Saturday, 06 June 2015 14:08

ይታደሏል እንጂ….!”

Written by  አሰፋ ጫቦ፤ Dallas Texas USA
Rate this item
(2 votes)

 ታየች በዛብህና ሻምበል ሐብተገብርኤል ጫቦ የጋብቻቸውን ኢዮቤልዩ በአል አርባምንጭ መድኃኔነዓለም ቤተክርስቲያን ሚያዚያ 27, 2007 የዳግመ ትንሳዔ ዕለት አከበሩ። ግርማ ሐብተገብርኤል በስልክ ነገረኝ። “ታዩንና ሐብቴን እንኳን ለዚህ በቃችሁ ብለህ ሳምልኝ!” አልኩት። “አሁኑኑ እሔዳለሁ!” አለኝ። ከድምጹ ቃና ኢዮቤልዩ በአሉ አሁንም በመከበር ያለ አስመሰለው። እኔ ባልኖርበትም ቤተክርስቲያኑ በልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው እንዲሁም በከተማዋ ኗሪም እንደተጣበበ ታየኝ። በቂ አትረፈዋል!
የታላቅ ወንድሜን የሻምበል ሐብተገብርኤል ጫቦን ፎቶ My Brother! MY Hero! ብዬ  Facebook ላይ ለጥፌ ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን (ሌሎችም ጎብኝዎች) ስለ ወንድምህ ከዚያ የተሻለ በል እንጅ አለኝ። እኔማ አንድ ቀን ስለሀብቴ መጽሐፍ እጽፋለሁ እላለሁ። ወንድሜ ስለሆነም ብቻ አይደለም። ሀብቴ አሁን አሁን “ወሰላም በምድር ስመረቱ ለሰብ / በምድር ላይ ለሰው ዘር ሰላም ይስመር/ያብብ“ ያለውን ያስታውሰኛል። “አሁን አሁን “ያልኩት፣ ልጅ ሆኜ ያ ሰላሙ ያናድደኝ ነበር:: አይቆጣ፤ አይናደድ፤ አይፈጥን፤ አይቸኩል:: ሁሌም ሰላም! ያው ነው!
ያ ዝንተአለም መረጋጋቱና ከልጆችዋ ለየት ያለ መሆኑ እናታችንን፤ እንዬን፤ ማቱኬን ያናድዳት ነበር። ማቱኬ ስትናደድ አጉል ነው። አፈር መሬት ታስግጣለች። በተገኘው!! በእጅዋም ጭምር!! የዚህ ጽዋ ዋና ቀማሽ ሀብቴ ነበር። ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ! ያው ነው! ማቱኬ ልጆችዋን ብቻ አይደለም። የልጆችዋ ልጆችም በዚያው ነው ያለፉት። የጎረቤትም ልጅ። አንዳንዴ የጎረቤት ያልሆነም ልጅ። አንዳንዴ ልጅ ያልሆነውንም። ”እንዲህ አይደረግም! እንዲህ አይባልም!” የምትለው ነገር ብዛቱ!! ፈረንጅ  Child Abuse የሚለው ነው። ታዲያ ከልጆችዋም ከልጅ ልጆችዋም ስሟን በመጥፎ ያስጠራ የለም። ይኸኛው መጥፎ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ማቱኬ አጆ የተያያዘ ብዙ ጥሩ ነገርም ነበራት:: ዋናው፤ አሁን የወገረችውን ልጅ ከደቂቃ በኋላ አቅፋ ትስመዋለች ወይ ታባብላለች። የሆነው ሆኖ ሲያልቅ ትፍቀዋለች መሰለኝ። አዲሱ እስኪተካ ያለፈው እንዳልነበር ይሆናል። “ትላንት…..በቀደምለት እንዲህ አድርገህ ነበር!” የሚል መዝገብ አልነበራትም። እያንዳንዱ ማቱኬ ስህተት ነው ያለችው ራሱን ችሎ እንደ አዲስ ይቀርባል።
የአብርሐም-የሣራ ቤት ይሁን ነው የሚባለው? ያ ከየት እንደመጣ ማን ያውቃል። ድንኳን እንጅ ቤት እንኳን አልነበራቸውም። “የታየችና የሀብቴ ቤት ያድርግላችሁ!” ቢባል እውነት ምርቃት ነው። ከጨንቻ ከወጣሁ ቆይቻለሁና አልፎ አልፎ እሔድ ነበር። በሔድኩ ቁጥር ቤቱ ሙሉ ነው። ብዙ ልጆች አልዋቸውና እነሱንም ይጨምራል። ሌላው ማን ማን እንደሆነ፤ ለምን እንደመጡ፤ ከየት እንደመጡ፤ ለማወቅ ትንሽ ጊዜ ይወስዳል። ሲመሽ ስለማይሔዱ እዚያው ኗሪ መሆናቸውን ያኔ አውቃለሁ። የሩቅ ዘመድ፤ የቅርብ ዘመድ፤ ከከተማ የመጣ ዘመድ፤ ከገጠር የመጣ ዘመድ፤ ዝምድናም የሌለው። ምኑ ቅጡ!!
