Saturday, 13 June 2015 15:26

የጂጂ እናት “የፍቅር ድንግልና!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(7 votes)


    በዘመናችን በሀሜት ጥርሶች ከሚዘለዘሉት ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የረዥም ልቦለዶች ከንባብ አደባባይ - መጥፋት ነው፡፡ ልብ ሰቃይ ድርሰቶች፣ በምክንያት የተደረደሩ ትርክቶች … አበባ የሰኩ …ዕንባ ያንጠለጠሉ … ሽቱ ያርከፈከፉ … በክፋት የከረፉ ዝንጉርጉር የህይወት ትዕይንቶችን እያሳየ፣ የነፍስን ትርታ የሚያስደንስ የጥበብ ሙዚቃ ለአንባቢዎቹ ናፍቆትና ረሀብ ነው፡፡
የዘመንን መዐዛ የያዘ ንፋስ፣ በፈጠራ ምትሀት ጨብጠው አየሩ ላይ የሚናኙ፣ ባህሉን ፖለቲካውንና ማህበራዊ ክንውኑን ከየዘመኑ ማማ ላይ ቆመው ሥዕሉን የሚያሳዩ ድርሰቶች ርቀት ምሥራቅ ከምዕራብ ያህል ሆኗል ብለው አፍንጫቸውን የሚነፉ አንባቢያንን በየጓዳው ሞልተዋል፡፡
ይሁንና በየጊዜው ደግሞ ይህንን አጥር ጥሰው፣ የዘመኑን ችግር ዘለው ብቅ የሚሉ ደራሲያን አይብዙ እንጂ አሉን፡፡ ከ1950ዎቹ መቋጫ ጀምረው እስከዛሬ ድረስ በየደረጃው ዘመናዊውን የአፃፃፍ መስመርና ልክ ተከትለው በመፃፍ ላይ ናቸው፡፡ ምናልባት በአፃፃፍ ፈንገጥ ያለው የአሁኑ የድህረ ዘመናይነት ተከታይ አዳም ረታ ካልሆነ በስተቀር አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ደራሲያንና ደራሲያት ከዚህ አጥር ብዙም የራቁ አይደሉም፡፡
ይሄንና በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚታተሙ መጽሐፍት በአብዛኛው ግለታሪኮችና የህይወት ታሪክ አሊያም በጋዜጦችና በመጽሔቶች የተፃፉ መጣጥፎች መድበል በመሆናቸው የረዥም ልቦለድ ረሀብ የሀገር ሆድ ሲያስጮህ ቆይቷል፡፡
አንዳንዴ ራቅ ብለው ብቅ - ብቅ የሚሉትም አንዳች የጥድፊያና ቴክኒካዊ ብስለት ችግር ይታይባቸዋል የሚለው ሀሜትም ሌላው የንትርክ መነሾ ነው፡፡ ይህንን ስንል ግን ስክን ያለ፣ ሥር ያለው ስራ የሚሰሩ እጅግ እጅግ ጥቂት ደራሲያን የለም ብለን እየካድን አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ተደጋግመው መታተም ሲገባቸው በአንባቢው የንባብና የመረዳት ልክ ተጋርደው ብዙ ሰዎች እጅ ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡
መነሻዬ የሀገራችንን ስነጽሑፍ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ አሊያም መለካት አይደለም፡፡ ዋና ጉዳዬ ሰሞኑን የታተመው የወይዘሮ ተናኜ ስዩም “የፍቅር ድንግልና” ረጅም ልቦለድ መጸሐፍ ነው። ማለቴ የመጽሐፉን ዳሰሳ በጥቂቱ ማካፈል። መጽሀፉ ከሌሎች ደራሲያን በተለየ እንድናየው የሚያስገድደን አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ደራሲዋ እስካሁንም መጽሐፍት ይዘው ብቅ ካሉት ይልቅ በዕድሜ ከፍ ያለች፣ ልጆችና የልጅ ልጆች ያየችም መሆንዋ ነው፡፡ (አንቺ ማለቴ የጥበብን ሰው “አንቱ” ማለት ዝምድናና ቅርበትን መግፋት ስለሚሆን ነው፤ የደራሲ ልብ በየትኛውም ዕድሜ እሸት ነው!) በዚያ ላይ ደግሞ ከቤታቸው ውስጥ ይመጣ የነበረው የጥበብ ምንጭ መነሻም ደራሲዋ ስለሚሆኑ ነው። ከእዚህ ቤት ከያኒዋ እጅጋየሁ ሽባባሁ (ጂጂ) ወጥታለች፡፡ እህቶችዋ ሶፍያ ሽባባው፤ ራሄል ሽባባውና ሌሎችም የጥበብ ሰዎች አሉ፡፡ እንግዲህ ሁሉ ነገር ቀልብ ይስባል፤ ነፍስ ይጋልባል ባይ ነኝ!
