የሚወያይ ጠቅላላ ጉባዔ በቅርቡ ተጠርቶ፣አልፋ ከተቻለ ወደ ሃዲዱ እንዲመለስ፤ ካልተቻለም የተሻለ ውሳኔ ቢወሰን ለሁሉም ይበጃል። በሽታውን የደበቀ በተዓምር መድሃኒት ሊገኝለት አይችልም፡፡  

Read 1552 times