በአብዛኛው አዲሳባ፤ ሌሎችም ከተሞች ኗሪ ነበርኩና ዘመድ ለመጠየቅ አልፎ አልፎ አርባምንጭ እሔድ ነበር። ያሁኑ፤ ከማእከላዊ እንደወጣሁ በወሩ ይሁን እንዲያ፤ እኔና ባለቤቴ፣
እህቴ፤ ግንብነሽ እና ባልቻ፤ ባለቤትዋ፤ አንድ ሹፌር ሆነን ሄድን። አምስት ሰው ማለት ነው። እንደተለመደው ቤቱ ጢም ብሎ ሞልቷል። ሲመሻሽ ወደ አራት ሰአት አካባቢ የሚሄደው ሄዶ ቀሪው ሲታይ አሁንም ጢም ያለ ነው። ቤቱ ደግሞ መጠነኛ ነው። “በቀለ ሞላ ሆቴል ማረፍኮ እንችላለን!!” ልል አስቤ ደንግጠው፤ “አሁን ምን አልክ?!” እንዳይሉኝ ፈርቼ ዝም አልኩ። ታደረ! ሶስት ይሁን አራት ቀን ቆይተን ተመለስን። ብዙ ነገር አወራን። የመኝታ እጥረት፤ የቦታ ጥበት ግን ወሬው ውስጥ አልነበረም። ምናልባትም ከኔ ሌላ የቦታ ችግር ይኖራል ብሎ ያሰበ ሰው ያለም አልመስል አለኝ።
ጦር ግንባር ከመላኩ በፊት ሀብቴ እድሜ ልኩን የሰራው ፖሊስ ክበብ ነበር። ለክበቡ የሚያስፈልገውን ለመግዛት አዲሳባ አዘዉትሮ ይመጣል። እኔም አልፎ አልፎ አርባምንጭ እሔዳለሁ ብያለሁ። አዲሳባ ይሁን አርባምንጭ የሀብቴ ስራ ያው ነው። መዞር፤ ይዞኝ መዞር ነው። ሰው ጥየቃ! የጨንቻ ሰው፣ የጋሞ  ሰዉ ጥየቃ። እገሌ፣ የእገሌ ልጅ፤ ከካቡራ፤ ገብርኤል ሰፈር፤ ከአየለ ሰፈር…..”አትጠያየቁም እንዴ? ይኸማ ጉድ ነው!” ይልና የረሳሁትን፤ ጭራሹንም የማላውቀዉንም መዞር ነው፤ መጠየቅ ነው። አዲሳባ ጥሩ ጠጅ ቤት የት ሰፈር እንዳለ አዙረው ያስተዋወቁኝ ሀብቴና እነዚሁ ሰዎች ናቸው። በዚህ ላይ እኔ ቤት አንድ ቀን ቢያድር ነው። “እኛን ባዳ አድርጎን ብለው ይቀየሙናል” ብሎ የሚያድረው አንድ ቀን አንዱ ቤት፣ ሌላ ቀን ሌላው ቤት ነበር። “ይቀየሙናል” ሲል እኔንም ጨምሮ ነው። ከጨንቻ ከወጣ፤ ከወጣሁ በስንት አመት አሁንም ልክ እንደ ጨንቻ ያስባል።
ይህ ደግሞ አንዴ አርባምንጭ የሔድኩ’ለት ታዴ የነገረኝ ነው። ታደሰ ታማ ከገጠር ጨንቻ መጥቶ የተማረ፤ ከሐብቴ ጋር አብሮ ፖሊስነት የተቀጠረ፤ አርባምንጭ ሲቆረቆር ከሐብቴ ጋር ከቆርቋሪዎቹ አንዱ የነበር፤ አሁን በሕይወት የሌለ ወንድማችን ነበር። በወሬ መካከል “ሀብቴ ቅዳሜና እሁድ ስራው የተጣላ ሰው ማስታረቅ ነው” አለኝ። “ሰው ሁሉ የሆነውን፣ የደረሰበትን፤ የሚስት፤ የባል፤ የልጆች ሚስጥር፤ ስሞታ፤ ክስ ለሐብቴ ይናገራል፤ ይናዘዛል” አለኝ። ”ታዲያ ሀብቴ ያስታርቃል! እንዴት እንደሚያስታርቅ ግን የታወቀ ነገር የለም” አለኝ።
