Saturday, 04 July 2015 10:24

ጠ/ሚኒስትሩ፤ በወንድማቸው አንደበት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(24 votes)

በልጅነታቸው ፖለቲከኛ የመሆን ህልም አልነበራቸውም
ወንድሞቻቸው በሙሉ ከመጀመሪያ ድግሪ በላይ የተማሩ ናቸው
ጠ/ሚኒስትሩ ለእናታቸው የተለየ ፍቅር አላቸው

ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ በ385 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ቦሎሶሶሬ ወረዳ ሶሬ አምባ ቀበሌ ውስጥ የተገኘሁት ለሌላ የስራ ጉዳይ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ሥፍራው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ የትውልድ ቀዬ ሲሆን በዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫም የተወዳደሩበት ሥፍራ ነው፡፡  ዕድል ቀንቶኝ ታዲያ
የጠ/ሚኒስትሩን ታናሽ ወንድም አቶ ደረጀ ደሳለኝን ለማነጋገር ቻልኩኝ፡፡
አቶ ደረጀ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በሂዩማን ኒውትሪሽን ፐብሊክ ኸልዝ ለላይ እየሰሩ መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡ ቆይታችን ያተኮረው ግን በታላቅ ወንድማቸው በጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዙሪያ ነበር፡፡
የዛሬው ጠ/ሚኒስትር ለቤተሰቦቻቸው እንዴት ያለ ልጅ ነበሩ? የተማሪነት ህይወታቸው ምን ይመስላል? ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን መልክ ያዘ? እኒህንና ሌሎች ታሪኮችን ከታናሽ ወንድማቸው ከአቶ ደረጀ ደሳለኝ አንደበት እንከታተል፡-

         ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ለቤታችሁ ስንተኛ ልጅ ናቸው? የልጅነት ህይወታቸውስ ምን ይመስላል?
እሱ ለቤታችን የመጀመሪያ ልጅ ነው። በአጠቃላይ ዘጠኝ ልጆች ነን ያለነው፤ አንዲት ሴትና ስምንት ወንዶች፡፡ እሱ የሁላችንም ታላቅ ነው፡፡ የልጅነት ህይወቱን በጥልቀት ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ እኔ የቤቱ የመጨረሻ ልጅ ነኝ፡፡ ግን አባ (ኃይለማርያም) በልጅነቱ በባህርይው የተረጋጋ፣ ትምህርቱን አጥብቆ የሚወድና ጥሩ ሥነምግባር የነበረው ልጅ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ጊዜውን በእረፍትና በመዝናናት  ለማሳለፍ የማይፈልግ ሥራ ወዳድ እንደነበር ወላጆቻችን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ለሁላችንም ምሣሌ ሆኖን ነው ያደግነው፡፡
ትምህርታቸውን የት ነው የተከታተሉት?
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ቡበቃ ሰልቃይንት እየተባለ በሚጠራ የካቶሊክ ሚሽን ት/ቤት ውስጥ ነው የተማረው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በወላይታ ሶዶ ሊጋባ ት/ቤት ተከታተለ፡፡  ከዚያም በከፍተኛ ውጤት ለዩኒቨርሲቲ በቃ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጅነሪንግ ሲመረቅ በከፍተኛ ማዕረግ የሜዳልያ ተሸላሚ ነበር፡፡ ከዚያም በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጠረ፡፡ ሁለተኛ ድግሪውን በፊንላንድ ተምሮ ከመጣ በኋላ በአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ የወተር ቴክኖሎጂ ዲን በመሆን አገልግሏል፡፡
የተማሪነት ህይወታቸውን እንዴት ነው ያሳለፉት?
በጣም ከባድ ህይወት ነበር፡፡ በተለይ ከአባታችን ሞት በኋላ ሁሉም ነገር እጅግ ከባድ ሆነ፡፡ አባታችን በአንድ የካቶሊክ ሚሽን ት/ቤት ውስጥ በአስተማሪነት ይሠራ ነበር፡፡ የምንተዳደረው በግብርና ቢሆንም አባታችን  በማስተማር በሚያገኘው ገቢ ነበር ብዙውን ነገር የሚሸፍነው፡፡ እናታችን የቤት እመቤት ናት፡፡ በግብርና ሥራው ከመሳተፍ ውጪ ሌላ ገቢ አልነበራትም፡፡ እናም የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ የነበረው አባታችን በ1975 ዓ.ም በህመም ምክንያት ሲሞት ቤተሰባችን ለከፍተኛ ችግር ተጋለጠ፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ ኃይለማርያም ወደ ዩኒቨርሲቲ ያለፈበት ጊዜ ነው፡፡ እናም ለእኛ መጥፎ ወቅት ነበር፡፡
ይህንን ክፉ ጊዜ ያለፍነው በዘመዶቻችን እርዳታና ድጋፍ ነበር፡፡ በወቅቱ ኃይለማርያም ተማሪ በመሆኑ ምንም ሊያደርግልን የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረም፡፡ በልጅነታችን በርካታ ውጣ ውረዶችን አይተን ነው ያደግነው፡፡ የረዥም ሰዓት የእግር መንገድ እየሄድን ነበር የምንማረው፡፡  በእኛ ህይወት ውስጥ የእናታችን ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ እሷ ሳትማር እኛን አስተምራ ለዚህ ደረጃ በማድረሷ በማድረጓ የላቀ ምስጋና ይገባታል፡፡
አቶ ኃይለማርያም በታናናሾቻቸው ህይወት ውስጥ ምን ቦታ አላቸው?
በጣም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ እንደነገርኩሽ ከአባታችን ሞት በኋላ ኑሮ ለእኛ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ያን ጊዜ አባ (ኃይለማርያም) ወደ ዩኒቨርሲቲ ያለፈበት ጊዜ ስለነበር ምንም የማድረግ አቅም አልነበረውም። ተመርቆ ሥራ ከያዘ በኋላ ግን ወደ ከተማ ሄደን ትምህርታችንን እንድንከታተል ብዙ ጥረት አድርጓል። ታላላቅ ወንድሞቼን አርባ ምንጭ ድረስ ወስዶ አስተምሮአቸዋል፡፡ እንደ ታላቅ ወንድምም እንደ አባትም ሆኖ ነው ያሳደገን፡፡ ለዚህም ነው ሁላችንም አባ እያልን የምንጠራው፡፡
በወጣትነታቸው የፖለቲካ ፍላጐት ነበራቸው? ወደ ፖለቲካው ዓለም የመግባት ፍንጮች ይታይባቸው ነበር?
ዝርዝሩን ባላውቅም ወደ ፖለቲካው ዓለም ይገባ ይሆናል የሚያሰኙ ምልክቶች ግን እንዳልነበሩት አውቃለሁ፡፡ ይህንን አስቦ ቢሆን ኖሮ ትምህርቱም ወደ ፖለቲካው ሣይንስ ያደላ ይሆን ነበር፡፡ እሱ እንደውም ማጥናት የሚፈልገው ሜዲስን (ህክምና) ነበር፡፡ የፖለቲካ ፍላጐት ግን እንጃ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የነበረውን የግል ፍላጐት በጥልቀት ለማወቅ ይቸግረኛል፡፡
ታዲያ ለምን ሜዲስን (የህክምና ሙያ) አላጠኑም?
በአጋጣሚ ነው፡፡ አባታችን ታሞ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ተኝቶ ሳለ ያስታምመው እሱ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የህክምና ሙያ ምን ያህል ከባድና አስቸጋሪ እንደሆነ በመገንዘቡ ሜዲስን የማጥናት ፍላጐቱን ገታው፡፡ እናም ትምህርቱን በኢንጅነሪንግ ሙያ ለመቀጠል ወሰነ፡፡
የሌሎቻችሁ የትምህርት ደረጃስ ምን ይመስላል?
ዘጠኛችንም ከመጀመሪያ ድግሪ በላይ ተምረናል። አንደኛው ወንድማችን በቅርቡ የፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ወስዷል፡፡ በአዋሣ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ዲንና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ እየሠራ ነው። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ይባላል፡፡ እህታችን በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ድግሪዋን ሰርታ፣ አዲስ አበባ ፔትሮሊየም ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ትዕግስት ደሣለኝ ትባላለች። በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ማስተርሱን ጨርሶ፣ አዲስ አበባ የአይሲቲ ምክትል ማናጀር ሆኖ የሚሰራ ገነቱ ደሳለኝ የሚባልም ወንድም አለን፡፡ በነርሲንግ ማስተርሱን ይዞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሜዲሲን (ህክምና) በመማር ላይ የሚገኘው ሌላው ወንድማችን ብሥራት ደሳለኝ ይባላል፡፡ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በፐብሊክ ኸልዝ ማስተርሱን እየተማረ የሚገኝ ዳዊት ደሳለኝ የሚባል ወንድም አለን፡፡