በጠና ዕድሜ የተዋጣላቸው የዓለማችን ደራሲያን በቁጥር ጥቂት ይሁኑ እንጂ አሉ። እንደ ጀርመናዊው ገጣሚ፣ ደራሲና የግብርና ባለሙያው ዎልፍ ጋጓግ ዓይነት፡፡ ገተ ተወዳጁን “ዘ-ፎስትን” ያስነበበው 80 ዓመት ካለፈው በኋላ ና፡፡ … ግን ደግሞ ገተ ወንድ ነው፡፡ እንደ ተናኘ ልጆች አያሳድግም። ዘጠኝ ወር አያረግዝም፤ ቤት አያሰናዳም፣ እንጀራ አይጋግርም፤ ልጆች አያጠባም። ተናኜ ግን በዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ እያለፈች፣ 349 ገፆች ያሉት መጽሐፍ ፅፋለች! … ግርምቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡
ያ - ብቻ አይደለም፡፡ ደራሲዋ የተለ ልምድ እንደነበራት ይነገራል፡፡ ገጠር ውስጥ እየኖረች፣ ለድሆች መብት ስትከራከር፣ ሰፈሬውን ሰብሰባ ቴአትር ስታሰራ… እንደኖረች በመጽሐፉ ምረቃ ቀን የተሰጠው እማኝነት ለነፍስ ጮሆ ያወራል። ምናልባትም ሌዎ ኤን ቶልስቶይ ውስጥ የሚታይ ርህራሄና ለድሆች የልብ ቅርብነት እንዳላት ያሳያል። ህይወቱን ከፍሎ፣ ከገበሬው ጋር ተጣብቆ እንደኖረው፣ ገበሬው በተራበ ቀን አዳራሽ አዘጋጅቶ፣ እንጀራ እንደቆረሰው ቶልስቶይ አይነት ልብ አላት ደራሲዋ! ያም ልብ ነው ፍትህን አነፍንፎ፣ ሽንቁር ቀድዶ፣ በብርሃን ዓይን ይህንን ህይወት ያየውና ከታሪክ ጉድጓድ የቀዳው፡፡ የእንባ ዘለላዎች ሲረግፉ በልቧ አጠራቅማ በሌላ አሸንዳ ወረቀት ላይ ሥዕል እንድታስቀምት ያደረጋት! ያ ልብ ነው መንሰፍሰፍና በሰው ህይወት ውቅያኖስ ላይ በሀሳብ መቅዘፍ ያመጣባት፡፡
አረንጓዴ መስክ ላይ ሆኖ ያረረ በረሀ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማለም ሌላ ዓይን ያስፈልጋል፣ በጠገቡበት አልጋ ተኝቶ፣ የሚቆረቁር መኝታን ማጣጣም ይከብዳል፡፡ …. ግና በፈጠራ ገንዳ ተጠምቆ፣ በፍቅር ዘይት ለታሸ ግን ሁሉ ቅርብ ነው፡፡ ተናኜ እዚህ ውስጥ የምትመደብ ከያኒ ትመስለኛለች፡፡
የተናኜ መሪ ገፀ ባህሪ በአካባቢው ወግ መሰረጽር በጨቅላ ዕድሜዋ ነበር የተዳረችው። ጨዋታ ሳትጠግብ ልጅነቷን ሳትጨርስ ነበር ነጥቀው ለሽፍታ የሰጧት፡፡ እናም የተስፋ አበባ የተመኘች ነፍሷ ሬት ልሳለች፤ በፍቅር የምትነድ ልብዋ በሀዘን ተዳፍናለች። ትዳር ተብሎም እንደ እንስሳ ስትቀጠቀጥ፣ ያለ አሳቢ ተጨብጣ፣ የወሲብ ጥመኞች እርካታ ስትሆን፣ በተቆጨና በነደደ ስሜት ከገፅ ወደ ገፅ እያነበብን ምናልባትም ወንድነታችንን ጠልተንና፣ ተፀይፈን እየገላመጥነው እንድንጓዝ ያደርገናል፡፡ ደግነቱ ግን ደራሲዋ በዚያ ሁሉ የሰቀቀን ወንዝ መሀል ውስጥ ሆና ሁሉም ወንድ እንዲህ ክፉ አይደለም በማለት፣ ከኩነኔው እምብርት፣ ከሲዖሉ አንጀት ውስጥ  ጎትታ ነፃ ታወጣናለች፡፡