ይህንን ማስታረቁን አንዴ አዲሳባም መጥቶ ሳለ አየነው። ፊት በር፤ ካፕቴን ደስታ ግቢ ነበር የተከራየነው። የኛው ወጣ ያለ በረንዳ ያለው ሲሆን ከፊት ለፊታችን ዝቅ ብሎ አንድ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የተከራየው ተለቅ ያለ ቤት አለ። ያን ዕለት ሀብቴ በረንዳው ላይ ቁጭ ብሎ ባልና ሚስቱ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲነጋገሩ ይሰማል። ተነስቶ፤ በር አንኳኩቶ ያስከፍትና ከመሸ በኋላ መጣላት ነውር መሆኑን ነግሮ፤ አስታርቆ፤ ራቱን እዚያ በልቶ ይመለሳል። ስመጣ እህቴ ገርሟት፤ ተናዳ፤ ተቆጥታ የሆነውን ነገረችኝ። ጠየኩት! ከሰዎቹ ጋር እንደማንተዋወቅና ተነጋግረንም እንደማናውቅ ነገርኩት:: በኛ ኑሮና በምናደርገው ተቆጣም፤ አዘነም። “ሰው ሲጣላ ዝም ተብሎ ይታያል ነዉ የምትሉኝ?” አለ:: “ነዉር’ኮ ነዉ !” አለ::  እግዜር እንደማይወደውም የነገረን መስለኝ። ከዚያ በወሩ ይሆን እንዲያ-- ያች ያስታረቃት ሴትዮ አራት ኪሎ መንገድ ላይ “ወንድምህ ጤናቸው ደህና ነው?” አለችኝ። የምን ወንድም? ጎረቤቴ እንደሆነች የዛንለት ነግራኝ ነበር ያውኩት።
ይኸ፤ የጨንቻና ያዲሳባ ግጭት አንዴ አባቴ፤ ዳና ጫቦ ሳዴ፤ አዲሳባ የመጡ ጊዜም ሆኖ ነበር። ያኔ የተከራየነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ጀርባ፤ አጥር ያለው፤ ብዙ ቤቶች ያሉበት ሰፊ ግቢ ነበር። እኔ ማታ ስራና ቀን ዩኒቨርስቲ ወጥሮኝ ብዙ ጊዜ እቤት ስለማልገኝ፣ የቤቱ ተጠሪ እህቴ ነበረች። ሶስት ህጻናቶቼም አሉ። አባቴ የመኝታ ሰአት ካልደረስ በስተቀር የቤቱ በር አይዘጋም ባይ ናቸው።” የሙት ቤት አይደል!” ይላሉ። ስለዚህም ማታም ቀንም ወንበር አውጥተው በረንዳው ላይ ይቀመጡና አላፊ አግዳሚውን “እንዴት አደራችህ? እንዴት ዋላችሁ? እንዴት አመሻችሁ?” ይላሉ። እህቴ፣ ግምብነሸ፣ “አንድ ነገር አድርግ እንጅ!  አገር ምን ይለናል!” ትለኛለች ። “ተይው ለጊዜው ጨንቻ እንደተመለሽ ቁጠሪው” ያልኳት መስለኝ። ከዚያ አባቴ ወደ መጡበት ከተመለሱ በኋላ የግቢው ሰው በሙሉ፤ ልጅ አዋቂው ያባቴን ጤንነት ጠያቂ ሆነ። እኛም በዚያ ሰበብ የግቢውን ሰው አወቅነው።
ሀብቴና ታየች በዛብህ፤ በዚህ ባለፈው አርባ አመታት ውስጥ ስንት ልጆች እንዳሳደጉ የሚያውቁ አይመስለኝም። እንዳልኩት የወለዷቸው አሉ። ብዙ ናቸው። ታዩም የጨንቻ ልጅ ነች። ታስሬ፣ የኔ ሶስት ልጆች ያደጉት እዚያው አርባ ምንጭ ነበር። እኔ ዘንድ ባህር ዳር እስከሚልኳት ግንብነሽን ያሳደጉ ናቸው። እሸቱ ጫቦን ያሳደጉ ናቸው። ያክስቶቻችንን ልጆችና የልጅ ልጆች አሳድገዋል። ይህ የቅርብ የቁርጥ ዘመድ መሆኑ ነው። አያውቁት ይሆናል ያልኩት---ከዚህ ከቁርጥ ዘመዱ ውጭ ሁለቱ በደግነታቸው በመንፈስ የወለዷቸውን ነው።