ወደ ፖለቲካ ዓለም ያደላው አንድ ወንድማችን በአረካ ወረዳ የወረዳው የፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ ሆኖ እየሰራ ነው፤ ማርቆስ ደሳለኝ ይባላል፡፡ እኔም ሁለተኛ ዲግሪዬን በሒዩማን ኒውትሪሽን ፐብሊክ ኸልዝ ላይ እየሰራሁ ነው፡፡ አሁን የመመረቂያ ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሁላችንም ከመጀመሪያ ድግሪ በላይ በሆነ ደረጃ ትምህርታችንን ተከታትለናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ሲመጡ ከቤተሰቦቻቸውና ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው ጋር በነፃነት የሚገናኙበት ሁኔታ አለ?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደልብ የመገናኘቱ ጉዳይ የለም፡፡ በነፃነት መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ድሮ በክርስትና ህይወቱ እንደልቡ ወደ ቸርችም ይሄድ ነበር። አሁን ግን እንደሱ የለም፡፡ ሁሌ እንደፈለገ መሆን አይችልም፡፡ የእነሱ ሥራ የሴኩዩሪቲ ሥራ ስለሆነ ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው፡፡ እንደ ድሮ መሆን የለም፡፡
ከእናታቸውስ ጋር ይገናኛሉ?
አዎ፡፡ ለእናቱ የተለየ ፍቅር ነው ያለው፡፡ እሷም እንደዚያው ናት፡፡ ከድሮ ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲ ሲመጣ በተለየ ሁኔታ ነበር የምትቀበለው፡፡ እሷ አሁንም ያው ናት፡፡ ለእሷ አሁንም የያኔው ልጇ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አለመሆኑ በእሷ ላይ ምንም ለውጥ አላመጣባትም፡፡ ታላቅ ከመሆኑም አንፃር ሁላችንም እናከብረዋለን፡፡ እንታዘዝለታለን፡፡ እናም ወደዚህ የሚመጣበት ጉዳይ ሲኖር እናቱን ሳያገኝ አይመለስም። በጣም ይወዳታል፡፡ ለሁላችንም እዚህ መድረስ እሷ የከፈለችው ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ እንደ አርሶ አደር አርሳ፣ ሳንራብ እንድናድግ ያደረገችው አስተዋጽኦ በቀላሉ  የሚገመት አይደለም፡፡ እናም ለእሷ የተለየ ፍቅር አለው፡፡ ትንሽ ከታመመች ወደ አዲስ አበባ ሄዳ ሕክምና እንድታገኝ ያደርጋታል፡፡
እናንተስ ወደ አዲስ አበባ ስትመጡ ከወንድማችሁ ጋር የምትገናኙት እንዴት ነው? በስልክስ የመነጋገር ዕድል አላችሁ?
እሱ የራሱ ስልክ የለውም፡፡ እኛ ደውለን ማግኘት የምንችለው በባለቤቱ በኩል ነው፡፡ እሱ ግን ደውሎ እናቱን አነጋግሮ ሲጨርስ፣ እኛንም በየተራ ያነጋግረናል። ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ በፈለግን ጊዜ አስቀድመን ደውለን ፕሮግራም እናስይዛለን። መምጣታችንን አስቀድመን አሣውቀን መኪና ይላክልንና ያለ ብዙ ፍተሻ እንድንገባ እንደረጋለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ጋር የት ተገናኙ? ጋብቻቸውስ እንዴት ነበር?
በዩኒቨርሲቲ ህይወት እንደተገናኙ ነው የማውቀው፡፡ ጓደኝነታቸውም እዚያው የተጀመረ ነው፡፡ ጋብቻቸውን የፈፀሙት በሠርግ ነው። ሰርጋቸው ሶርአምባ ወይንም በእኛ የትውልድ ቦታ ላይ ነው የተደረገው፡፡ በመንፈሳዊ ሥነስርዓት ቃልኪዳን ፈጽመው ነው የተጋቡት፡፡ ጊዜው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
ስንት ልጆች አፍርተዋል? ልጆቹ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ሶስት ሴት ልጆች ነው ያላቸው፡፡ ሁሉም በጥሩ ደረጃ ላይ እየተማሩ ነው የሚገኙት፡፡  አንደኛዋ በአምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነች፡፡ ሌላዋ በስኮላርሽፕ ወደ አሜሪካ ሄዳ እዚያ እየተማረች ነው፡፡ አንደኛዋ (ኩኩ) እሷም እንዲሁ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ትገኛለች፡፡
የልጆቹ ባህርይ እንዴት ነው?
ልጆቹ በሚያስገርም ሁኔታ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ፣ ትሁቶችና ፍፁም በጥሩ ሥነምግባር የታነፁ ልጆች ናቸው፡፡ እኛ እንኳን ወደ እነሱ ጋ በምንሄድበት ወቅት እንደዘመኑ ልጆች በራሳቸው ጉዳይ ተጠምደው፣ እኛን የሚረሱ ልጆች አይደሉም። ፍፁም ትሁት በሆነ መንገድ ተቀብለው ነው የሚያስተናግዱን፡፡
ወደ አዲስ አበባ መጥታችሁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በምትገናኙበት ወቅት ቆይታችሁ ምን ይመስላል?
ቤት ሄደን ከእነሱ ጋር ስንገናኝ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነው የምናሳልፈው፡፡ ወንድማችን ከቤተሰቦቹ ጋር መጫወትን አጥብቆ ይወዳል፡፡ ያለፈውን ነገር፣ የድሮውን ሁኔታ እያነሳን እንስቃለን፡፡ ደስ የሚል ቤተሰባዊ ጊዜን ነው የምናሳልፈው፡፡ ሁላችንም እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በእጅጉ እንናፍቀዋለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዴት ይገልፁዋቸዋል?
ሰው ከባዶ ነገር ተነስቶ በጥንካሬ ትልቅ ቦታ መድረስ እንደሚችል በማሳየት፣ ለሁላችንም ትልቅ ሞዴል ለመሆን ችሏል፡፡ በግል ደግሞ እንደ ታላቅ ወንድምም እንደ አባትም ሆኖ ያሳደገን ትልቅ አርአያ የምናደርገው ሰው ነው፡፡ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድን ተመላልሶ ተምሮ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ሊታመን የማይችል ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ወንድማችን ግን ይህንን አድርጐ አሳይቶናል፡፡









Read 14099 times