ታዲያ ይህ ታሪክ የተዘረዘረበት ቦታ፣ ድርጊቱ የተከወነበት አካባቢ ጎጃም ውስጥ ግንድባ ነው፡፡
ገፀ ባህሪዋ እመቤት፤ አካላዊ ገፅታዋ ገፅ 5 ላይ እንዲህ ይታያል፡- የዓስር ዓመቷ እመቤት ፈጠን እያለች ትራመዳለች፡፡ ያዘለቻት ትንሽ እንስራ ስላልከበደቻች አይደለም፤ እናቷ “ቶሎ ተመለሽ” ብላት እንጂ። የተነገራትን እረስታ ከእኩዮቿ ጋር ስትጫወት ስለቆየች ያንን ለማካካስ ነው የምትጣደፈው፣ ከፈትል የተሰራ ጥብቆ መሳይ ቀሚስ ለብሳለች፡፡ በጋሜዋ መሀል ያለው ቁንጮ ሽሩባዋ በተራመደች ቁጥር ወዲህና ወዲያ ይወዛወዛል፡፡”
ይህቺን ጨቅላ ያገባት ጨካኙና ወንበዴው ደምስ ነው፡፡ ደምስ እንደ ልቡ ነው፡፡ እንደ ሜዳ አራዊት ነው፣ የመታውን መትቶ፣ የገደለውን ገድሎ፣ በሀገሩ ላይ ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፡፡ ይፈራል። ያቺ ትንሽ አበባ የገባችው እዚህ አውሬ እጅ ነው። የእመቤት ትኩስ ፍቅር ልብ የተቀመጠው እዚህ የበረዶ ድንጋይ ውስጥ ነው፡፡ ሳቆችዋን የዋጠው ይህ በጭካኔ ጨለማ ውስጥ ያለ አረመኔ ነው፡፡ እንግዲህ ተስፋዋን ካዳፈነው ከዚህ ሰው ጋር ሶስት ዓመት ያህል እንባዋን ስትረጭ ኖራለች፡፡ ከዚያም በኋላ ህይወትዋ የምጥ፣ ኑሮዋ ድጥ ነበር፡፡
ለጥቆ ያገቡዋት ቱጃርም የነፍስዋን ኡኡታ አላረገቡትም፤ የምኞት ክንዶችዋን ሰብረው፣ የራዕይዋን ርቀት አሽመደመዱዋት እንጂ! … የእመቤት ጥቃት ብዙ ነው፡፡ በእመቤት ውስጥ የምናያቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶች የደረሰባቸው በደል፣ የተፈፀመባቸው ግፍ - ዝግንን የሚል ነው፡፡
“የፍቅር ድንግልና” ውስጥ እመቤትን ብቻ አይደለም የምናየው፤ ለዚያ ጉስቁልናዋ ምክንያት የሆነውን አስተሳሰብ፣ ባህልና፣ እምነት እንጂ፡፡ በዚያ ዘመን፣ በዚያ ባህል “ሴት ሰው አይደለችም” ተብሎ የሚታመን ይመስላል፡፡ ባይሆንማ ኖሮ እንዴት ህግ ባለበት ሀገር ባንዲራ በሚውለበለብበት አደባባይ፣ አንድ ዜጋ በሀገሯ እንደ በግ እየተነዳች፣ ለወንዶች ወሲብ ስካር ማብረጃ ትሆናለች!? ነፃነት አላት በምትባል ሀገር የምትኖር ዜጋ፣ እንዴት በጨለማ ትኖራለች…?! እንባዋን የሚያይ፣ ሙግትዋን የሚያዳምጥ ህግስ እንዴት አይኖርም? ይህ ብቻ አይደለም፣ “ከፋሽስቱ ጣሊያን እጅ ህዝባችንን ነፃ እናወጣለን” ከሚሉት አርበኞች ሳይቀር የደረሰባት መደፈርና ጥቃት፣ “ምንድነው?” እንድንል ያስገድደን ይሆን?