“ሰው የዘራውን ያጭዳል!” የሚባል ከሆነ  ይህ በርግጥ ለታዩና ሀብቴ እውነት ነው። የኔ ልጆች ሁለት፤ ሶስት፤ ሁለት ወልደዋል። ትልቋ የትልቁ ልጅ መሀንዲስ ነች። ግምብነሽና ባልቻ ምን የመሳሰሉ፣ አሁን ልጆች መውለድ የጀመሩ አምስት ወንዶች ልጆች አድርሰዋል። እሸቱ በዚህ አመት ምን የመስለ፤ አገር የሚያኮራ፤ሀብቴና ታዩን የሚያኮራ የጋሞ፤አማርኛና እንግሊዝኛ መዘገበ ቃላት አውጥቷል። አምስት ልጆች፤ ሶስት እንግሊዚዊት ኬኒያዊት፤ ሁለት ከእንግሊዛዊ እንግልዚዊት ወልዷል። የሎንዶኑ ልጆች ስማቸው ቴዎድሮስና ማቱኬ ናቸው። ቴዎድሮስ በአጼው፤ ማቱኬ በናታችን ስም። የዩንብርስቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው።  ቴዲ ዉትድርና ገብቶ ጄነራል  መሆን ይፈልጋል። ኢትዮጵያዊ ቴዎድሮስ የእንግሊዝ ጄነራል  ሲሆን  ራሱን የቻለ ታሪካዊነትም ይኖረዋል ብለን እናስባለን። ጄነራል ናፒርን እናስታውሰዋለንና!
ሀብቴ ከሌሎቻችን ተለይቶ የራሱ፤ ራሱን የቻለ ቅጣት ደሞ ነበረው። ምግብ ላይ ነው። ተሰብስበን በአንድነት ነው የምንበላው። ማን ምን ያህል በላ እንደ የግለሰቡ ያለያያል። የኔው “ከተገቢው በላይ ትጎርሳለህ፤ ቶሎ ቶሎ ትውጣለህ፤ አታላምጥም፤ አታጣጥጥም፤ ለፍቼ ነው የሰራሁት፤ ማጣጣሚያው ያለው አፍህ ውስጥ ነው እንጅ ሆድህ ውስጥ አይደለም” የሚል ነው። አንድ ሁለቴ በማጅራቴ ተጎትቼ ተባርሬአለሁ። የሐብቴ የዚያ ተቃራኒ ነው። ሊታዘብ፤ ሊመለከት እንጅ ሊበላ የመጣ አይመስልም። ቆንጥሮ ያንኑ አልደቅ ያለ ይመስል ሲያላምጥ ይኖራል። “ብላ እንጅ! “ቃው! “ብላ ብየሀለሁ!” ሌላቃው! ሀብቴም አልፈጠነ እንዬም አልተለወጠች። ቃውቋሚ ሆነ
ስለ ሀብቴ ብዬ የየማቱኬን መጥፎ ምስል ስዬ እንዳልሆን። የተከበረች፤ የተወደደች፤ የተፈራች፤ ርህሩህ፤ ደግ ሰው፤ ደግ አናት ነበረች።
ሻምበል ሀብተገብርኤል ጫቦ በጭንቁ፣ በምጡ ተተኪ ትውልዳችንን ጭምር በፈጀው ዘመን በደቡብም በሰሜንም ጦር ግን ባር ዘምቷል።” የአሳ ግማቱ ከወደ አናቱ!!” እንዲሉ፤ ህዝባችንን፤ ሠራዊታችን ከጫንቃዉ ተፈናጠዉ ከአናቱ እንዲብረከርክ፤ እንዲዳከም ባነቀዙት ሰበብ ሲፈታ ህብቴ አስመራ ነበር። መንግስቱ ኃይለማርያም የፈረጠጠለት አስመራ ነበር። ፋይዳው ምን ድነበር? የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ሀብቴ ለእናት አገራችን ድርሻውን ከፍሏል።
አስመራ ወደ መጨረሻው ገደማ ያደረገው የሚገርመኝ፣ የሚደንቀኝም፣ የሚያስፈራኝም አንድ ነገር ነበር። አንድ፣ ለተይ የምትባል፣ ሴት አንድ ቀን ጥዋት በር ተንኳኳ ናት ገባለች። በጥቂት አማርኛ፤ በአብዛኛው ትግሪኛ“ አነ ይቤ ተስብእዩ!” ትለኛለች። ከአስመራ የረከሰ፤ ካዲሳባም የረከሰ እያመላለሰች የምትተዳደር ነች። “ሀደ ችግር ሲኖር አስፋ ነገሪ ሀብቴ ኢሉ!” አለች። አሁን ችግሩ፤ በጣም አስቸኳይና አጣዳፊ ጉዳይ ካልሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በረራ አቁሟል። ሀብቴ “አሰፋ የማይችለው ነገር የለም!” እንዳላት ሁሉ አስመራ ለመሔድ መልሴን ትጠብቃለች። “አልችልም! የሚቻል አይመስለኝም!” የሚል መልስ ለመቀበል የተዘጋጀች አትመስልም። የሚፈረድባትም አይመስለኝም!
እስቲ ከሰአት በኋላ ተመለሽ ብዬ ወዳጄ ወደ ነበረው ወደ አስግድ ወልደአማኑኤል ቢሮ ሔድኩኝ። ነገርኩት! እኔም በተራየ “አይቻልም!” የሚል መልስ አልቀበልም አልኩኝ። ደውሎ ደዋዉሎ አንድ መቀመጫ ለነገ አገኘልኝ። ይኸ እንግዲህ መንግስቱ በፈረጠጠ ማግስት ነበር። አስግድ የመገናኛ ሚንስቴር ነበር። የሀብቴ የዘራውን ማጨድ አንድ ሌላ በቅርቡ የሆነ ነገር አስታወሰኝ። የአክስቴን የልጅ ልጅ፤ አዜብን መካከለኛው ምስራቅ ሳነጋግር የሐብቴን ነገር አነሳን። “አሴ ምን ያደርጋል! አረጀ’ኮ!” አለችኝ፣ አምርራ! ማርጀት አይገባዉም! የለበትም! የምትል ትመስላለች። በሌላ ቀን አዲሳባ ደውዬ እመቤት አሰፋን ሳነጋግር፣ ይህንን አዜብ ያለችኝን ነገርኳት። “እኔ በነአዜብ እቀናለሁ!” አለችኝ። “ለምን?” ስላት “ሀብቴን እወደዋለሁ! ሚስጥርም እናወራለን! እነ አዜብ ግን ከኔ የበለጠ የሚወዱት ስለሚመስለኝ እቀናባቸዋለሁ!” አለችኝ። እመቤት እነ አዜብን የምትለው አህትማማቾቹን ጨምራ ነው። ሳምሶን አሰፋን ከብዙ ጊዜ በኋላ የዛሬ ወር ገደማ ሳነጋግረው፣ ቆንጆ ቤት መስራቱን ነገረኝ። ከዚያ በጣም ሞቅ ደመቅ ባለ ቃና “አሴ ሃብቴ መጥቶ ቤትን አየው! አንድ ክፍል ይኸ ያንተ ነው ማንም አይነካውም ብዬ አሳየሁት!” አለኝ። ይህንን ሲል የድምጹ የደስትና ኩራት ቃና የተለየ ነበር። በሌላ ቀን ሐብቴን ሳነጋገረው ሳምሶን ያለውን ነገርኩት። ልክ እንደ ሳምሶን ሞቅ ደመቅ ባለ ድምጽ፤ “አዎን! የኔን ክፍል አሳይቶኝ፣ ቤቱንም ክፍሉንም በጣም ወደድኩት!” ኩራት በተሞላበት ድምጽ።