በአጠቃላይ የእመቤት የህይወት ዘመን ገፅታ የታሪክ ድምፅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በህይወት ውስጥ የሴት ልብ ጥንካሬ፣ በወንዶች ቢታገዝ ምን ያህል ውጤት እንደሚኖረው የምናይበት ቀዳዳም አለ።
የመጽሀፉን ሙሉ ታሪክ መነካካት የአንባቢን ፍላጎት መዝጋት ስለሆነ ውስጡ ባልገባም መጽሐፉ ውስጥ ብቅ ብቅ ያሉት ሰዎች ሁሉ የየራሳቸው መልክ ያላቸው ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ እንደ አንባቢ ከስሜቴ ውስጥ ስስዋን - መዝዞ ሆዴን ያባባውና አንጀቴን የበላው የእመቤት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የጀግናው በላይ ዘለቀ ታሪክ እንደገና ውስጤን ቆስቁሶ፣ ሀዘኔን ጐልጉሎ፣ እንደ እግር እጣት አንገብግቦኛል፡፡ ለሀገር ነፍሱን የሰጠ ጀግና፣ ስለ ሀገሩ ሕይወቱን በሞት ሰይፍ ላይ የነዳ ጐበዝ፣ “ነፃነት ተገኘ” በተባለ ማግስት በገዛ ሀገሩ በሞት መቀጣቱ፣ የኢትዮጵያን የግፍ ግድያ ሚዛን ሰማይ ያስነካዋል፡፡
ደራሲዋ በላይን ስታወራ ከጐኑ ስለ በላይ የተቋጠሩ ስንኞችን፣ የተቀነቀኑ ዜማዎችን አንተርሳለች፡፡
“ሞት” አይቀርም አያ ሥጋ ከለበሱ
ውነት ሙቶ ነወይ የምትላቀሱ፡፡
አባ ኮስትር በሌ ሙተህ ነወይ ለካ
ጀግናው ጀግናው ጐበዝ በአንተ ሳይለካ፡፡
አንቺ የበላይ እናት አንጀትሽን ልቁረጠው
የልጅሽን አንገት ገመድ ቆራረጠው
ድንጋይ ተወርውሮ ዓይኑን አፈረጠው፡፡
እነዚህ ስንኞች ወደ ሦስት አቅጣጫ ያወራሉ፤ ወደ ሕዝቡ፣ ወደ ራሱ ወደ በላይና ወደ እናቱ!
የዚህ ጐበዝ ታሪክ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መንገድ ሕይወታቸው ካለፈ ጀግኖች ይበልጥ የሚከነክንና የሚቆረቁር ነው፡፡ “ጣሊያን ሠቀለው” ቢባል፣ አንጀቱ ተቃጥሎ ነው፤” እንላለን። ግን የገዛ ሀገሩ ሰቀለችው!...መጽሐፉ ውስጥ አንዱ ከንካኝ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ፣ ያ መቼት ከተነሳ በርግጥም በላይ መቅረት የለበትም። ደራሲዋ ደግ አድርጋለች፡፡
መቼቱን ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ያደረገው ይህ መጽሐፍ፣ በጊዜው በሁለት ቢላ የሚበሉትንም ያሳያል፡፡ ባንድ በኩል አርበኞችን የሚያግዝ፣ በሌላ በኩል ለፈረንጆች የሚያደገድግና ሀብት የሚያጋብስ ነው፡፡ ይህም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሁሌ እውነት ነው፡፡
በዚሁ የታሪክ አጋጣሚ ከጣሊያኖች ጋር ቂጥ የገጠመ ባለሥልጣንን ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ሲሞግቱት፤ ሰውየው ልቡን ወደ ሀገሩ ለመመለስ፣ ልጆቹን ለማሳደግ በይፋ መክዳት እንዳለበት ነበር የተናገረው፡፡ ይህ ያኔም ነበር፣ አሁንም ወደፊትም ይኖራል፡፡ ታማኞችም ከሀዲዎችም ሊኖሩ ግድ ነው፡፡ ክርስቶስን እንኳ የከዱትና የሸጡት ሰዎች እንደነበሩ ማስታወስ ከፍ ያለ መረጃ ይሰጣል፡፡