ሐብቴ እንጀራ ይጋግራል፤ ወጥ ይሰራል፥ ዶሮም ይበልታል። ልጆች ሆነን፤ አንዴ ከአባታችን ጋር ገጠር ሔደው፤ አባታችን ታመው እንጀራ ጋግሮ አበላቸው ሲባል መስማቴ ትንሽ ትንሽ ትዝ ይለኛል። አንድ ሰሞን አርባምንጭ ሰነበትኩና ተሰብስበን ስናወጋ የሀብቴ የእንጀራ፤ ወጥና ዶሮ መበለት ተነሳ። “እውነት ነው እንዴ?” ያልኩኝ መሰለኝ። ሐብቴ ከመመለሱ በፊት ታዩ ”አሴ እውነት ነው! እኔንኮ ወጥ መስራትና ዶሮ መበለት ያስተማረኝ ሐብቴ ነው!” አለች። ያለቀ፤ የተረጋገጠ፤ አገር ያወቀው፤ ጸሐይ የሞቀው ነገር እንደምታወራ ዘና ብላ፣ እንደዋዛ! ገርሞኝ “ታዩ አታፍሪም?!” አልኴት:: በሳቅ ሞተች። “አሴ! ምኑ ነው የሚያሳፍረው? እውነትኮ ነው!!” አለች፡፡ ፍርጥም ብላ። ይገርመኛል! ታዩ፤ ከሚገርሙኝ ነገሮችዋ አንዱ ግልጽነትዋ እንደ ሕጻናት ነው:: ከኢትዮጵያም ኢትዮጵያ፣ ጨንቻ፣ ሀብቴ እንዴት ለምን ብሎ ተማረው?
ታዩና ሀብቴ ልጆቻቸውን፤ የኔን ልጆች፤ የዘመድ አዝማድ ልጆች ተንከባክበው፤ አሳድገው ለቁም ነገር አበቁ። የሚመሰገኑ፤ የሚያስመስግኑ እንጅ አንድም “አሳዳጊ የበደለው!” የለባቸውም። ከሁሉም በላይ ግን እናታቸውን፤ ማቱኬ አጆን፤ አባታቸውን፤ ዳና ጫቦ ሳንኬ ሳዴሐማያሬን በወግ በማእረግ ጦረው፣ የቁርጥ ቀን ሲመጣም በክብር ወደ ዘለአለማዊ ቤታቸው ሸኝተዋል።
የኤፍሬም አሰፋ ባለቤት፤ ተቀባሽ አንጣል፤ “የልጄን ስም ቅዱስ ነው” ብላ ደብዳቤ ጻፈችልኝ። “ባሌን ቅዱስ ኤፍሬም ለማለት ስለፈለኩና ከተቀደስ ቤተሰብ ጋር ስለተጋባሁ ነው” አለች። “አገራችንን (ጋሞን) አታውቂ፤ ቤተሰቡን በሙሉ እኔን ጭምር አታውቂ..” ስላት “ያወኩት በቂ ነው!” አለች። ተቀባሽ፣ የሐረር ልጅ ነች:: ይህንን ለእህቴ በስልክ ስነግራት ለቅሶዋን ለቀቀች። “ምን ያስለቅስሻል?” ስላት “እንዬ ይህንን ሳትሰማና ሳታይ ሞተች:: የሷም ርቃት ነው እንዲህ ያደረገን!” አለች። ለሀብቴም በሌላ ቀን ነገርኩት። ከትከት ብሎ ሳቀ! ሳቁ ሁለቱም ልክ ናቸው ለማለት  ነበር። ሐብቴ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ  አንድን ነገር የማሳጠርና የመግለጽ መንገድም ያለው ይመስለኛል። ሳቁ ከዚህ ውስጥ አንዱ መሆኑ ነው።
የመጽሐፉን ስም ረሳሁት እንጅ አንድ ፈረንጅ መጽሐፍ ውስጥ” አያንዳንዱ ከተማ፤ መንደር ቢያንስ አንድ የዋሕ፤ አንድ ጅል፤ አንድ ወፎፌ፤ አንድ አስታራቂ፤ አቀራራቢ ሰው አለው “ይላል። በኔ ግምት ሐብቴ ከነዚህ አንድ አስታራቂ፤ አቀራራቢዎቹ ውስጥ የሚደመር ይመስለኛል። ለያንዳንዱ መንደር፤ ከተማ፤ ለሐገሬም --- አንዳንድ ሐብቴን እመኛለሁ።
ለዚህም ነው “ይታደሏል እንጅ….!” ያልኩት። ሐብቴን እኛ ያገኘነው ታድለን እንጅ ታግለን አይደለም!

Read 7520 times