ሌላው በእመቤት ሕይወትና በታሪኩ ውስጥ ጠንካራ ሚና ያላቸው ገፀ ባህሪ አቶ ባለህ ናቸው። እኒህ ሰው ገብስማ ፀጉር፣ አይነ ኮሎ፣ ጥርስ መልካም ናቸው፡፡ ቀልድና ቁምነገር ያውቃሉ። ሁሉንም የሚጠቀሙት ግን ጊዜና ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ነው፡፡ ስለዚህም የመፍትሔ ሰው ናቸው ብላቸዋለች፤ ደራሲዋ፡፡ ምናልባትም ደራሲዋ በነገረችን እውነት፤ መሥመሩን ሳይለቁ የተጓዙና ስነ ልቡናዊና ማኅበራዊ መልካቸውን በታሪኩ ውስጥ ያስነበቡ፣ በጥንቃቄ የተቀረፁ፣ ገፀ ባህሪ ናቸው፡፡ በጊዜውና ውሣኔ በሚያስፈልግ ሰዐት ደፋር፣ መጠንቀቅ በሚገባ ጊዜ ከሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ ውሣኔ ሰጪ ናቸው። ይህንን ደግሞ ከደምስ ጋር በነበረው ድብብቆሽ፣ በኋላም በአቶ ቦጋለ ቤት ድፍረት የተሞላ ውሣኔ አሳይተውናል፡፡
በታሪኩ ውስጥ በምክንያት አንድ መስመር ውስጥ ገብቶ ከእመቤት ሕይወት ጋር የተጋመደው ሙላትና ሙላት የሚረዳቸው የኔ ቢጤ ሴት ወይዘሮ (እማ ዘሬ) ለታሪኩ መፋፋም እንደማራገቢያ ጠቅመውታል፡፡ በተለይ ሙላት የታሪኩ ግንድ ላይ የበቀለ ሌላ ፈርጣማ ግንድ ሆኖ የዋናውን ታሪክ ቁመት ተለካክቶታል፡፡
በብረት አጥር፣ በክልከላ ወሰን የተቀመጠውን የእመቤትና የሙላት የፍቅር ነበልባል አሸንፎ እንዳይወጣ፣ የተጠፈነገበት የምክንያትና የሃይል ገመድ ደራሲዋን አንድ ደራሲ ከሚሾርባቸው ጠንካራ መንስኤና ውጤት ተርታ የሚያስመድብ የጥንካሬ ምስክር ነው፡፡
መጽሐፉ ውስጥ ብዙዎቹ ግጭቶች ምክንያታዊና አሳማኝ ናቸው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፣ የታሪኩ ድንኳን ሳይረግብ እየረገጡ የሚያሸጋግሩ በቂ ካስማዎች የተዘጋጁለትም ነው፡፡
የጐጃምን አካባቢ አጠቃላይ አውድ በመጠቀም ቤተክርስቲያን አካባቢ ታሪኩ የሚከርርበትን መንገድ መደልደልዋ በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ ምዕራፍ 35 ላይ አዛዥና ሙላትን ለማገናኘት የተቀየሰው ስልት ግሩም የሚባል ነው፡፡
ሌላው ደራሲዋ አንዳንድ ጉዳዮች ተሰውረው ታሪኩን እንዳያደነጋግሩ የምትጠቀምበት መንገድ አንገት የሚያስነቀንቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙላት ጉም ኢየሱስ ገዳም በሄደ ጊዜ፣ ከእመቤት ጋር ጠበል ቅመሱ ወደተባሉበት ሰው ቤት ሲሄዱ፣ አባትዋ “መንገዱ እንዳይጠፋችሁ” ማለታቸው በኋላ ለሚፈጠረው የእመቤትና የሙላት የናፍቆት ጊዜ ጥሩ የምክንያት ሽንቁር ነው፡፡ ሁለቱ  ሲላፉና ሲጫወቱ፣ ያቺ “መንገዱ ጠፋብን” የምትል ቀብድ ባትኖር ጉድ ይፈላ ነበር!
በአጠቃላይ መጽሐፉ ውስጥ እጅግ በርካታ ውበትና ጥንካሬዎች አሉ፡፡ በተለይ ግጭቶቹ በመንስዔና ውጤት የታጀቡ ናቸው፤ ሴራውም በምቾት የምንፈስስበትና ትንፋሽ እስክናጣ ልባችንን የሚሰቅል ሆኖ የተነደፈ ነው፡፡
በዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ሊካተቱና ሊጠቀሱ የሚገባቸው ነገሮች ሁሉ በመጽሐፉ ውስጥ ጥቅም ላይ ውለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት ምክንያቱን ባላውቀውም - ደራሲዋ በምልሰት መተረክ ግን አልፈለገችም ወይም ዘንግታዋለች፡፡
ምናልባት አንዳንድ ቦታ ደግሞ የተጐዱትን ለማገዝ፣ የወደቁትን ለመካስ የሚደረግ ነገር ያየሁ ይመስለኛል፡፡ አርስቶትል ወዶ ስለቀደደለት ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም - Poetic justice ይስተዋልበታል፡፡
በጥቅሉ ግን ይህቺ እናት ደራሲ ይህንን በ349 ገፆች የተቀነበበ ረጅም ልቦለድ፤ ልብ በሚያንጠለጥልና አንዳች ረብ ባለው ርዕሰ ጉዳይ አብስላ በመፃፍ ለተደራሲ ማቅረብዋ “አጀብ” የሚያሰኝና በአድናቆት የሚያስጨበጭብ ነው፡፡ ድንቅ ነው ወይዘሮ ተናኜ!  

Read 6910 times